>
5:13 pm - Sunday April 18, 8551

ህዝብ እንዳይደናገር እኛም እንናገር!!! (መሳይ መኮንን)

ህዝብ እንዳይደናገር እኛም እንናገር!!!
መሳይ መኮንን
* ስለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አዲሱ መጽሀፍ አይደለም። ይልቅስ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በሰፊው ስለተነሳው የቀድሞ የኢሳት ባልደረቦች ጉዳይ እንጂ። 
ነገሩ እዚህ ደረጃ ደርሶ በአደባባይ ይህን መሰል ንትርክ መምጣቱ ለኢሳት ክፉ አጋጣሚ ነው። ለትግሉ እየተባለ የሌሎችን ገበና በመሸፈን ብዙ ርቀት ሲሄድ የነበረው ኢሳት የራሱን የውስጥ ጉዳይ ለአደባባይ እርቃኑን መስጠቱ አንገት ይሰብራል። የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሁለቱም ወገኖች ምን ያህል ጥረት ተደርጓል? እስከየት ጥግ ድረስ ተጉዘዋል? ችግሩ የማይፈታ ካንሰር ደረጃ ደርሶ ነበርን? ብዙ ጥያቄ ይነሳል። ሁለቱም ለእነዚህ ጥያቄዎች የየራሳቸው መልስ ሊኖራቸው ይችላል። እኔ በአንደኛው ወገን ለተመደብኩት ግን ችግሩን ለመፍታት በርካታ ጥይቶች እያሉ ሳንጠቀምባቸው ከሽፈዋል በሚለው ሀሳብ እስማማለሁ። ወደ ፍሬ ነገሬ ልግባ።
በኢሳት ጉዳይ የአንዱ ወገን ጩኸት በበረከተበት ሁኔታ ዝም ማለቱን አልቻልኩም። ከአንድ ሳምንት በላይ በዘለቀውና ‘’እኛ የመርህና የእውነት ሰዎች፡ ተገፍተን የወጣን የኢሳት ጋዜጠኞች’’ የሚለው የጽሁፍና የድምጽ መልዕክቶች ተደጋግመው ሲሰሙና ሲጻፉ መደናገርን ከመፍጠር ባለፈ ታሪክ በተሳሳተ ትርክትና እውነት ባልሆነ መስመር ላይ ተቸንክሮ እንዳይቀር በመስጋት ነው ወደዚህ መንደር የመጣሁት። በውስጥ መነጋገር ቢቻል ጥሩ ነበር። የአደባባይ እንካ ሰላንቲያውን በፍጹም አልወደውም። ወደዚህ ከመምጣቴ በፊትም ከተወሰኑት ‘’ተገፋን’’ ያሉት የቀድሞ ባልደረቦቻችን ጋር ለማውራት ስልክ በመደወል ሙከራ አድርጌ ነበር። መልስ የሚሰጠኝ አልነበረም። ከኢትዮጵያ መልስም እየሄድንበት ያለውን አካሄድ በተመለከተ እንወያይ የሚል ጥሪ ላቀረብኩለት ሰው የተሰጠኝ ምላሽ ‘’ አርምሞ ላይ ነኝ። ማንንም ማናገር አልፈልግም’’ የሚል ነበር። ለማንኛውም የተነገረው ሁሉ እውነት ነው ወይ? ማን ነው ተገፊው? ማንስ ነው ገፊው? ማን ነው የታፈነው? መርህና እውነት ምንድን ነው? ህዝብ እየተደናገረ ያለ ስለመሰለኝ ይህቺን ማስታወሻ ለመጻፍ ተገድጄአለሁ።
እዚህ ላይ ማስመር የምፈልገው የማንንም ዋጋ ለማራከስ አልመጣሁም። ጎብዝ ወንድሞቼና እህቶቼ ናቸው። በኢሳት ውስጥም ሆነ በህይወታቸው ውድ ዋጋ ከፍለዋል። ኢሳት ላይ ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል። ኢሳት ባለው ውሱን አቅም እነዚህ ባልደረቦች የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የራሳቸው አድማጭና ተከታይ መፍጠር የቻሉ፡ ለኢሳት ከፍ ብሎ መታየት የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ መሆናቸውን እንደባልደረባ፡ እንደአንድ ወዳጃቸውም በደማቁ የምመሰክረው ሀቅ ነው። በነበረን ቆይታ ብዙ መልካም ነገሮችን በጋራ አብረን አይተናል። ውጣ ውረዱን አብረን ዘልቀናል። አንድ የሚያደርጉን አያሌ ነገሮች ነበሩ። አሁንም ይኖራሉ። ለህዝባቸው የዋሉትን፡ የከፈሉትን ዋጋ ማሳነስ በሰማይም በምድርም የሚያስጠይቅ ነው። መጥፎ አጋጣሚ መንገዳችንን እስከቀራኒዮ አለማዝለቁ ቢያስከፋም አብረን የተጓዝንበት የ8ዓመታት መንገድ ግን ፍጹም በሀገር ፍቅር ስሜት፡ እኔነት በሌለው ህዝባዊ ወገንተኝነት የታጀበ በመሆኑ የሚያኮራ የጋራ ታሪክ አለን ብዬ አምናለሁ። አሁን የተፈጠረው ችግርም ያንን ወርቃማ አንደነታችንን የሚያደበዝዘው አይደለም። ያ ታሪክ ተጽፏል። እንዳለ ይቀመጣል። በአዲስ መስመር የተጀመረው የልዩነት ታሪክም ራሱን ችሎ የሚቆም እንጂ የነበረውን አጥፍቶ ብቻውን የሚታይ አይሆንም።
ወደ ሰሞኑ ጉዳይ ልመለስ። ከኢሳት ‘ተገፍተን’ የወጣን ‘የመርህና የእውነት’ ሰዎች ብለው አዲስ ሚዲያ ለማቋቋም መግለጫ የሰጡት የቀድሞ ባልደረቦች ህዝብ እያደናገሩ መሆኑን መግለጽ እንዳለብኝ ተሰምተኞል። ውሸት ሲደጋገም እውነት መስሎ ይቀራል የሚለው በገቢር እየታየ ስለመሰለኝ ቢያንስ ህዝቡ በዚህ በኩል ያለውን እውነት አግኝቶ የራሱን ፍርድ መስጠት መቻል ይኖርበታል። ከዚህ በኩል ዝምታ መስፈኑ የእነሱን ጩኸት የእውነት አስመስሎታል። ይህን የምጽፈው በአንጃነት ተፈርጆ በዛኛው ወገን ያሉት ተብሎ የተጠቀሰውንና አሁን ኢሳት ውስጥ የቀረውን ቡድን ወክዬ አይደለም። እኔ በውስጤ በየትኛውም ቡድን የተሰለፈ የቡድን አቋም እንደሌለኝ አምናለሁ። ‘’የመርህ ሰዎች’’ በለው ለራሳቸው ዋንጫ ሸልመው ሌላውን ተንበርካኪ አድርገው ለመሳል እየሞከሩ ያሉት የቀድሞ ባልደረቦች ጩኸት የማን ጩኸት እንደነበረ ስለምንተዋወቅ ፍርዱን ለህሊናችን እተወዋለሁ። ኢሳትን በዚህን ክፉ የታሪክ አጋጣሚ አደጋ ላይ ጥለው ለመውጣታቸው የሰጧቸው ምክንያቶች ቅንነት የሌላቸው፡ አብዛኞቹ እውነት ያልሆኑ፡ በባዶ ሴራ የተሞሉ መሆናቸውን ለመመስከር መቼም የምፈራው አይሆንም። የተወሰኑትን በዚህ ጽሁፌ እገልጻቸዋለሁ።
 
ኢሳትና ግንቦት ሰባት
ተገፋን ብለው የወጡት የቀድሞ ባልደረቦች ለውሳኔ ካቀበቋቸው ምክንያቶች አንዱ የግንቦት ሰባት እጅ ጥምዘዛ ነው። የንቅናቄው መሪዎች በኢሳት ውስጥ እጃቸውን አስገብተው በፖለቲካ የሚተቿቸውን ጋዜጠኞች በእጅ አዙር እንዲቀነሱ አድርገዋል፡ ንቅናቄው ከኢሳት ጋር እንዲፋታ በመታገላችን ለመገፋት ተዳርገናል የሚል ሀሳብ አንስተዋል። ቃል በቃል ባላስቀምጠውም የግንቦት ሰባት ጣልቃ ገብነት ለዚህ ውሳኔ እንዳበቃቸው ገልጸዋል። መቼም ስብሰባዎቻችን በሙሉ በቃለ ጉባዔ የተያዙ ስለሆኑ አንድ ቀን ወጥተው ለህዝብ ይፋ ይደረጋሉ ብዬ እጠብቃለሁ። በአስተዳደርና በቦርድ ደረጃ የግንቦት ሰባት ጣልቃ ገብነትን አቋም ይዘው ሲሞግቱ በዚህም ተፈርጀው የንቅናቄው ጠላት ተደርገው ሲብጠለጠሉ የነበሩ እነማን እንደሆኑ እናውቃለን።
ግንቦት ሰባት ከኢሳት ላይ እጁን ያንሳ፡ የእስከዛሬው ይበቃል፡ ከዚህ በኋላ በአንድም ይሁን በሌላ የማንም ተጽዕኖ የሌለበት ፕሮፌሽናል ሚዲያ ይሁን የሚለውን አቋም ስናራምድ የነበርንን የኢሳት ባልደረቦች እግር በእግር እየተከተሉ ሲቃወሙን፡ አንገታችንን እንድንደፋ ሲጥሩ የነበሩ ባልደረቦች ዛሬ ጩኸታችንን ቀምተው ከኢሳት ለመውጣታቸው እንደምክንያት አድርገው ሲጠቅሱት ስሰማ የሰው ልጅ እንደምን ጨካኝ ነው እንዳስባለኝ መደበቅ አልፈልግም። የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት የተወላገደ ትርክት ሲቀርብ ዝም ማለትን ህሊናዬ አልፈቀደውም። እኛን የግንቦት ሰባት ጠላት፡ እነሱን ወዳጅ እንዲመስሉ አድርገው በመሃላችን ልዩነቱ እንዲሰፋ በፊትለፊትና በጀርባ የተለያዩ ግፊቶችን ሲያደርጉ የነበሩት በዋናነት አሁን ግንቦት ሰባት ገፋን ብለው ለህዝብ የቀረቡት የቀድሞ ባልደረቦቻችን መሆናቸውን ህዝብ ማወቅ ያለበት ይመስለኛል። እውነት ነውና መቼም በጩኸት አይሸፈንም።
የኢሳት ቦርድ
የኢሳት ቦርድ ላይ ማን ምን አቋም እነደነበረው የኢሳት ጣሪያና ግድግዳ እንኳን አፍ አውጥተው መናገር ቢችሉ የሚናገሩት ሀቅ አለ። የኢሳት ቦርድን በተመለከተ አሁን ቦርዱን ሰበብ ምክንያት አድርገው የህዝብ ድጋፍ ለመሸመት ብዙ ርቀት የሄዱት የቀድሞ ባልደረቦች ለህሊናቸው የምተወው ጥያቄ ቢኖር ማን ነው ይህን ቦርድ ሲሞግት የነበረው? ማንስ ነው ለቦርዱ ጥብቅና ቆሞ በጋዜጠኞች መሃል ልዩነቱ እንዲሰፋ ያደረገው? የሚል ነው። መቼም ለክራችን የምንቆም ከሆነ ለዚህ ጥያቄ ሁላችንም በህሊናችን የተቀመጠ እውነት አለና ከዚያ መሸሽ አያስፈልግም። እኔም ሆንኩ አንዳንድ ባልደረቦች የቦርዱን የተሳሳተ መስመር ስንተች፡ ቦርዱ እንዲቀየር ስንወተውት ኖረናል። በስብሰባዎች ላይ ከቦርዱ ራስ ውረዱ እስክንባል ድረስ ጠንካራ አቋም ይዘን ስንከራከር የነበርን ባልደረቦች ላይ ተቃውሞ ከማሰማት ባለፈ ለቦርዱ ሰዎች ስለእያንዳንዳችን መረጃ በማቀበል የቦርዱ ጠበቃ ሆኖ ከቆዩት መሃል አንዳንዶቹ ዛሬ ‘’ቦርዱ ገፋን’’ የሚል ምክንያት አቅርበው ስሰማ በእውነቱ አፍሬአለሁ።
ቦርዱ ሌሎችን ሲገፋ ያን ጊዜ የት ነበሩ? ቦርዱ እኛን ደብቆ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ መክፈቱን ሲነግረን በጥፍራችን ቆመን ስንቃወም በእውነት እናንተ የት ነበራችሁ? የራሳችንን ቦርድ እናቋቁም፡ የድርጅት ቆብ የደፉ የቦርዱ አባላት ይቀየሩ ብለን በድፍረት ስንናገር በዝምታ ጭምር ሀሳባችንን ስታንኳስሱ የነበራችሁ ዛሬ እኛን ‘’የቦርዱ ውሳኔ ተባባሪ’’ አድርጎ ለማሳየት እንዴት ድፍረቱን አገኛችሁ? ቢያንስ በግሌ የቦርዱ አመራር ስልጣን ይልቀቅ የሚል የውስጥ ማስታወሻ መጻፌን ከዘነጋችሁት ላስታውሳችሁ። ለቦርዱ የገንዘብ እጥረት ጥሪ ምላሽ የሚሆን ሀሳብ በማቅረብ፡ ሰራተኞችን ለመቀነስ የሚያስችል የፕሮግራሞች መታጠፍ እቅድ ያወጣ ግለሰብ እንደምን ዛሬ ‘’ሰራተኛ መቀነሱ አግባብ አይደለም’’ የሚል አቋም ለማራመድ ወኔ አገኘ? ከቦርዱ የተለያዩ ኢፍትሃዊ ውሳኔች ጋር በምክረ ሃሳብ ደረጃ የተሳተፈ ሰው ዛሬ ላይ ምን የተለየ ወንጀል ተሰርቶ ነው ቦርዱ ላይ የሃጢያት ፋይል የከፈተው? ይህንንም ለህሊና ፍርድ እተወዋለሁ።
ቦርዱን በተመለከተ አዲስ አበባ የሄዱትና አሁን ከኢሳት ጋር የቀሩት ባልደረቦች የወሰዱት አቋም ከዚህ ጽሁፍ ጋር ተያይዟል። ኢሳትን የማንም ተጽዕኖ ያላረፈበት ነጻ እንዲሆን እንዲሁም ቦርዱ አካሄዱን እንዲያስተካክል እልህ አስጨራሽ ትግል ስናደርግ ‘ተገፋን’፡ ታፈንን’ የሚሉት የዛሬዎቹ ከሳሾች አንዳንዶቹ አድፍጠው ዝምታን መርጠዋል፡ የተወሰኑት ከቦርዱ ጋር ተባባሪዎች ነበሩ። ዛሬ በአንዲት ጀምበር ምን ተአምር ተገኘና ዝምታው ተሰበረ?
ኢሳትና አፈና
የአፈናው ክስ የብዙ ወዳጆችን ቀልብ እንደወሰደ ተረድቼአለሁ። ለሚዲያ ነጻነት ከቆመና ሀሳብን በነጻነትን የመግለጽ መብት እንዲከበር መታገልን የህልውናው ምሶሶ ካደረገ ተቋም አፈና ተፈጸመ መባሉ የሴረኞችን ብቻ ሳይሆን የቅንዎችንም ጆሮ መጥለፉ የሚጠበቅ ነው። የምናምናቸው፡ ለኢሳት አወንታዊ አመለካከት ያላቸው የቅርብ ጓደኞቻችን ሳይቀር ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ የአፈናው ክስ አንገታቸውን እንዳስደፋቸው በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹት ታዝቤአለሁ። አልፈርድባቸውም። እውነቱ ግን ምንድን ነው? በኢሳት አፈና ተፈጽሟልን?
በኢትዮጵያ የተከሰተው ለውጥ የኢሳት ባልደረቦችን በተለያየ አቋም እንዲሰለፉ ማድረጉ የአደባባይ እውነት ነው። ለኢትዮጵያ መልካም እድል ይዞላት መጥቷል በሚል ስሜት ለውጡን የደገፉት በአንድ ወገን ሲቆሙ፡ ለውጥ የለም፡ ነውጥ ነው ብለው ገና ከጅምሩ እርግማን ማዝነብን የመረጡት ደግሞ በሌላ ወገን ተሰልፈዋል። መሀል ላይ ወዲህና ወዲያ የሚመላለሱም እንዳሉ አውቃለሁ። ምናልባት እኔ ከዚህኛው መሀል ላይ ከቆመው ቡድን ልሆን እንደምችል እገምታለሁ። ይህ ሁኔታ የኢሳትን አካሄድ መላቅጡ የጠፋበት እንዲሆን አድርጎታል። ከአንድ የሚዲያ ተቋም ወጥነት የሌለው፡ ፍጹም አራምባና ቆቦ የሆኑ መልዕክቶች መተላለፋቸው በአድማጭና ተመልካቹ ዘንድ ውዥንብርን ፈጥሯል። ለኢሳት ክፉና አደገኛ ፈተና ሆኖ ተደቅኗል። ምንም እንኳን የሀሳብ ልዩነት በሚል የቁልምጫ ስም በመግለጽ ልዩነቱን የደገፉ ተመልካቾች ቢኖሩም አጠቃላይ የተቋሙ አካሄድ በኢትዮጵያ በሚታየው ያልተረጋጋ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ሚና ይዞ ቀጠለ። ሀገሪቱ የገባችበትን ቀውስ የሚያራግብ፡ በቋፍ ላይ የሚገኘውን አንድነት የበለጠ የሚያናጋ፡ ኢሳትን ከተቋቋመለት ዓላማና መርህ ጋር የሚያላተም ሆኖ አረፈው።
ይህ አካሄድ የሆነ ቦታ መስተካከል እንዳለበት በየጊዜው በስብሰባ ላይ ይነሳል። ኢሳት በከፍተኛ ደረጃ በሶስቱም የገቢ ምንጮቹ ላይ ኪሳራ እየገጠመው የመጣው በዚሁ ወጥነት በሌለው፡ ቀውስ በሚያራግብ የሚዲያ አቅጣጫችን መሆኑ ለሁላችንም የተገለጠ ሀቅ ነበር። በተለይ ከሀገር ቤት የሚደርሱን የህዝብ አስተያየቶች አካሄዳችንን በአስቸኳይ አስተካክለን ሃላፊነት የሚሰማውና፡ ወቅቱን የሚመጥን የሚዲያ ፖሊሲ እንዲኖረን የሚጠይቁ ነበሩ። ከማንኛውም ወገን ተጽዕኖ የሌለውና በነጻነት የሚንቀሳቀሰው የኢሳት ኢዲቶሪያል ኮሚቴ ይህን የመወሰን ስልጣን ቢኖረውም ሁሉም የኢሳት ባልደረቦች የሚሳተፉበት ተደጋጋሚ ምክክር አስደረገ። አያሌ ስብሰባዎች ተከናወኑ። ሁለቱን ወገኖችን ለማቀራረብ የሚያስችሉ አካሄዶች ላይ ሰፊ ውይይቶች ተካሄዱ። በመጨረሻም የኢሳትን አቅጣጫ የሚወስን ስምምነት ተደረሰና ሁላችንም የምንገዛበት ኢዲቶሪያል ፖሊሲ ተቀረጸ።
በአጭሩ የፖሊሲው ሀሳብ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ከግንዛቤ ያስገባ ሚዛናዊ፡ እውነተኛ ዘገባና ትንተናዎች እንዲሰጡ የሚያደርግ አቅጣጫ ነው። የፖሊሲው ዋና መገለጫም እውነተኛና ህዝብን ከህዝብ የማያጋጩ ዘገባዎችን ማቅረብ በሚል ሊቀመጥ ይችላል። ከፍጹም ውዳሴና መረን ከለቀቀ እርግማን በመውጣት የለውጡ ሃይሎችን ክፍተት በእውነተኛ መረጃዎች እየጠቀሱ፡ ከስሜት በጸዳ ትንተና ለህዝብ ማቅረብ የፖሊሲው ዝርዝር ሀሳብ ነው። ላለፉት ስምንት ዓመታት በመጣንበት መንገድ መቀጠል እንደማንችል በደማቁ አስምረን ኢትዮጵያን ከተደቀነባት አደጋ ለማዳን ኢሳት ወቅቱን የሚመጥን የሚዲያ ቁመና እንዲኖረው ተስማማን። ይህ የሆነው በህዳር ወር ላይ እንደሆነ አስታውሳለሁ።
እንግዲህ የአፈናው ትርክት የሚጀምረው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው። አሁን ‘’ተገፋን’’ ‘’አፈና ተፈጸመብን’’ የሚል ስሜት ኮርኳሪ ክስ ይዘው አደባባይ የወጡት የኢሳት ባልደረቦች ለተስማሙበት ፖሊሲ ባለመገዛት ያልተጣሩ፡ በቅጡ ያልተፈተሹ ዜናዎችን፡ ትንተናዎችን ማቅረባቸውን ቀጠሉበት። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የበረከተው ጭብጨባ ጠልፏቸው የወሰዳቸው እነዚህ ባልደረቦች ኢሳትን የለውጡ ሃይሎች መምቺያ መሳሪያ እንዲሆን የሚያስችል መስመር ላይ ወጥተው ግስጋሴአቸውን ቀጠሉ። በህወሀት ዘመን ያደረግነውና ትግሉን ይጠቅማል ብለን ያካሄድነውን የሚዲያ እንቅስቃሴ በመድገም፡ ኢትዮጵያን ከአደጋ ከመታደግ ይልቅ ይበልጥ ቀውስ የሚያራግብ አቅጣጫ ይዘው ነጎዱ። ይህን የሚያደርጉት ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነትና አንደነት ሲሉ እንደሆነ ይነግሩናል። እኛን ወይም በወዲህ ያለነውን ከለውጡ ሃይሎች ጋር ወዳጃሞች እንደሆነን አምነው፡ በሴራ የተለበጡ፡ ከአሉባልታ ከረጢት የሚመዘዙ የሀሰት መረጃዎችን በእጃቸው ሞልተው፡ ለእኛ ታፔላ በመለጠፍ፡ የእነሱን አካሄድ ግን የኢትዮጵያን ትንሳዔ የሚያበስር አድርገው በመውሰድ ቀጠሉ። የምር ለሀገርና ለወገን አሰበው ነው? አይደለም ብዬ በድፍረት አልናገርም። የከፈሉት ዋጋና የጀርባ ታሪካቸው ስለሀገራቸው ብዙ ቀናና መልካም ስሜት እንዳላቸው አሳምሬ አውቃለሁ። ለምን ይህን መስመር እንደተከተሉ የሚናፈሱትን አሉባልታዎች ባላምን እመርጣለሁ።
እንግዲህ ለተስማሙበት ኢዲቶሪያል ባለመገዛት ኢሳትን የጸረ ለውጥ ሃይሉ ልሳን አድርጎ መቀጠል የመረጡት እነዚህ ባልደረቦቻችን ይህን ማድረጋቸው ለመርህ ተገዥነት፡ ለእውነት ዘብ መቆም እንደሆነ አድርገው ጭምብል አጠለቁለት። ለውጡን ማንኳሰስ በእነሱ መዝገበ ቃላት ውስጥ ‘’የመርህ ሰው’’ የመሆን ትርጉም ተሰጠው። የዶ/ር አብይን እግር እየተከታተሉ በየቀኑ መቀጥቀጥንም ‘’ለእውነት የቆሙ’’ ለመሆናቸው ማረጋገጫ አድርገው ወሰዱት። መብታቸው ነው። ኢሳት ግን በየቀኑ እየሞተ ነበር። በተለይም የተወሰንን ባልደረቦች ወደ ኢትዮጵያ መሄዳችንን ተከትሎ ሜዳውንም ፈረሱንም ያገኙት እነዚህ ‘’የመርህ ሰዎች’’ ያለከልካይ የኢሳትን አቅጣጫ እነሱ በቀረጹት መልክ ይዘውት ከፍ ብለው ወጡ። በአዲስ አበባ ቆይታችን የምንከታተለው ኢሳት እኛ የኖርንበት እስከማይመስለን ድረስ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍርሃት ውስጥ የሚከቱ፡ ፍጹም ሃላፊነት የራቃቸው የዜናና የትንታኔ ዝግጅቶች መለቀቃቸው በጉዞአችን ላይ ሳይቀር ችግሮችን ደቀኑብን። ከዚያ ሆነን ‘’አረ በህግ አምላክ’’ ብለን ብንጮህ የሚሰማን አጣን። ይባስ ብሎም አዲስ አበባ የሄዱት ስኳር ቀመሱ፡ ቤተመንግስት ተጋበዙ፡ የሚል አሉባልታዎችን ይዘው ስማችንን በሚያጎድፍ፡ ክብራችንን በማይመጥን መልኩ ፈረጁን።
በኢትዮጵያ ቆይታችን ከ10 በላይ ያልተረጋገጡ፡ አንዳንዶቹም ፌክ የሆኑ መረጃዎች በዜና መልክ በኢሳት ተላለፉ። በዕለታዊ ፕሮግራም የለውጡ ሃይል ላይ ዘመቻ የከፈቱ ትንተናዎች በየቀኑ ቀረቡ። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ባለው የለውጥ ሃይል ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበትና በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ተመልሶ እንዲገባ በማድረግ ረገድ የኢሳት ሚና የአንበሳው ድርሻ ሆኖ አረፈው። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰጥ ላይክና ሼር መለኪያ ተደርጎ የኢሳት ስኬት በዚሁ እየተመዘነ ይገለጽ ጀመር። ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የፈሰሰው ዲጂታል ሃይል የፈጠረው ሙቀት የባልደረቦቻችንን አይኖች ሸበበው። ይህም መሬት ያለውን እውነታ እንዳያዩት አደረጋቸው። ኢሳት መስመሩን ሳተ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ባለውለታ የሚለው መታወቂያው እየደበዘዘ መጣ።
ከኢትዮጵያ መልስ ይህ ነገር መቀጠል እንደሌለበት በማመን ድጋሚ ስብሰባዎችን ማድረግ ጀመርን። በሁለት ቀናት ስድስት ሰዓታት የፈጁ ሰፊ ስብሰባዎች ተደረጉ። የህዳር ወሩን አዲሱን የኢዲቶሪያል አቅጣጫችንን እንድናከብር ጥብቅ የሆነ አቋም ተያዘ። ከኢሳት ቦርድ የተወከለው አቶ ነአምን ዘለቀ በተገኘበት ግልጽ የሆነ የኢሳት አካሄድ በድጋሚ ስምምነት ላይ ተደረሰበት። ቦርዱ ኢሳት ሚዛናዊና እውነተኛ መረጃዎችን በማቅረብ የለውጡን ሃይል መተቸት እንደሚችል በመግለጽ ጋዜጠኞቹ በሃላፊነት እንዲሰሩ አቅጣጫውን አሳወቀ። ከህዳሩ ስምምነታችን የተለየ አልነበረም። ለሁለተኛ ጊዜ ቃል ገብተን ስምምነታችን በድምጽ በተቀረጸ ቃለ ጉባዔ የተረጋገጠበት ፖሊሲ እንድንከተል ተወሰነ። ምን ዋጋ አለው?! ይህም ስምምነታችን ሊፈርስ አንድ ሌሊትን እንኳን እድሜ አልነበረውም። የስምምነታችን ፊርማ ሳይደርቅ የዚያኑ ቀን እነዚህ ባልደረቦቻችን በጀመሩት መንገድ ቀጠሉበት። እርግማኑን አጠናክረው ገፉበት። ቀውስ ተኮር የሚዲያ ፕሮፖጋንዳውን በእጥፍ ጨምረው ብቅ አሉ።
የዚህን ጊዜ ነው እንግዲህ ስልጣንና መብት ያለው የኢዲቶሪያል ኮሚቴ ፖሊሲውን ሊያስፈጽም ጡንቻውን ማፍታት የጀመረው። ኢሳት በከፍተኛ የገንዘብ ችግር ከወዲህ ወዲያ እየተላተመ፡ በአካሄዱም ሀገር ላይ ቀውስን እያቀጣጠለ መሄዱ ለሁላችንም ጥሩ ጊዜ ከፊታችን እንደማይኖር ታውቆናል። እናም በኢዲቶሪያል ውስጥ የምንገኝ አባላት ፖሊሲውን ለማስፈጸም ተንቀስቀስን። ይሄን ጊዜ ነበር ‘’የአፈና’’ ትርክቱ ስጋና አጥንት ለብሶ መቆም የጀመረው። በአጭሩ ‘አፈና’ በሚል ኢሳትን በአደባባይ ለእርድ ያቀረቡት ባልደረቦች የተስማሙበትን የኢዲቶሪያል ፖሊሲ ለመገዛት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ለማሳየት የመዘዙት የሽፋን ክስ ነው። አይሆንም እንጂ እንደምኞቱማ በኢሳት ፍርስራሽ ላይ የራስን ሚዲያ ለመገንባት ለወራት የዘለቀውን እቅድ ለማስፈጸም የተቀናበረ የሀሰት ድራማ ነው። አንድ እግሩን ኢሳት ውስጥ ሌላኛውን ከውጭ አድርጎ ለወራት አድፍጦ የቆየ ሰው ይህቺን አጋጣሚ ኢሳትን በማዋረድ ሊጠቀመባት መፈለጉን የማናውቅ የመሰለው ካለ ጅሎቹ እኛ አይደለንም። (ይቀጥላል)
Filed in: Amharic