>

እየደመሩ ማፍረስ፤ እያፈረሱ መደመር ( ያሬድ ሀይለማርያም)

እየደመሩ ማፍረስ፤ እያፈረሱ መደመር
ያሬድ ሀይለማርያም
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት ከአንድ ፓርቲ ህልውና፣ ውህድ መሆን ወይም ፍቺ ጋር መያያዙ እጅግ ያሳዝናል። ኢህአዴግ ዛሬ አጋሮቹን በውህድ የሚደምርበት፤ መስራቿን ህውሃት የሚቀንስበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የህውሃትን መደመርም ሆነ መቀነስ የድርጅቶች ጉዳይ ብቻ አድርጎ ማየት የዋህነት ብቻ ሳይሆን አገሪቱ የተደገሰላትንም በቅጡ አለመረዳት ይመስለኛል።
የኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ መሆን ለአገሪቱ ፖለቲካ መሻሻል ትልቅ ፋይዳ ያለውን ያህል ውህዱ ሁሉኑም የድርጅቱን አካላት አሳፍሮ መቀጠል አለመቻሉ ደግሞ ብዙ መዘዞች እንዳሉት በቅርቡ “የኢህአዴግ ውህድ መሆን እንድምታዎቹ” በሚል አጭር ጽሑፍ በዝርዝር ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ። አንዱ መዘዝ እንግዲህ ሰሞኑን ከመቀሌ የተሰማው የde facto state ሆኖ መቀጠል ጉዳይ ነው።
ብዙዎች እንደ ሰበር ዜና ሲያወሩት አስገርሞኛል። ትግራይ እኮ de facto state  ከሆነች ውሎ አድሯል። የፌደራል መንግስቱ በትግራይ ላይ ሥልጣኑን ካጣ ቢያንስ ከአመት በላይ ሆኖታል። ይህንን በተደጋጋሚ በጽሁፎቼም ውስጥ አንስቼዋለው። የአብይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ትግራይን እንደማይጨምር ብዙ ምልክቶችን እኮ ስናይ ቆይተናል። ትግራይ ላለፉት ሁለት አመታት በህውሃት እና በህውሃት ብቻ ነው ስትተዳደር የቆየችው።
ዲፋክቶ ስቴት ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችሏት ነገሮችም ቀድሞውንም የተመቻቹላት እና የተሟሉላት ክልል ነች። የታወቀ ድንበር ወይም አከላለል (a defined territory), የታወቀ የክልሉ ነዋሪ (a permanent population)፣ በመንግስት ቅርጽ የተዋቀረ መንግስታዊ አስተዳደር (a government) እና ከሌሎች አገሮች ጋር የመደራደርና ግንኙነት የመፍጠር አቅም ያለው (a capacity to enter into relations with other states) በቅርቡ የክልሉ መንግስት አዲስ አበባ የሚገኙ የውጭ አገር ቆንጽላዎችን መቀሌ ድረስ ጋብዞ ያደረገው ውይይት ይህን አቅም የማሳያ አንዱ ምልክት ይመስላል።
እኔ ዛሬ ከአብይም ሆነ ለውጡን ከሚመሩት ሰዎች ብሰማ ደስ የሚለኝ ከዚህ ውህደት በፊት ትግራይን ወደ መሃል ለማምጣት እና ውጥረቱን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሸምጋዮች ለመፍታት የሄዱትን እርቀት እና ያደረጉትን ጥረት በዝርዝር ቢያስረዱኝ ነው። ለእኔ እንደሚገባይ ከሄዳችሁም ሂዱ የሚለው መንገድ ቀድሞም የተመረጠ ይመስላል። እንዲያ ከሆነ ከህውሃት ጋር ዛሬ የሚደረገው ውይይት ስንብቱን በግላጭ ማድረግ ብቻ ነው።
የኢህአዴግ  ወደ ህብረብሔራዊ ውህድ መሄድ ለአገር ሊበጅ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ይህ ተስፋ በተሳካ ሁኔታ እውን ሊሆን ይችል የነበረው ህውሃትንም ባካተተ መልኩ ቢሆን ነበር። የህውሃት ማፈንገጥ አንድም ቀድሞውንም ድርጅቱ በግማሽ ልብ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ በይደር ያቆየውን የመገንጠል ህልም እውን ለማድረግ ይህን የውህድ ክስተት እንደ ገፊ ምክንያት የወሰደው ይመስላል። አለያም ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዳትቀጥል እና በቅርቡ መቀሌ ላይ እነ ፕ/ር እስቂየል እና በቀለ ገርባ ሲዶልቱበት የነበረውን የኮንፌዴሬሽን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ያለመ ነው የሚሆነው።
የኮንፌዴሬሽን ፕሮጀክት አካል ከሆነ ገና ስንናጥ መክረማችን ነው። የትግራይን ፈለግ የሚከተሉ እና እራሳቸውን እያሟሟቁ ያሉ ብዙ ኃይሎች አሉና። ለማንኛውም፤
+ ህውሃት ከውህዱ ካፈነገጠች ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል እና በቀረው የአገሪቱ ክፍል መካከል ያለው ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል?
+ ህውሃት ትግራይን አሳልፎ ይሰጣል ወይ? ነጻ ምርጫ በክልሉ ውስጥ እንዲካሔድ ይፈቅዳል ወይ?  ካልፈቀደስ?
+ የትግራይን ሕዝብ ከህውሃት ማን ነው የሚያላቅቀው? ወይስ እራስህን ነጻ አውጣ ተብሎ ይተዋል?
የፓርቲ ህልውና እና የአገር ህልውና በአንድ ቅርጫት ውስጥ ሲቀመጥ መዘዙ ብዙ ነው። ያ ደግሞ ሆነ ተብሎ ለብዙ አመት የተሰራበት ትልቅ ፕሮጀት ነው። እንግዲህ ቀጣይዋን ኢትዮጵያ ምን ትመስል ይሆን?
ኢትዮጵያ ዛሬም የሕዝቦቿ አልሆነችም። ጥቂት ግለሰቦች እና ድርጅቶች በቁመናዋ ላይ፣ በወደፊት እጣ ፋንታዋ ላይ፣ በሉአላዊነቷ ላይ፣ በሕዝቧ ኑሮ ላይ በር ዘግተው ይወስናሉ።
Filed in: Amharic