>
8:38 am - Saturday December 10, 2022

ቤተመንግሥት ላይ ምን አይነት ምልክት ይቀመጥ? (ታዬ ደንደአ)

ቤተመንግሥት ላይ ምን አይነት ምልክት ይቀመጥ?

ታዬ ደንደአ
 
1. አንበሳ፦ ከሞዓ አንበሳ ጋር ተያይዞ አሉታዊ ስሜት ሊፈጥር ከመቻሉም ሌላ የ80ውን ብሔረሰብ እሴቶች ሊያንፀባርቅ ባለመቻሉ እረፍት አልባ ንትርክ ያስነሳል።
2. ግመል፦ አርብቶ አደሩን በሚገባ ሲወክል፤ ደጋውን ወገን ያገላል። ግመልን ለማይመገቡ ወገኖች ሌላ ትርጓሜ ያሰጣል።
3. የመደመር ምልክት፦ ቢደረግ በእርግጠኝነት ክርስትናን ለማጉላት ነው የሚል የማያባራ ሙግት ይፈጥራል።
***** ለዚህ “ቡራቡሬ” ወገን የሚመጥነው ቡራቡሬ ምልክት ነው።
*
ፒፎውል (ፒኮክ/ ፒሄን)
1. ቡናማ ቀለም ያላት ፍጥረት ስትሆን ብርሀን ሲያርፍባት የተለያዩ ህብረቀለማትን ታመነጫለች (80 ብሔረሰብ + የተለያዩ እምነቶች + የፖለቲካ አመለካከቶች + ፆታዎች…)
2. ይህንን ውበት ይዘው ፍጥነታቸው በሰአት ከ10_16 ኪሎሜትር ሲሆን (በሉላዊነት ዘመን ለጊዜው በዚህ ፍጥነት ብናድግ ይበቃናል)
አደጋ ሲያጋጥማቸውም በከፍታ መብረር ይችላሉ።
3. ቤተመንግሥቱ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ያስተናግዳል። በአንዳንድ የዓለም ሀገሮች “ፒፎውል / ፒኮክ”፦ የትህትና የደግነት የዕውቀት የጥበብ ወዘተርፈ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ሂንዱይዝም ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ ነው።
4. ፒፎውል፦ 11 የተለያዩ ድምፆችን በማውጣት በርካታ አይነት ጥሪዎችን የማድረግ ብቃት አላቸው። እነዚህ ድምፆች ሲነጋና ሲመሽ እርስበርስ በመጠራራት ድንቅ መስተጋብር የሚያደርጉበት ነው። እኛም በመልካም እና በአደጋ ጊዜ በወል ቆመን ማለፍ እንዳለብን ያመለክታል። ጥሪዎቹ ፍቅርንና በአደጋ ጊዜ መጠንቀቅንም አመላካቾች ናቸው።
5. ፒኮኮች፦ በአደጋ ጊዜ ኃይለኛ ተዋጊዎች ናቸው። እባብን ሳይቀር ቀጥቅጠው የመግደል ድንቅ ብቃት አላቸው። መርዘኛ እባቦችን የማጥፋትና ወደ ግዛታቸው እንዳይገቡ መከላከል ላይም የሚደነቅ ብቃታቸውን አስመስክረዋል።
6. ፒፎውል፦ ከሰዎች ጋር የመቀራረብ እና የመሰናኘት ልዩ ሁኔታ አላቸው። አፍቃሪ የመሆናቸውን ያህል ከነኳቸው አፀፋዊ ምላሻቸው ጠንካራ ነው።
7. ህብረቀለማት፦ ሰማያዊ አረንጓዴ  ቡናማ ወርቃማ ቀይ… ቀለማትን የተላበሱ ልዩ መስህብ ያላቸው ናቸው።
8. ስጋንም ሆነ ዕፅዋትን የሚመገቡ Omnivores መሆናቸው በራሱ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ።
ከዚህም አልፎ አያሌ መዘርዝሮችን መተንተንና ማስተንተን ይቻላል።
መከራከሪያው ከኢትዮጵያውያን እሴት ጋር አይገናኝም ከሆነ፤ የትኛው ነው የሚገናኘው? ብሎ መሰነጣጠቅና ጥላቻ ማመንጨት አይከብድም። አስቸጋሪው በጥበብ ፍቅርን መመሥረት ነው።
*
አንበሳ፦ የመስበር የማድቀቅ ምልክት ሆኖ፦
“ዘራፊ ማልአባሺ ወዲ-ሰበይቲ” ማለት ለለመደ ቁምነገርና ፍቅር አይጥመውም።
*
በዚህ ዙሪያ መፃሕፍት ማዘጋጀት ቢቻልም።
ቤተመንግሥቱ በር ላይ ብቻ ነው ያለው ማነው?!
መንግሥት የሚኖርበት ዋና ቤት አለ።
የእምዬ ምኒልክ ቤተመንግሥት አለ። በዚህ ውበት ላይ ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ሥፍራዎች እና ቅርሶች ከረቂቅ መልዕክት ጋር በአቢቹ “ተደምረው” እኚያውልህ!!! መሥራት ባትችል ግባና ጎብኝተህ፤ ውበትን ማድነቅ የሚችል ህሊና ካለህ ብቻ አድንቅ! (መንገድ ላይ ሱሪ ከመፍታትና ወገብ ከመፈተሽ ሳትላቀቅ – አቃቂር ለማውጣት አትውተርተር።)
*
የቤተመንግሥቱን በር አልፈህ ገብተህ ከብፌው አድንቀህ መሸመት ይከብድሀል። የትየለሌ ድንቅ ውበት!!!
ምንድነው ከአምስት  ሜትር ባነሰ በር ላይ ተገትሮ፤
2ኪሎሜትር × በ1.5ኪሎሜትር የሆነ፤ የ6,000 ዘመን ታሪክ የሚንፀባረቅበት ቤተመንግሥት መተቸት?!
የአንበሳ ፍቅር እንዲወጣልህ እዚያው ቤተመንግሥቱ ፓርክ ውስጥ ህያው አንበሶች አሉ። ዋሻ ጭምር…  ከሰው ስጋ እየከጀሉ፤ አሥረን የምንዝናናባቸው።
ኧረ ግመልም ከፈለግህ በቅርፅ ተውቦ አለልህ!!! (ካስፈለገ የአዲስ አበባ አየር ከተስማማው ከነነፍሱ ማስገባት ይቻላል።)  ይጠናቀቅና ትርጉሙም ከነሥፍራው ይገለፅ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይን የሥልጣን ዘመን ይባርክ። አትራፊ ሀገርና ህዝብ ናቸውና!
Filed in: Amharic