>

ኦህዴድና ብአዴን የተሳለላቸውን ካራ ከሩቁ ማየት አለባቸው (ያሬድ ጥበቡ)

ይሄ የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት መንስኤ ከወያኔ ብልጥ ፍላጎት የመነጨ ነው። ወያኔ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ተሰሚነት በተሸረሸረ ቁጥር ሌሎች አማራጭ ህጋዊ ጠለላዎችን ሲፈትሽ ሁለት አመታት ሆነው ። አንዱ ጠለላው ውሳኔዎችን ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በማውጣት፣ በሌሎች አማራጭ መዋቅሮች መተካት ነው ። ለዚህም የድምፅ የበላይነት የሚያገኝበትን የአናሳ ብሄረሰቦች መዋቅር ይጠቅመኛል ብሎ አሰላሰሏል ። ይህንንም ለማዘጋጀት በቀዳሚነት የሱማሌን፣ ቀጥሎም የቤኒሻንጉልና ጉሙዝ፣ ሐረሪ፣ ጋምቤላና አፋር ክልሎችን ሲያሽኮረምም ነው የከረመው ። በነዚህ ላይ ብዙም የማይተማመንበትን የደቡብ ክልል መጠነኛ ድጋፍ ካገኘ፣ የበላይነት እንደሚኖረው አስልቷል ። በአንዳንድ ተንታኞች ግምት፣ እንዲያውም ለሱዳን ተሰጠ የሚባለው መሬት ወደፊት ትግራይ ስትገነጠል ትግራይንና ቤኒሻንጉልን የሚያገናኝ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግልና፣ ትግራይ በአደራ የሱዳን የመሬት ባንክ ውስጥ ያስቀመጠችው ሃብት ነው የሚሉ አልታጡም ።

ለማንኛውም፣ አሁን ኦህዴድና ብአዴን የተሳለላቸውን ካራ ከሩቁ ማየት አለባቸው ። የደህንት ምክርቤቱ በጋራ ከመምከር ያለፈ ምንም አይነት የመወሰንም ሆነ ረቂቅ ለውሳኔ የማቅረብ መብት የለውም ብለው ፀንተው መቆም ይኖርባቸዋል ። አቅሙና ዝግጅቱ ካላቸው፣ እንዲያውም በውስጡ ያለመሳተፍ መብት እንዳላቸው ሊያውቁ ይገባል ። ከዚህ የወያኔ ብልጠት መማርም ካለባቸው ነገሮች አንዱ፣ እነዚህ የውሁዳን ብሄረሰቦች ክልሎች፣ ለወያኔ መጋለቢያ ብቻ የሚተው እንዳልሆኑና፣ ከወያኔ ተፅእኖና ፍርሃት እንዲወጡ ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ማወቅ ነው ። በተለይ ከ42 በላይ ብሄረሰቦችን የሚያቅፈውን የደቡብ ክልልና ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ተገቢው ጥረት ሳይደረግ እንደወያኔ መፏለያ ሜዳ መተው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ደቡብ ወደለውጡ ሰፈር እንዲቀላቀል ተገቢው ትግል መካሄድ ይኖርበታል ።

ወያኔ፣ ህጋዊ የመዋቅር ለውጥ በማድረግ የድምፅ የበላይነት የሚያገኝባቸው በሮች ሲዘጉበት ወደ ወታደራዊ አመፅ ለመሸጋገር መወሰኑ አይቀርም ። ይህ እንዳይሆን ኦህዴድና ብአዴን በመከላከያውና ደህንነቱ ውስጥ ያሏቸውን መካከለኛና ዝቅተኛ መኮንኖች እንዲሁም ሰፊውን የጦር ሃይል የለውጡ አካል ለማድረግ አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ። ለዚህም ትልቁ መሳሪያቸው በክልሎቻቸው ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃኖች ናቸው ። የተጀመረው በረጅምና ሰላማዊ የውስጠ ድርጅት ትግል በመጀመሪያ ኢህአዴግን ቀጥሎም ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ትግል በመሆኑ፣ ቢቻል ደህንነቱና መከላከያው ከፖለቲካ ውጪ ቆመው የሃገር ዳር ድንበር የማስጠበቅ ተልእኳቸውን እንዲወጡ፣ ይህን ማድረግ የሚያስችል የቆየ አደረጃጀት ከሌላቸው ግን የለውጡን ሠፈር እንዲቀላቀሉ መቀስቀስና ማዘጋጀት ያስፈልግ ይመስለኛል ።

የኦህዴድና ብአዴን መሪዎች አሁን እንቅልፍ፣ እረፍት የሚሹበት ወቅት አይደለም ። ከመቐለ ሲዘገብ እንደምሰማውና፣ በራሴም ልምድ ከማውቀው፣ የወያኔ መሪዎች ቀን ቀን የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፣ ማታ ማታ ደግሞ የፖሊትቢሮና የቀድሞ ጎምቱ መሪዎች የጋራ ስብሰባ እየተካሄደ፣ ሳይተኙ እየሰሩ ነው ። የኦህዴድና ብአዴን መሪዎች ያንን የሚመጥን ትብአትና ጥንካሬ ካልኖራችሁ በራሳችሁ ላይ አደጋ ነው የምትጋብዙት ። ለጥቂት ጊዜ ለመጎዳት መወሰን ይኖርባችኋል ። ምናልባት ወደ ቤተሰቦቻችሁ መሄድ እንኳ የማትችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ። ይህን ለጊዜው ተቀበሉት ። ቀን እስኪያልፍ ያለፋል አይደል የተባለው? ቻሉት ወንድሞቼ!

ከዞኖች በቀጥታ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን አቋርጡ ። ደህንነትን በሚመለከት ከፌዴራሉ ጋር ያለው ግንኙነት፣ በክልሉ ፕሬዚደንት ቢሮ ስር ብቻ አንዲሆን አድርጉ ። መረጃ ላይ ያላችሁ የበላይነት ወሳኝ ነው ። በዚህ ላይ አትደራደሩ ። የያዛችሁት የለውጥ እንቅስቃሴ ወደሞት ሽረት ትግል ሊያመራ ስለሚችል፣ በመረጃ ላይ ቁጥጥር ያለው የሚያሸንፍበት ሂደት መሆኑን ተረዱ ።

ከመረጃው ቁጥጥር ተለይቶ የማይታየው የክልሉና ብሄራዊ ድርጅቶቹ አመራር ተዋፅኦ ጉዳይ ነው ። ኦህዴድ ውስጥ ይበልጥ አስተማማኝ እየሆነ የመጣ ቢሆንም፣ ብአዴን ውስጥ ገና ስር አልሰደደም ። አሁንም እነ ታደሰ ጥንቅሹ የማይናቅ ቦታ ይዘው ይገኛሉ ። ብአዴን ውስጡን ከወያኔ ተላላኪዎች ማፅዳት ይጠበቅበታል ። መዘግየት ዋጋ እንደሚያስከፍልም እነ ገዱ መረዳት ይኖርባቸዋል ። ከአመራሩ እውቅና ውጪ ከወያኔ ጋር በግል የሚገናኙና መረጃና መመሪያ የሚያቀብሉ የብአዴን አመራር አባላት፣ በዚህ ተግባራቸው እንዳይቀጥሉ የሚከለክል ውስጣዊ አሰራር (ማእቀብ)፣ ሰላማዊ ትግሉ አስተማማኝ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል ። ዝርዝሩን ለእናንተ እተወዋለሁ። ከኢህዴን ታሪክ መማር ያለባችሁ ብቸኛ ትምህርት ቢኖር፣ እነ ታምራትና ታደሰ የኢህዴን አመራር የማያውቀው የፒ አር ሲ 77 ሬዲዮ ግንኙነት ከመለስ ጋር የነበራቸው መሆኑ፣ የኢህዴንን ነፃነት ለመጋፋትና ድርጅቱን ወያኔ እግር ስር እንዲወድቅ ለማድረግ የተጠቀሙበት መሆኑን ነው ። ከራሳችሁ ታሪክ ተማሩ!

በመጨረሻም፣ ወያኔ ህጋዊነት ወደሌለው የብሄራዊ ደህንነት መዋቅር የሄደው በፓርላማው ውስጥ የበላይነት ሊኖረኝ አይችልም ብሎ ስለሰጋ ነው ። ከዚህ መማር ያለባችሁ፣ የፓርላማ መድረኩን መጠቀም ህጋዊ ትግሉን እያጎለበተው የሚሄድ መሆኑን ነው ። በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውስጥ ያላችሁን የድምፅ የበላይነት ተጠቅማችሁ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ውሳኔዎችን አሳልፉ ። ህዝቡ በናንተ ላይ ማሳየት የጀመረውን ተስፋ ወደ ድጋፍ ለመቀየር የሚችሉ የፖለቲካና ህጋዊ ውሳኔዎች ሁሉ በማከታተል አሳልፉ ። ለምሳሌ ፓርላማው የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በመወሰን፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ በቀለ ገርባ፣ መረራ ጉዲና ወዘተን ያካተተ የስም ዝርዝር ለፕሬዚደንቱ በማቅረብ አሁኑኑ በምህረት እንዲለቀቁ ማድረግ ይችላል ። ይህ ሁሉ የተወካዮች ምክርቤት ተግባር እንዲከናወን ግን፣ የጄኔራል አባዱላ ገመዳ አፈጉባኤ ሆኖ መቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነው ።

 አባዱላ ዱሮ በበረሃ፣ አሁን ደግሞ “የምወክለው ድርጅትና ህዝብ ሲንቋሸሽ ዝም ብዬ አላይም” በማለት ከሞት ጋር ተጋፍጠዋል ። ይህ ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ችሮታ ነው ። የሚያኮራ ገድል ነው ። እንዲህ ሞትን የደፈረ ቆራጥ የፓርላማው አፈጉባኤ ሆኖ መቀጠል ወሳኝ ነው ። ተረባርባችሁ፣ አባዱላ ራሳቸው ያስገቡትን የሥራ መልቀቅያ ማመልከቻ እንዲስቡት ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ይመስለኛል ። እርሳቸው ፈቃደኛ ባይሆኑ እንኳ ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ በሥራቸው እንዲቀጥሉ ማድረግ ይጠቅማል ባይ ነኝ። ጊዜን ሥሩበት እንጂ፣ እይሥራባችሁ! አይዟችሁ! የኢትዮጵያችን ትንሳኤ በእጃችን ነው።

Filed in: Amharic