>

የናይል ሸለቆ ፖለቲካ፣ ታሪካዊ ምልከታና ዛሬ ያለንበት ተጨባጩ እውነታ (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የናይል ሸለቆ ፖለቲካ፣ ታሪካዊ ምልከታና ዛሬ ያለንበት ተጨባጩ እውነታ

ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


ከቪክቶሪያ ሀይቅ የሚነሳወ ነጭ አባይ እና ከኢትዮጵያ ጣና ሀይቅ ከፍተኛ ቦታዎች የሚነሳው ጥቁር አባይ ሱዳን መዲና ካርቱም ላይ ሲገናኙ ታላቁን የናይል ወንዝ እንደሚፈጥሩ የመልክአ ምድር አጥኚዎች ያስተምሩናል፡፡ በሌላ አነጋገር ከ86 ፐርሰንት በላይ የውሃ መጠን የሚይዘው አባይ ወንዝ ካርቱም ሲደርስ መጠሪያው ናይል በመባል ይቀየራል፡፡ በነገራችን ላይ የናይል ወንዝ በምድራችን ላይ ከሚገኙት ወንዞች ሁሉ ታላቁ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይህ ለአካባቢው ሀገራት ህብረት መጠናከርና ለልማት በእጅጉ ጠቃሚ የሆነ ወንዝ  ከቅርብ ግዜ ወዲህ የግጭት መንስኤ ወደ መሆን እያዘነበለ ይገኛል፡፡ የንትርክና ውዝግብ ማእከል ሆኗል፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው የኤፍራትስ እና ቲግሪስ ወንዞች በኢራቅ፣ ያንግቲዝ ወንዝ በቻይና፣የሚሲሲፒ ወንዝ በተባበረችው አሜሪካ የስልጣኔ ምንጭ እንደነበሩት ሁሉ፣ የናይል ወንዝም የስልጣኔ ማእከል  እና የሃይል ምንጭም ነበር፡፡ ስለ ናይል ወንዝ የሚያወሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው  ልብወለድ እና ታሪካዊ መጽሐፍት ለብዙ ክፍለ ዘመናት ተጽፈዋል፡፡ ቅኔዎች ተቀኝተዋል፡፡ የናይል ወንዝ አካባቢ ሀገራት የሀይል ሚዛናቸውን ለማስተካከል ከጥንት እስከዛሬ አሉ፡፡ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጡንቻቸውን ለማፈርጠም የሚሄዱበት መንገድ እሩቅ ነው፡፡ በተለይም የግብጽ የአካባቢው ሃያል ሀገር ለመሆን በብዙ ባጅታለች፡፡ በጥንት ዘመን ደግሞ ኢትዮጵያ ግብጽን በሃይል ትገዳደርበት በነበረበት ዘመን የናይል ወንዝን እንደማስፈራሪያ ትጠቀምበት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ330 በኋላ እስከ 1959 ድረስ ባሉት አመታት ውስጥ ((from 330 AD to 1959 )ኢትዮጵያን የገዙት የኢትዮጵያ ነገስታት ግብጽ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አቡን የሚሆኑ ጳጳሶችን በፍጥነት ሳትልክ ስትቀር አባይን እንገድባለን በማለት ለግብጽ መልእክት ይልኩ እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡ ወይም በግብጽ ግዛት በሚኖሩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ግብጽ በደል ስትፈጽም ተመሳሳይ የማስፈራሪያ መልእክት ከኢትዮጵያ ነገስታት ይደርሳት እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡ በነገራችን ላይ ግብጾች የናይል ወንዝን ከእግዜአብሔር እንደተሰጣቸው ጸጋ ነው የሚቆጥሩት፡፡ የናይል ወንዝ  እስከወዲያኛው ድረስ ከእግዛብሔር የተሰጠን ጸጋ ስለሆነ ከቻሉ ከምንጩ ለመቆጣጠር የሚሄዱበት መንገድ እሩቅ ነው፡፡ ግብጽ የአባይን ወንዝ ከምንጩ ለመቆጣጠር ዋነኛ አላማዋ ካደረግች ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት በቀጥታ ጦር ሰብቃ የሀፍረት ሸማ ተከናንባ ተመልሳለች፡፡ ኢትዮጵያን ለሚያደሙ ሀገር በቀል ከሃዲዎችና የውጭ ወራሪዎች መጠነ ሰፊ እርዳታ ስትሰጥ የቆየች ሀገርም ናት ግብጽ፡፡ ይህ ሁሉ የግብጽ ሴራ ዋነኛ ማጠንጠኛው የአባይን ወንዝ ከምንጩ ለመቆጣጠር ካላት ጽኑ ፍላጎት ይመነጫል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የምትገኘው ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን የምትመለከተው እንደ የፖለቲካ እውነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎትና ምኞት በናይል ወንዝ አኳያ ህጋዊ ድርድር ማድረግ እንደሆነ የቆየ አላማዋ ነው፡፡ 

ሁላችንም እንደምንገነዘበው ውሃ በአካባቢው እጅግ ጠቃሚና ውዝግብ የሚፈጥር ነው፡፡ በነገራችን ላይ የናይል ወንዝን ለመጠቀም በአካባቢው ሀገራት መሃከል በርካታ ስምምነቶች ተደርገው ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያና እንግሊዝ መሃከል ( እ.ኤ.አ.1902) ngloEthiopian Treaty (1902)፣ የእንግሊዝና ግብጽ ውል ( እ.ኤ.አ.1929 ይህ በአካባቢው የሚገኙ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ ሀገራትን ያጠቃለለ ነበር፡፡) he Anglo-Egyptian Treaty (between Egypt and Britain representing its colonies in the region) in 1929, እ.ኤ አ. በ1959 የናይል ወንዝን ለሱዳንና ግብጽ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል  የሚፈቅደው ስምምነት the 1959 Treaty that allocated water between Egypt and Sudan ፣ በቅርብ ግዜ ውስጥ ደግሞ ማለትም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015 ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ ያደረጉት ስምምነት ይጠቀሳሉ፡፡ ( ይህ ሶስቱ ሀገራት የፈረሙበት ውል የናይል ስምምነት በመባል ይታወቃል፡፡) ሁላችንም እንደምንገነዘበው የታላቁን የአባይ ወንዝ ግድብ ለማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ታላቁን የህዳሴ ግድብ  ለመገንባት መንፈሳዊ ወኔ የታጠቀችው ( በአባይ ወንዝ ላይ የውሃ ግድብ የምትገነባው ) በራሷ ተነሳሽነት ህዝቧን ከችጋር ለመገላገል አስባ አውጥታ አውርዳ ነው፡፡ ከማናቸውም ሀገራት ጋር አልተፈራረመችም፡፡ ተፈጥሮአዊ መብቷን በመጠቀም ይህን ምዝብር ህዝብ ከችጋርና መከራ ለመገላገል ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ደግሞ ወደ እድገት ጎዳና ለመራመድ የስልጣኔ ጮራ ለመፈንጠቅ ነው፡፡

ከአለም የፖለቲካ ታክ እንደምንማረው በቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ግዜ ኢትዮጵያ እና ግብጽ የሁለቱ ሃያል ሀገራት የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረትና የተባበረችው አሜሪካ ወዳጅ ነበሩ፡፡  ከሁለቱ ሀገራት ማናቸው ናቸው በአካባቢው የበለጠ የጂኦፖለቲካ ጠቀሜታ ያላቸው ? (የበለጠ ስልታዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር የትኛዋ ናት ?) ግብጽ ወይንስ ኢትዮጵያ ? እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን የመሰሉ የጂኦግራፊ ጠበብት( አፈሩን ገላባ ያድርግላቸው)፣ እውቁ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣ የበርታ ኮንስትራክሽን ባለቤት የነበሩት ኢንጂነር ታደሰ ሀይለስላሴ ( ነብስ ይማር በነገራችን ላይ የአባይን ወንዝ እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ጥልቅ ጥናት ያቀረቡ ቢሆንም ያለፉትም ሆነ አሁን ያለው አገዛዝ የእኚህን ኢትዮጵያዊ የአይምሮ ጭማቂ ለመጠቀም አልቻሉም፡፡) ወዘተ ወዘተ በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጨረሻ እና 1960ዎቹ መጀመሪያ  ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ( ያንዬ ንጉሰነገስት አጼ ሀይለስላሴ የኢትዮጵያ ንጉስ ነበሩ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ወንዞች ካርታና ጥናት የተሰራው በተባበረችው አሜሪካ የጥናት ቢሮ ነበር፡፡ (the US Bureau of Reclamation ) በነገራችን ላይ የታላቁ አባይ ወንዝ ግድብ አቅድ እና ውጥን የተጀመረው በተጠቀሱት አመታት እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ የውሃ ግድብ ለመስራት የመልክአ ምድር ጥናት (The geographic survey of the Blue Nile, ) የተጀመረው ያንዬ ነበር፡፡

     በነገራችን ላይ በኒውዮርክ የተባባረችው አሜሪካ ግዛት ይገኝ የነበረ የምህንድስና ተቋም( an American engineering firm, J.G. White Engineering Corporation of New York  ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡) ከላይ ከተጠቀሰው ጥናት በፊት የአባይ ወንዝ ምንጭ በሆነው የጣና ሀይቅ ላይ ግድብ ለመስራት ወጥኖ እና አቅዶ ነበር፡፡ ሆነም ግን ይሁንና እንደ ጎርጎሪሲያኑ አቆጣጠር 1936 ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በመወረሯ  ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይህ የተባበረችው አሜሪካ እና ኢትዮጵያ በጣና ሀይቅ ላይ የውሃ ግድብ ለመስራት አድርገውት የነበረው የሁለትዮሽ ስምምነት የታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት( ሱዳንማ ግብጽ) ቅኝ ገዢ የነበረችውን ታላቋን ብሪታኒያ በእጅጉ አሳስቧትም አስጨንቋትም ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር ታላቋ ብሪታኒያ ኢትዮጵያ እና የተባበረችው አሜሪካ በነበራቸው መልካም ግንኙነት ደስተኛ እንዳልነበረች ከአካባቢው የፖለቲካ ታሪክ እንማራለን፡፡

በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1960 የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ታላቁን የአስዋን ግድብ በመገንባት በምድር ላይ ትልቁን ሰው ሰራሽ ሀይቅ እውን አድርጋለች፡፡ የአስዋን ግድብ መገንባት ዋነኛው አላማው የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት በመስኖ የእርሻ መሬት ለማልማት እና የውሃውን ፍሰት በመቆጣጠር በየግዜው ግብጽን የሚደቁሳትን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከአስዋን ግድብ በተቃረነ መልኩ ኢትዮጵያ በራሷ ህዝብ ትብብርና አንድነት እንዲሁም የገንዘብ ወጪ ታላቁን የአባይ ወንዝ ለመገደብ ስትነሳ በርካታ ጭቅጭቆችን አሰንስቷል፡፡ የብዙ ሀገራት አይንም አርፎበታል፡፡ ( ከቅርብም፣ከሩቅም ያሉ ሀገራት ወይም የኢትዮጵያን መነሳት የማይሹ ሀገራት እየተቀበዘበዙ ይገኛሉ፡፡) ለምን ህሊና ያላችሁ ጠይቁ መልሱንም በተመለከተ በየሰፈራችሁ፣ ማኪያቶ ወግ ላይ በመወያየት ፈልጉት፡፡

የአካባቢውን ጂኦፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታ በጥልቀት ለሚመረምር ኢትዮጵያዊ ግብጽ ትኩረት የምታደርገው 80 ፐርሰንት ያህሉን የውሃ መጠን ለናይል ወንዝ የሚያዋጣውን ጥቁር አባይን ከምንጩ መቆጣጠር መሆኑን ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም ግብጽ ከሆነላት ኢትዮጵያን መከፋፈል ወይም የተዳከመች ኢትዮጵያን ማየት የግብጽ የብዙ ዘመናት ህልምና ምኞት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተዳከመች እና በከሳች ጊዜ የጥቁር አባይን ወንዝ ምንጭ እቆጣጠራለሁ በማለት መጠነ ሰፊ ዝግጅት ካደረገች ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽ አጀንዳዋን የምታስፈጽመው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊሆን ይቻለዋል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የግብጽ አቅድ ሱዳንን ጠቅልሎ ከመያዝ እቅዷ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ግብጽ ሱዳንን በቁጥጥሯ ስር ለማዋል ወይም በቅኝ ገዢ ብሪታኒያ፣ ግብጽና ሱዳን ስምምነት መሰረት ሱዳንን ጠቅልላ ለመያዝ በብዙ ባጅታለች፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሱዳን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1956 ከእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች መዳፍ ስር በመውጣቷ የግብጽ ህልም ለግዜውም ቢሆን መክኖ ቀርቷል፡፡ ግብጽ ግን ተኝታ አድራ አታውቅም ፡፡ ሌላ ሴራ ሌላ አቅድ ከማውጣት አልቦዘነችም፡፡ ከአረባዊነት ማንነት ጋር በማያያዝ ሱዳን እና ግብጽ አንድነታቸውን ማጥበቅ አለባቸው ከማለት ባሻግር የናይል ወንዝን ጉዳይ አረባዊ አጀንዳ ለማድረግ የማትቆፍረው ጉድጓድ የማትበጥሰው ቅጠል የለም፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካዊና አረብ ማንነት አኳያ ውጥረትን እንዳነገሰ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ለአብነት ያህል የደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል መሰረት በአረብ ሱዳኖች በደል ደረሰብን በሚል እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ደቡብ ሱዳን አማጽን ራሳቸውን እንደ አንድ አፍሪካዊ እንጂ አረብ መሆናቸውን ተናግረው አያውቁም፡፡ ከዚሀ ባሻግር በሱዳን ዳርፉርና ኑቢያ ግዛት ውስጥ የተፈጸሙት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወይም ግጭቶች መነሻና መሰረታዊ ምክንያት በተጠቀሱት የአረባዊነት ማንነት በግድ ለመጫን በተደረጉ ውሳኔዎች እንደሆነ ይነገራል፡፡ (the root of conflicts in Darfur and the Nuba region. )  ራሳቸውን እንደ አረብ ዝርያ የሚቆጥሩትና በካርቱም መንግስት የሚደገፉት የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች የፈጸሙት ግፍ ተነግሮ አያልቅም፡፡

ኢትዮጵያን ገሸሽ በማድረግ ግብጽ የምታደርገው መስፋፋት አቅድ በሌላ አቅጣጫም ማየት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም ከምእራብ የቀይ ባህር ጫፍ እንድትርቅ የማድረግ የዘመናት ሴራዋ የተሳካ ይመስላል፡፡ የቀይ ባህርን የአረብ ሀይቅ እንደርገዋለን በሚል አቅድ የሰከሩት ገብጾችና ሸሪኮቿ የአረብ ሀገራት ለገንጣይና አስገንጣዮች ለዘመናት በአደረጉት መጠነ ሰፊ እርዳታ ተሳክቶላቸው ኢትዮጵያን ያለተፈጥሮ የባህር በር አስቀርተዋታል፡፡ በእነ የጦር መርከብ ኢትዮጵያና ሌሎች የጦር መርከቦች 1000 ኪሎሜትር የባህር በሯን ስትጠብቅ የነበረችው ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን፣ ሌሎች የአረብ ሀገራት ፣ እንዲሁም በኮሎኔል መንግሰቱ ሀይለማርያም አገዛዝ የበገኑት ወይም የተናደዱት ምእራባውያን በተለይም የተባበረችው አሜሪካና ታላቋ ብሪታኒያ በሸረቡት ሴራ ዛሬ የበይ ተመልካች ሆናለች፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ በቀይባህር አኳያ የነበራትን ስልታዊ ጠቀሜታ በታሪካዊ ጠላቶቿ ተነጥቃለች፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ማሳዘን ብቻ አይደለም ህሊናን ያደማል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

በነገራችን ላይ የአረብ ሀገራት የቀይ ባህርን የአረብ ሀይቅ የማድረግ ህልም እንደው ዝም ብሎ የተወጠነ አልነበረም፡፡ የአረብ ሀገራት በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች ( በተለይም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በቁጥር ይልቃሉ) ከቀይ ባህር አኳያ በማራቅ ከእስራኤል በስተደቡብ አቅጣጫ ጠንካራ የባህር ይዞታ እንደሚኖራቸው አስበው አቅደው ነበር ኢትዮጵያን ለማዳከም የተነሱት፡፡ ይህን ተከትሎ በኤርትራ የተነሱትን አማጺ ሀይሎች ሲረዱ እንደነበር ከአለም የፖለቲካ ታሪክ እንማራለን፡፡ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ በነበረችበት ጊዜ በማእከላዊ መንግስት ላይ አኩርፈው ብረት ላነሱ የግዜው የኤርትራ  አማጺዎች( በአብዛኛው እንደ ሱልጣን ሳሊህ የመሰሉ የእስልምና ተከታይ የሆኑ አማጺያን በቁጥር ከፍ ይሉ ነበር፡፡)  ለአብነት ያህል ለኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር Muslim-dominated Eritrean Liberation Front (EPLF), Front (ELF ፣ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ግንባር (የደፈጣ ተዋጊ ሆኖ የጀመረው እ.ኤ.አ. 1961 ነበር) Eritrean People’s Liberation Front (EPLF)  ኢትዮጵያን ያዳክሙልናል በማለት ስለወሰኑ መጠነ ሰፊ እርዳታ ደርጉላቸው ነበር፡፡ እዚህ ላይ በግዜው ለነበሩት ለገንጣይና አስገንጣይ ሀይሎች የስንቅና ትጥቅ ማከማቻ የሱዳን ሚና የላቀ እንደነበር የአሁኑ ትውልድ ልብ ሊለው ይገባል መልእክቴ ነው፡፡  (ምንም እንኳን) ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የታሪክ፣የባህልና ኢኮኖሚ ታሪክ ጥብቅ ቁርኝት እንዳላት ቢታወቅም ይህን መራር የታሪክ እውነት በመካድ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1961 ጀምሮ የኤርትራ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ከኢትዮጵያ ለመለየት የደፈጣ ውጊያ መጀመሩን እንዲሁም  በመጨረሻም ከ30 አመታት መራራ የርስበርስ የወንድማማቾች ጦርነት በኋላ መቋጫው ኤርትራ የምትባል  አዲስ ሀገር ውልደት እንደሆነ ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞ የግብጽ መሪ የነበሩት ገማል አብዱል ናስር Gamal Abdul Nassir እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1950ዎቹ በግብጽ ዋነኛ ተዋናይነት የእስልምና እና አረብ አንድነት ፍልስፍና a Pan-Arab and a Pan-Islam unity under Egypt’s sponsorship ያቀነቅኑ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ከዚህ ባሻግር ጀማል ከደቡብ የመን ጋር ለአጭር ግዜ የቆየ አንድነት ለመመስረት ጥረት አድርገውም ነበር፡፡ ( በነገራችን ላይ ደቡብ የመን በመለክአ ምድር አቀማመጥ ከግብጽ ጋር የምትዋሰን ሀገር ካለመሆኗ ባሻግር ከግብጽ ድንበር እጅግ እርቃ የምትገኝ ሀገር መሆኗን ልብ ይሏል፡፡ ) ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ግብጽ አንዳንድ የአረብ ሀገራት በአንገታቸው ላይ ሸምቀቆ እያጠበቁ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ቢያድርባቸው እውነትነት አላቸው፡፡ ታሪክ ፍንትው አድርጎ እንደሚያስተምረን ግብጽም ሆነች ሸሪኮቿ ለዘመናት ኢትዮጵያን ከማድማት ተቆጥበው አያውቁም፡፡  ይህ መራር የታሪክ ሀቅ  ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ዘመን ግብጽ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ሆና ቆይታለች፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ የግብጽ ጠንካራ ሰው የነበሩት ገማል አብዱልናስር በእስልምና ሃይማኖት አስተካው ወዳጃቸውን አሰባስበው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ እስልምና እምነት ተከታዮችን በመቀሰቀስ ኢትዮጵያን ድጋፍ አልባ ለማድረግ በብዙ ባጅተዋል፡፡ በተለይም ቺትዮጵያዊ የሙስሊም እምነት ተከታዮችን በአጉል ቅስቀሳ በማነሳሳት በአጼ ሀይለስላሴ መንግስት ላይ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ብዙ መንገድ ተጉዘዋል፡፡ በሙስሊም ሃይማኖት ሽፋን በኢትዮጵያ የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች የራሳቸው ራስገዝ ያስፈልጋቸዋል የሚል መርዘኛ ቅስቀሳም ያደርጉ ነበር፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የግብጽ ምኞትና ፍላጎት የጥቁር አባይን ወንዝ ከምንጩ መቆጣጠር የሚስችላትን ሴራ መጎንጎን እንጂ ለኢትዮጵያውያን የእስልምና ተከታዮች የሚደማ ልብ ኖሯት አይደለም፡፡ ቆላና ደጋ የምትወርደው፣የምትወጣው፡፡ እንሆ ዛሬም ቢሆን ከግብጽ የሚጎርፍላቸውን እርዳታ ተገን አድርገው የሚያደሙ ኢትዮጵያዊ አማጺ ሀይሎች ወይም የሃይማኖት አቀንቃኞች ሁለት ሶስት ግዜ ደግመው ደጋግመው እንዲያስቡ እንማጸናለን፡፡ ምንግዜም ቢሆን የግብጽ ስትራቴጂክ አላማ ኢትዮጵያን ማዳከም እና የጥቁር አባይ ወንዝን ከምንጩ ለመቆጣጠር እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ ይህ የግብጽ የቆየና የብዙ ዘመን ህልምና አቅድ ዛሬ ባሰበት እንጂ አልመከነም፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያ ተዳከመች ብላ ባሰበች ግዜ የቆየ ህልሟን እውን ለማድረግ ስትል  እንቅልፍ አትተኛም፡፡

በዛሬው ዘመን ኢትዮጵያ የአረብኛ ቋንቋ የሚችሉ የሙስሊም ምሁራንና ተከራካሪ ዜጎች አሏት፡፡ ግብጽና ሌሎች የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኙ ሀገራት የሚዘሩትን መርዝ፣ በኢትዮጵያውን መሃከል ሃይማኖት ተኮር ግጭት እንዲፈጠር የሚጎነጉኑትን ሴራ ከማክሸፍ አኳያ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን በተመለከተ በየጊዜው የሚወጡ የተዛቡ መረጃዎችን በማረም ታሪክ የማይዘነጋው ውለታ የዋሉ ኢትዮጵያዊ የሙስሊም እምነት ተከታዮች ጥቂትም ቢሆኑ አሉ፡፡ በእውነቱ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በቅርቡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 11 2021 በመስቀል አደባባይ የተካሄደው የረመዳን ጾም አፍጥር ፕሮግራም የተሳካ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ የሙስሊም እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውን መሪዎች ለኢትዮጵዊ ቄስ ጉርሻ ሲያጎርሱ የሚያሳየን ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ የእስልምና እና ክርስትና እምነት ተከታዮች ለዘመናት በፍቅርና አንድነት መኖራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቆ የነበረው የጉርሻ ስነስርአት ህብረትና ትብበራቸውንም የሚያሳ ነበር፡፡

ይህ በግምት ከ15000 በላይ የሃይማኖቱ ተከታዮች ታደሙበት በተባለው የአፍጥር ፕሮግራም ላይ ግድቡ የአኔ ነው የሚል መፈክር መሰማቱ ብሔራዊ ስ፣ሜትን የሚቀሰቅስ ነበር፡፡ ግብጽ ለምትነዛው የልዩነት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ተገቢ መልስ ነበር፡፡ ኢትዮጵውያን የሃይማኖት ልዩነቶች እንደማይገድባቸው ማሳያ ነበር፡፡ ፊስቲቫሉ የአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵውያንን ወደ አንድነት ያመጣ ክስተትም ነበር ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡

ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያዊ ክርስቲያንና ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ወጣቶች አንድ ላይ ሆነው በህብረት በፍቅር የመስቀል አደባባይ አካባቢን በማጽዳታቸው ታሪክን እንደገና አድሰውት ነበር፡፡ በጥንት ዘመን የነበረው የሃይማኖት መከባባር ዛሬም እንዳለ አሳይተዋል፡፡ በተለይም በአሁኑ ዘመን በሃይማኖት መሃከል ልዩነት ለመፍጠር ለሚቅበዘበዙ የውጭ ሃይሎች አስተማሪም ነበር፡፡ የሃይማኖትን ልዩነት ተገን አድርገው እሳት ለመጫር ለሚሞክሩ የውጭ ጽንፈኛ ሀይሎች የኢትዮጵያውያን ሙስሊምና ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ለዘመናት በሰላም እና በፍቅር እንደኖሩት ሁሉ ዛሬም ያ መንፈስ እንዳለ ማሳያ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ ከላይ የሰፈረው የትብብር መንፈስ ግብጽ እና ሌሎች እኩያን ኢትዮጵያን በሃይማኖት ልዩነት ሰበብ እንዲጋጩ ያቀዱት ሴራ መክሸፉን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵውያን ግብጽ የኢትዮጵን አንድነት ለማላላት እንደምትሰራ፣ በኢትዮጵያ ሰላም፣ፍቅርና አንድነት እንዳይኖር ብዙ እርቀት እንደምትጓዝ፣ ወዘተ ወዘተ ከተገነዘቡ ውለው አድረዋል፡፡ በሌላ በኩል እንደቀደሙት የግብጽ ገዚዎች ሁሉ ( ማለትም እንደ አንዋር ሳዳት፣ሆስኒ ሙባረክ፣ ሙርሲ ሁሉ) የግብጹ መሪ አልሲሲሲ የናይል ወንዝን ፍሰት የሚያቆም ማናቸውም እንቅስቃሴ ቀይ መስመር እንደማለፍ ይቆጠራል በማለት በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን ተነግረዋል፡፡ ግብጽ መሪዎች በአባይ ጉዳይ ላይ ከጥንት እስከ ዛሬ ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡

ፕሬዜዴንት አልሲሲ በናይል ወንዝ ላይ አለኝ የምትለውን ታሪካዊ ድርሻ ለማስከበር ማናቸውንም እርምጃ እንወስዳለን እንዳሉት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ከግብጽ የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመመከት በህብረት አንድነት መንፈስ መቆም አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ በየግዜው ጡንቻዋን ለኢትዮጵ ለማሳየት የተለያዩ ዘዴዎችን በትጠቀምም በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ውስጥ ሁለተኛው የውሃ ሙሊት አቅድ በመጪው ሐምሌ 2021( እ.ኤ.አ.) ወር አጋማሽ ገቢራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ባሻግር የሃበሻ ገጽ አንባቢያን ለአንድ አፍታ ታሪክን እንዲያስታውሱ፣ እንዳይዘነጉ እማጸናለሁ፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1960 እስከ 1970 ባሉት አመታት ሶማሊያ የኦጋዴንን መሬት ወራ ስትይዝ ግብጽ ከጀርባ ነበረች፡፡ እብሪተኛው መሃመድ ሲያድባሬ የታላቋን ሶማሊያ የቅዠት ካርታ ይዞ ሲነሳ እንደው ዝም ብሎ አልነበረም፡፡ ሶማሊያ በኢትዮጵያ፣ዲጂቡቲ እና ሰሜን ኬንያ  የሶማሊኛ ቋንቋ የሚናገሩ ዜጎች የሚኖሩበትን ግዛቶች በማጣመር የታላቋን ሶማሊያ ሪፐብሊክን የመመስረት ሴራ ጀርባ የግብጽ እጅ አለበት፡፡ በአካበቢው ግዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳውን የሰአት ቦምብ ቀብራ የሄደችው እንግሊዝ ብትሆንም ይህን እኩይ ሴራ በማቀጣጠል ግብጽ ወደር አይገኝላትም፡፡ ግብጽ የኢትዮጵያን አንድነት ከሚጎዱ የፖለቲካ ሴራዎች ጀርባ አለች፡፡

በነገራችን ላይ የኦጋዴኑ ጦርነት የሲያድባሬን ጦር ድሬዳዋ እና ሀረር ከተማ ድረስ አስጠግቶት ስለነበር በግዜው የነበረው ወታደራዊ መንግስት ለጦር መሳሪያ እርዳታ ሲል ወደ ቀድሞዋ የሶቪዬት ህብረት ፊቱን አዙሮ ነበር፡፡ የተባበረችው አሜሪካ የሶሻሊስት ርእዮት ተከታይ የነበረውን ደርግ በመቃወሟ ምክንያት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1903 ጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያና አሜሪካ የኢኮኖሚ፣ባህልና ፖለቲካ ግንኙነት በኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም አገዛዝ ዘመን ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ከቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ጋር የጋለ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የነበራት ሲሆን፣ በአፍሪካው ቀንድ ሁነኛ የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ወዳጅ ሀገር ነበረች፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ በአብዮቱ ዋዜማ ሶማሊያ ከአሜሪካ ጋር መልካም ግንኙነት ነበራት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ1966 ዓ.ም. በፊት የሶማሊያን ጦር ሰራዊት ያሰለጠነችውና ያስታጠቀችው የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ቋሚ ወዳጅና ጠላት የለም በሚለው የሀገሮች ፖለቲካዊ ፍልስፍና መሰረት የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገር ለመሆን ግዜ አልፈጀበሳትም ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር ደቡብ የመንባ የኩባ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር እኩል በመሰለፍ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ደማቸውን አፍሰዋል፡፡ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡ በመጨረሻም የሲያድባሬ ወራሪ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር የሀፍረት ሸማ ተከናንቦ እንዲለቅ ታሪክ የማይዘነጋውን መስእዋትነት ከፍለዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ድንበር ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር፡፡ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ በከፍተኛ ወታደራዊ ማእረግ ኢትዮጵያን ያገለገሉ ኢትዮጵያዊ ጄኔራሎች  ባዘጋጁት መጽሐፍት ውስጥ እንደጠቀሱት የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት የጦር አማካሪዎች በኢትዮጵያ የጦር ሀይል ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ነበሩ፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ይካሄድ በነበረው የርሰበርስ ጦርነት በቀድሞዋ ሦቪዬት ህብረት የጦር አማካሪዎች ስህተት ወይም የእብሪት ውሳኔ ኢትዮጵያደምታ ነበር፡፡ ለጦር ሀይሉ ሽንፈትም ከሚጠየቁት መሃከል እነኚሁ የጦር አማካሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በቀይባህርም ላይ በመርከቦቻቸው ያሻቸውን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በምእራብ አውሮፓ ሀገራት፣ በተባበረችው አሜሪካና በብይነ መንግስታቱ የስብዓዊ መብት ወኪል ጥወቀስ ትከሰስ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ የተማሩ ልጆቿና እድሉ የገጠማቸው ሁሉ በአለም ላይ እንደ ጨው ዘር ተበትነው ቀርተዋል፡፡ በእውነቱ ለመናገር የኢትዮጵያ እድል ያሳዝናል፡፡ ግዜው የስደት ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያን የረጅም ግዜ ታሪክ የተጻረረ ነበር፡፡ በቀደሙት አመታት የስደተኞች መጠጊያ የነበረች ሀገር( አርመኖች፣የመን እና በርካታ የአረብ ሀገራት ዜጎች፣ የቱርክ ዜጎችን ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ ምድር በስደት ከመጡ በኋላ በክብር ይኖሩ እንደነበር እናስታውሳለን፡፤) እንዲያ እንዘጭ ብላ መውደቋ ሲታሰብ አይምሮን ይረብሻል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከደርግ ዘመን በከፋ መልኩ ስደት ጨምሯል፡፡ በተለይም ወደ አረብ ሀገር በህገወጥ መንገድ ለመጓዝ ሲሞክሩ የባህር አውሬ ሲሳይ የሚሆኑ ፣አረብ ሀገራት ከደረሱ በኋላ ደግሞ አንዳንድ  ከእብድ ውሻ በከፉ አሰሪዎቻቸው በደል የሚደርስባቸው ኢትዮጵያውያን ኑሮ ሲታሰብ ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) አነገትን ያስደፋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ አይነት ብሔራዊ ውርደት ለመውጣት እንደ ታላቁ የአባይ ግድብን የመሰሉ ታላላቅ ፕሮዤዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በአንድነት መቆም ይገባናል፡፡ የሀገሩን በሬ…….. እንዲሉ ለወጣቱ ሰፊ የስራ መስክ በሀገር ቤት መክፈት ከተቻለ ስደትን በከፊልም ቢሆን መግታት ይቻላል፡፡ ከግብጽም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር መገዳደርም ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ክፍል ሁለት ይቀጥላል

 

Filed in: Amharic