>
5:14 pm - Sunday April 30, 0473

ከታሪክ  እውነት  አለመማር የአለም አቀፉ ህብረተሰብና የኢትዮጵያ ዝምታ (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

ከታሪክ  እውነት  አለመማር

የአለም አቀፉ ህብረተሰብና የኢትዮጵያ ዝምታ

                                               

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1984 ( በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1977) ከሁለተኛ የአለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አስደንጋጭና ከባድ የሰብአዊ ቀውስ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተከስቶ እንደነበር ታሪክ ፍንትው አድረጎ ያሳየናል፡፡ በግዜው የተከሰተው ድርቅና ጠኔ በህዝብ ላይ የሚያደርሰውን እልቂት ለመቋቋም የተቋቋመው መስሪያ ቤት በሻለቃ ዳዊት  ( ዛሬ ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ) ይመራ የነበረው የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ነበር፡፡ (the Relief and Rehabilitation Commission (RRC) )  ይህ መንግስታዊ ተቋም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በችጋር እንዳያልቁ ዋነኛ ሃላፊነት ነበረው፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የታሪክ ፌዝ ሆነና የወታደራዊው ደርግ መንግስት የ10ኛውን የአብዮት በአል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ድርቅና ጠኔው በአስከተለው ሰብአዊ ቀውስ ምክንያት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለአለም ህብረተሰብ እና በ10ኛው የኢትዮጵያ አብዮት በዓል ላይ እንዲገኙ ለተጋበዙ የአፍሪካ መሪዎች የኢትዮጵያ አብዮት ያስገኘውን ውጤት እና ድሎች በተመለከተ ለማቅረብ ተቸግረው እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡ በግዜው የኢትዮጵያ እርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ አስከፊውን የ1977ቱን ድርቅና ጠኔ ውጤት በተመለከተ በየጊዜው ለኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ምክረ ሃሳብ እንዳቀረቡ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ግን ይህ ችግር ያልፋል፣ ትልቅ ክብረ በአል ከፊታችን ተደቅኗል፣የአንተን ትልቅ ጭንቀት የአብዮት በአሉ ካለፈ በኋላ እንደርስበታለን ካሉ በኋላ አሁን ማተኮር ያለብን በ10ኛው የአብዮት በዓል አከባበር ላይ መሆን አለበት የሚል ምላሽ ከኮሎኔል መንግስቱ እንዳገኙ በአንድ የጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረውታል፡፡ ምንም እንኳን ይሁንና ድርቅና ጠኔውን መደበቅ ወይም ሌላ ጊዜ እናየዋለን የሚለው የወታደራዊው መንግስት ውሳኔ የህዝቡን ችግር  በከፍተኛ ደረጃ አባባሰው እንጂ ያመጣው ሁነኛ መፍትሔ አልነበረም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1984 የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ለለጋሽ ሀገራት ተወካዮች አንድ ኮንፍረንስ በማዘጋጀት የድርቁና ጠኔውን ስፋት ካብራራ በኋላ ወደ አምስት ሚሊዮን ረሃብተኞች ለሚደርሱ ረሃብተኞች እርዳታ እንደሚያስፈልግ ለአለም አሳውቆ ነበር፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር የነበሩት ሻለቃ ዳዊት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ግንቦት 1984 ወደ ተባበረችው አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ላይ በተካሄደው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ካውንስል ላይ በመገኘት የሚከተለውን አቤቱታ አሰምተው እንደነበር በአንድ የጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረውታል፡፡ እጠቅሳለሁ፡፡ 

‹‹ ዛሬ ከፊታችሁ ቆሜ ለዚህ ካውንስል የማመለክተው ጉዳይ ከሚያሳምም ሃላፊነት የሚመነጭ ነው፡፡ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የማመለክተው ጉዳይ በመላው ኢትዮጵያ አስከፊ ድርቅ መከሰቱን ነው፡፡ ድርቅና ጠኔው ተወዳዳሪ የለውም፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅና ችጋር ስፋቱ የትዬሌሌ ሲሆን አሰቃቂም ነው፡፡ ስለሆነም አለም አቀፉ ህብረተሰብ አስቸኳይ እርዳታ መለገስ አለበት የሚል ተማጽእኖ ነበር ያቀረቡት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከአለም አለቀፉ ህብረተሰብ የተገኘው ምላሽ አጥጋቢ አልነበረም፡፡ ስለሆነም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በጥቅምት 1984 አዲስ አበባ በጊዮን ሆቴል በተዘጋጀው የለጋሽ ሀገራት ኮንፍረንስ ላይ ለተገኘቱ ተወካዮች ሻለቃ ዳዊት የአውሮፓ ከተሞች፣ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ገለጻ ከማድረጋቸው ባሻግር እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መጋቢት 1984 አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዶ ስለነበረው የለጋሽ ሀገራት ተወካዮች ስብሰባ በተመለከተ አስታውሰዋቸዋል፡፡

እንደ ሻለቃ ዳዊት ጽሁፍ ከሆነ የወታደራዊው መንግስት የአለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ በጠየቀ ስድስት ወራት ውስጥ በድርቅና ችጋር የተጠቁት ርሃብተኛ ኢትዮጵያውያን ወደ ሰባት ሚሊዮን ግድም ደርሶ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በየቀኑ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ተስፋ መቁረጥ ወይም ወደ ሞት ጎዳና ይጓዙ ነበር፡፡ በግዜው ይታይ የነበረው የሰው ልጆች ስቃይና መከራ በጣም አስደንጋጭና ለማመን የሚያስቸግር ሁነት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ለለጋሽ ሀገራት ተወካዮች የተዘጋጀው ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ ማለታቸው ነው፡፡ የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሪክተር ሟቹ አቶ ተፈሪ ወስንና ቡድናቸው አንድ ላይ በመሆን በሚስተር ሚካኤል ቡረክ የሚመራው የእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ የጋዜጠኞች ቡድንና እውቁ የቴሌቪዥን ፊልም አንሺው ሞሃመድ አሚንን ጨምሮ በአስቃቂ ሁኔታ የሚገኙ ርሃብተኞችን፣ የመድሃኒትና ምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ኢትዮጵያውያን፣ የተጠለሉበትን ‹‹ የኮረም መጠለያ ›› እንዲጎበኙ ተፈቀደላቸው፡፡ ይሄን ተከትሎ በሚስተር ሚካኤል በርክ (Mikael Burke  ) ይመሩ የነበሩት የእንግሊዙ ዜና አውታር የጋዜጠኞች ቡድን  እንደጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 23 ቀን 1984 በምስል አስደግፈው ለአለም የናኙት የ30 ደቂቃ የምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባ በዘመናዊው አለም ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ አስከፊ ድርቅና ጠኔ በኢትዮጵያ እንደተከሰተ የሚያሳይ ሁነት በአለም አይምሮ ውስጥ ዶሎ( እንዲቀረጽ) አድርጎ ነበር፡፡ ከዚህ ከእንግሊዝ ጋዜጠኞች የምንገነዘበው ወይም የምናስተውለው ቁምነገር ቢኖር ፕሬስ ወይም ጋዜጠኝነት ለእውነት ስትቆም (ሲቆም) የአለምን አይምሮ መግዛት እንደሚቻል ነው፡፡ ስለሆነም ጋዜጠኞች ሁሉ ለእውነት ዘብ መቆምን መርሆአቸው ማድረግ አለባቸው፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጠኞች በጊዜው የማይሻ እውነትን ነው፡፡ እርግጥ ነው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1984 ( 1977 ዓ.ም.) በኢትዮጵያ ፌሽታ አልነበረም፡፡ ወይም ደስታና ተድላ አልነበረም፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያዊ ዜጎች በችጋር ምክንያት እንደ ቅጠል የረገፉበት አሳዛኝ አመት ነበር፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጠኞች ለአለም ይፋ ያደረጉት የርሃብ ትእይንት ማናቸውንም ጤናማ አይምሮ ያለውን ሰው የሚረብሽ ሁነት ነበር፡፡ በተለይም እንደ ሻለቃ ዳዊት አይነቱ ሰው አይምሮ ውስጥ ከሚሊዮን ጊዜ በላይ የሚያስተጋባ እውነትን ነው የእንግሊዝ ጋዜጠኞች የዘገቡት፡፡ በግዜው የነበሩት የእንግሊዝ ዜና አውታር ቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኞች እንደዘገቡት ከሆነ በለሊትም ሆነ ጸሃይ ስትወጣ ( ሲነጋጋ በቀን ብርሃን) በኮረም የረሃብተኞች መጠለያ የሚታየው ስቃይና መከራ ነበር፡፡ በረሃብና ችጋር አንጀታቸው የታጠፈ እናቶች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናትና ሴቶች፣ ወጣቶች እዛም እዚህም ወድቀው ይታዩ ነበር፡፡ በአጭሩ በመጽሀፍ ቅዱስ የተጠቀሰው ርሃብ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰተ ይመስል ነበር፡፡ በግዜው የነበሩ ሰራተኞች ቦታው ( ኮረምን ማለታቸው ነው) በምድር ላይ ለገሃነም የቀረበ ቦታ ይመስል ነበር፡፡

“ Dawn, and as the sun breaks through the piercing chill of night on the plain outside Korem it lights up a biblical famine now-in the 20th century. This place, say workers here, is the closest thing to hell on earth…”

በነገራችን ላይ የጋዜጠኛ በርክ (Buerke) እና የዝነኛውን ፊልም አንሺ አሚን (Amin’s ) የዘገቡትን ይህን የርሃብተኞች አሳዛኝ ሰቆቃ የተመለከተ ግለሰብ አይምሮው ይረበሻል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አንድ ቁምነገር ለማድረግ (ለመሥራት) ለራሱ ለህሊናው ቃል ይገባል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አቅሙ የፈቀደውን ያህል ለራሱ፣ በራሱ ቃል በመገባው መሰረት የሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ መወሰኑ የሰውነት ባህሪው ነው፡፡ በቀድሞው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አገዛዝ ( ደርግ) የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ( ዛሬ በአፍሪካ፣ በተለይም የአፍሪካው ቀንድ የግጭት ጥናት ተጠባቢ ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ )  ‹‹ የደም እንባ ›› (Red Tears) በተሰኘው ጥናታዊ መጽፋቸው ላይ የነበረውን የችጋር ትእይንት መራር እውነት በሰፊው ሄደውበታል፡፡ እንደሚከተለው ለመትቀስ እሞክራለሁ፡፡

  ‹‹ የእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ ጋዜጠኞች የተጠቀሙበት ቃላት፣ ሀረጎች በጣም ጠንካራና አጥንትን ዘልቀው የሚገቡ ነበሩ፡፡ ቃላቶቹ ሆን ተብለው የተመረጡ ነበሩ፡፡ ከዚህ ባሻግር ተስፋ የቆረጡ ፊቶች፣ በየጥጋጥጉ የወደቁና ከእህል መያዣ ጆንያ ወይም ማዳበሪያ በተሰሩ ጨርቅ የተሸፈኑ አስክሬኖች በቴሌቪዥን መስኮት በመታየታቸው የተነሳ የእንግሊዞችን መንፈስ እና ልብን ሰብሮት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ከ425 በላይ አለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሚን ያነሳውን አሰፈሪና እረዳት አልባ ኢትዮጵያውያንን ፎቶግራፎች ለአለም እንዲታይ በማድረጋቸው የተነሳ በተለይም የምእራቡ አለም ህዝብ ልቡ ተነካ፡፡ የሀዘን ስሜት ተሰማው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ልበ ደንዳና የነበሩት የእንግሊዙ ዜና አውታር ቢቢሲ ጋዜጠኞች በዜና ማንበቢያ ክፍል ውስጥ እንዳሉ እንባቸው ኩልል ብሎ ፈሰሰ፡፡ ምንም እንኳን የቢቢሲ ጥናታዊ ዘገባ በምእራቡ አለም የታየ ቢሆንም ከዚህ በተጨማሪ በተባበረችው አሜሪካ የሚገኘው የዜና አወታር ኤንቢሲ (NBC ) የተባበረችው አሜሪካ መንግስት አፋጣኝ ምላሹን እንዲሰጥ ሲል ከእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ የጥናት ፊልም በመወስድ የአራት (4) ደቂቃ የረሃቡን አስከፊነት የሚያሳይ ፊልም በመላው አሜሪካ እንዲታይ አድርጎ ነበር፡፡ ኤንቢሲ ሰቆቃ የሚታይበትን ፊልም ከለቀቀው በኋላ  ብብዙ የተባበረችው አሜሪካ ግዛቶች ይኖሩ የነበሩ የያንጊዜው  የአሜሪካ ህጻናት በየመኖሪያ ቤቶች በመንቀሰቃስ የእርዳታ ቁሳቁሶችን መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ መሰረታቸውን ታላቋ አሜሪካ ላይ ያደረጉና ቁጥራቸው የትዬሌሌ የሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶች ኢትዮጵያን  በበጎ ፈቃደኝነት ለመርዳት በሰፊው ተሰለፉ፡፡ ከዚሁ ባሻግር በአርቲስት ቦብ ጌልዶፍ ይመራ የነበረው ሮክ የሙዚቃ ባንድ ዛሬ ሰር ባንድ ክሪስመርስ መሆኑን ታውቃላችሁ በሚል ርእስ ባቀረበው የሙዚቃ የቀጥታ ስርጭቱ ደግሞ አለምን ማነቃነቅ ችሎ ነበር፡፡ በተባበረችው አሜሪካ የታወቁ ዘፋኞች ማይክል ጃክሰን (Michael Jackson )፣ ሃሪ ቤላፎንቴ( Harry Belafonte )፣ ሊኦኒሪች (Leone Richie )፣ኩዊንሲ ጆንስ (Quincy Jones,)፣ ሰቴቭ ዎንደርስ (Stevie Wonders )፣ ወዘተ ወዘተ ‹‹ እኛ የአለም ሰዎች ›› (We Are the World  ) በሚል የሙዚቃ ስልት አለም ህዝብን ሰብአዊ ስሜት በማነሳሳት (በመቀስቀስ ) ለኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ ለማሰባስብ ታሪክ የማይዘነጋው ውለታ ውለው  ነበር፡፡ የሙዚቀኞቹ ውጤትም የአለም ህዝብን ሰብአዊ ስሜት ያሳየና አስደናቂም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የሙዚቃውን ትእይንት የማያሳዩ መጽሀፍት ታትመው ነበር፣በውጤቱም ፍላጎት የተቀሰቀሰባቸው አንባቢዎችና ተመራማሪዎች ስለ ነጻ ፕሬስ መንፈስ ሃይልነትና ስለ ሰብአዊነት የበለጠ እውቀት ገብይተውበታል፡፡ ››

ሆኖም ግን ይሁንና የጊዜው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አገዛዝ በእጁ ላይ ችግር ነበረበት፡፡ ምክንያቱም በ1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ድርቅና ጠኔ አለምአቀፍ ተሰሚነት ካገኘ የሚጎረፈውን ምላሽ ለማቆም አያስችለው ስለነበር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የእርዳታ ማስተባበሪናያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች የተከሰተውን የነበረውን ተፈጥሮ ቁጣ የበለጠ ትራጄዲክ ድራማ በማድረግ የውጪው ማህበረሰብ የበለጠ ትኩረት እንዲያደርጉ ለማሳሳብ በሚያደርጉት ጥረት አኳያ ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቃ ነበር፡፡

 ሆኖም ግን ይሁንና እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር ታህሳስ 4 ቀን 1984 በታላቋ አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ተካሂዶ በነበረው የብይነ መንግስታቱ አመታዊ ጉባኤ ላይ ተገኝተው የነበሩት ሻለቃ ዳዊት የሚከተለውን ጥሪ አስተላፈው ነበር፡፡

‹‹ ምንም እንኳን መንግሰታት ( የምእራባውያን መንግስታት ማለታቸው ነው) የታቅርኖ ንግግሮችን ቢያሰሙም፣ የፕሮፓጋንዳ ይዘት ያላቸውን ዲስኮሮችን ቢያሰሙም እና ኢትዮጵያውያን  ተራ ዜጎች፣ ወንዶችና ሴቶች ላሳዩን ደግነት ልባችን ተነክቷል፡፡ ይህ ሁሉ መንፈሳችንን ያበረተዋል፡፡ በአለም ላይ የሰብአዊ ስሜት እንዳለ እንዲሰማን አድርጎናል፡፡ አለም አቀፍ አንድነት ያለ ስለመሆኑ በራስ መተማመን ያሳድርብናል፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት ወገኖቻችንን በህይወት ለማትረፍ እንደሚቻል አበረታቶናል፡፡ ›› ይህ በእንዲህ እንዳለ ከወታደራዊው አገዛዝ ቁንጮ መሪ ከነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ጋር እንዴት ግጭት ውስጥ እንደቶዶሉ ሲያብራሩ እርሳቸው የተከሰተውን ድርቅና ጠኔ የምእራቡ አለም በግልጽ እንዲሰማ በመፈለጋቸው ነበር፡፡ ለማናቸውም ሻለቃ ዳዊት ምክንያታቸውን እንደሚከተለው አስፍረውታል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ግንቦት 1985 እኔ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አገዛዝ ሊቀመንበር ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም በሃሳብ መግባባት አልቻልንም፡፡ የእኔ ንግግር ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር በፍጹም ተቃራኒ ነበር፡፡ ከዛች ግዜ ጀምሮ ግንኙነታችን ሻከረ፡፡ ከስርአቱ ጋር ለመስራት እንደማልችል አረጋግጫለሁ፡፡ በእኔ በኩል የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ትኩረት ብዙ ግዜ አጭር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዴ ሁሉንም የሚያስፈልገንን እርዳታ ካገኘን የሟቾችንና እርሃብተኞችን ቁጥር መቀነስ ያስችለናል፡፡ ሆኖም ግን ኮሎኔል መንግስቱ የጸረ ኢምፔሪሊዝም ትርክታቸውን ለማቅረብ እየተዘጋጁ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ለኢትዮጵ ህዝብ ባደረጉት ንግግራቸው ላይ የምእራቡ አለምና የተባበሩት መንግስታት ስላደረጉት እጅግ ጠቃሚና ህይወት አድን እርዳታ ሳይገለጹት አልፈዋል፡፡ ኮሎኔሉ የምእራቡ አለም ደረገው እርዳታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት አንዱ ስትራቴጄያቸው ነው ሲሉ ነበር የተሰሙት፡፡ ኮሎኔሉ መእራባውያንን ኢምፔሪያሊስት ናቸው ሲሉ ይወቅሷቸውም ነበር፡፡ አክለውም በአደባባይ እንደተናገሩት ምእራባውያን የሀዘን ስሜት የተሰማቸው በማስመሰል ለአመታት ከታገልነት የሶሻሊስት እርእዮት አለም አለያይተውን የራሳቸውን የርእዮት አለም ሊያጠምቁን ነው ሲሉ ነበር በድጋሚ የወቀሷቸው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ድርቅና ጠኔ እጅጉን ያሳሰባቸው ሻለቃ ዳዊት እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር ግንቦት 1985 ላይ ተካሂዶ በነበረው የብይነ መንግስታቱ ማህበር አመታዊ ጉባኤ ላይ በመገኘት የሚከተለውን መልእክታቸውን አሰምተዋል፡፡

‹‹ ልክ የዛሬ አመት በብይነ መንግስታቱ ጉባኤ ፊት ቆሜ ባቀረብኩት መልእክት ጭንቀትና እረዳት አልባነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የአለም ህብረተሰብ በሚሊዮን ለሚቆጠረው ለረሃብተኛው ኢትዮጵያዊ ያሳየው ሰብአዊ ስሜት አስደናቂ ነበር፡፡ በከፍተኛ ቁጥር የሚገመቱ የአለም ሀገራትና ህዝቦች ኢትዮጵውንን ለመርዳት ተረባርበው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለለጋሽ ሀገራት፣ መንግስታዊ ላልሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለተባበሩት መንግስታ ድርጅት ልዩ ወኪሎች፣ ለወንዶችና ሴቶች ላደረጉት ሰብአዊ እርዳታ ጥልቅ አክብሮቱን ያቀርባል፡፡

ምንም እንኳን እኔና ኮሎኔል መንግስት በሁለት የተለያዩ መንግስታት ውስጥ ያለን ቢመስልም በፈጸምኩት ድርጊት ምንም ጸጸት እንደማይሰማኝ በግልጽ መናገር እሻለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው የሰብአዊ ቀውስ ፖለቲካዊ ለማድረግ መሞከርን የምቀበለው አይደለም በማለት ሞግተውም ነበር፡፡ በእኔ አስተሳሰብ ዩኤስኤይድ፣ በአሜሪካና ምእራብ አውሮፓ ይገኙ የነበሩት የሰብአዊ ድርጅቶች አላማቸው ህይወትን ማዳን ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከሰብአዊ እርዳታ ባሻግር በአንዲት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት የለባቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው ችጋርና ጠኔ ከ95 ፐርሰንቱ በላይ የሰብአዊ እርዳታ የመጣው ከምእራቡ አለም ነበር፡፡ ለተባበሩት መንግስታም ቢሆን የሰብአዊ እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ የሚያቀርቡት እነኚሁ የምእራቡ አለም ሀገራት ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ እጅግ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ እርዳታ ከአለሙ ህብረተሰብ የቀረበው በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅና ጠኔ የሚያስከትለውን እልቂት ለመቀነስ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር በሀገራችን ሰሜን ኢትዮጵያ 1977 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረው ድርቅና ችጋር አስፈሪ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ያጠቃና ቁጥራቸው ቀላ የማይባል ውድ የሰው ልጆችንና እንሰሳትን የፈጀ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ነበር፡፡ ለዚህም ነው የአለም ህዝብ ፣ በተሌም የምእራቡ አለም ከሁለተኛው አለም ጦርነት ወዲህ ለአንዲት በተፈጥሮ ታደለችና ታሪካዊት ሀገር፣ በዋነኛነት በመትፎ አገዛዝ ምክንያት በተፈጥሮ ቁታ ለተደቆሰች ሀገር እጅግ ብዙ (Stephanie Simmonds )የሰብአዊ እርዳታ ያቀረበው፡፡ በነገራችን ላይ አንድ የምእራቡ አለም ምሁር ስቴፋኒ ሲሞንደስ የሚባል የምእራቡ አለም ለኢትዮጵያ ያቀረበውን ግዙፍ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚከተለው አስፍሮት ይገኛል፡፡ እጠቅሳለሁ፡፡

‹‹ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1985 ለኢትዮጵያ የተላከው ሰብአዊ እርዳታ 50 ኪሎ ግራም በሚይዝ ከረጢት ውስጥ ከተጨመረ በኋላ፣ እያንዳንዱን 50 ኪሎግራም የያዘውን ከረጢት ወደላይ እየደራረብን ብንከምረው ወደ ላይ ወደ ሰማይ፣ ከባህር ጠለል በላይ ለማለት ነው 3000 ማይልስ ከፍታ መፍጠር ይቻላል፡፡ ተመሳሳይ 50 ኪሎግራም የሚይዝ ከረጢትን ከአንድ ጫፍ ተነስተን እየደረደርን ብናስቀምጣቸው የምድር ወገብን ግማሽ እርቀት መሸፈን ይቻለናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የእርዳታ እህል በአይሮፕላንና በከባድ መኪናዎች ለማመላለስ የፈጀው ጊዜ ደግሞ ወደ ጨረቃ ላይ ለሰባት ጊዜያት ያህል ደርሶ ለመመለስ የሚያስችለውን ጊዜ ፈጅቶ ነበር፡፡ ለማናቸውም በእንግሊዝናኛ ቋንቋ የቀረበው  ጽሁፍ የበለጠ ገላጭ በመሆኑ መጥቀሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡

 “ If all the food delivered to Ethiopia in 1985 were packaged in 50kgs bags and placed one on top of the other, the resulting stack would be 3000 miles high. If the same bags were placed end to end they would extend halfway round the equator. The mileage covered by relief trucks and planes in 1985 was equivalent to seven trips to the moon and back “ (WHOh rep in the UN emergency office, Stephanie Simmonds)

ውድ የሀበሻ ገጽ መጽሔት አንባብያን እውን ኢትዮጵያ ዛሬ በምግብ ራሷን የቻለች ሀገር ለመሆን በቅታ ይሆን አይመስለኝም፡፡ እውን በኢትዮጵያ በችጋር ውስጥ ያሉ ዜጎች ኖሩ ይሆን መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡ በእኔ በኩል በዋናዋ ከተማ አዲስ አበባና በብዙ የሀገሪቱ ትንንሽ ከተሞች ሳይቀር ኑሮአቸው ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) በልመና ላይ የተመሰረተ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን ፣ እህቶቻችን፣ አባቶችና ህጻናት፣ ሴቶች ሳይቀሩ ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ከተፈጥሮ ቁጣ ተጠቂዎች ባሻግር መሆኑ ነው፡፡ ለማናቸውም ይህ ጉዳይ ሁላችንንም ሊያሳስበን ገባል፡፡

እንደ መደምደሚያ 

ኢትዮጵያ ዛሬ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተዶለች ሀገር ሆና ትታየኛለች፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍል ፣ በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተክል ዞን ፣ በምእራብ ወለጋ ዞን፣ በየጊዜው የሚከሰተው፣ የሚሰማው አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንቅልፍ ሊነሳ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም በአካባዎቹ ሰላም እንዲከበር ልዩ ትኩረት በመስጠት በህይወት የመኖር መብት የማስከበር መንግስታዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ እማጸናለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያ ምድር ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ከወዳጅ ሀገራት ጋር በእውነትና እውቀት መሰረት ላይ በመሆን መነጋገር አለበት ስል በአክብሮት አስታውሳለሁ፡፡ በተረፈ ቁጭ ብለን የሰቀልናቸውን ችግሮች ነገ ተነገወዲያ ቆመን ለማወርድ እንቸገራለን የሚለው በብርቱ የምሰጋበት ጉዳይ መሆኑን አበክሬ አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬ የነብሰ በላዎችና ሰው መሳይ አውሬዎች መርመስመሻ ( መፈንጫ) በሆነችው ለአብነት ያህል በተፈጥሮ ዘይት የበለጸገችው ሊቢያ የተፈጠረው ሁነት በእውነቱ ሊያስተምረን ይገባ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ያቺ የሰሜናዊት አፍሪካ አንጸባራቂ ኮከብ የነበረችው ሊቢያ፣ ሀብታም ሀገር የነበረችው ሊቢያ ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የባሪያ ንግድ ይካሄድባታል ተብሎ ሲነገር ማስደንገጥ እና ማሳዘን ብቻ ሳይሆን በፍጥነት የኢትዮጵያ መጽኢ እድል አይምሮአችን ውስጥ ሊደውል ይገባዋል፡፡  ሊቢያ ለዚህ ቀውስ በዋነኝነት የተዳረገችው በነጻነት እጦት ነበር፡፡ መሃመድ ጋዳፊ ለህዝባቸው ሀብትና ንብረት ሰጡት እንጂ ነጻነትን አላጎናጸፉትም ነበር፡፡ ድንገት ጊዜ ስትከዳቸው ያ ለዘመናት የታፈነ ህዝብ በምእራቡ አለም አይዞህ ባይነት በተለይም ፈረንሳይ፣ ጣሊያን አሜሪካ ጭምር ተገፋፍቶ ጋዳፊን ከስልጣን አሸቀንጥሮ ጣላቸው፡፡ ሲያልቅ …… እንዲሉ የጋዳፊ አሟሟታቸውም ጭምር አላማረም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሊቢያውያን በአፍሪካ ምድር የተከበሩትን ጋዳፊን ከስልጣናቸው ቢወርዱም የተመኙትን ነጻነት አላገኙም፡፡ የውጭ መንግስታት ነጻነትን ሊሰጡን አይቻለቸውም፡፡ እነርሱ የሚያልሙት በእኛ ኪሳራ የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅምን ማስላት ነው፡፡ ዛሬ ሊቢያ አንድ ጠንካራ መሪ በማጣቷ በጦር አበጋዞች ተወጥራለች፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዚህ የምንማረው ቁም ነገር ነጻነት ምን ያህል ለሰው ልጅ ደህንነትና እድገት አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ በብልጭልጭ አለም (ቁስ) አንታለል) ፣ከዚህ ባሻግር የመን፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን ምድር ላይ የሚከሰቱ የሰብአዊ ቀውሶች መማሪያ እንዲሆኑን ለበርካታ ጊዜያት የኢትዮጵያ ጉዳይ በሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ኡኡታ መሰማቱ ለላንቲካ አይመስለኝም፡፤ አሁንም በፍጥነት እንድንነቃ እማጸናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ የውጪው አለምም ጆሮ የሰጠው አይመስለኝም፡፡ በእኔ በኩል በአሁኑ ጊዜ  ማለቴ ነው፡፡ አለም አቀፉ የነጻ ፕሬስ  (The global free press is the most powerful weapon we have at the moment, ) በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመዘገብ ትልቅ ጉልበት ያለው ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነው የፖቲካ አጣብቂኝ፣ በተለይም ስለ አሳሳቢው የጎሳ ፖለቲካ ውጤትና ጉዳቱ በተመለከተ አለም አቀፉ የነጻ ፕሬስ ለአለም ሰላም ወዳ ሀገራትና ህዝብ በማሳወቅ እንዲረዱ ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡የኢትዮጵያን ክፉ ማየት የማይፈልጉ ወዳጅ ሀገራትም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ይመክራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ነጻ ፕሬስ በአለምም ሆነ በኢትዮጵያ አደጋ ከመከሰቱ በፊት በእውነት እና እውቀት መሰረት ላይ ሆኖ ለመንግስታት እና ለህዝብ አስተማሪ መልእክቶችን ስለሚያቀርብ መጠነ ሰፊ ችግሮች ተቀስቅሰው የርስበርስ እልቂት ከመከሰቱ በፊት፣ ስደትና ሞት ሳይከሰት በፊት መከላከል ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ 1977 ዓ.ም. ላይ ተከስቶ ለነበረው አሰከፊ ድርቅና ጠኔ በተመለከተ ለቀሪው አለም በቅድሚያ ያሰወቀው የነጻው ፕሬስ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ነጻው ፕሬስ የድርቁን መጠንና ስፋት በእውነት እና እውቀት መሰረት ላይ በመሆን ለአለም ስላሳወቀ ነበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ርሃብተኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ቅጠል ከመርገፋቸው በፊት የምእራቡ አለም የእርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች በፍጥነት የደረሱላቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር ያላቋረጠ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግስታት ልዩ ወኪሎችና የህዝብ ውትወታ ተጨምሮበት ነው የምእራቡ አለም  ሰብአዊ እርዳታ በችጋርና ጠኔ ተገርፎ ለነበረው በሚሊዮን ለሚቆጠረው ኢትዮጵያዊ ወገናችን  የደረሰው፡፡ ነጻው ፕሬስ ለአንድ ሀገር እንደመስታወት ሚቆጠር ችግር ጠቋ፣ መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውሶች ከመከሰታቸው በፊት ለአንድ ሀገር መንግስትም ሆነ ለአለም የሚሳይ መሆኑን በፍጹም መዘንጋት የለበትም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአለም መንግስታት፣ አለም አቀፍ ሰብአዊ መብት አስከባሪዎች እና የታወቁ አለም መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ የሚሰጡት ትኩረት አጥጋቢ መስሎ አይታየኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያን አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ሙሉበሙሉ ትኩረት አልሰጡትም ብሎ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ግን አዳጋች መስሎ ይታየኛል፡፡ ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ እንዲሉ እኛው ኢትዮጵያውያን የህብረት ችቦ መለኮስ ባለመቻላችን ለሀገራችን ስር የሰደደ የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ማምጣት እንዳልቻልን ማወቁ አዋቂነት ነው፡፡ ቢያንስ ላለመስማማት መስማማት ያባት ነበር፡፡ በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ብዙዎቻችን ለሀገር መድህን የሚሆኑ ሃሳቦችን ማንሸራሸር ሲገባን እርበርሳችን እንናቆራለን፡፡ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊጠቅሙ የሚችሉ ሃሳቦችን ማንሸራሸር ሲገባን፣ ስለማንችስትር እና ሊቨርፑል የእለት ውሎ ጉሮራችን እስኪነቃ እንጮሃለን፡፡ ኢትዮጵያ ስለገጠማት ከባድ ፈተና የሚጮሁ ፣ የሚጽፉ፣ ሃሳብ የሚሰነዝሩ ኢትዮጵያውያን ጥቂቶች ናቸው፡፡ በእውነቱ ለመናገር ህሊናን ያደማል፡፡ በመናናቅ፣ በአለመከባበር፣ በመለያየት፣ ሀገርን ማዳን እንደማይቻል ለመረዳት ሰላሳ አመት ፈጀብን፡፡ ዛሬም ብዙዎች ከጎሳ ፖለቲካ መገላገል ባለመፈለጋቸው የኢትዮጵን መከራ አራዝመውት ይገኛሉ፡፡ ለሀገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች የመጀመሪያ መፍትሔ አመንጪዎች እኛው ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ቀሪው አለም የእሳት አደጋ ተከላካይ ሆኖ ይደርስልን ይሆናል እንጂ አንዴ ከገባንበት የመከራ አዘቅት በፍጥነት ሊያወጣን አይቻለውም፡፡ የግራም ነፈሰ ቀኝ አንዳንድ አለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ለመምከር ጉባኤ ጠርተው የምሁራንን ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውን በቅርቡ ከጀርመን ድምጽ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል ፕሮግራም ላይ እንደሰማው አስታውሳለሁ፡፡ መቀመጫውን ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ያደረገው ይሄው አለም አቀፍ የምሁራን ስብስብ ተቋም በአዘጋጀው የምሁራን ምክክር ላይ እጅግ ተቃሚ ምክረ ሃሳቦች ተንሸራሽረው ነበር፡፡ በተለይም ዶክተር ለልኡል አስራተ ካሳ ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ ላለፉት ሰላሳ አመታት የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ እንደማበጃት በብዙ መልኩ መናገራቸውን፣ መጻፋቸውን አስታውሰው፣ አሁንም ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱን ከጎሳ ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ ተማጽኖአቸውን አሰምተዋል፡፡ እዚህ ሀገር ቤትም በቅርቡ የተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ውይይት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ( በነገራችን ላይ አንዳንድ እንደ ፕሮፌሰር መራራን የመሰሉ አንጋፋ ፖለቲካ ሰዎች ለኢትዮጵያ የሚበጃት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች የሚያደርጉት ውይይት ሳይሆን ብሔራዊ ዲያሎግ ነው ማለታቸው ተገቢ ነው ብሎ ጸሃፊው ያምናል፡፡) ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ግዜ ውስጥ የኢትዮጵያ አስቸጋሪ የፖለቲካ ጉዳይ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዊ ምሁራን ‹‹ ማይንድ›› በሚባል ተቋም አማካኝነት በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል ያለውን ልዩነት ለማስታረቅ የሁሉም ዜጎች ተወካዮች ያሉበት አንድ ጉባኤ እንዘጋጃለን ሲሉ መሰማታቸው ለኢትዮጵያ አንድ ተስፋ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በመጨረሻም ቸር ተመኝ፣ ቸር እንድታገኝ እንዲሉ ቸር ወሬ ያሰማን በማለት እሰናበታለሁ፡፡

 

ማጣቀሻ፤– ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ዶክተር ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ያዘጋጁትን ጥናታዊ ጽሁፍ ተጠቅሜአለሁ፡፡

Filed in: Amharic