>

ይድረስ ለአምባሳደር አንደብርሃን ወልደጊዮርጊስ (ኦሃድ ቤንዓሚ)

ይድረስ ለአምባሳደር አንደብርሃን ወልደጊዮርጊስ
“ኤርትራን የማከብረው አገሬን ስለምወድ ነው!!”
ኦሃድ ቤንዓሚ

*..ኤርትራ ውስጥ ተወልዶ እንዳደገ እና በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የበላ አብዛኛውን ከንቱ የጦርነት ድራማ በቅርበት እየተከታተለ ለኖረ ኢትዮጵያዊ ይህ አዲስ የዲፕሎማሲ ግኑኙነት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ብዙ ፍልስፍና አያስፈልገውም፡፡ ህይወቴና ኤርትራ ተያይዘዋል፤ ከኤርትራ ጋር የረጅም ዘመናት ታሪክ አለኝ
አምባሳደር አንደብርሃን ወልደጊዮርጊስ ይባላሉ፤ በአንድ ውይይት ላይ ስሜን እና ምድቤን እንዳነሱ አንድ ወዳጄ አይቶ ይህችን ያያዝኳትን ፊልም ቆርጦ ላከልኝ፡፡ፊልሙንመጫን አልቻልኩም፡፡ ግን ግድፈት ስላለበት ይህን ጽሁፍ ልልክላቸው ወደድኩ፡፡ አምባሳደሩን አላውቃቸውም፡፡ ትንታኔያቸው በሳል ነው፡፡ ነገር ግን እኔን ያስቀመጡበት ቦታ ትልቅ ስህተት አለበት እና አራሴን ልገልጽ መረጥኩ፡፡ አምባሳደሩ አሁን ባለው የፕሬዚደንት ኢሳያስ መንግስት ደስተኛ አለመሆናቸው የተደበቀ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረው ግኑኙነትም ለኤርትራ የሚኖረውን ፋይዳ ያሳንሱታል፡፡ ያ ግን አመለካከታቸው ነው፡፡ መብታቸውም ነው፡፡ነገር ግን ስለኔ ሲናገሩ “አንድ አሁን ያመጡት ኦሃድ ቤንዓሚ የተባለ …” ያሉት ነገር አለ፡፡ ከዚህ ልጀምር፤ እኔን ማንም አላመጣኝም፡፡ ብዙም እየወጣሁ መናገር ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ግኑኙነት ስሜቴን ልቆጣጠርባቸው ከማልችልባቸው ነገሮች አንዱ ነው፡፡
ኤርትራ ውስጥ ተወልዶ እንዳደገ እና በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የበላ አብዛኛውን ከንቱ የጦርነት ድራማ በቅርበት እየተከታተለ ለኖረ ኢትዮጵያዊ ይህ አዲስ የዲፕሎማሲ ግኑኙነት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ብዙ ፍልስፍና አያስፈልገውም፡፡ ህይወቴና ኤርትራ ተያይዘዋል፤ ከኤርትራ ጋር የረጅም ዘመናት ታሪክ አለኝ፤
ልጆች በነበርንበት ወቅት የኤርትራን መገንጠል አንፈልግም ነበር፡፡ ተወልደን ስናድግ መጀመሪያ የተነገረንን እያመንን ነው የምናድገው፡፡ ይህ በግጭቶች አካባቢ ተወልደው የሚያድጉ ልጆች ባሕሪያዊ እጣ ፈንታ ነው፡፡ ጦርነቱ ግን እድሜ ልካችንን እያሳደደን ሲሄድ፣ ሰብዓዊው እና ሰላማዊ ኪሳራው ሲያሻቅብና ዉጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የመተንበይ አቅማችን እየጨመረ ሲሄድ ቆም ብለን እናስባለን፡፡ በዙሪያችን ደግሞ ሁኔታውን የሚያብራሩልን ሰዎች ስናገኝ የተሻለ ዕድል ፈጥሮ መንገዱን ያሳጥርልናል፡፡
የ2ኛ ደረጃ ትምህርቴን ከአጠናቀቅኩ በኋላ መሃል አስመራ ላይ የነበረውን ምግብ ቤታችን ውስጥ ሰፋ ያለ ጊዜዬን በስራ ላይ አሳልፋለሁ፤ ምግብ ቤታችንን በርካታ የመሃል አገርና የመንግስት ሰዎች ይገቡበታል፡፡ የደህንነት ሰዎችም ያዘወትሩታል፡፡ ከአንዳንዶቹ ጋር ወዳጆች እንሆናለን፡፡ በነዚህ አመታት ውስጥ ሁለት ሰዎች የማልረሳው ስሜት ፈጥረውብኛል፡፡ የመጀመሪያው አሁን በህይወት የለም፤ ሻምበል አለማየሁ ይባላል፤ ከምስራቅ ጀርመን በደህንነት ሙያ ሰልጥኖ እዛው መስሪያ ቤት ውስጥ ይሰራ የነበረ ሰው ነው፡፡ ስለኤርትራ ጉዳይ ተነስቶ ስንከራከር “ግን እኮ መብታቸው ነው፤” ብሎ ስለ መሰረታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች፣ የኮሎኒያሊስት ድንበሮች ውሳኔ እና የኤርትራ ፌዴሪሽንን አፈራረስ ይተርክልኛል፡፡ ይህ የመጀመሪያው አይን ገላጭ አጋጣሚዬ ነበር፡፡ ሁለተኛው የባሕር ኃይል ሻምበል የነበረ አሁን የት እንዳለ የማላውቀው የቤተሰባችን ወዳጅ የነበረ ሰው ተመሳሳይ ነገር ይግረኝ ነበር፡፡ የት እንዳለ ስለማላውቅ ስሙን አልጠቅስም፡፡ የሚገርመው ግን ያኔ ቦታ ባንሰጠውም አሁን ሳስታውስ ሁለቱም አማራዎች ናቸው፡፡
እነሱ ያሉት ባይዋጥልኝም የሰጡኝ ገለጻ ከአእምሮዬና ከሕሊናዬ አውጥቼ የምጥለው አለሆነም፤ ሶስተኛው የአንዲት የገዛ-ባንዳ ጢሊያን አካባቢ ጓደኛዬ ገጠመኝ ነው፡፡ አንድ ወቅት እቤታቸው ስንጫወት አምሽተን ልትሸኘኝ የግቢው በር ላይ ቆመን ከመሰነባበታችን በፊት ከርቀት ከሰሜናዊው የአስመራ ከተማ ተራሮች ጀርባ የከባድ መሳሪያ ጥይቶች (ምን አልባት 40 ጎራሽ BM) እሳት እየተፉ የጨለማውን አድማስ እየሰነጠቁ ሲወነጨፉ እናያለን፡፡ ርቀት ስለነበረው እሳታቸውን እናያለን እንጂ ድምጻቸውን መስማት አንችልም፤ ጉዳዩ የተለመደ ክስተት ነው፡፡ “ጦርነት አለ ማለት ነው፤” አልኩኝ በለሆሳስ አንደበት፤ እሷ ግን በሃሳብ ተውጣ በጨለማው ባዶነት ላይ አይኖቹን አንሳፋ ቀርታለች፡፡ ዝምታ ውጧታል፡፡
አተኩሬ ስመለከታት አይኖቿ እንባ አቅርረዋል፡፡ ትዝ አለኝ ሁለት ወንድሞቿና አንዲት እህቷ የነጻነት ትግሉን ተቀላቅለዋል፡፡ እነዛ የአርባ ጎራሽ ሚሳይል መድፎች ለኔ የጦርነት ዜናዎች ናቸው፤ ለሷ ደግሞ በረሃ ባሉት ወንድሞቿ እና እህቷ ላይ የሚዘንቡ የሞት መልዕክተኞች ናቸው፡፡ ይህ የእያንዳንዱ ኤርትራዊ ቤተሰብ ታሪክ ነው፤ ስሜቷን አለመረዳት አይቻልም፡፡ አጋጣሚው አመለካከቴን በጣም እንደፈተነው አስታውሳለሁ፡፡
ኤርትራዊት ሚስቱን “ዘመዶችሽን አንጫጫናቸው፤” እያለ ሲሳለቅ የነበረ አንድ የመሃል አገር ጨካኝ ሰው ሲናገር እና ዋይታቸውን ትግርኛ አጥርቶ መናገር በማይችል አፉ “እዋይ አነ ወዲኦምና ወዲኦምና” (ወይኔ ጉዴ ወይኔ ጉዴ ጨረሱንኮ ጨረሱን እኮ) እያለ ሲያላግጥበት የሰባት አመት ልጅ ነበርኩ፤ ያኔ በኮልታፋ አነጋገሩ ስቄያለሁ፤ ነፍስና ፖለቲካ እያወቅኩ ስመጣ ግን “ምንድን ነበር ያለው ያ ጨካኝ ሰው?” ብዬ እጠይቃለሁ፤ ሁኔታው አሁንም እንደ ፊልም ይታየኛል፡፡ ከአእምሮዬ ለመጥፋቱ ሁሌም ይገርመኛል፡፡
እነዚህ እና ሌሎች ብዙ ነገሮች ስለ ኤርትራ ጉዳይ ያለኝን አቋም እንድፈትሽ፣ የኮለኔሉን የጦርነት አማራጭ በተለይም የቀይ ኮከብ ዘመቻ ውድቀት ሁሉን ነገር እንድጠይቅ ቢያደርጉኝም በኤርትራ መገንጠል ማመን ትልቁ ችግሬ ነበር፡፡ ግን በኤርትራውያን ላይ ይፈጸሙ የነበሩ በደሎችን መቀበል ደግሞ ይከብደኝ ነበር፡፡ በተራ ጥርጣሬ በአሰቃቂው የማርያም ግምብ እስር ቤት ውስጥ ታስረው አጎቴ “ሰበ-ስልጣኖችን” ለምኖ ያስፈታላቸውን ወጣቶች አስታውሳለሁ፤ የሚለምንላቸው ሰው የሌላቸውን ወጣቶች ቤት ይቁጠረው፤ አማርኛ መናገር የሥርአቱ ጠባቂ ተደርጎ ሌላው የሚሸማቀቅባቸውን ዘመናት አልረሳቸውም፤ ከፋሲካ ዋዜማ ቤተክርስቲያን መልስ ያለምንም ጥፋት ቁም ተብሎ የተገደለ ጓደኛም ነበረኝ፡፡ ሌሎች ብዙ ግፎችን መጥቀስ ይቻላል፤ “እዛ ሰፈር እንኳን ሰው ዛፍ እንዳይቀር፤” የሚሉ እርምጃዎች የሚወሰዱባቸው ቀበሌዎችና የገጠር መንደሮች ታሪክ ብዙ ነው፡፡ በአጭሩ ኤርትራ ውስጥ ከፍተኛ ብዙ ግፍ ተፈጽሟል፡፡ የወንጀሉ ተጠያቂ ባንሆንም ከሕሊና ክስ እና ፍርድ ማመለጥ ግን አንችልም፡፡ ትግራይ ውስጥም ደርግ ተመሳሳይ በደሎች ይፈጽም እንደነበረ ሳላሰምርበት ማለፍ አልፈልግም፤ ደርግ ብዙ በደሎችን ፈጽሟል፡፡
በዩኒቨርስቲ ዘመኖቼ የማነባቸው መጻህፍት፣ የመረጥኩት የትምህርት ዘርፍ እና ከኤርትራውያን ጋር የነበረኝ ቅርበት ብዙ ነገሩን ጠለቅ ብዬ እንዳየው አድርጎኛል፡፡ በውስጤ እያመንኩበት እንኳን ከዩኒቨርስቲ ጓደኞቼ ጋር ስንገናኝ ክርክሩ ላይ እበረታ ነበር፡፡ መገንጠል የተሻለው አማራጭ ነው ብዬ አላምንም ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይ ከሁለቱ ኤርትራውያን ጓደኞቼ ሚሊዮን ኃይሌ ቀለታ እና ኢብራሒም ሲራጅ ጋር በሳል ክርክሮች እናደርጋለን፡፡ የፈለኩትን ያክል ላሳምናቸው ብሞክርና የራሴ የምለው እውነት ቢኖረኝም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ግን መለወጥ አይቻልም፤ ደርግ ተሸነፈ፡፡
ግንቦት 16፣ 1983 ኤርትራ ነጻ ሃገር ሆነች፡፡ ከዚህ በኋላ ከእውነታው ጋር መላተም ጥቅም የለውም፤ ስለዚህ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የኤርትራን ሉኣላዊነት ያከበረ ለሁለቱ አገሮች ሰላማዊና ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያለው ግኑኙነት ላይ ከመስራት የተሻለ ውለታ ለሃገሬ ላደርግላት አልችልም፡፡ ኤርትራን የማከብረው አገሬን ስለምወድ ነው፤
በዘመናት ውስጥ ያየሁት እና የተረዳሁት ነገሮች ኤርትራ ከሁሉም ጎረቤቶቿ በላይ ለኢትዮጵያ የምታስፈልግ ሃገር መሆኗን ነው፡፡ በተጨባጭ አጭር አገላለጽ አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ስልሳ እና ከዛ በላይ ለነበሩት አመታት ከፍተኛዎቹ የፖለቲካ ምስቅልቅሎቿን የወረሰችው ከኤርትራ ጋር በተያያዙ ችግሮች ነው፡፡ ብዙ ዋጋ ከፍለንበታል፡፡ አሁንም እየከፈልንበት ነው፡፡
ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩትም አንዱን ብቻ ልጥቀስ፡፡ ኤርትራ ውስጥ ያልሰለጠነ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሽምቅ ተዋጊ ኖሮን አያውቅም፡፡ የማይካድ ነው፡፡ ግን ይህን ፈርተን ሳይሆን አዎንታዊውን እንደምታ አስበን ከተራመድን ኤርትራ ለኢትዮጵያ የምታስፈልግባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡
አስራ ሰባቱንም እዚህ ላይ በመጥቀስ አላሰለቻችሁም፤ ዋና ዋናዎቹን ልናገር፡፡
 በኢኮኖሚ የሚኖረንን ጥቅም ካሰላነው ሁለቱ አገሮች ተመጋጋቢ ሁኔታ አላቸው፣ የቀይባህርን በመጠቀም ከነጅቡቲ እና ሌሎች አጎራባች አገሮች ጥገኝነት እንድናለን፡፡ እስካሁን ጂቡቲ ላይ ያፈሰስነውን ኤርትራ ላይ ኢንቨስት ብናደርገው የበለጠ የተጠናከረ ግኑኙነት ይኖረናል፡፡ ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ ይሆንልን ነበር፤
 በዲፕሎማሲ፣ ኤርትራ ታስፈልገናለች፤ ምክንያቱም እኛ ወዳጅ ካላደረግናት ጠላቶቻችን መጠቀሚያ ሊያደርጓት ይችላሉና፤ ስለዚህ ኤርትራን ወደ ምርጥ ጎረቤት ሃገር (most favored neighboring nation status) ሆነ ደረጃ ለማምጣት መስራት አለብን፤
 በሰላም (peace) ከለካነው እስካሁን በታሪካችን ከኤርትራ ጋር ያደርግናቸው ጦርነቶች ከፍተኛውን ኪሳራ ያስከተሉብን ናቸው፡፡ አሁንም ይህን በማያዳግም ሁኔታ ካልቋጨነው ተመልሰን እዛው ልንገኝ እንችላለንና በሳል ዲፕሎማሲ ያስፈልገናል፡፡
 በደህንነት (security) ጉዳይ ካየነው ኤርትራውያን ያውቁናል፡፡ ከነሱ ጋር ሰላም ከሆንን የውስጥ ጠላቶቻችንን እድል ማዘጋት እንችላለን፡፡ (ምሳሌው ግልጽ ነው፤) በተጨማሪም ግኑኙነታችን አድጎ የጦር ቃል ኪዳን የተፈራረሙ ሃገሮች ብንሆን ደግሞ የበለጠ የተፈራን እና የተከበርን አገሮች እንሆናለን፡፡ (ሱዳን ወደ ድንበራችን ጠልቃ ስትገባ ኤርትራ ወታደሮቿን ያስጠጋችበት ሁኔታ በቂ ማስረጃ ነው፤) የኤርትራ ጂኦፖሊቲካል መልከኣ ምድር ብዙ ወሳኝ ነገሮች አሉት፡፡
 በአለም አቀፍ ግኑኙነት ከተመለከትነው ከጎረቤቶቿ ጋር የምትስማማ አገር የተሻለ የአለም አቀፍ ግኑኙነት አቅም ይኖራታል፡፡ አገራችን የአፍሪካ የቅኝ ግዛት አገሮችን ነጻ ለማውጣት ብዙ የደከመች እና የተመሰከረላት አገር ነች፡፡ ከኤርትራ ጋር ባለው ሁኔታ ግን ንጉሱ የሄዱበት አካሄድ ያንን ገጽታዋን ያበላሸና አገሬን አደራዋን የበላች ሞግዚት ያደረገ ጥቁር ጠባሳ ነበር፡፡
 በሕዝብ ለሕዝብ ግኑኙነት ከተመለከትነው ያሉን በርካታ የጋራ እሴቶቻችንን ተጠቅመን የምስራቅ አፍሪካን ትልቁን ጂኦ-ፖሊቲካል እና ኢኮኖሚያዊ አምባ መፍጠር እንችላለን፡፡ ይህን የሚፈሩት አገሮች ብዙ ናቸው፤ ኤርትራውያን ጥሩ የሥራ ባህል አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለኤርትራውያን ጥሩ ልብ አላቸው፡፡ የሃምሳ አመት ጦርነት (ከወያኔ በፊት ሰላሳ በወያኔ ጊዜ 20 አመታት) ቅራኔዎች፣ ግጭቶች እና ጦርነቶች ሊቆርጡት ያልቻሉት ጠንካራ ባህላዊ እና ወንድማማቻዊ ግኑኙነት አለን፤ ጋዜጠኛው ዮናስ አብራሃም እንደሚለው “እየተገዳደልንም እንዋለድ ነበር፤”፡፡ ይህን ግኑኙነት ማሳደጉ ለሁላችንም ይጠቅመናል፡፡ በርግጥ የኤርትራውያን የመዋጥ ስጋት እና የኢትዮጵያውያን ቀይባሕርን የማግኘት ጉጉት (ambition) እና ሌሎች ችግሮች ለዚህ ውጤት እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፤ ነገር ግን በመቀራረብ እና በመረዳዳት ሁሉንም ስጋቶች አንድ በአንድ ማስወገድ ይቻላል፡፡
 ይህ የመጨረሻው የግሌ ትዝብት የምለው ነው፡፡ ኤርትራውያን ጥሩ ሕዝቦች ናቸው፤ በጦርነት ያጣናቸው አልማዝና ዕንቁዎች ናቸው፡፡ በሰላምና በፍቅር ልባቸውን መመለስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የተበደሉት እነሱ ናቸውና ተነሳሽነቱ ከኛ መምጣት አለበት፤ (ስለ መሬትና የባሕር በር አደለም የማወራው፤ ስለ ውድ ሕዝብ ነው፤)
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ጥቅሞች በተመሳሳይ ሁኔታ ለኤርትራም የሚሰሩ ናቸው፡፡
ስለዚህ ለአምባሳደር አንደብርሃን ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት አጭር ነው፡፡ ይህን ቢያውቁልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ማንም የላከኝ ወይም እርሶ እንዳሉት “አሁን ደግሞ ያመጡት ኦሃድ ቤንአሚ የሚባል..” አይነት ሰው አይደለሁም፡፡ ከጠሯቸው ሰዎች ጋር በፍጹም የምፈረጅም አይደለሁም፡፡ ስለራሴ ብዙ ማውራት አልወድም፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ግኑኙነት ዙሪያ የተሻለ እና የበለጠ ነገር እንዲመጣ አንዳንድ ነገሮችን የመስራት ፍላጎት ስላለኝ መንገዴን የመጥረግ ኃላፊነቱ የራሴ ስለሆነ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው መልካም ግኑኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲያድግ እፈልጋለሁ፤ የምችለውንም አደርጋለሁ፡፡
ምክንያቱም አገሬ ከአምባገነን አመራር ውስንነት፣ የጦርነቱን የመጨረሻ ውጤት ማየት ካለመቻል የኤርትራን ጦርነት ሁለንተናዊ ምንነት ካለመረዳት የተነሳ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡ የሷ ላልሆነ የባድመ መሬት ለበቀል ማወራረጃ በተከፈተ ጦርነት ከአስራ አምስት ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሰባ ሽህ ወጣት ልጆቿን አጥታለች፤ የሰላሳ አመቱን የመተላለቅ አሃዙን ማስላት ያስፈራል፤ በዘመቻ ፈንቅል ከአርባ ስምንት እስከ ሰባ ሁለት ሳዓታት ውስጥ በተካሄደ ውጊያ ታንኮች ብቻ 163 አጥታለች፡፡ 163 ትምህርት ቤቶችና ክሊኒኮች ይከፍትልን ነበር፡፡ አስመራ አየር ኃይል ኤርፖርት የነደዱትን አውሮፕላኖች ሳንረሳው ማለት ነው፤ የአስራ አንዱ ቢሊዮን ብር ዕዳም ብዙ መሰረተ-ልማት እና ታላላቅ የእርሻ ጣቢያዎች ከፍቶ ረሃብን ታሪክ ያደርግልን ነበር፤ በመጨረሻም ከ450,000 በላይ ወታደሮች እንዲሁ ተበትነውባታል፡፡ እንደው እነዚህን ለምሳሌ አነሳሁ እንጂ በሰላሳ አመታት ውስጥ ከሁለቱም ወገን የጠፋውን የሰው ህይወት፣ የወደመውን ሃብት፣ አገር ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ ምስቅስቅል፣ እና ትውልድ የወረሰውን ድህነት መከራ እና ዘረኝነት ትክክለኛ ግምገማ ለማድረግ ራሱን የቻለ ጥናት እና ምርምር ያስፈልገዋል፤ ማንም ለጉዳዩ ቅርበት ያለውና ሕሊናውን ለማመዛዘን የሚጠቀም ኢትዮጵያዊም ሆነ ኤርትራዊ እንዳይደገም እና ወደዛ ምዕራፍ እንዳንመለስ የሚችለውን ከማድረግ ወደኋላ አይልም፤
ለዚህ ነው የኤርትራን ምንነት መረዳት አስፈላጊ እና ወደተሻለ እና የላቀ የፖለቲካ ግንኙነት መምጣት አለብን ብዬ የማምነውና የምናገረው፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ለገጠሟት ችግሮች ተጠያቂዋ ኤርትራ ነች ማለቴ እንዳልሆነ ማብራራት የሚጠበቅብኝም አይመስለኝም፤
አምባሳደር ከቻሉ ያግዙኝ ካልቻሉ ደግሞ እውነታውን ተረድተው ይከታተሉኝ፡፡ ኤርትራን የምወደው አገሬን ስለምወድ ነው፤ አመሰግናለሁ፡፡
የቻላችሁ ይህን ደብዳቤ ለአምባሳደር አምደብርሃን ወልደጊዮርጊስ አድርሱልኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
Filed in: Amharic