>
5:21 pm - Tuesday July 21, 0099

አጼ ምኒልክ ደሃ ሲበደል፣ ፍትህ ሲጓደል አይሆንላቸውም፤  ሰብአዊነቱስ ማን እንደ እምዬ??? (ሞገስ ዘውዱ ተሾመ)

አጼ ምኒልክ ደሃ ሲበደል፣ ፍትህ ሲጓደል አይሆንላቸውም፤  ሰብአዊነቱስ ማን እንደ እምዬ???
ሞገስ ዘውዱ ተሾመ

አምዬ ምንሊክ ሲነሳ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የአድዋ ጦርነት፣ የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ትግል፣ የዘመናዊ ኢትዮጵያ ግንባታ ነው። ዛሬ ግን ስለ ፖለቲካ አላነሳም፣ ውዝግብ ውስጥም አንገባም። ዛሬ እምዬ ምንሊክን ከሰብአዊነት አንፃር ብቻ እናስታውሳቸዋለን። ይሄንንም አለም የመሰከረው፣ አገር ውስጥም የሚታወቅ፣ ተሰንዶ የሚገኝ ነው።
በእርግጥ “እምዬ” የተባሉት ያለ ምክንያት አይደለም። በኢትዮጵያ ታሪክ እምዬ ተብሎ የተጠራ ንጉስም ሆነ አስተዳዳሪ እስካሁን የለም። እምዬ የደግነት፣ ፍትህ፣ የእናት እንክብካቤ እና ፍቅር ተምሳሌት ነው። እምዬ ደሃ ሲበደል፣ ፍትህ ሲጓደል አይሆንላቸውም። በአባ መላ ፊታውራሪነትም የፍትህ ስርዓቱን ፈር ለማስያዝ ሞክረዋል።
የእምዬ ምንሊክ ፍፁም ሰብአዊነት፣ ለጠላት እንኳን መራራት፣ ጦርነትም ህግና ስርዓት እንዳለው በዚያ ባልሰለጠነ ዘመን በተግባር ለአለም ያስተማሩ ናቸው። ከብዙ በጥቂቱ፣ ከንጉስ ተክለሃይማኖት ጋር ሲዋጉ ከማረኩት በኋላ “ስትወጋኝ የቆየህ ቢሆንም ከተሸነፍክ በኋላ በቀል አላውቅም” በማለት እርቅ አውርደዋል። ወደ ደቡብ በዘመቱ ግዜም ንጉስ ጦናን ከማረኩ በኋላ ” የዚህን ሁሉ ህዝብ ደም በከንቱ አፈሰስን። አሁንም ቢሆን የድሃውን ሀብትና ንብረት አትዝረፉ፣ ፍትህም አይጓደል” በማለት ታሪክ ሰርተዋል።
የጣልያንን ጠላት፣ ለዚያውም ድንበር ብቻ ሳይሆን ባህር ተሻግሮ ለመጣው “ፍልፈል” ፣ ፍፁም ርህራሄ አሳይተዋል። መጀመሪያ ገና ጦርነቱ ሳያልቅ በመቀሌው ከበባ (the siege of Mekelle) 900 የሚያህል የጣሊያን ወታደር በውሃ ጥም ሊያልቅ ሲል፣ ልምናቸውን ተቀብሎ ውሃ እንዲጠጡ፣ ጦርነት ከፈለጉ ግን በሜዳው እንዲገጥሙ አድርጓል። ከጦርነቱ በኋላ ወደ 3000 የሚጠጉ ምርከኞች እጣ ፈንታ አነጋጋሪ ነበር። አብዛኛው መኳንንት፣ እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ እንዲቀጡ፣ ቅጣቱም በባህላዊ መንገድ እንዲሆንና እጃቸው እንዲቆረጥ ሀሳብ አቅርበው ነበር። እምዬ ምንሊክ ግን “ጦርነትም ቢሆን ወግ አለው፣ ጦርነት ሰብአዊትን አይገፍም። ወደ አገራቸው መመለስ የፈለጉትም ተለቀው በነፃ ይሂዱ” በማለት በርካታ የጣሊያን ምርኮኛ ወደ አገሩ ተሸኝቷል። ለዚያውም ስንቅ ለሌለው ተቋጥሮለት።
እናም እምዬ ምንሊክ ከ130 አመታት በፊት ለጠላት ያሳዩትን ሰብአዊነትና ርህራሄ እኛ ዛሬ አለም በሰለጠነትበት ዘመን እንዴት ለወንድም( እህቶቻችን) ማሳየት አቃተን? እኛ በልተን እያደርን ሌላው ኢትዮጵያዊ በማያውቀው ጦርነት በረሃብ ሲሞት ማየት ለኛ የቁም ሞት፣ የውርደት ሁሉ ውርደት ነው።
Filed in: Amharic