>

ከ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጋር ተያይዞ የተዘጋጀ የኢሰመጉ መግለጫ ....!

ከ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጋር ተያይዞ የተዘጋጀ የኢሰመጉ መግለጫ ….!

ጥቅምት 22/2015ዓ.ም  

መግቢያ፡ 

የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ በመግለጽ ትምህርት ሚኒስቴር የቅድመ ዝግጅት ስራ በመስራት ከተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በየአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በማጓጓዝ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናውን ወስደዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ቀደም ሲል ሲሰጥ የነበረው የማትሪክ ፈተና በተለያዩ አካባቢዎች ፈተናው እንደሚወጣና ይህንን ቸግር መፍትሔ ለመስጠት በዩኒቨርሲቲዎች ቢስጥ ችግሩን እንደሚቀርፍ በማመን ፈተናዎችን በዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት በወሰነው መሰረት መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናውን ተፈትነዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን ለመቅረፍ የወሰደው እርምጃ እጅግ በጣም ጥሩ አና የሚበረታታ

እርምጃ ነው፡፡ ይሁንና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናውን ግቢ እና ቴክኖሎጂ ካምፓስን በሚያገናኘው ድልድይ ላይ የተዘረጋው የብረት መሻገሪያ በመሰበሩ የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን፣ ጥቂት ተማሪዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን እና በርካታ ተማሪዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ከምስራቅ ጎጃም ዞን ተንጉማ፣ ፈለገብርሀን እና ከደብረወርቅ ሀለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ መፈተኛ ጣብያ የገቡ ተማሪዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ፈተናውን ሳይፈተኑ ጥለው ወጥተዋል፡፡

ጥቅምት 01/2015 ዓ.ም በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ በዩኒቨርስቲው ለመፈተን ከተመደቡ ተማሪዎች መካከል አንድ ተፈታኝ ተማሪ የፈተናውን ስርዓት ባለመከተሉ ለእስር ሲዳረግ ሌሎች ተፈታኝ ተማሪዎች የታሰረው ተማሪ ይፈታ በሚል ተቃውሞ እንደጀመሩና ጉዳዩም እየሰፋ ሄዶ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ግድያዎች እና እስራት ይቁሙ ወደሚል ተቃውሞ አድጎ በተፈጠረው ግርግር 3 ፈታኝ መምህራን እና 3 ተፈታኝ ተማሪዎች ከፍተኛ እና ቀላል የአካል ጉዳት ሲደርስባቸዉ አንድ ተፈታኝ ተማሪ ደግሞ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ማለፉን፣ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች አንፈተንም በሚል ግቢዉን ጥለዉ እንደወጡ፣ የእምነት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን በማምጣት ለማግባባት እንደተሞከረ እንዲሁም እረብሻውን አስነስተዋል ተብለው የተጠረጠሩ 30 ተማሪዎች በደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት ታስረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ10ቀን በላይ ከታሰሩ በኋላ መፈታታቸውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በተጨማሪም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፈተናው አስቀድሞ ተሰራጭቷል በሚል ባልተረጋገጠ መረጃ ምክንያት አንዳንድ ተማሪዎች ፈተናውን ሳይፈተኑ ጥለው መውጣታቸውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በተጨማሪም የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከጥቅምት 05 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ መፈተኛ ማዕከላት የገቡ ሲሆን ጥቅምት 07 ቀን 2015  ዓ.ም ስለፈተናው ገለጻ ከተደረገላቸው በኋላ ከጥቅምት 08 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ፈተናውን ወስደዋል በእነዚህ የፈተና ቀናት ውስጥ ምንም አይነት ችግር እንዳልተፈጠረ እና ፈተናው በሰላማዊ ሁኔታ መጠናቀቁን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

ተያያዥ የህግ ድንጋጌዎች፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 6(1) እና  9(1) ላይ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት በቃል- ኪዳኑ (ICPR) የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2(1) እና 2(2) ይደነግጋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት  ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 14  “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። የከፍተኛ ትምህርትአዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 1ሐ ላይ ተማሪዎች በተቋሙ ግቢ ውስጥ ህገ-መንግስታዊ ሰብዓዊ መብታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቀ የመኖር መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥትአንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ3 የተያዙ ሰቀዎች ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳላቸው በግልጽ ይደነግጋል በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ3 በወንጀል ክስ የተያዘ ወይም የታሰረ ሰው ከዳኛ ወይም በህግ ስልጣን ከተሰጠው አካል ዘንድ በአፋጣኝ ሊቀርብ እንደሚገባ የኢሰመጉ ጥሪ፡

 በሀዋሳ እና በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሞቱ ተማሪዎች ኢሰመጉ ሀዘኑን እየገለጸ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ተማሪዎች በቂ ህክምና እንዲያገኙና ወደፊት ፈተናውን የሚፈተኑበትን መንገድ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲያመቻች፣

 በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ከዋናው ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ ካምፓስ የሚያሸጋግረው ድልድይ የመደርመስና በተፈታኞች ላይ የሞት አደጋ የማድረስ እንዲሁም የፈተና ስርዓቱ እንዲቃወስ ምክንያት የሆኑ አካላት ማለትም ግንባታውን ካከናወኑና ጥራት ማረጋገጫ ከሰጡ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ላይ ተገቢ ምርመራ በማድረግ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ፣

 በመቀደላ አምባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ፈተናውን ሳይፈተኑ የወጡ ተማሪዎች ሳይፈተኑ የወጡበትን ምክንያት በተገቢው ሁኔታ በማጣራት እነዚህ ተማሪዎች ለቤተሰብም ለሀገርም ሀብት በመሆናቸው ጥፋተኛ ተማሪዎችን በሚገባ በመለየት ፍትሀዊ የሆነ ውሳኔን እንዲሰጥ፣  በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት በነበረ ተቃውሞ በተፈጠረ ግርግር ምክንያት የሰው ህይወት በመጥፋቱ መንግስት ጉዳዩን በማጣራት ጥሰት ፈጻሚዎችን በህግ እንዲጠይቅ፣

 ትምህርት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተማሪዎች ለወደፊት ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ በማስተማርና በማነጽ ረገድ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Filed in: Amharic