>

ተቃውሞ ከሁለት ማዕዘናት  (ግርማ ካሳ)

ተቃውሞ ከሁለት ማዕዘናት 

 

ግርማ ካሳ

የደቡብ አፍሪካዉ ስምምነት ለኢትዮጵያዉን መልካም ዜና ነው፡፡ የተለያዩ ቅር የተሰኘንበት ነገር ሊኖር ቢችልም፣ ቢያንስ ጦርነቱን አቁሟል፡፡ ቢያንስ ዛሬ ሰው እየተገደለ አይደለም፡፡

አንዳንድ የትግራይ ተወላጅ ዳያስፖራዎች እንዲሁም የሕወሃትን አቋም ሲያንጸባርቁ የነበሩ አክቲቪስቶችና የሚዲያ ተቋማት፣  የደቡብ አፍሪካን ስምምነት እየተቃወሙ ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ሰልፍች እየተደረጉ ነው፡፡   በሲያትል በተደረገው ተቃውሞ በመኪና፣ ቢጫና ቀይ የሆነውን የቪትናም የሚመስለውን አርማ ለጥፈው ዋና መንገድን እስከመዝጋትም ደርሰዋል፡፡

የርዮት ሜዲያ ቴዎድሮሶ ጸጋዬ ፣ የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት፣ “የትግራይን ሕዝብ ለአራጆች ያቀረበው ሰንድ” ብሎታል፡፡ “Military and Foreign Affairs Network” በሚል ዩቲብ ሜዲያ ላይ ካርታ እያሳየ ዘገባ የሚሰራ፣ ብዙ የህወሃት አክቲቪስቶችም የሚጠቅሱት ፣ ግ ስሙን የማይገልጸው፣ ራሱን ፣ “voice of reason”፣ አንድ ወዳጄ ግን “voice of unreason”ብሎ የሚጠራው፣ አፍቃሪ ሕወሃት ግለሰብ፣ “extermination agreement” ነው ያለው፡፡ እነዚህን እንደ ምሳሌ ጠቀስኩ እንጂ ተቃውሞው በውጭ አገር መጠነ ሰፊ ነው፡፡

ላለፉት ሁለት አመታት ነገሮች እጅግ በጣም ጦዘው ነበር፡፡ እንኳን አክቲቪስቶች ሰላማዊ በሆኑ የትግራይ ሰዎችና ሌሎች መካከል፣ በባልና ሚስቶች መካከል ፣ ለረጅም ጊዜ ጓደኛሞቹ በነበሩ መካከል መከፋፈሉ፣ መቃቃሮች ነበሩ፡፡ ሁላችንም በጦርነቱ ምክንያት አብደን ነበር፡፡ ሁላችንም ውስጣችን እሳት ነው የነበረው፡፡ እሳት ላይ የነበረ ምጣድ እንዲቀዘቅዝ  ትንሽ ጊዜ እንደሚያስፈልገው፣ አሁንም ነገሮች እስኪቀዘቅዙ ትንሽ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በመሆኑም የነዚህ ወገኖች ተቃውሞ ለምን እንደሆን ይገባኛል፡፡

በኔ እምነት ምጣዱ ቶሎ እንዲቀዘቅዝ የማድረግ ሃላፊነት ያለበት የብልጽግና መንግስት ነው፡፡ እነዚህ ተቃውሞ የሚያሰሙ ወገኖችን ልብ የማሸነፍ ስራ መሰራት መቻል አለበት፡፡ አብይ አህመድ በአርባ ምንጭ  አሸነፍን ወዘተ እያለ ሲደነፋ እንደነበረው፣ ምጣዱን ከማቀዝቀዝ ይልቅ፣ የበለጠ እሳት የመለኮስ ስራ ከመስራት ብልጽግናዎች መቆጠብ አለባቸው፡፡  ይልቅ የትግራይን ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን በቶሎ በማሟላት፣ ህዝቡን በማክበር፣ በርግጥ ስምምነቱ ፣ “extermination” ሳይሆን “salvation” መሆኑን ማሳየት ነው የሚገባችው፡፡

በትግራይ ዳያስፖራ መካከል የተነሳው ተቃውሞ አንዱ ነው፡፡ ከሌላም ማእዘናት ፣ ከአማራ ማህበረሰብ ተቃውሞዎችም እያቆጠቆጡ ነው፡፡ በተለይም በስምምነቱ የነ ወልቃይት ጉዳይ፣  የህወሃት ሰነድ በሆነው፣ አማራ ጠልና ጸረ አማራ ተደርጎ በሚቆጠረው ሕገ መንግስት መሰረት ይፈታል የተባለው፣ ለአማራው ማህበረሰብ ንቀት እንደማሳየት ነው፡፡ የአማራውን ማህበረሰብ ከብልጽግና መንግስት ጋር በቀጥታ ወደ ጦርነት ሊወስደው የሚችል፣ ምን አልባት የነ አብይ አህመድ እድሜ የሚያሳጥር time bomb ነው፡፡  በዚህ ጉዳይ ላይ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውድ ከእሳት ጋር አትጫወቱ አይነት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በጦርነቱም፣ ጀነራል ታደሰ ወረዳ  በብዙ ቦታ  የአማራ ኃይሎች ውጊያ ሲያደርጉ እንደነበረ በይፋ የገለጸበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ ኮረምን ለማስለቀቅ በተደረገ ከባድ ውጊያ፣  ኮረም ከመደረሱ በፊት ያለችዋን ስትራቲጂክ ቦታም፣ ዛታን የያዘው የአማራ ፋኖና ሚሊሻ ነው ብሎ ነው የተናገረው፡፡ ከዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት ፣ ወልቃይት፣ ራያ፣ ጠለምት ሙሉ ለሙሉ በአማራ ኃይሎች ስር ነው ያሉት፡፡

በዚህ መልኩ ከፍተኛ የሆነ የታጠቁ፣ የተደራጁ ፣ ብቃት ያላቸው የአማራ ኃይሎች ባሉበት፣ የአማራውን ማህበረሰብ አግልሎ፣ ብቻውን የብልጽግና  መንግስት ከህወሃት ጋር ተነጋግሮ ፣ የወሰነውን ውሳኔ፣ እነ ወልቃይት ላይ ሊተገብር አይችልም፡፡ በአጭሩ አነጋገር የደቡብ አፍሪካ ስምምነት የሚሰራው  proper Tigray  በተባለው ነው እንጂ ወልቃይት፣ ራያና ጠለምትን አይመለከትም፡፡

ይህን ስል በነ ወልቃይት ባሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ንግግር አያስፈልግም ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን “እነ አብይና ህወሃቶች ብቻ በነ ወልቃይት ጉዳይ የመወሰን የሞራል ብቃት የላቸውም፡፡ የደቡብ አፍሪካው ስምምነት እነ ወልቃይትን አይመለከትም” ማለቴ  እንጂ፣ በወልቃይት ጉዳይ ላይ ውይይቶችማ መደረግ አለባቸው፡፡ በነ ወልቃይት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጋሩዎች አሉ፡፡ ብዙ የተፈናቀሉ አሉ፡፡ በመሆኑም የትግራይ ሽማግሌዎችና ልሂቃን፣ ከአማራ ሽማግሌዎችና ልሂቃን ጋር በመሆን፣ በቅንነት ተነጋግረው፣  እነርሱ እራሳቸው ሊፈቱት የሚችሉት ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡  ሁሉንም አሸናፊ ያደረገ፣ ዘላቂ መፍትሄም ማግኘት ይቻላል፡፡

ለማጠቃለል በትግራይ ዳያስፖራዎችም፣ በአማራ ማህበረሰብ አክቲቪስቶች ዘንድ ፣ በተለያዩ መልኩ ተቃወሞ እንዲነሳ እያደረገ ያለው ራአሱ ብልጽግና በመሆኑ፣ አራት ኪሎ ያሉት የሚሰሩትንና የሚያደረጉትን ነገር፣ እኛ ነን የምናወቀው በሚል ጥጋብ ሳይሆን፣ የአማራውን፣ የተጋሩን ማህበረሰብ ስሜትና ፍላጎት ባካተተ መልኩ ፣ አይምሯቸው ካጠረው ከዘር ፖለቲካዊ አስተሳሰ ውጭ ውጥተው መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡

Filed in: Amharic