>

ድብልቅ ስሜት የፈጠረብኝ የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ እና ስምምነት (ከይኄይስ እውነቱ)

ድብልቅ ስሜት የፈጠረብኝ የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ እና ስምምነት

ከይኄይስ እውነቱ

በቅድሚያ ለተዋሕዶ ሃይማኖታቸውና ላንዲት ቤተክርስቲያናቸው መንፈሳዊ ተጋድሎ በማድረግ በሰማዕትነት ያለፉ ወገኖቻችንን አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ በክብር ይቀበልልን፡፡ ነፍሳቸውን በመካነ ዕረፍት ያኑርልን፡፡ ለቤተሰቦቻቸው አጽናኙንና አረጋጊውን መንፈስ ቅዱስ ይላክልን፡፡ በእስር በእንግልት ለሚገኙት መፈታትን፤ ለብፁዓን አባቶቻችን ጥበብንና ጥብዐትን ይስጥልን፡፡ ማኅበረ ካህናቱን ይጠብቅልን፡፡ ለምእመናን ደግሞ ጽናቱን ይስጥልን፡፡ 

ትናንት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢኦተቤክ በጭራቁ ዓቢይ አኅመድ የጐሣ አገዛዝ ከመጣባት ስደትና መከራ ጊዜያዊ እፎይታ ያገኘችበትን ውሳኔና ስምምነት የቤተክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ከሰጠው መግለጫ ሰማሁ፡፡ ‹‹ጊዜያዊ እፎይታ›› የሚለው ሐረግ የግሌ አረዳድ ነው፡፡ ወረድ ብዬ እመለስበታለሁ፡፡ ዜናውን ከብፁዓን አባቶቻችን እንደሰማሁ ውስጤን የደስታ ስሜት ባይሰማኝም የሰማዕታቱን ደም ከንቱ ያላስቀረ፣ የምእመናንን ጽናት የተመለከተ፣ የእናቶችን እምባ ያበሰ፣ በየገዳማቱ ያሉ የእውነተኛ አባቶችና እናቶችን ጸሎት የሰማ፣ ለብፁዓን አባቶቻችን ጥብዐትን ሰጥቶ በጥበባዊ አመራር ሕዝበ ክርስቲያኑን አንድ ልብ ያደረገ የአባቶቻቸንን አምላክ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገንሁ፡፡ ለካስ አልተወንም፡፡ በጨካኝ ዓላውያን እጅ ጨርሶ እንድንጠፋ አልፈረደብንም አልኹ፡፡

በመቀጠልም የውሳኔውን መግለጫ እና የስምምነቱን ይዘት በጥሞና አዳምጬ ቤተክርስቲያኒቱን ለመከራና ፈተና ለዳረጋት ዲዮቅልጥያኖሳዊ አገዛዝ ካቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎችና አንዲት ቤክ፣ አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ መንበር/ፓትርያርክ ብላ ከተነሣችበት አቋሟም ጋር ወደ መመርመር ገባሁ፡፡ በዚህም መሠረት፤

1ኛ/ ‹‹በቅርቡ በቤተክርስቲያናችን ተከስቶ የነበረው ችግርም በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት ተፈቷል፡፡ … ቅድስት ቤክ በ3ቱ አባቶች ወደ ቤክ መመለስ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡›› የሚለው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ክፍል የኢኦተቤክ አንዲት ቤክ፣ አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ መንበር/ፓትርያርክ ብላ የተነሣችበትን መሠረታዊ አቋም ለጊዜውም ቢሆን ያስጠበቀችበት ስምምነት በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ መንፈሳዊ ተጋድሎዋ ፍሬን ያፈራና አሸናፊነቷን ያስመሰከረ ሆኖ ይታያል፡፡

2ኛ/ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአፈንጋጩ ቡድን ጋር እንደማይጋገር በቀደመ መግለጫው ካስታወቀ በኋላ ከአገዛዙ ጋር ለመነጋገር ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ሀ/ አገዛዙ በቤተክርስቲያኗ (በሃይማኖት) ጉዳይ ቀጥታ ጣልቃ በመግባትና ለዚህም ዓላማው አፈንጋጩን ቡድን መሣሪያ በማድረግና በፌዴራልና በኦሮሚያ የሚገኙ ሠራዊቶችን በማሰማራት በምእመናን ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ከማድረሱም በተጨማሪ አብያተክርስቲያናትን በኃይል ሰብሮ በመግባት የቤተክርስቲያን ክብር በመዳፈሩ፣ ቅርሶች በመጥፋታቸው እና በርካቶችንም አፍኖ በማሰሩና በመሰወሩ የዘመናችን ዲዮቅልጥያኖስ ዓቢይ በይፋ ወጥቶ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ ለ/ አፈንጋጩን ቡድን አንድ ቦታ ሰብስቦ በሕገ ወጡ ቡድን በኃይል የተያዙትን አብያተ ክርስቲያናት ባስቸኳይ ለቅቆ እንዲወጣና ለሕጋዊው የኢኦተቤክ አካላት እንዲመልስ፤ ሐ/ ለሞቱትና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ምእመናን ቤተሰቦች ተገቢውን ካሣ እንዲከፍልና ጉዳት የደረሰባቸውንም አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠግን፤ መ/ ያሰራቸውን ምእመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ፤የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አፈንጋጮቹን የቀደመ ማዕርጋቸውንና ክብራቸውን መልሶ ከመቀበሉ በተጨማሪ በስምምነቱ የተመለከቱትን ቃሎች ገብቶላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የተደረገው ከቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱም ሳይሟላ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የስምምነቱን ይዘት አንድ ባንድ ካነበቡ በኋላ የጠ/ቤ/ክ/ሥ/አስኪያጁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በሰጡት ማብራሪያ በፊደል ‹መ› የተገለጸውን በሚመለከት ከአገዛዙ ጋር እየተነጋገርን ነው ከሚል ባለፈ የተፈጸመ ነገር የለም፡፡ 

ደጋግሜ እንደገለጽሁት የዚህ ጐሠኛ ሥርዓት መሠረትና ጉልላቱ ውሸት ሲሆን፣ ከአእምሮው የተለየው ዓቢይ ደግሞ ቅጥፈትና ክህደት ሁለተኛ ተፈጥሮው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አገዛዙንም ሆነ ይሄን በሽተኛ ግለሰብ ከኢትዮጵያ ምድር ካልተወገዱ በቀር ለአምስት የሰቈቃ ዓመታት በተግባር የተፈተነውን እውነት ክደን ይታመናል/አይታመንም የሚለው ጥያቄ ርባና ቢስ ነው፡፡ በመሆኑም በቅድመ ሁኔታዎቹ መፈጸም ረገድ የአባቶች ውሳኔ ጎዶሎ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በተጨማሪም ከሊቀ ጳጳሱ ማብራሪያ የሞቱትንን አካል ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናን ቤተሰቦች መልሶ ማቋቋም በሚመለከት ምእመናንን አስተባብረን የሚቻለንን እናደርጋለን የሚለው ንግግር በእጅጉን ቅር አሰኝቶኛል፡፡ የማይተካ ሕይወታቸውንና ‹ትዳራቸውን› የሚሰጡ ምእመናን ባሉበት ቤተክርስቲያን ከካዝናዋ ገንዘብ አውጥታ አስፈላጊውን ጊዜ ሳትሰጥ ማድረግ ሲገባት ምእመኑን ጠይቄ የሚለው በየትኛውም መመዘኛ  ሲታይ ከአባቶች የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ምእመናን ባገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ በራሳቸውን ተነሣሽነት የድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡ እንቅስቃሴውንም ጀምረውታል፡፡ ቤተክህነቱ ግን እየቀደመ  አርዓያ ሊሆን ይገባል፡፡

3ኛ/ ከመግለጫውና ስምምነቱ ይዘት የተረዳሁት ብፁዓን አባቶቻችን ከምእመናኑ አልፎ የሌሎች እምነት ተከታዮችን ያስደመመው የመጀመሪያ ጥንካሬአቸው መጨረሻው ላይ የታየ አይመስልም፡፡ ለአገዛዙ ሸብረክ ሲሉ አስተውዬአለሁ፡፡ ምናልባትም አደጋ ለመቀነስ የታሰበ  ሽብረካ ይመስላል፡፡ ሀ/ ‹‹ከሕገ ወጡ ቡድን ጋር ምንም ዓይነት ንግግር አናደርግም፡፡›› ባሉበት አንደበት ከአፈንጋጩ ቡድን ጋር ውይይት/ንግግር በሚል የቋንቋ ጨዋታ ‹‹ድርድር›› እንዳደረጉ በስምምነቱ ከተራ ቊ. 1 እስከ 6 የተመለከቱት ፍሬ ጉዳዮች በግልጽ ያሳብቃሉ፡፡ በተለይም በተራ ቊ. 6 ‹‹በ3ቱ አባቶች የተሾሙት አባቶች ቀድሞ ወደነበሩበት የክህነት ማዕርግ ይመለሳሉ፤ ከነርሱ ውስጥ በቤክ ሕግና ሥርዓት ተመዝነው የሚያሟሉት እንደገና በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሾሙ ይደረጋል፤›› በማለት የተገለጸው የአፈንጋጮቹን ሕገ ወጥ ድርጊት የሚያጸድቅ ይመስላል፡፡ ለ/ የፈተናው ጠንሳሽና በዚህም የደረሰው ጥፋት ኃላፊና ተጠያቂ የሆነው የጐሣ ሥርዓቱ አለቃ መሆኑን ጠንቅቀው እያወቁና በቀደመ መግለጫቸውም በድፍረት ሲያነሱ ቆይተው፣ በመጨረሻው የሲኖዶሱ መግለጫም ሆነ የስምምነቱ ማብራሪያ ጊዜ ከሕዝብ የተተፋውን ጭራቅ ለማወደስ የሄዱበት መጠን በእጅጉን የሚያስተዛዝብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ቤተክህነቱ ከቤተመንግሥቱ ጋር በቀጣይ ለሚኖረው ግንኙነት እንደ ቀድሞው በማጎብደድና ለሕገ ወጥ ድርጊቱ ቡራኬ እየሰጠ እንደሚቀጥል ማሳያ በሚመስል መልኩ መጥፎ ምሳሌነት የሚተው ሆኖ አይቼዋለሁ፡፡ 

4ኛ/ ሲኖዶሱ በመግለጫው ‹‹በቅርቡ በቤተክርስቲያናችን ተከስቶ የነበረው ችግርም በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት ተፈቷል፡፡›› ቢልም አፈንጋጩ ቡድን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን እጅ በይሁዳዊ አሳሳም ከመሳሙ ባለፈ ቤተክርስቲያናችንና አገራችንን ሊያጠፋ ከነበረው ግዙፍ ጥፋት በእውነት ተጸጽቶ ይቅርታ ስለመጠየቁ አልሰማንም፡፡ ምናልባት ውግዘቱ ሲነሣ የሚፈጸም ሥርዓት እንደሆነም ግልጽ አይደለም፡፡ ልብና ኵላሊትን የሚፈትንና የሚመረምር አንድ አምላክ ቢሆንም፣ ይቅርታ የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ሥርዓት ቢሆንም፤ የአገዛዙን ቤተክርስቲያንን ብሎም አገርን የማጥፋት ተልእኮ ዐውቀው፣ ተባብረው ዐቅደውና ተዘጋጅተው ያፈነገጡት ኃይሎች፣ ከቀናት በፊት ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ ግለሰቦች፣ ከዛም አልፎ ለበርካታ ምእመናን ሕይወት ማለፍና ቋሚ የአካል ጉድለት፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን እስርና እንግልት፣ ለበርካታ አብያተ ክርስቲያናት መደፈርና ቅርሶች መውደም ምክንያት የሆኑ ሰዎች ባንድ ጀምበር ተገልብጠው ከልባቸው ተመልሰዋል ብሎ ለመቀበል የተለየ አእምሮ ይጠይቃል፡፡ ቢያንስ አግባብነት ያለው ጥርጣሬ ነው፡፡ 

ተመልሰናል ባሉት አፈንጋጮችና በጐሠኞቹ አገዛዝ በኩል ያለኝ ሥጋት፤

ሀ/ በይቅርታ ተመልሰዋል የተባሉት ‹3ቱ ሊቀ ጳጳሳትም› ሆኑ 26ቱ ሕገ ወጥ ተሿሚዎች ኑፋቄ፣ ቀኖና ቤተክርስቲያን እና አስተዳደራዊ ጥሰት በመፈጸማቸው ከቤተክርስቲያን አንድነት ተወግዘው የተለዩ መሆናቸው በሲኖዶሱ ውሳኔ በይፋ የተገለጸ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም የአገዛዙን አጥፊ ተልእኮ እያወቁ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት መሣሪያ ሆነዋል፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ረድቶን ሊመጣ ያለውና አሁን ከተፈጸመው ጥፋት በእጅጉ የከፋ አገርን ሊያፈርስ የሚችል ጥፋት ባይደርስም የግለሰቦቹን ጥፋት ባገር ደረጃ ብናስበው የአገር ክህደት ወንጀል ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ 

አሁን ከቤተክርስቲያኗ አፍንግጠው የወጡት ሕገ ወጦችን (በተለይ 3ቱን) በሚመለከት ቤተክርስቲያን በመርህ ደረጃ የምትከተለው መንፈሳዊ ሥርዓት በእውነተኛ ንስሐ እስከተመለሱ ድረስ ለምሕረትና ይቅርታ ደጆቿን ክፍት ማድረግ ቢሆንም፤ መዓርጋቸውን ጠብቃ መመለሷ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያስከትል ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም፣ ሀ/ እነዚህ ግለሰቦች በሲኖዶሱ ውሳኔ ኑፋቄ መፈጸማቸው የተገለጸ በመሆኑ፤ ለ/ የግል ሕይወታቸውም ለቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲባል መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ለያዙት ማዕርጋት የሚበቁ አባቶች ከነውርና ነቀፋ የነፁ መሆን ይኖርባቸዋልና፡፡ ይህ አባባል በያዙት ማዕርጋትና ክህነት ይመለሱ የተባሉትን 26 ሕገ ወጥ ሲመት የተቀበሉትን ይመለከታል፡፡ የስምምነቱን ተራ ቊ. 6 ይመለከታል፡፡ ቀኖናና ሕገ ቤተክርስቲያን ተጠብቆ ቢልም የ‹ድርድር› ውጤት በመሆኑ በጐሣ ተዋጽኦ ወደሚል ተሂዶ የኑፋቄ አደጋ እንዳያመጣ ሥጋት አለኝ፡፡ ሐ/ ከሁሉም በላይ በአገዛዙ ቤተክርስቲያንን የማፍረስ ተልእኮ ተሰጥቷቸው የተሰማሩ መሆኑን ካፈነገጡበት ጊዜ ጀምሮ ይፋ መሆኑ እየታወቀ፣ ከይቅርታ በላይ በሆነ ጥፋት ከ37 በላይ የሚሆኑ ምእመናን ሕይወታችን አጥተው÷ እልፎች ቆስለው÷ በርካቶች ካህናትና ምእመናን ታስረው በእንግልት እያሉ፣ በአንዳንድ አህጉረ ስብከቶች አብያተ ክርስቲያናትን በአረማውያን አሰብረው ማስደፈራቸውና ቅርስና ንብረትም ማጥፋታቸው ሲታይ፤ መ/ አፈንጋጮቹ የፈጸሙት ድርጊት በዓለማዊው ሕግም በወንጀልና በፍትሐብሔር የሚያስጠይቅ መሆኑ ከግምት ሲገባ፤ በይቅርታ ይመለሱ ቢባል እንኳን ይቅርታው በነበራቸው መዓርግና የክህነት አገልግሎት የሚያስቀጥላቸው አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመሆኑም እነዚህ እስከ መዓርጋቸው የተመለሱ ግለሰቦች ይህንን አፍራሽ ተልእኮ በቀጣይ ላለመፈጸማቸውም ምንም ዓይነት ዋስትና አይኖርም፡፡ 

ለ/ በጨላማ ላይ ገደልና የዛፍ ጥላ ሲጨመርበት ጨለማው እጅግ የጸና እንደሚሆን ‹ጽልመትን እና ጽላሎተ ሞትን› እያነፃፀሩ መጻሕፍተ ቤተክርስቲያን ይነግሩናል፡፡ አለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያችን የንግሥና መንበር ላይ የሚገኙት ጊዜ የሰጣቸው ‹ቅሎች› በጐሠኛነት ላይ ድንቊርናን ደርበውበት ከአእምሮአቸው የተለዩ በቁማቸው ሥጋ የለበሱ አጋንንት ሆነዋል፡፡ እነዚህ ጉዶች ሰሞኑን በተዋሕዶ ሃይማኖታችን፣ በቅዱስ ሲኖዶስና በብፁዓን አባቶቻችን ላይ ያሳዩት ድፍረትና ንቀት፤ በካህናትና በምእመናን ላይ እያደረሱ ያለው ግፍና መከራ፤ በቤተክርስቲያን ቅርሶችና ሀብቶች ላይ እያደረሱ ያለው ውድመት ከድንቊርናና ዕብደታቸው የመነጨ ነው፡፡ ዛሬ አረሚው ዐቢይ በኢኦተቤክ ላይ እየፈጸመ ያለውን አገዛዛዊ ሽብር/መዋቅራዊ ጥቃት አላየሁም አልሰማሁም በማለት ለአረሚው ሰይጣናዊ ተግባራት ምክንያት ፍለጋ የሚዋትት ሰው ካለ አንድም ከኢትዮጵያዊነትና ከሰውነት የተለየ፣ አንድም ከማኅበረ አጋንንቱ የተደመረ በሽተኛ ነው፡፡

የጀመርነው መንፈሳዊ ተጋድሎ የቤተክርስቲያናችንን ህልውናና ተቋማዊ ልዕልና በማስከበር ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንም መታደግ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ምእመናንና አባቶች በተጠንቀቅ ጸንተን ቤተክርስቲያናችንን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ የጐሠኞቹ ሥርዓት – መሥራቹ ወያኔ ሕውሐትም ሆነ ወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ – አጽራረ ቤተክርስቲያን መሆናቸውን ላለፉት 32 ዓመታት በይፋ በአፍም፣በመጣፍም እንዲሁም በለየለት የጭካኔ ተግባራቸው አስመስክረዋል፡፡ እነዚህ ዐረማውያን – አጋንንታዊ አስተሳሰባቸው፣ ይህንን ተግባራዊ የሚያደርጉበት የሕግና የአስተዳደር መዋቅራቸው እንዲሁም ለዚሁ ዓላማ ድጋፍ የሚያደርግ የሠራዊትና የጸጥታ ኃይላቸውና የሀብት ምንጫቸው እስካለ ድረሰ – በኢትዮጵያችን ሠልጥነው እስከቆዩ ድረስ የኢኦተቤክ እንደ አገር ዓቢይ ዓምድ፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ዋስትና አይኖራቸውም፡፡  የዐረሚው ትእቢት ከከለዳውያን/ሰናዖር ሰዎች ልቆ እግዚአብሔርን ለመገዳደር ያለመ በመሆኑ በክፋቱ ሊቀጥልበት ይችላል፡፡ ምናልባት ከሕይወቱ በላይ ስለሚሳሳለት ሥልጣን ብሎ ለጊዜው ቢያፈገፍግ እንኳን አድፍጦና አድብቶ በሌላ ዙር እንደሚመለስ አትጠራጠሩ፡፡ ምክንያቱም የተነሣበት ዓላማና በ‹አሳዳሪዎቹም› የተሰጠው ጥብቅ ተልእኮ ነውና፡፡ ይህም ዓላማ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ወያኔ የፈጠረለትን ኦሮሚያ የሚባል ተምኔታዊ አገር እውን ማድረግ ነው፡፡ 

በቀጣይ ምን ይደረግ?

ምንም እንኳን ‹ውኃ ሽቅብ እንደማይፈስ› ቢታወቅም፣ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ተግባራዊ እንዲሆኑ ዕቅድ የተያዘ እንዳለ ብሰማም፣ ልዩ ልዩ ማኅበራት ጥናትና ምርምር አድርገው ያቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦች እንዳሉ ብረዳም፤ ብፁዓን አባቶቼ ከድፍረት ሳትቆጥሩብኝ እንደ አንድ ምእመን ጥቂት ማሳሰቢያዎች አሉኝ፡፡ ይኸውም የመጣብንን ፈተና በሚመለከት በረጅም ጊዜ በጥናትና ባጭር ጊዜ ብትመክሩባቸው በሚል የሚከተለውን በትህትና አቀርባለሁ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ቅዱስ ሲኖዶስ በስምምነቱ ተራ ቊ.10 ላይ ‹‹የገጠመን ፈተና ይበልጥ ውስጣችንን ለመፈተሽ…ለበጎ እንጠቀምበታለን›› ተብሎ ከተገለጸው አባባል ጋር የተዛመደ ነው፡፡ 

1ኛ/ ቤተክርስቲያናችን ውስጧን (ከጠቅላይ ቤተክህነት እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን)  በመንፈሳዊ ሹመት ረገድ፤ በሰው ኃይል ምልመላና ቅጥር ሥራ አመራር ረገድ፤ ለካህናትም ሆነ ለአስተዳደር ሠራተኞች የሚፈጸም የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓት ወጥነትን በሚመለከት፤ በፋይናንስ ሥራ አመራር ረገድ፤ በንብረትና ቅርሶች ሥራ አመራር ረገድ፤ ደግማ ደጋግማ ራሷን ፈትሻ ከማጥራት ጋር፣ ሀገር-አከል ለሆነ መንፈሳዊ ተቋም የሚመጥን አቋም እንዲኖራት የማድረግ፤ ይሄ ደግሞ በስምምነቱ ተራ ቊ. 10 በግልጽ የተቀመጠ ሐሳብ ነው፡፡

2ኛ/ ቤክ አሁን ካለው ዓላዊም ጋር ይሁን ባጠቃላይ ቤተመንግሥቱን ከሚቆጣጠር ማንኛውም አካል ጋር ስለሚኖራት – ነፃነቷን፣ መብቷን፣ ክብሯንና ልዕልናዋን የሚያስጠበቅ – ግንኙነት በሚመለከት ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ መርህ ሊኖራት ይገባል፡፡ በዓለማዊው ፖሊሲ እንደምንለው በጥናት ቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ፤ ካለም ሳይዛነፍ ተግባራዊ በማድረግ ራሷን ከውጫዊ ጣልቃ ገብነት መመከት ይጠበቅባታል፡፡ ለማንም ጋጠ ወጥ መንበርከክ አይኖርባትም፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በአገዛዙ የጥፋት ተልእኮ ቡራኬ በመስጠት ተባባሪ ልትሆን አይገባም፡፡  

3ኛ/ አሁን ከቤተክርስቲያኗ አፍንግጠው የወጡት ሕገ ወጦችን (በተለይ 3ቱን) በሚመለከት ቤተክርስቲያን በመርህ ደረጃ የምትከተለው መንፈሳዊ ሥርዓት በእውነተኛ ንስሐ እስከተመለሱ ድረስ ለምሕረትና ይቅርታ ደጆቿን ክፍት ማድረግ ቢሆንም፤ መዓርጋቸውን ጠብቃ መመለሷ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያስከትል ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም፣ ሀ/ እነዚህ ግለሰቦች በሲኖዶሱ ውሳኔ ኑፋቄ መፈጸማቸው የተገለጸ በመሆኑ፤ ለ/ የግል ሕይወታቸውም ለቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲባል መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እንደ ቤተክርስቲያን ቀኖና ለያዙት ማዕርጋት የሚበቁ አባቶች ከነውርና ነቀፋ የነፁ መሆን ይኖርባቸዋልና፡፡ ይህ አባባል በያዙት ማዕርጋትና ክህነት ይመለሱ የተባሉትን 26 ሕገ ወጥ ሲመት የተቀበሉትን ይመለከታል፡፡ የስምምነቱን ተራ ቊ. 6 ይመለከታል፡፡ ቀኖናና ሕገ ቤተክርስቲያን ተጠብቆ ቢልም የ‹ድርድር› ውጤት በመሆኑ በጐሣ ተዋጽኦ ወደሚል ተሂዶ የኑፋቄ አደጋ እንዳያመጣ ሥጋት አለኝ፡፡ ሐ/ ከሁሉም በላይ በአገዛዙ ቤተክርስቲያንን የማፍረስ ተልእኮ ተሰጥቷቸው የተሰማሩ መሆኑን ካፈነገጡበት ጊዜ ጀምሮ ይፋ መሆኑ እየታወቀ፣ ከይቅርታ በላይ በሆነ ጥፋት ከ37 በላይ የሚሆኑ ምእመናን ሕይወታችን አጥተው÷ እልፎች ቆስለው÷ በርካቶች ካህናትና ምእመናን ታስረው በእንግልት እያሉ፣ በአንዳንድ አህጉረ ስብከቶች አብያተ ክርስቲያናትን በአረማውያን አሰብረው ማስደፈራቸውና ቅርስና ንብረትም ማጥፋታቸው ሲታይ፤ መ/ አፈንጋጮቹ የፈጸሙት ድርጊት በዓለማዊው ሕግም በወንጀልና በፍትሐብሔር የሚያስጠይቅ መሆኑ ከግምት ሲገባ፤ በይቅርታ ይመለሱ ቢባል እንኳን ይቅርታው በነበራቸው መዓርግና የክህነት አገልግሎት የሚያስቀጥላቸው አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

Filed in: Amharic