>

ያልተቀቡ ነገስታት እና የልሂቃን ጅምላ ጭፍጨፋ

ያልተቀቡ ነገስታት እና የልሂቃን ጅምላ ጭፍጨፋ

ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው

እንደ መግቢያ

 

በፋኖ የውስጥ ጉዳይ ሒስ ሳቀርብ እየጎረበጠኝ ነው። ከአንባቢ መካከልም ‘የሰራዊቱን እና የአመራሩን ተስፋ ይቀንሳል፣ ለጠላት ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል’ በሚል  ሒሱን የሚተቹ እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ሆኖም ሚዲያው በሓላፊነት ላይ ያሉ አመራሮችን መግራት ይገባዋል። በዝንጀሮ መንገድ ቁልቁል እየተንደረደሩ ያሉ መሪዎች ወስደው ገደል ውስጥ ሳይከቱን አውራ ጎዳናውን ማመላከት ያስፈልጋል።  ፋኖ ወደ መደበኛ ሰራዊትነት እያደገ ነው። ደርጅቷል። በውዳሴ የማይለመልምበት፣ በሒያሴ የማይኮሰምንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በአንፃሩ አገዛዙ አንድ ሀሙስ የቀረው ነው። በፕሮፖጋንዳም ቢሆን ሊያሸንፍ የማይችልበት ደረጃ  ላይ ደርሷል። በመሆኑም በዝንጀሮ መንገደኞች እየተፈፀመ ያለውን የምሁራን ጅምላ ጭፍጨፋ (Brain Genocide) ማጋለጡ ተገቢ ይመስለኛል። ይህም ከፈፅሞ መክሸፍ ይታደገናል። ትግሉንም ይገራዋል። 

 

የልሂቃን ጥላቻ

 

በአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች ዘንድ በአስደንጋጭ ደረጃ የልሂቃን ፍራቻ፣ ጥላቻ፣ ማግለል፣ ስም ማጥፋት፣ ማሰር እና ግድያ ይታያል። ይህ የተማረውም ሆነ ያልተማረው፣ ሽማግሌውም ሆነ ጎልማሳው መሪ እየፈፀሙት ያለ ተግባር ነው። ያለባቸውን የአቅም ማነስ የሚሸፍኑት በአላዋቂዎች ተከበው በመኖር ነው። በሳል የፖለቲካ ግንዛቤ ያላቸውን ፋኖዎች አታስጠጉ እንደተባሉ ሁሉ በየሰበቡ ሲሸሹ ይስተዋላል። ለዚህ ፍላጎታቸው ሲባል አርበኛን እየነቀሉ ባንዳ ይተክላሉ። ሰሞኑን በጎጃም እየሆኑ ያሉት ደግሞ አስደንጋጭ ናቸው። 

ሰሞነኛ ጉዳዮች

አርበኛ ዘመነ ካሤ  በስልጣን ፉክክሩ ውስጥ መገፋቱን ሲገልፅ የአባ ኮስትር በላይ ዘለቀን አሟሟት አንስቶ ነበር። በርግጥም ይህን ያነሳው በወንዝ አጥር ለመከለል እንደ ነበር ግልፅ ነው። ለዛሬ የታሪክ ሰበዝን ስለመዘዘበት እንድምታ ዝርዝር ሀተታ ውስጥ አልገባም። ስለ አሟሟቱ ብቻ ያለውን ላንሳ:- 

ዘመነ አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ በብር ከሃምሳ ገመድ ታንቆ መገደሉን እና ዛሬም ልጆቹ በድኅነት የሚኖሩ መሆናቸውን ጠቅሷል። በርግጥም ጀግናው አባ ኮስትር ፋሽስት ጣልያንን ድል ካደረገ በኋላ በወንድሞቹ ተገድሏል። እንዲገደል ታላቁን ሚና የተጫወቱት ጣልያን ከተሸነፈች በኋላ ኢትዮዽያን ቅኝ ግዛታቸው የማድረግ ፍላጎት የነበራቸው እንግሊዞች እነደሆኑ የሚያትቱ የታሪክ ተንታኞች ቢኖሩም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን ከደሙ ፈፅሞ ማንፃት የሚቻል አይመስለኝም። በርግጥም በላይ ዘለቀ ከእንግሊዛዊዉ የጦር መሪ ኮሎኔል ሳንፎርድ ጋር የነበረው አለመግባባት፣ ፖለቲካዊ ፍላጎት የነበራቸውን የእንግሊዝ ወታደር “ክላልኝ ይህስ ራሱ ጣልያኑ ነው” እያለ ያጋልጥ የነበረበትን ብሎም በመጨረሻ ሳንፎርድ በጀኔራል ዊንጌት እንዲቀየሩ የእንግሊዝን መንግስት ጭምር ያስገደደበትን ክስተት ስንደምረው አባ ኮስት በላይ ዘለቀ በእንግሊዞች ዘንድም በክፉ የሚታይ መሆኑን ይጠቁመናል። ያም ሆነ ይህ የአባ ኮስትር ጉዳይ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ እንዳለው ነው። 

“እናት ኢትዮዽያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!”

የአባ ኮስትርን የግፍ ግድያ ያስታወሰን አርበኛ ዘመነ ካሤ እርሱም አርበኛ ጌራ ወርቁን ለመግደል አፋፍ ላይ ይገኛል። ሰሞኑን ጌራ በተገኘበት እንዲገደል የአማራ ፋኖ በጎጃም መወሰኑን ሰምተናል። እኔም ባደረግሁት ማጣራት ለጉዳዩ ቅርብ ከሆነ ፋኖ አረጋግጫለሁ። በእነ ኮሎኔል ጌታሁን መኮንን የተጀመረው አርበኞችን የማሳደድ እንቅስቃሴ ቀጥሏል። በእነ አርበኛ አፈወርቅ ፍስሐ የቀጠለው አርበኞችን የመረሸን ተግባር ዛሬም አልቆመም። በዚህ ልክ አማራ አምጦ የወለዳቸውን አርበኞች ማጥፋት ስንት አመት ለመንገስ ይሆን? 

ሰሞኑን ከጌራወርቅ በተጨማሪ አርበኛ ጥላሁን አበጀ፣ የአማራ ፋኖ በጎጃም ሦስተኛ ክፍለ ጦር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው አርበኛ ይበልጣል የእውነቱ፣ የሦስተኛ ክፍለ ጦር የቀጣናዊ ትስስር ሓላፊው አርበኛ አየነው አስፋው እና የቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ ክፍለ ጦር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው አርበኛ ምስጌ ዘድንግል (ከመደበኛ ስሙ ይልቅ በዚህ ይጠራል) ከሚሳደዱት መካከል ናቸው። በነገራችን ላይ እነኝህን ፋኖዎች ነገ በአደባባይ አስወጥተው መሳደዳቸውን እንዲያስተባብሉ ያስገድዷቸው ይሆናል። ይህን ካደረጉ የቁም ተስካር እንዳወጡ ይቆጠራል። 

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሃይል በሚል ስያሜ በጎጃም የፋኖ እንቅስቃሴ ሲጀመር በመገናኛ ብዙሃን ከሚታወቁ ሦስት መሪዎች መካከል ጥላሁን አንዱ ነበር። እነርሱም አርበኛ ዘመነ ካሤ፣ ካፕቴን መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ እና ራሱ ጥላሁን ናቸው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርበኛ ጥላሁን የተገለለ ይመስላል። ሰሞኑን በከተበው መጣጥፍም ከአመራርነት ተገፍትሮ ወደ ደጋፊነት መወርወሩን ጠቅሷል። ስለዚህ የእርሱ መሳደድ ሲንከባለል የመጣ ይመስላል። በአንፃሩ ሌሎቹ ሦስቱ ለእስር የታጩት አስረስ ማረ ላደራጀው “አንድ እንደ አስር” ለሚሉት የማህበራዊ ሚዲያ ፕሮጀክት ምቹ ባለመሆናቸው ነው። በርግጥ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም ይኖሩታል። ለመሆኑ “አንድ እንደ አስር” ምንድን ነው?

አንድ እንደ አስር

ይህ ፕሮጀክት አንድ ሰው ቢያንስ አስር የተለያዩ ሀሰተኛ የፌስቡክ አካውንቶችን በመፍጠር ለከፍተኛ አመራሮች የገፅታ ግንባታ የሚሠራበት ነው። ለአመራሮች ስጋት የተባሉ እውነተኛ አርበኞችን ደግሞ ስማቸውን በማጥፋት የስብዕና ገደላ ሥራዎችን ይሰራል። ከአማራ የአንድነት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የጠሏቸውን በሌሎች ጠቅላይ ግዛት ያሉ ፋኖዎች ያራክሳል። 

ፕሮጀክቱ በጦር ግንባር በእያንዳዱ ብርጌድ ቢያንስ አንድ ሰው በመመልመል ያሳትፋል። በተቋሙ 48 ብርጌዶች መኖራቸውን ልብ ይሏል። በተመሳሳይ ከግንባር ውጭ እና በባሕር ማዶ ሌሎች አባላት አሉት። 

አባላቱ  የሚመለመሉት የማንሰላሰል አቅማቸው ዝቅ ያሉት ተመርጠው ነው።  የሚጠቀሙባቸው ሐሰተኛ አካውንቶች በአመዛኙ በሰፈር ስም የተሰየሙ ናቸው። ይህም አማራን ከአማራነት ብቻ ሳይሆን ከጎጃምም አጥብቦ በየመንደሩ ለመበጣጠስ የታሰበ ነው። ወጥ የሆነ አማራዊ የፖለቲካ ማሕበረሰብ እንዳይፈጠር የሚደረገው ክልከላ አካል ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የወያኔ የዞኖች አወቃቀር ነው። ወያኔ ዞኖችን ሲያደራጅ እንዲበጣጠስ የፈለገውን አማራን ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋ በማለት ከፋፍሎ አደራጀ። የጋራ ፖለቲካዊ ማንነት እንዲገነባ የፈለገውን ትግራይን ደግሞ ደቡብ ትግራይ ዞን፣ ምዕራብ  ትግራይ ዞን በማለት አደራጀው። 

ይህ የማሕበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ጸረ ኦርቶዶክስ ነው። በዚህ ተጽዕኖ ምክንያት ታላላቅ መስቀሎችን በአንገታቸው ያጠልቁ የነበሩ ፋኖዎች ማውለቅ ጀምረዋል። የጠመንጃቸው አፈሙዝ ላይ መስቀል አስረው የነበሩት በጥሰውታል። በገለልተኝነት እሳቤ አረማዊነት እየተስፋፋ ይገኛል። ይህ በፊታውራሪነት እየተሠራ ያለው በአስረስ ማረ ነው። በቅርቡ ለውግዘት የሞኣ ተዋሕዶ አጀንዳ ሲነሳ የተለኮሰው በዚሁ የ”አንድ እንደ አስር” ፕሮጀክት ነበር። የእንቅስቃሴው አስተባባሪ “የነጠላ ስር ቁማርተኞች” በሚል ርዕስ አጭር መጣጥፍ አሰራጭቶ ነበር ፊሽካውን የነፋው። ወደ ሰሞነኛው የአርበኛ ጌራ ወርቁ ጉዳይ እንመለስ።

  በተገኘበት ይገደል

  1. “. . .የነበሩ የአንድነት ጉባዔዎች ይገምገሙ፣ እንደ አማራ አንድ ያልሆንበት ችግር ይተንተን፣ መፍትሔ እንፍጠርለት፣ ለሕዝባችን የመለያያ ድንበር አንፍጠርለት፣ መጭውን ፖለቲካዊ አካሄድ በተመለከተ የሁኔታዎች ትንታኔ እንሥራ፣  ርዕዮተ ዓለም እንቅረፅ. . . “ እነኝህ ጌራወርቅን በእነ አርበኛ ዘመነ ካሤ በኩል በጠላትነት ያስፈረጁት አስተያየቶቹ ናቸው። በተገኘበት እንዲገደል የተወሰነውም በዚሁ ምክንያት ነው። ከሁሉም በከፋ ወጥመድ ውስጥ ያስገባው ደግሞ የአማራ ፋኖ በጎጃም ከፍተኛ አመራሩ የትግል አፈፃፀም ግምገማ እና ማሻሻያ እንዲያደርግ ያቀረበው ጥያቄ ነው። “ጦሩ ይጠይቀን። ለአንድ አመት ከሰባት ወር ሪፎርም አላደረግንም። አልገመገምንም። ክፍለ ጦሮች በየጊዜው ግምገማ እና ሪፎርም ያደርጋሉ። በድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ግን ይህ አልሆነም” ብሏል። ግድያ ያስወሰነበት ዋነኛው ሓሳብ ይህ ነው። ከሥልጣን ያወረዳቸው ያህል አድርገው ቆጥረውታል። ያለተቀቡ ነገሥታት ደንግጠዋል። ይነግሡ ዘንድ የተነገረው ትንቢት የከሸፈ መስሏቸዋል። እናም ፈሩ። የፈሪ ዱላቸውንም አነሱ።

በተለይም እንደ ግራወርቅ አይነት በየዘርፉ የበሰሉ ልሂቃን ደግሞ ባልተቀቡ ነገስታት ዘንድ እንደ ስጋት ይታያሉ። ልሂቅ ጠልነቱ የሚያመሳስለው በቀኝም ሆነ በግራ የተሰለፈው ኃይል  የጌራ በአጠገቡ መኖር ያሳክከዋል። ምክንያቱም ጌራወርቅ በመንፈሳዊ፣ በሰላማዊ አለማዊ እና በወታደራዊ አለማዊ የትምህርት ዘርፎች እውቀትን የጨበጠ ነው። 

 መንፈሳዊ

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዳዊት የደገመ፣ ድጓ ፆመ ድጓ ያወቀ፣ ቅኔ የገበረ፣ መፅሐፍ ያመሰጠረ ነው። አስመስክሮ ተማሪ ቤት ባይከፍትም ለመምህርነት ሩቅ አይደለም። ቅኔ ቤት ከኔታ ያሬድ ጨጎዴ አስመስክሯል። 

ሰላማዊ አለማዊ

በሶሾሎጂ እና ሶሻል አንትሮፖሎጂ የትምህርት ፀርፍ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል። በዚሁ ሙያ ለረጅም ጊዜ ሲሠራ ቆይቷል። በሶሻል ወርክ በባሕር ዳር በማስትሬት ተመርቋል። የከፍተኛ ውጤት ባለቤትም ነው።


ወታደራዊ አለማዊ

በሶሾሎጂስትነት ከሚያገለግልበት ሙያው ተነስቶ በጀኔራል አሳምነው ጽጌ ግብዣ ወደ ጃራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ በመግባት የአማራ ልዩ ሃይልን ተቀላቀለ። ስልጠናውን ጨርሶ ከተመረቀ በኋላ በተለያዩ ግንባሮች ተዋግቷል፣ በማሰልጠኛ እና በጦር ግንባር የተደረጉ ወታደራዊ ስምሪቶችን አስተባብሯል። በተለይ በመተከል እና በሸዋ ሮቢት ለአማራ ሕዝብ ተዋግቷል፣ አዋግቷልም። 

 ፖለቲካዊ

የአማራ ወጣቶች ማህበርን በማቋቋም የአማራን ወጣቶች ከጫፍ እስከ ጫፍ ካደራጁ፣ የአማራን ብሔርተኝነት ካስፋፉ ወጣቶች መካከል ጌራወርቅ ወርቁ ግንባር ቀደሙ ነው። በመላው የአማራ መስተዳድር እና በአዲስ አበባ ማህበሩን አደራጅቷል። ኦርቶዶክሳዊ ለዛን በተጎናፀፉ ሰርሳሪ የአደባባይ ንግግሮቹ ብዙዎችን አንቅቷል። ዛሬ የሚያሳድደው አስረስ ማረ የብአዴን ነገረ ፈጅ በነበረበት ሰዓት ጌራ ለአማራ ሕዝብ ታግሏል። እንደ ዛሬው የድል ጮራ አይተው ሳይሆን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደ ሻማ ከበሩ ታጋዮች መካከል ነው። በተለይ ከጀኔራ አሳምነው ጽጌ ግድያ በኋላ በተደጋጋሚ በአገዛዙ ታስሯል። 

 ፋኖነት 

ጌራ የዚህ ዘመን ፋኖነት ሲጀመር ጀምሮ ያለ ነው። በተለይም ከመስከረም 2015 ዓ.ም. በዝሕብስት በረሀ እና በቡሬ የከፈለውን ዋጋ በቅርበት አይቻለሁ። በሰከላ እና አካባቢው አሁን ያለውን ፋኖ በማደራጀት ግንባር ቀደሙ ነው። በጦር ሜዳ በርካታ ጀብዱዎችን ፈፅሟል። ከእነዚህ መካከል ያሬድ ኪሮስ የተባለውን የትግራይ ተወላጅ ኮሎኔል ጨምሮ 117 የጠላት ሰራዊት አባላትን የማረከበት አንድ ውጊያ ይጠቀሳል። ሆኖም አስረስ እና ቡድኑ ከወያኔ ጋር ላደረጉት ያልተቀደሰ የአጥንተ ሰባራ ጋብቻ ጥሎሽ አድርገው ሸኙት። ኮሎኔሉ የተሸኘው የትግራዩ ስታሊን ገብረ ስላሴ እና የአማራ ፋኖ በጎጃም አመራሩ አስረስ ማረ ባደረጉት የስልክ ግንኙነት ነው። 

ኮሎኔሉ ከተማረከ በኋላ ሰከላ፣ ጉደራ ላይ በእነ ጌራ ጥበቃ ስር ተቀምጦ ነበር። ሆኖም በአመራሮች ትዕዛዝ ከእነ ጌራ ተነስቶ ወደ ፋግታ ከተማ ተወሰደ። በዚሁ ከተማ ሦስት የተለያዩ መኖሪያ ቤቶች ተከራይቶ ለደኅህነቱ ሲባል ሦስቱንም ቤቶች እያፈራረቀ ይኖርባቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ከአማራ ፋኖ በጎጃም ለይስሙላ አንድ አጃቢ የተመደበለት ቢሆንም ነፃነቱን እንዳይጋፋው ታዝዞ ስለነበር እምብዛም አይቆጣጠረውም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ አጃቢውም ሳያውቅ በእነ አስረስ ትብብር ወጥቶ እንዲሄድ ተደርጓል። ሆኖም ያሬድን ለመልቀቅ ከወያኔ የተቀበለውን ገንዘብ ለማጭበርበር ብሎም በሰራዊቱ ላይ የሚነሳበትን አመፅ ለማስቀረት ሲል አስረስ ጌራወርቅ ነው የለቀቀው በሚል አስነገረ። ከመናገርም በዘለለ ጌራወርቅን አሰረ። ሰውየው በወቅቱ በጌራ ቁጥጥር ስር አለመሆኑን ያወቀው በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ሰራዊት ግን ብዥታ ውስጥ አልገባም፣ አስቀድሞም በዕዝ ቁጥጥር ስር መሆኑን ያውቃልና። ጌራ ሸኝቶታል ተብሎ ቢታሰብ እንኳን እርሱ የሚመራው ክፍለ ጦር ከሚንቀሳቀስበት ቀጣና አልፎ የመሸት አይችልም። 

በአጠቃላይ ጌራወርቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የተሻለ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ታጋዮች ከትግሉ እየተገፉ ነው። ይህ በአስቸኳይ መቆም አለበት። አገዛዙን ለመጣል በሚደረገው ትግል፣ አዲስ ስርዓተ መንግሥት ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት ብሎም አዲሱን ስርዓተ መንግሥት ጤናማ አድርጎ ለመቀጠል በፋኖ ውስጥ ያሉ ልሂቃን ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ልንጠብቃቸው ይገባል!

 

Filed in: Amharic