አፋሕድ የፋኖን የመጀመሪያ የተሟላ ፍኖተ-መርህ (ማኒፌስቶ) ይፋ አድርጓል !!!
/
-ጥቅምት — 12፣ 2018 ዓ.ም።
/
ከብሶት ትግል ወደ መርህ ትግል የሚያሸጋግረን የአማራ ተጋድሎ የወደፊት ተስፋ የሆነው ይህ ፍኖተ-መርህ ተጠናቋል።
የፋኖ እንቅስቃሴ በምስራቅ አፍሪካ ካሉት ግዙፍ ሃይሎች አንዱ ወደ መሆን ተሸጋግሯል። በወታደራዊ ኃይል እና በድርጅታዊ አቅም በመጎልበቱ፣ እንዲሁም ፋኖ ከፍተኛ ድሎች በማስመዝገቡ ሰፊ እውቅናና ተዓማኒነት አግኝቷል። ተፅዕኖው እየሰፋ ሲሄድ የርዕዮተ-ዓለም ግልጽነት እንዲኖረውና የፖለቲካ መስመሩንም እንዲያሳውቅ ከተለያዩ አቅጣጫዎች፣ በተለይም ከዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ ጥሪዎች ሲስተጋቡ ቆይተዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ለዚህ ጥሪ ምላስ ለመስጠት ረቂቅ ፍኖተ መርኁን ከወራት በፊት ለአንባብያን አቅርቦ ከማኅበረሰቡ አስተያየት ሲሰበስብ ቆይቷል። እነሆ ዛሬ ከፋኖ አባላትና አመራሮች፣ ከደጋፊዎች እና ከሰፊው ማኅበረሰብ በተገኙ አስተያየቶችና ሃሳቦች የዳበረውን ፍኖተ-መርኅ ለሕዝብ ይፋ የምናደርገው በታላቅ ደስታና የኃላፊነት ስሜት ነው።
ይህ ፍኖተ-መርህ ከፖለቲካዊ መግለጫ በላይ – ለሕጋዊነት፣ ለተዓማኒነት፣ ለግልጸኝነት፣ ለአንድነትና ለአሳታፊ ፖለቲካ ስትራቴጂያዊ ንድፍ ነው።
ውጣ ውረድ በበዛበት በዚህ የፋኖ ጉዞ ውስጥ አዲስ ምዕራፍን ከማመላከትም በተጨማሪ፣ የድርጅቱን ግቦች፣ እሴቶች እና ራዕይ በግልፅ ያሳያል።
ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን የጨበጡ ተከታታይ መንግሥታት የአማራን ህዝብ ለሥርዓታዊ የዘር ማጽዳት ጅምላ ግድያዎች(ጄኖሳይድ)፣ ለፖለቲካ መገለል እና የባህል መዛባት አጋልጠውት ቆይተዋል። የአማራ ሕዝብ ለሺህ ዓመታት ለሀገር ግንባታ ያበረከተው አስተዋፅዖና የከፈለው መስዋዕትነት እንደ ወንጀል ተቆጥሮ፤ ጀግንነቱን የሚያንቋሽሽ ትርክት ተፈብርኮበታል፡፡ በማግለል የተጀመረው መገፋት ወደ ኅልውና አደጋ ተሸጋግሯል፤ እልቂት፣ መፈናቀል እና ተቋማዊ ጥላቻ የአማራን ሕዝብ ከጥፋት አፋፍ ላይ አድርሶታል።
በዚህ አውድ የአፋሕድ ፍኖተ-መርህ የፋኖን እንቅስቃሴ የወለደውን ታሪካዊ ኢፍትሃዊነት፣ የፖለቲካ ክህደት እና የአማራን ሕዝብ ድምጽ የማፈን በደል በማሳየት ሊያሳካቸው ቃል ኪዳን የሚገባላቸውን የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የሕዝባዊ ሉዓላዊነት እና የሰብአዊ መብት እሴቶች በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
ከተቃውሞ ባሻገር፣ ፍኖተ-መርሁ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና በትብብር በመልማት ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፕሮግራሞችን ያካተተ ነው።
አፋሕድ ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለጭቁንና ጭቆናን ከሚጋፈጡ ማኅበረሰቦች ሁሉ አጋርነቱን ገልጾ ትግሉ የሚመራው በበቀልና በጥላቻ ሳይሆን በእውነትና የወገናቸውን የአማራን ሕዝብ ኅልውና ለማረጋገጥ መሆኑን ነው።
ይህ ፍኖተ መርህ ለትግሉ ወሳኝ አቅጣጫ አመልካች ሲሆን፣ ለሰፊው የአማራ ህዝብ መሰብሰቢያ ጥላ – ትውልዶችን በፍትሕ እና በተስፋ የሚያገናኝ የጋራ ራዕይ ሆኖ ሲያገለግል፣ ለሰፊው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብም ፋኖ እንዴት ወደ ትጥቅ ትግል እንደተገፋ፣ ንቅናቄው አሁንም ለበቀል ሳይሆን ለፍትህ፣ ለእኩልነት እና በሰላም አብሮ ለመኖር እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣል።
አፋሕድ ይህን ፍኖተ-መርህ ይፋ በማድረግ፤ በነጻነት፣ በክብር እና በእኩልነት የሚያምኑ ሁሉ ከእውነት ጋር፣ ከፋኖ ጎን፣ በአጠቃላይም በደጀንነት ከአማራ ሕዝብ ጋር እንዲቆሙ ጥሪውን ያቀርባል። ከፊታችን ያለው መንገድ የትግል ብቻ ሳይሆን ስልጣኔን እንደገና የመገንባት እና ፍትሓዊት የተባበረች ኢትዮጵያን የመፍጠር ነው።
የአፋሕድን ፍኖተ መርህ ለማንበብ፤⇓
AFPO-Manifesto_Bilingual_20October2025
“ክብር እና ሞገስ ለሰማዕታት!!!
ድል ለአፋሕድ እና የአማራ ፋኖ ሁሉ!!!
ድል ለአማራ ሕዝብ!!!
ድል ለኢትዮጰያ ሕዝብ!!!
/
ጥቅምት 12፣ 2018 ዓ.ም።