በ77 ቢሊዮን ብር ጉድለት ስሙ በተደጋጋሚ የሚነሳው የህወሓቱ አባይ ፀሃዬ “ፌዴራል ፕሮጀክቶች በክልል ህዝብ ብዛትና የመሬት ስፋት ይለካ የሚለው በአማራና ኦሮሞ የጋራ መድረኮች ላይ የተነሱት ጉዳዪች የብአዴንና ኦህዴድ አመራር አባላትንም ያካተተ አስተሳሰብ ስለሆነ ፣ እንዲህ አይነት አመለካከት ይዘው አንድ ድርጅት ነን፣ ደህና ነን እያልን አብረን መቀጠል አንችልም ። ይህ አስተሳሰብ በተግባር ከሚውል ኢህአዴግን መቅበር ይቀላል” ብሏል ። አባይ ከተናገረውም በላይ የተናገረበት ድምፀትና ስሜት የሚገርም ሆኖ አግኝቼዋለሁ ።ግር የሚለው ነገር እስከዛሬ ድረስ በምን ቀመር ነበር ፌዴራል ፕሮጀክቶች ለክልሎች ሲከፋፈሉ የቆዩት? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው ።
በዜግነት ደረጃ ይሆን? አንደኛ ደረጃ ዜጋ ትግራይ ስለሆነም ከአጠቃላይ የፌዴራል ፕሮጀክቶች 51 በመቶ። ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሱማሌ ***በመቶ፣ እየተባለ ነበርን ሲቀመር የኖረው? ወይስ ለወያኔዎች ስግብግብነት በሚጠቅም ደረጃ “በማስፈፀም አቅም” በሚል ማደናገሪያ? እስቲ ቀመሩን የምታውቁ መረጃውን ወዲህ በሉ ። የአማራና ኦሮሞ ክልሎች ከኤሊቶቻቸው የፀዱ እንዲሆኑ ለሩብ ምእተ አመታት ብዙ ግፍ ሲፈፅም የነበረው ወያኔ፣ በአንፃሩ ትግራይ ሁሉንም የኤሊት አቅሟን ከማዳበር አልፋ በትግራዋይነት የሚሰለፉ ፈረንጆችን እስከማፍራት እንድትሄድ ካደረጉ በኋላ፣ “የሌሎች ክልሎች ፌዴራል ፕሮጀክቶችን የማስፈፀም አቅም ዝቅተኛ ስለሆነ ግንባታው ሁሉ ወደ ትግራይ ይምጣ” የሚለው እምነትና አሠራር ማክተሚያው ወቅት ላይ ደርሰናል ። የኦሮሚያና አማራ ክልልም በስደትና በሃዘን የተነጠሏቸውን ኤሊቶቻቸውን የሚያቅፉበት ወቅትም ሩቅ አይደለም ። እስከዚያው ብቸኛው “ፍትሃዊ” አሠራር የፌዴራል ፕሮጀክቶችን ከህዝብ ብዛት አኳያ ማከፋፈል ነው።
በአሁን ሰአት በትግራይ አዲስ የሚከፈተውን የአድዋ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ፣ አራት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። ይህ ሲሰላ ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ አንድ ዩኒቨርሲቲ ተሰርቷል ማለት ነው። የ2000 ዓምን የህዝብ ቆጠራ እንደ መነሻ ብንወስድ ኦሮሞ 32 በመቶ፣ አማራ 28 በመቶ የህዝብ ድርሻ አላቸው። በትግራይ ስሌት በሌሎቹም ክልሎች ዩኒቨርሲቲዎች ይከፈቱ ከተባለ፣ ኦሮሚያ 32 ዩኒቨርሲቲዎች፣ አማራ ክልል 28 ዩኒቨርሲቲዎች ሊከፈትላቸው ይገባል ። የመንገዶችንና ሆስፒታሎችንም ግንባታ በሚመለከት እንዲሁ። እነዚህ ክልሎች ትግራይ ላይ እስኪደርሱ፣ ከአሁን በኋላ ትግራይ ውስጥ አንዲትም ኪሎሜትር መንገድ መሥራት ላይቻል ነው። ምን ይሻላል?
አባይ ፀሃዬ እንደሚመኘው የኦህዴድንና ብአዴንን አመራሮች አስተሳሰብ ለመቀየር ጊዜው የረፈደ ይመስለኛል። የክልሎቹም ህዝብ ስሱነትና ንቃት ሲጨመርበት አመራሮቹ ቢፈልጉ እንኳ ህዝቡ ሊፈቅድላቸው አይችልም። ይኮረኩማቸዋል። ስለሆነም ቀውሱ ይባባሳል። አባይ የተነበየውም “በኢህአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ” አነጋገርም ተፈፃሚ ይሆናል። አባይ በንግግሩ ላይ “በህገመንግስቱ ላይ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለማቆም ያለመ የሚለውን ወይ መለወጥ አለብን እስከማለት ደርሷል። እንዲህ ወርዶ ከማሰብ ግን ኢትዮጵያችን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች ሊኖሯት እንደማይችሉና፣ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ መሆን እንዳለበትና እንደሚገባው መቀበል የቀለለውና የተሻለው መንገድ ነው። የትግራይን ህዝብ ግን አንደኛ ሰረጃ ዜግነትህን አልቀበል ስላለ ኢህአዴግን ለመበተን አስበናልና ተባበረን የሚለው የአባይ ፀሃዬ ጥሪ፣ ባንተ ስም ወንጀል ማድረግ የምንችልበት እድል እየጠበበ ነውና አስጥለን፣ ደብቀን ከማለት ያለፈ ትርጉም የለውም። እኔ የማውቀው የትግራይ ህዝብም ለእንዲህ አይነት ተገንጣይ ወንጀለኛ አስተሳሰብ ይተባበራል የሚል ግምት የለኝም።