>
5:18 pm - Tuesday June 14, 8681

ኢትዮጵያ የዘነጋቻቸው ድምፆች (ጌታቸው ሺፈራው)

 ምርጫ 97  ኢትዮጵያውያን አደባባይ ወጥተው ድምፃቸው እንዲያሰሙ ያስቻለ ክስተት ነበር። መጨረሻው ባያምርም ሕዝብ የሰጠው ድምፅ እንዲከበር የቻለውንና ወቅቱ የፈቀደውን አድርጓል። መሪዎቹ ሲታሰሩ ጮኋል። ሆኖም በዚህ ሁሉ ጩኸት  ሀገርና ሕዝብ የዘነጋቸው ድምፆች ሞልተዋል።   ከቅንጅት ጋር ተገናኝታችኋል  የተባሉትን ከፍተኛ መኮንኖች መጥቀስ ይቻላል። ለመሆኑ ከቅንጅት ጋር ተገናኝታችኋል ተብለው አሁንም ድረስ በእስር የሚማቅቁ ስለመኖራቸው የምናውቅ ስንቶች ነኝ? የቅንጅት አመራሮች ከተፈቱ ከአመታት በኋላ በቅንጅት ተከሰው የተፈረደባቸውን ማን አስታወሳቸው?
ትህነግ(ህወሓት)/ኢህአዴግ ገደል አፍፍ ደርሶ በአፈና ተቋሙ ከተመለሰበት ምርጫ 97 በኋላ የአፈና ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ግምገማ ተደርጓል። አንዱ የግምገማ ማዕከል መከላከያ ሰራዊቱ ነበር። አቶ መለስ በጭካኔ ባዘዙት መጠን ያልጨፈጨፈ ሁሉ የቅንጅት አባልና ደጋፊ ነህ ተብሎ ተወርፏል፣ ተባሯል፣ ታስሯል።  ከምርጫው ማግስት በ1998 ዓም በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ በተደረገው ግምገማ ሰለባ ከሆኑት መካከል ኮ/ል አበበ አስራት፣ ኮ/ል ጎሳዬ ቦጋለ፣ ኮ/ል  ተስፋዬ ኃይሉ፣ ኮ/ል ተስፋዬ ለማ፣ ኮ/ል  ጌትነት አድማሱ እና  ሻ/ል ካሳሁን ንጉሴ ይገኙበታል።  እነዚህ ከፍተኛ መኮንኖች በዋነኛነት የተገመገሙት  ከቅንጅት ጋር ግንኙነት ነበራችሁ ተብለው ነው። ምን አልባት በተባለው መጠን አልገደሉ ይሆናል፣ ምን አልባት አቶ መለስ በተናገሩት መጠን አላስጨፈጨፉ ይሆናል፣ ምን አልባት “ኢህአዴግን እናድን!” ሲባሉ “እኛንኮ ገለልተኛ ናችሁ፣ ወታደር ናችሁ ብላችኋል” ብለው የሙያ ጉዳይ በማይነሳበት ወቅት የሙያ ጥያቄ አንስተው ይሆናል።
ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ በግምገማ ወቅት እንዳልተስማሙ ይነገራል። በዚህም መሰረት ስንትና ስንት የሙስና ጉድ በሚወራበት የጦር ኃይል ውስጥ  “በእየ ክፍሉ ለሚሰሩ አባላት በሙሉ ለመንግስት ሥራ ተብሎ የመጣውን አቡጂዲ ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጣቃ አቡጅዲ አከፋፍለዋል” የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል። ዋነኛው የክሱ ማጠንጠኛ “ከነውጠኛው ቅንጅት ጋር ግንኙነት በማድረግ” የሚል ሲሆን በወቅቱ የቅንጅት አመራር ከነበሩት አቶ በድሩ አደም ጋር በመገናኘት መሳርያ እና ጥይቶችን ለማይመለከታቸው አካላት አሳላፈው ሰጥተዋል ይላል።
የክሱ ዝርዝር” ሆን ብለው እና አስበውበት በወቅቱ ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ  በሚል ስያሜ ይጠራ የነበረው ነውጠኛ የፖለቲካ ድርጅት  ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ይረዳው ዘንድ  ያደርግ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊቱን ለአመፅ  ማነሳሰሰት ተግባር ላይ ድጋፋቸውን  ለመስጠትና ተልዕኮውን ለማሳካት” አግዘዋል የሚል ሲሆን ጠፍተዋል የተባሉ ሽጉጦችን ለማን እንደተሰጡ እንኳን በግልፅ ያብራራ አልነበረም። በምስክርነት ሂደቱ “ሸጠው ተጠቅመውበታል” ያለም ምስክር ነበር። በሌላ በኩል የሰራዊቱ አባላትን ቅንጅትን እንዲደግፍ በይፋ እንደቀሰቀሱ ተደርጎም ክስ ቀርቦባቸዋል።  ከቅንጅት ጋር ነበራቸው የተባለውን ግንኙነት ለማጀብ ሲባል ” ሁለት ኩንታል ሲመረንቶ፣ስድስት ጣቃ አቡጀዲ……” የክሰ ዝርዝር ላይ ተቀምጧል።  ስድስቱም ከፍተኛ መኮንኖች በሶስት ክሰ ጥፋተኛ ተብለዋል።  ዋነኛውና በሌሎች ክሶች የታጀበው ክሳቸው “በፈፀሙት ነውጠኛ ከሆነው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ በጠራው ሕገ ወጥ የሆነ ስብሰባ በመካፈል ወንጀል፣ ሰራዊቱን ቅንጅትን እንዲደግፍ በማድረግ ወንጀል……” የሚል ነው።
“ነውጠኛ” የተባለው ቅንጅት  አመራሮች  ሐምሌ 13/1998 ዓም  በይቅርታ ተፈትተዋል። በዚህ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ  “ነውጠኛ” ሲሉት ከነበረው ቅንጅትም ጋር “ቂም፣ ቁርሾና መጠቃቃት” እንደማይኖር መግለጫ ሰጥተው ነበር።  መስከረም 1999 ዓም “ከነውጠኛው ቅንጅት ጋር ግንኙነት አድርጋችኋል” የተባሉት ከፍተኛ መኮንኖች የተከሰሱበት ቅንጅት አመራሮች ሲፈቱም  የሚገባቸውን ያህል ያልተጮኸላቸው መኮነኖች ግን በእስር ላይ ነበሩ።  “የኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ነው” የተባለለት 2000 “ሚሊኒዬም”ን ተከትሎ ሕዳር 27/2000 ዓም በዋስትና ቢለቀቁም ክሱ ቀጥሏል።  የተከሰሱበት የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከተፈቱ  ከ2 አመት በኋላ መጋቢት 2001 ዓም “ከነውጠኛው ቅንጅት ጋር በመገናኘት” የሚል ክስ ቻርጅ ደረሳቸው። ሀምሌ 17/2001 ዓም የተከሰሱበት ቅንጅት አመራሮች ከእስር ከተፈቱ ከ2 አመት ከአራት ቀን በኋላ  ብ/ጄኔራል  በርሄ ተስፋይ፣ ብ/ጄኔራል ዘውዱ እሼቴ፣ ብ/ጄኔራል  ጌታቸው ጉዲና፣ ኮ/ል ዘውዱ ኪሮስ  እና ኮ/ል ጌራወርቅ ደረሰ ባስቻሉት ወታደራዊ የጦር ፍርድ ቤት  2ኛ ምድብ ችሎት  ኮ/ል አበበ አስራት እና ኮ/ል ጎሳዬ ቦጋለ የ23 አመት ፅኑ እስራት፣ ኮ/ል ተስፋዬ ኃይሉ 21 አመት፣ ኮ/ል ተስፋዬ ለማ 16 አመት፣  ኮ/ል ጌትነት አድማሱ አስር አመት እንዲሁም  ሻ/ል ካሳሁን አስራ አምስት አመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
እነዚህ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተፈረደባቸው ከ”ነውጠኛው” ቅንጅት ጋር ተገናኝታችኋል በሚል ነው። እነዚህ የጦር መኮንኖች በእስር ላይ እያሉ የቅንጅት አመራሮች ተፈትተዋል። አብዛኛዎቹ የራሳቸውን ድርጅት አቋቁመው ነበር። ከእነሱ ጋር ተገናኝታችኋል የተባሉትን መኮንኖች ግን ያስታወሰ አካል አልነበረም። አሁንም የሚያስታውሳቸው አላገኙም። በወቅቱ የህዝብን ይሁን አግኝቶ በነበረው ቅንጅት የተከሰሱት እና አስታዋሽ ያጡት  የጦር መኮንኖች በገዥዎቹ ዘንድ ይደርስባቸው የነበረውን የጥላቻ በትር  ለመረዳት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው የቅጣት ማቅለያ ዋና አስረጅ ይሆናል። ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ባቀረበው የቅጣት ይክበድልኝ ጥያቄ “ወንጀሉን የፈፀሙት በከሃዲነት፣ በወራዳነት፣ በወስላታነት………” ብሎ ማቅረቡን ብ/ጄኔራል በርሄ ተስፋይ የመሩት ፍርድ ቤት በውሳኔው ስድቡን ቃል በቃል አስፍሮታል። እነዚህ መኮንኖች ከሳሾቻቸው በችሎት ሲዘልፏቸው የተከሰሱበት ድርጅት፣ አመራርና ሕዝብ ያስታወሳቸው አይመስልም። ምርጫ 97 ተስፋ ይዞላት መጥቷል ተብላ የነበረችው ኢትዮጵያ ለበርካቶች ስትቆዝም፣ እነዚህን ከፍተኛ መኮንኖች ዘንግታቸዋለች።
 ከተከሳሾቹ መካከል  ኮ/ል አበበ አስራት እና ኮ/ል ጎሳዬ ቦጋለ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ፣  ኮ/ል ተስፋዬ ኃይሉ በእስር ላይ እያሉ ሕይወታቸው አልፏል።  ኮ/ል ተስፋዬ ለማ፣ ኮ/ል ጌትነት አድማሱ እና ሻ/ል ካሳሁን ንጉሴ እስራቸውን ጨርሰው በቅርቡ ወጥተዋል ተብሏል።
እነዚህ መኮንኖች ሀገራቸውን ያገለገሉ፣  ምን አልባትም ገዥዎቹ በሚወስዱት ከመጠን ያለፈ ጣልቃ ገብተነት “ለምን?” ብለው በመጠየቃቸው ምክንያት “ይቅርታ” በተደረገበት ጉዳይ ዋጋ የከፈሉ ናቸው።  የአብዛኛዎቹ መከላከያ ምስክሮች እንዳስረዱት መኮንኖቹ ከቅንጅት ይልቅ ኢህአዴግን የሚደግፉ ነበሩ። ሆኖም ኢህአዴግን መደገፍ ወንጀል አልተባለባቸውም።  የቅንጅት አመራር ከሆኑት በድሩ አደም ጋር ተገናኝነት መሳርያ ከግምጃ ቤት አስወጥተዋል ለተባሉት መኮንኖች አቶ በድሩ መከላከያ ሆነው ቀርበው “አላውቃቸውም” ብለዋል። መጀመርያውንስ ለቅንጅት መሳርያ ምን ያደርግለታል? መከላከያ ምስክሮቻቸው  መኮንኖቹ የኢህአዴግ ደጋፊ  ናቸው ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፣ ነገር ግን ኢህአዴግን መደገፍ በቂ ሆኖ አልተገኘም። አቶ መለስ “ውሰዱ” ያሉትን እርምጃ አለመውሰድ፣ እየወሰዱም ቢሆን “እንዲህ ማድረግ አልነበረብንምኮ” ማለት “ነውጠኛው ቅንጅት ጋር ግንኙነት አለው” ተብሎ 23 አመት ያስፈርዳል።
ለምሳሌ ያህል በደርግ መቶ አለቃ የነበሩት  ኮ/ል ጎሳዬን ብንመለከት፣ መጀመርያ በኢህአዴግ ታስረው ነበር። የመሃንዲስ ሙያቸውን የፈለገው ኢህአዴግ ታስረውበት ከነበረው ጦላይ አውጥቶ የሰራዊቱ አባል አደረጋቸው። ኮ/ል  ጎሳዬ ኦጋዴን ላይ በግዳጅ በነበሩበት ወቅት ግራ እጃቸውን አጥተዋል። የሰራዊቱ አካላት በአካል መጉደል ሲሰናበቱ ኮ/ል ጎሳዬ እንዲቀጥሉ ተደርጓል። በአንድ እጃቸው ሲያሰራቸው የነበረው ስርዓት በኋላ “ከቅንጅት ጋር ተገናኝቷል” ብሎ እስር ቤት ወርውሯቸዋል። ኮ/ል ጎሳዬ የስኳር በሽተኛ ናቸው፣ እጃቸውን አጥተዋል፣ አንድ ኩላሊታቸው ከስራ ውጭ ሆኗል። በይቅርታ ተዘግቷል በተባለ ምርጫ 97 በብዙ የጤና እክል በእስር ላይ የሚገኙትን እኚህ ሰው ብዙዎቻችን አላስታወስናቸውም።  “እስረኛ ይፈታ” ብለን ስንዘምት ረስተናቸዋል! አሁንም አልተፈቱም!
በእስራቸው ወቅት ሕዝብ የጮኸላቸው፣ ሲወጡም በክብር የተቀበላቸው የቅንጅት አመራሮች ሲወጡ ሲመሩት በነበረው ድርጅት ስም የታሰሩት እንዲፈቱ የወተወቱ አይመስለኝም፣ ሕዝብም የዋናዎቹን መሪዎች መፈታት እንጅ ልክ እንደነዚህ ከፍተኛ መኮንኖች በቅንጅት ስም የታሰረ፣ ተስፋ ይዞ መጣ በተባለው ምርጫ 97 ስም አሁንም ድረስ በእስር የሚማቅቅ እንዳለ አላስታወሰም! ልክ እንደነዚህ መኮንኖች በርካታ ድምፆች ተዘንግተዋል፣ መደብደባቸው፣ መታሰራቸው መሞታቸው አይታወስም!  ሀገር የዘነጋቻቸው በርካታ ድምፆች ሞልተዋል!
(ፎቶው በቅንጅት ክስ 23 አመት ተፈርዶባቸው በዝዋይ እስር ቤት የሚገኙት የኮ/ል ጎሳዬ በጋለ ነው)
Filed in: Amharic