>
5:13 pm - Saturday April 19, 3614

ከቶ ማን አዚም አደረገብን? (ቴዎድሮስ መብራቱ)

እነሱ እንደዚህ ነበሩ፡፡ አዎ በዙፋን ሊጣሉ ይችላሉ፣ አዎ በግዛት ማስፋፋት ጦር ሊማዘዙ ይችላሉ!
አዎ በአለመስማማት ሊሸፍቱ ይችላሉ! ባገር የመጣን ነገር ለመመለስ ግን፣ ጠላትን ለመጣል ግን፣ ሰብዓዊነትን ለማስከበር ግን፣ ኢትዮጵያን ለማዳን ግን በአንድ ላይ ይቆማሉ፣ በአንድ ላይ ይሰለፋሉ፣ በአንድ ላይም ድል ያደርጋሉ፡፡
                       ****
ይህንን ሰሞን ነፍሳቸውን ይማረውና ኘ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ባቋቋሙት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም (IES) በ1988 የተሰናዳ ሰነድ እያነበብኩ ነበር፡፡ ግሩም ነው!! አጃይቭም እንጅ!
የ“አድዋ ውሎ” የሰነዱ መጠሪያ ነው፡፡ የዓይን እማኞች ምስክርነትን ሥመ-ጥሮቹ የታሪክ ሊቃውንት ለ100ኛ ዓመት መታሰቢያ የሰነዱት ነበር ….
ኢትዮጵያዊነቴን የምር ወደድኩት፣ አከበርኩት፣ ለካ እንዲህ ያጌጠ ታሪክ ባለቤት ነን! ለካ እንዲህ የጀግኖች ዘር ነን! ለካ ህብረት ነበረን፣ ለካ ፍቅር ነበረን ፤ለካ ደግነት ነበረን፤ ለካ ብልሃት ነበረን ….
አንድ በአንድ ከሰነዱ እንምዘዝ
ጀግንነት
“- – – – –  ፈታውራሪ ገበየሁ ግን ታሞ ሰንብቶ ነበርና በበቅሎ ተቀምጦ መሳሪያ ሳይዝ ዘንግ ብቻ ይዞ አይዞህ ዕይርሞ (ጥይት?) ያለቀብህ በጎራዴ በለው! እያለ ሲያዋጋ ዋለ፡፡ ሰውም ….. እጄን ያዘኝ! ነፍጤን ተቀበለኝ እየተባባለ በገደሉ እየተቆናጠጠ ወጥቶ ጣሊያንን ድል አደረገው፡፡ በዚያም ሰሞን ሰው ሁሉ ገበየሁ ገበየሁ ብሎ አነሳው፡፡
ጎበዝ አየሁ ብሎ አወጣለት፡፡ (23)
ይህ ብቻ አይደለም የጀግናው ወሮታ ጠላት አድዋ ስላሴ ጉልላት ላይ መድፍ ጠምዶ የወገንን ጦር ሲፈጀው ደረት ለደረት እንደ እባብ ተስቦ ጎትቶ ሲያወርደው ጊዜ
           “አድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
            ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው” ተባለላቸዋ!!
ጀግንነት ይቀጥላል – – –
“……ምሽትም በሆነ ጊዜ ሊቀ መኳስ አባተና በጅሮንድ ባልቻ ተጠሩ፡፡ እንግዲህ ከዚህ ጉድባ ውስጥ ያሉትን ኢጣልያኖች ሳላወጣ ወዲያና ወዲህ አልልም እናንተም አረር እንዳይመታችሁ መታኮሳችሁን አብጁ ብለው አዘዙአቸው፡፡ ሊቀ መኳስ አባተም ካሽከሮቹ
ጋር ሆኖ የኢጣሊያውን ዘበኛ አባሮ በስተግራ በኩል ካቡን ክቦ (መሽጎ) መድፎቹን መትረየሱንም አልቦበት (ጠምዶበት) ነበር፡፡ ደግሞ በስተቀኝ በኩል በጅሮንድ ባልቻም እንደዚሁ ሌሊቱን ሲክብ አድሮ መድፎቹን መትረየሱንም አለበበት (አነጣጠረበት)፡፡ ኢጣሊያኖችም ጦሩ እንደቀረባቸው ባዩ ጊዜ መድፋቸውንም ነፍጣቸውንም ጠንክረው ይተኩሱ ጀመር፡፡ሊቀ መኳስ አባተም ብልህ ዓይነጥሩ ነፍጠኛ ነውና ኢጣሊያኖች ታቦተ እየሱስን አውጥተው የገቡበት ቤተክርስቲያን በመነጥር እያየ፤ እየመዘነ መስኮቱን በመድፍ ይመታው ጀመር፡፡ የመድፋቸውንም መንኩራኩር በመድፍ ሰበረው፡፡ (27)
ለዚህም ነው ለካ ዘር ማንዘሩ ከየትም ይሁን ከየት ጀግናን ማወደስ ባህሉ የሆነው ማኀበረሰብ (አንዳንዶች ተረተኛ እያሉ ከእውነት እና ከእውቀት ቢጣሉም)
           “አባተ አባ ይትረፍ አዋሻኪ ነው
            መድፍን ከመድፍ ጋር አቆራረጠው”
ብሎ የተቀኘላቸው፡፡
የሊቀመኳስ አባተ ቧ ያለው ጀግንነት ይቀጥላል “….ሊቀመኳስ አባተም ኢጣሊያው ከጉድባው (ምሽጉ) እስኪወጣ ድረስ እንቅልፍ አልተኛም ወገቡን አልፈታም፡፡ እንዳይንቀሳቀሱ አስጨንቆ አስጠብቦ በመድፍና በመትረየስ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ በዚያ ሰሞን ሊቀመኳስ አባተ የሰራውን ሥራ ሌላ ሰው ሊያደርገው አይችልም፡፡” (29)
ይሄ ነው እንግዲህ የዓይን እማኞች ምስክር፡፡ እነ እውነት ብርቁ፤ እውቀት ድንቁ! አድዋን አታጋኑት! ይሉናል ፤ አታካብዱት! ይሉናል እነሱ ለምን እንደሚያቀሉት ባይገባንም፡፡ ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ ባልነበረበት በዚያ ዘመን በዲግሪ ተለክቶ የሚተኮሰውን መድፍ እንዴት ቢዋሃዱት! እንዴትስ ቢያውቁት ነው የመድፉን አፍ በመድፍ የበተኑት?
በሰነዱ ውስጥ ልቤን የሚነካው የአያቶቻችን ጀግንነት ብቻም አይደለም ርህራሄያቸውም እንጂ …… መቀሌ ላይ በውሃ ጥም ጣሊያኖች ሊያልቁ ሲሉ እንዲህ ሆነ፡- “ከዚህ በኋላ አጼ ምኒልክ ኢጣልያኖችን በማሩአቸው ጊዜ በጅሮንድ ባልቻን ልከው ሰውም ከብቱም ውሃ ይጠጣ ብለው ዘበኞቻቸውን አዘዙ፡፡ ኢጣልያኖችንም ይህንን በሰሙ ጊዜ ወደ ውሃው ሲወጡ ዘመዱን ለመገናኘት የናፈቀ ሰው ይመስላሉ እንጂ ጠላት ወዳለበት ይሄዱ አይመስሉም፡፡ ከብቱም ውሃ ጠጣ – – – –  አንዲቷም ውሻ በሩ ቢከፈትለት ሩጣ ወጥታ ከውሃው ደርሳ ጠጣችና….”
እንደምን ያለ ርህራሄ ነው?የብሱን አቋርጦ፣ውሃውን ተሻግሮ አገር ሊያጠፋ ለመጣ ጠላቱ እና በጦርነት መሃል እንኳ ለከብቱም፣ለውሻውም የሚያዝን ህዝብ፣የሚያዝን ንጉስ! እውነት የገዛ ወገኖቹን በአንትራክስ በሽታ ይገድላቸዋልን?
ደስ የሚለው፣ ቅድመ አያቶቻችን ቸርነታቸው እና ደግነታቸው ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ እርቅ እንጂ የሞኝነት፣የጅልነት እና ያላዋቂነት፣ አለመሆኑ ነው “ነገር ግን – – – -“ አሉ እምየ ምኒልክ – – -እነዚህን ሰዎች ከነመድፋቸው ከነነፍጣቸው መስደዴ የሞኝነት፣ አይምሰልህ፡፡ ስለ ፍቅር ያደረኩት ነው፡፡ አሁንም ብትታረቁም ድንቅ! ጦነት ከከጀላችሁ እነዚን ጨምራችሁ ጠቅላችሁ ኑ ብለው ከነመድፋቸው ከነነፍጣቸው ሰደዱ”
እንዲህ ነበሩ ጥቁሩ ሰው! ለምነው፣ ተማፅነው፣ እምቢ ላለላቸው ፤ አልሰማ ላላቸው ነበር ክንዳቸውን የሚያሳዩት፡፡ በግዛት አንድነትም ጊዜ የሆነው ይሄው ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ እድሜ ለአክራሪ ዘውጌኛ ፓለቲከኞች  ይሁንና በአድዋ ጦርነት የምኒልክ ተሳትፎ አልነበረም ይላሉ፣ አንዳንዴ ቤተክርስቲያን እያስቀደሱ ጦርነቱ ካለቀ ከደቀቀ ወዲያ ነው የደረሱት ይላሉ፣ሌላ ጊዜ ከኋላ ሆነው ነበር ሌሎቹ ከፊት ላስመዘገቡት ድል ነው በከንቱ የሚሞገሱት ይላሉ? ማለት መብታቸው ቢሆንም እኛ ግን በአይን የነበሩትን፣ ዋኖቻችን የነገሩን እናምናለን፣ እንቀበላለንም፡፡
“እጼ ሚኒልክም የፊተኛውን ጦር ድል ካደረጉት በኋላ ወደፊት ተጓዙ፡፡ በላላውም በኩል ጦር እየጨመሩ ተከተሉት፡፡ ተራራውንም በዘለቁ ጊዜ 2ሺ የሚሆን ኢጣሊያና ባሻባዙቅ (ጣሊያኖች ለባንዶቹ የሰጧቸው ማዕረግ) ከዋሻ ተጠግቶ በር ይዞ አገኙት፡፡ እዚያም ላይ አጼ ምኒልክ ከበቅሎ ወርደው መድፈኞችን አሳልበው 10 10 ያህል በመድፍ ሲጥሉባቸው ያን ጊዜ ከዋሻ ያለው ኢጣሊያና ባሻባዙቅ እግዚኦ! ብሎ ጮኸ – – -” (41)
እንደገናም በሌላ ገጽ፣ “ነገር ግን ንጉሱ የፊተኛውን ጦር አባራሪውን ተከትለው በሩን አልፈው በዘለቁ ጊዜ ደግሞ እንደገና የኢጣሊያ ጦር እንደሳር እንደቅጠል ሆኖ ተሰልፎ ቆየ፡፡ ተኩሱም ከፊተኛው ተኩስ የበለጠ ሆነ፡፡ የኢጣሊያ ሰዎች ከዚህ ላይ ወደቁ” (40)
ይሄው ነው ታሪኩ! እሳቸውማ ጀግና ባይሆኑ፣ እሳቸውማ ደግ ባይሆኑ፣ እሳቸውማ እምየ ባይሆኑ ያ! ሁሉ ጦር እንዴት ይሰበሰብ ነበር? እንዴትስ ይዋጋ ነበር? እንዴትስ ድል ያደርግ ነበር?
“የምኒልክ ደግነት እንኳን ወንዱን ሴቱንና መነኩሴውን አጀገነው” እንዲሉ ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ፡፡
ተራ በተራ እናረጋግጥ …….
“- – – – – –  በዚያን ጊዜ እቴጌም ጥቁር ጥላ አሲዘው ዓይነርግባቸውን ገልጠው በእግራቸው ሲሄዱ ነበር፡፡ ሴት ወይዛዝርትም የንጉሰ ነገሥቱም ልጅ የወ/ሮ ዘውዲቱ ደንገጡሮች ተከትለዋቸው ነበር፡፡የኋላው ሰልፍ እንደመወዝወዝ (ማፈግፈግ?) ሲል ባዩት ጊዜ ቃላቸውን አፈፍ አድርገው “አይዞህ አንተ! ምን ሆነሃል? ድሉ የኛ ነው! በለው!” አሉ፡፡ ወታደሩም የተናገሩትን ቃልና እቴጌንም ባየ ጊዜ መሸሽ አይሆንለትም እና ጸጥ አለ፡፡ እቴጌም ነፍጠኞችን በግራ በቀኝ አሰልፈው በዚያ ቀን የሴቶችን ባህርይ ትተው እንደተመረጠ እንደጦር አርበኛ ሁነው ዋሉ፡፡ የእቴጌም መድፈኞች እቴጌ በቆሙበት በስተቀኝ መልሰው መልሰው መድፍ ቢተኩሱ በመካከል የመጣውን የኢጣሊያ ሰልፍ
አስለቀቁት፡” (40)
እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዬጵያ ይሏል እንዲህ ነው
“ …በደጉ ንጉስ በምኒልክ ጊዜ ከባህር ወዲያ መጥቶ አገራችን እንዴት ይገዛዋል ብሎ ንዴትና ብርታት በሰራዊቱ ሁሉ በልቡ መልቶበት ነበር፡፡ ፈረሰኛውም ወደ ተኩሱ ሲሄድ እግረኛም ጋሻና ጠበንጃ ይዞ ሲሮጥ አፈጣጠኑ ከዚህ ቀደም ባይን ታይቶ በጆሮ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ የሰውም ልቦና ይህንን ይመስላል ብሎ ሊመረምር አይችልም፡፡ ፈረሰኛውም እግረኛውም ዓቀበቱንና አግድመቱን አልብሶት የዘለቀ ጊዜ እንደ ሐምሌ ጎርፍ መስለ፡፡” (32)
“- – – ሰራዊቱም ስለሀገሩ፣ ስለመንግስቱ ተናዶ ነበርና መድፍን ይመታኛል ነፍጡም ይጥለኛል እሞታለሁ ብሎ ልቡ አልፈራበትም፡፡ ተካክሎ ጀግኖ ነበር፡፡ ጌታው ቢወድቅ ሎሌው አያነሳው ወንድሙ ቢወድቅ ወንድሙ አያነሳውም ነበር፡፡ የቆሰለውም ሰው አልጋው (ዙፋኑ) ይቁም እንጂ ኋላ ስትመለስ ታነሳኛለህ በመሃይም ቃሌ ገዝቼሃለሁ ይለው ነበር፡፡ ዕይርም (ጥይት) ያለቀበት እንደሆነ የቆሰለውን ሰው ከወገቡ ዝናሩን እየፈታ እያባረረ ወደፊት ይተኩስ ነበር፡፡ ሰውም ከመንገድ ርዝመት ፤ ከተኩስ ብዛት የተነሳ ደክሞት የተቀመጠ እንደሆነ የምኒልክ ወሮታ የጮማው የጠጁ ይህ ነውን? እየተባባለ እንደገና እየተነሳ ይዋጋ ነበር፡፡”
ምኒልክን አርቆ አሳቢ ያስባላቸው ይሄ ብቻ አይደለም? ተርታውን ሰው ማሰለፍ ብቻም ሳይሆን በዙፋናቸው ላይ የሸፈቱባቸውን? በአንድ ወቅት ተቀናቃኝ የነበሯቸውን፤ ጦር ተማዘው የነበሩትን ሁሉ ነው ወደ ፊት፤ ወደ ጦር ግንባር በፍቅር ማርከው ያመጧቸው፡፡
አብነቶችን እንሰንጥር…
“- – – – – በዚያም ጊዜ በገደል በዱር የነበረው ሽፍታ ሁሉ ይህንን ሰምቶ መግባት ጀመረ፡፡ አጼ ምኒልክም
ከሽፍትነት እየተመለሱ የገቡትን መኳንንት እንደ ማዕረጋቸው እየሸለሙ መቀሌ እንገናኝ እያሉ በየሃገራቸው ሰደዱአቸው፡፡” (25)
እንደገናም
 “- – – – – – በዚያም ቀን ደጃች ጓንጉል ዘገየ፡፡ ሲወዱት ሲያፈቅሩት ሳለ ከአዲስ አበባ ከድቶ ወደ በረሃ ገብቶ ነበር፡፡ እሱ ግን የጦር ጊዜ ነውና ይማሩኝ ልምጣ ከጌታየ ጋራ ልሙት ብሎ ገብቶ ከአጼ ምኒልክ ተገናኘ፡፡ሰራዊቱም መኳንንቱም በእንደዚህ ያለ ጦር ጊዜ መጥቼ ከጌታየ ጋራ ልሙት በማለቱ እጅግ አደነቀ፡፡” (21)
ይሄ ነው የእሳቸው ባህርይ፣ ይሄ ነው የእሳቸው መገለጫ ሌላው ሌላው አፈሪክ ነው ተስፋየ ገብረአባዊ- – – –
በጣም የሚገርመው በእንባቦ ጦርነት ተፋላሚ የነበሩት የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖትም ከምኒልክ ጎን ተሰልፈው ነበር “ንጉስ ተክለሃይማኖትም ወደ ኋላ ቀርተው ነበርና በበጌምድር በኩል መጥተው በታኅሣሥ 15 ቀን ከአጼ ምኒልክ ተገናኙ” እንዲል ሰነዱ፡፡
እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ የአጼ ዮሐንስ አልጋ ወራሽ እንደሚሆን ይጠበቅ የነበረው (በዙፋን ባላንጣ መሆናቸው ነው) የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ጉዳይ ነው፡፡ አጼ ምኒልክ ከመኳንንቶቻቸው ጋር ሲማከሩ ጠላት ወደ አውደ ውጊያው ወጥቶ ካልተዋጋ እኛው ራሳችን ካለበት ድረስ እንወጋዋለን በማለት ደመደሙ፡፡ በኋላ የሆነውን
ከሰነዱ እንጥቀስ
“…..ይህ ምክር ካለቀ በኋላ የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ተሰልፎ በፈረስ ሆኖ መጣ፡፡ እሱም ይህ ምክር እንዳለቀ ባየ ጊዜ አንድ ነገር ልናገር ይፍቀዱልኝ ብሎ ወደ ንጉሰ ነገስቱ ቀርቦ እንዲህ አሉ፡፡
 “…እንደተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ይህን ሁሉ ልናስፈጀው ነውን? አጼ ዮሐንስ መተማ ሄደው ከዚያ እንኳ ከእንጨት አጥር ያን ሁሉ ሠራዊት አስፈጁ፡፡ እኛም ከካብ (ምሽግ) ድረስ ሄደን ይህን ሁሉ ሠራዊት አናስፈጅም አሉ፡ ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ (37)
አጼ ምኒልክ በሃሳቡ በመስማማት ይህንን ለሌላው አስተላለፉ፡፡
እነሱ እንደዚህ ነበሩ፡፡ አዎ በዙፋን ሊጣሉ ይችላሉ፣ አዎ በግዛት ማስፋፋት ጦር ሊማዘዙ ይችላሉ! አዎ በአለመስማማት ሊሸፍቱ ይችላሉ! ባገር የመጣን ነገር ለመመለስ ግን፣ ጠላትን ለመጣል ግን፣ ሰብዓዊነትን ለማስከበር ግን፣ ኢትዮጵያን ለማዳን ግን በአንድ ላይ ይቆማሉ፣ በአንድ ላይ ይሰለፋሉ፣ በአንድ ላይም ድል ያደርጋሉ፡፡
ታዲያ እኛ የዚህ ዘመን ግርምቶች! ከቀደሙት እንዳንማር፣ የሃገር ፍቅራቸውን በልባችን እንዳናትም፣ ህብረት አንድነታቸውን እንዳናስቀጥል፤ ነገራቸውን ሁሉ እንዳናስተውል – – – – ከቶ ማን አዚም አደረገብን??
ለአድዋ ድል መታሰያ 
Filed in: Amharic