>

ያልተነገረው የደጃዝማች በየነ ወንድም አማገኘሁ ታሪክ  (አቻምየለህ ታምሩ)

ዛሬ  ወድቃ  የምትገኘው ኢትዮጵያ አገራችን በተለያዩ ዘመናት ከራሳቸው በላይ ላገራቸው የሚያስቡ፤  ምክራቸው አገር የሚያውል ትላልቅ ሰዎች  ነበሯች። የሀያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ከነበሯት  ልጆች  መካከል በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በደጅ አጋፋሪነት፤ በልጅ እያሱ ዘመን በሊጋባነትና በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን  ጊዜ  ደግሞ በደጃዝማችነት የሚታወቁት፤ በፈረስ ስማቸው አባ ሰብስብ በመባል የሚጠሩት  በየነ ወንድማገኘሁ ቀዳሚው ናቸው።
በዚህ ጽሑፍ የበየነ ወንድማገኘሁን ማንነት እና በመጨረሻም ለኢትዮጵያ የከፈሉትን የመስዕዋትነት ታሪክ እናወሳለን። የታሪኩ  ምንጮቻችን   የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል «ቼ በለው»፤ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ «ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ ፩ኛ መጽሐፍ»፤ የአምባሳደር ዘውዴ ረታ «ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ፣ በምኒልክ፣ በኢያሱ፣ በዘውዲቱ ዘመን»፤ የልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ «ካየሁት ከማስታውሰው»፤  የአለቃ ገብረእግዚአብሔር ኤልያስ «የሕይወት ማስታወሻ፣ አቤቱ ኢያሱና  እቴጌ ዘውዲቱ» እና  የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ «የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ» መጽሐፍቶች ናቸው።
በሕዝብ ዘንድ “ሊጋባው በየነ” በሚል የሚታወቁት  ደጃዝማች በየነ ወንድም አገኘሁ አባ ሰብስብ የሸዋ ቡልጋ ተወላጅ ሲሆኑ የተወለዱት በ1868 ዓ.ም. ነው።  በየነ አባ ሰብስብ በተወለዱበት ቡልጋ  አካባቢያቸው በሚገኝ የቆሎ ትምህርት ቤት ገብተው ሲማሩ ከቆዩ በኋላ ወደ አንኮበር በማቅናት  የቅኔ፣ የመጸሐፍትና  የቤተ መንግሥት ትምህርት  ቀስመዋል። ወጣቱ በየነ ንቁና ፈጣን ስለነበሩ  በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በደጅ አጋፋሪነት ሥራ ተመድበው ብዙ ዘመናትን አገልግለዋል። ዳግማዊ ምኒልክ አርፈው  ልጅ እያሱ መንበረ መንግሥቱን በ1905 ዓ.ም. ከተረከቡ ከሁለት አመት በኋላ ኀዳር 12 ቀን 1907 ዓ.ም. ከአጋፋሪነት ወደ ሊጋባነት ከፍ ያሉበትን ሹመት  ተሰጥቷቸዋል።  ልጅ እያሱ ሃይማኖት ለውጠው የመንግሥቱን ሥራ አልተከታተሉም ተብለው በትወነጀሉ ጊዜ ግንባር ቀደም ሆነው የተናገሩ እሳቸው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። በ1909 ዓ.ም. ልጅ እያሱ ከስልጣናቸው ከወረዱና ንጉሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ከነገሱ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ደግሞ ባለ ሙሉ ስልጣን አልጋ ወራሽ  ከሆኑ በኋላ ሊጋባ በየነ በደጃዝማችነት ማዕረግ መጀመሪያ  በባሌ  ከወራት በኋላ ደግሞ  ወደ ወላይታ ተዛወረው  አውራጃ ገዢ ሆነው ተሾሙ።
ለአምስት አመታት ያህል ወላይታን እንዳስተዳደሩ በ1915 ዓ.ም. የወላይታ ባላባቶች በአገረ ገዢያቸው በደጃዝማች በየነ ወንድም አገኘሁ ላይ ክስ ስላቀረቡ ነገሩን ለመመርመር ግራዝማች ቆርቾ የሚባሉ  የአልጋ ወራሽ ተፈሪ ወንበር [ዳኛ ማለት ነው] ከአዲስ አበባ ወደ ወላይታ ተላኩ። የክሱ ዓይነት፣ “ወህኒ ቤት ተቃጥሎ በእስረኞቹ ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ ደጃዝማች በየነ በግቢያቸው ግብር እያበሉ ዝም ብለው ለእርዳታ ሳይደርሱ ቀርተዋል የሚልና በጠቅላላም በአስተዳደር በድለውናል” የሚል ነበር። ወንበሩም ነገሩን ከመረመረ በኋላ ክርክሩ አዲስ አበባ ቢደረግ የሚሻል መስሎ ስለታያቸው ይህንንኑ ጉዳይ ለበላይ አካል አስታወቁ። ስለዚህ የወላይታን ግዛት ነጋድራስ አስቤ እንዲጠብቁ ተደረገና ተከራካሪዎቹ ባላባቶችና ደጃዝማች በየነ ወደ አዲስ አበባ እንዲወጡ የበላይ ትእዛዝ ተላለፈላቸው።
በዚህ ጊዜ ሌሎች ሰዎችም በደጃዝማች በየነ ላይ የነፍስ መግደል ወንጀል አቅርበውባቸው ነበር። የነገሩም አነሣሥ እንደሚከተለው ነው።
ደጃዝማች በየነ ፊታውራሪ ኃይሌ አባ ይርጋ የተባለ ረዳት ነበሯቸው። ፊታውራሪ ኃይሌ አባ ይርጋ በደጃዝማች በየነ ወንድም አገኘሁ ቤት በአጋፋሪነት  የሚያገለግሉ ናቸው። እኒህ ሰው ለጉዳያቸው ወደ አዲስ አበባ ቤተ መንግሥትና ወደ ሌላም ስፍራ በየጊዜው ይልኳቸው  ነበርና በዚህ ምክንያት ከልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጋር ለመተዋወቅ ስለበቁ በአለቃቸው በደጃዝማች በየነ ላይ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም ነገር እያመላለሱ “ይናገሩ  ጀመር”። እንዲያውም  በሚስጥር “የአልጋ ወራሽ አገልጋይና  ነገር አመላላሽ ሆኗል” ተብለው ተወራባቸው። ደጃዝማች በየነ ይህን ወሬ ከሰሙ በኋላ ፊታውራሪ ኃይሌ አባ ይርጋ ወደ ወላይታ ሲመለስ እጃቸውን አስይዘው አሰሯቸውና የጭፍራ አለቆች እንዲጠብቋቸው አደረጉ። ለጥበቃ የታዘዙ ሰዎች ግራዝማች አበራና ግራዝማች ተክሌ የተባሉ የመቶ አለቆች ሲሆኑ፣ አቶ ተበጀ የተባሉ የኀምሳ አለቃም የእስረኛው ቁራኛ ሆነው እንዲጠብቁ ታዝዘው ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ እስረኛው ከጠባቂዎቹ ጋር በወዳጅነት ተስማምተውና ግብዣ አድርገው በመጠጥ አሰከሯቸው። እንቅልፍ ሲወስዳቸውም ሌሊት  የታሰሩበትን ፈትተው በመውጣት ወደ አዲስ አበባ ሸሽተው አመለጡ።
በማግሥቱ ጧት መጋቢት 12 ቀን 1915 ዓ.ም. ደጃዝማች በየነ ቤተ ክርስቲያን ተሳልመስ ወደ ግቢያቸው ሲመለሱ የእስረኛውን መጥፋት ስለነገሩዋቸው ተናደዱና ችሎት አድርገው ጠባቂዎቹን ለፍርድ አቀረቧቸው። እስረኛው እንዴት እንዳመለጠ ጥያቄና ምርመራ ከተደረገ በኋላም ለማምለጥ የቻሉት ጠባቂዎቻቸው ሰክረው በመተኛታቸውና በቸልተኛነታቸው መሆኑ ስለታወቀ በችሎቱ ላይ የነበሩ ፈራጆች “ትቀጣላችሁ፣ ቅጣቱን ግን የበላይ ያውቃል” እያሉ  እንደቆየው የፍርድ ልማድና የዘመኑ መንፈስ  እየተቹ በሦስቱም ላይ ፈረዱባቸው። ደጃዝማች በየነም በጥፋተኞቹ ላይ  ፍርዱን አርባ ጅራፍ እንዲገረፉ  ስላዘዙ ሶስቱ ጥፋተኞች አርባ ጅራፍ ተገረፉ። ሁለቱ የመቶ አለቆች ተገርፈው ከተነሱ በኋላ፣ ቁራኛ የነበረው ያምሳ አለቃ ተበጀ ሲገረፉ ጅራፉ ከወደጫፉ ተበጥሶ ነበር። ገራፊውም ሥራውን ቀጥሎ በጉንድሉ ስለገረፋቸው አቆሰላቸውና በቁስሉ ምክንያት ታመው  ከጥቂት ቀን በኋላ ሞቱ። ስለዚህም በአዲስ አበባ የሚገኙት የኀምሳ አለቃ ተበጀ ዘመዶች ለልዑም አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ አቤት ስላሉ ደጃዝማች በየነን በነፍስ ገዳይነት ከሰሷቸው። ከዚህ በተጨማሪ  አለቃ ሀዋዝ የተባሉ ባሕታዊንም  ያለፍርድ አስገርፈሃል የሚል ክስም ቀርቦባቸው ነበር።
ከዚህ በኋላ የባላባቶቹ አቤቱታና የነፍስ መግደል ወንጀሉ አዲስ አበባ ከልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ  ችሎት ቀርቦ ነገሩ ተመርምሮ ግንቦት 9 ቀን 1915 ዓ.ም. በደጃዝማች በየነ ስለተፈረደባቸው በመጀመሪያ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ቤት ዘጠኝ ወር ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አንኮበር ከተማ ተዛውረው ወህኒ አዛዥ በነበሩት በደጃዝማች አሰፋ ልዑል ሰገድ እጅ ዘጠኝ ወር ታሰሩ። ከዚህ በኋላ በ1917 ዓ.ም. በጥር ወር ምሕረት ተደርጎላቸውና ካሳ ከፍለው  ከአንኮበር ወጡና በወሊሶ ወረዳ በርስታቸው ላይ እንዲቀመጡ ተፈቀደላቸው።
በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የተከበሩና የታፈሩ፣ ልጅ እያሱን ከመንግሥት ለመሻር አድማ ተደርጎ በነበረ ጊዜም  ከመሪዎቹ አንዱ የነበሩት ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁ በዘመኑ ፍትህ ይይዘው በነበረው ከፍተኛ ግምት የተነሳ በነፍስ ወንጀል ተከሰው ከተፈረደባቸው እስራት ሊያመልጡ አልቻሉም። ፍትህ የሌለበት የጨለማ ዘመን ተደርጎ ከአርባ ሶስት አመታት በላይ የተዘመተበት ያ ዘመን ለፍትህ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰጥበት ዘመን ነበር።
ከአንኮበር  ከተማ እስረኝነት አሞክሮ ተደርጎላቸው በወርሃ ጥር እስራቱ በምሕረት ቀረላቸውና ወደ አዲስ አበባ ሳይገቡ በርስታቸው ላይ ተቀምጠው ሳለ ባንድ በኩል ወደ ከተማ እንድገባ ይፈቀድልኝ እያሉ አማላጅ እየላኩ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮነንን ይለምኑ ጀመር። በሌላ በኩል ደግሞ የአልጋወራሽን ሥልጣን በመቃወም የሤራ ቃል እየጻፉ ለየመኳንንቱ ይልኩ ጀመር። ተቃውሟቸውም “ንግሥት ዘውዲቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮነን የመንግሥቱን ሥልጣን ሊይዙ አይገባም። የአልጋ ወራሽ ሥልጣን  ከንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ መንግሥት በኋላ መሆን አለበ” የሚል ነበር።
ከዚህ ሌላ ለጦር ምኒስትሩ ለፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲኔግዴ  በሚስጥር ደብዳቤ እየተላላኩ  “አልጋ ወራሽ የፈረንጅ ደንብ ባገራችን ሊያስገቡብን ነውና ሳያስገቡብን አሁኑን እንበርታ፣ ከትልልቅ ሽማግሌዎች የተረፉ እርስዎ ነዎትና ሁሉም ይረዳዎታል፣ ሴቷ እንኳ በዘነዘና ትረዳለች፣ እኔም ልምጣ ልርዳዎ ሰዎችን ያስመልሱልኝ” የሚልና ሌላም ልዩ ልዩ የሤራ ቃል ጽፈው ኖሮ ወሬው ስለ ተሰማና ደብዳቤውም ስለተገኘ እጃቸውን ተይዘው ታሰሩ።
ደብዳቤዎን ለልዑል አልጋ ወራሽ ያቀረቡትም ራሳቸው የጦር ምኒስትሩ ናቸው እየተባል ይነገራል።  ከዚህ በኋላ ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁ ሚያዚያ ሰባት ቀን 1917 ዓ.ም. ከልዑል አልጋ ወራሽ ችሎት ቀረቡ።  ለአባ መላ ሀብተ ጊዮርጊስ የተጻፈው  ደብዳቤ የሳቸው መሆን አለመሆኑን የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠየቁ። “ይህ ደብዳቤ ቃልህ አይደለም ወይ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “የኔ ቃል ነው” የሚል የእምነት ቃል ከሰጡ በኋላ ፈራጆች ተራ በተራ እየተነሡና እየተቹ “ያስቀጣል” እያሉ ፈረዱባቸው። በዚህ ጊዜ ደጃዝማች በየነ አልጋወራሽ ተፈሪን የሚያስቆጣ ትርፍ ኃይለ ቃል በፉከራ ስለተናገሩ፣ ቅጣት እንዲጣልባቸው ተፈረደባቸው። ፈራጆችም “ጣለው ግረፈው” የሚል ትዕዛዝ ስላስተላለፉ  በወቅቱ ልማድ መሰረት ባለጎፈሬ ገራፊዎች እዚያው ባደባባዩ እመሬት ላይ ሲያስትኟቸው፣ አሁንም አልጋ ወራሽን ኃይለ ቃል የተሞላበት ትርፍ ቃል በፉከራ መናገራቸውን ቀጠሉ። በዚህን ጊዜ ሃይለኛው በየነ ወንድማገኘሁ አልጋወራሽን በኃይለ ቃል መናገራቸውን ባለማቆማቸው በወቅቱ ደንብ መሰረት በጅራፍ ይገረፉ ጀመር። 29 ጅራፍ እንደተገረፉ የአጼ ምኒልክን ስም በመጥራታቸውና  እነራስ ሥዩምና ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ቆመው አልጋ ወራሽ ተፈሪን ግርፋቱን እንዲያስቆሙ ስለለመኗቸው ግርፋቱ ቆመላቸውና ተነሱ። ቀጥሎም በደጃዝማች አባ ሻውል እጅ እንዲታሰሩ ወዲያው እለቱን  በባቡር አሣፍረው ወደ ሐረር ወሰዷቸው።
ባለታሪካችን “ሊጋባው” በየነ ወንድማገኘሁ በሐረር የነበራቸው የእስር ቆይታ ከመጠናቀቁ በፊት  አልጋወራሽ ተፈሪ ንጉሠ ነገሥት ከመሆናቸው በፊት በ1921 ዓ.ም.  ንጉሥ ተፈሪ ተብለው ሲነግሱ  የንግሥና በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ   በየነ አባ ሰብስብን በምህረት  ለቀቋቸው።  ደጃዝማች በየነ ከእስር እንደተለቀቁ  ንጉሥ ተፈሪ  የጎንደር አገረ ገዢ  አድርገው ይሾሟቸው።  በዚህን ጊዜ  አገረ ገዢ እንዲሆኑ የተሾሙት   ደጃዝማች በየነ የአገረ ገዢነቱን ሹመት   እምቢኝ ብለው  “አገሬን እንጂ ያሰረኝንና የገረፈኝን  መንግሥት አላገለግልም” በማለት ሹመቱን ሳይቀበሉት ቀሩ። ኃይለኛው በየነ ወንድማገኘሁ ከእስር በኋላ የተሰጣቸውን ሹመት እንደማይቀበሉ ሲገልጹም በንጉሥ ተፈሪ ላይ  ኃይለ ቃል ተናግረናውል  በመባላቸው እንደገና ለእስር በግዞት በግንቦት ወር 1923 ዓ.ም. ወደ ኮንታ ተላኩ።  “ያሰረኝን መንግሥት አላገለግልም” በሚል  በያዙት የልበ ሙሉነትና አቋምና ኩራት  ሹመት አልቀበልም ብለው ለእስር  ሲዳረጉ የሰማው ያገራችን ሰው  ስለኩሩነታቸውና ጅንነታቸው እንዲህ ብሎ ገጠመላቸው፤
ጠጅ አልጠጣም ብሎ ውሃ እየለመነ፤ 
እንደኮራ ሞተ እንደ ተጀነነ፣ 
የጎንደር ባላባት ሊጋባ በየነ
በግጥሙ ጠጅ የተባለው እምቢ ያሉት የጎንደሩ የደጃዝማችነት  ሹመቱ ሲሆን፤ በውሃ  የተመሰለው  ደግሞ  ቀዝቃዛ ወደሆነው  የኮንታ ክፍል  የተጋዙበት የእስሩ ሁኔታ ነው። ይህ በሆነ በጥቂት አመታት ውስጥ  ፋሽስት ጥሊያን መረብን ተሻግሮ ኢትዮጵያ ወረረ። ሹመት ሲሰጣቸው  “አገሬን እንጅ ያሰረኝ መንግሥት አላገለግልም” ያሉት ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁ  የኢትዮጵያ በፋሽስት ጥሊያን መወረር በሰሙ ጊዜ ግን በግዞት ከሚኖሩበት  ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደብዳቤ ጻፉ። ለንጉሠ ነገሥቱ በጻፉት ደብዳቤም  «አገሬን ከወራሪ  ቀንበር ነፃ ለማድረግ ቁርጥ አድርጊያለሁ» ሲሉ አስታወቁ። ተፈቀደላቸውና ከኮንታ ወጥተው ወደ ጦር ግንባር ዘመቱ።
በመስከረም ወር 1929 ዓ.ም. የታወጀውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የክተት አዋጅ ተከትሎ በሰሜንና በኤርትራ የመጣውን የፋሽስት ወራሪ ጦር ለመመከት የዘመተውን በቤጌምድር እና በሰላሌ ገዥ በልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ዋና ጠቅላይ አዝማችነት ይመራ በነበረው የሰሜን ጦር ውስጥ በተንቤን ግንባር በመሰለፍ የካቱት 19 ቀን 1929 ዓ.ም. ተንቤን ላይ በተካሄደው ጦርነት ላገራቸው ሲዋጉ ግንባራቸው  ላይ ተመተው  በጀንግነት ተሰውተዋል።  ማይጨው ግንባር ሆነው የደጃዝማች በየነን መሰዋት የሰሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  «አንተ ግንባርህን ለአገርህ  እንደሰጠህ   እኛ ደግሞ ደረታችንን  ለሀገራችን እንሠጣለን»  ማለታቸው በታሪክ ተመዝግቧል።
ልበ ሙሉው ደፋር በየነ አባ ሰብስብ አገረ ገዢ ተደርገው ሲሾሙ አልፈልግም ብለው፣ ጠላት አገራቸውን ሲወር ግን ከግዞት  ወጥተው አገራቸውን ከወረረ ፋሽስት ጋር ሲዋጉ በጀግንነት ተሰው። የግራ ፖለቲከኞቻችን ወደ ኋላ እያዩ ያፈረሷት አገር እንደዚህ አይነት ከባድ መስዕዋትነት የተከፈለባትን ኢትዮጵያ ነው።
ከሰሞኑ ግዛቸው ተክለማርያም የሚባል ድምጻዊና የማሲንቆ ባለሞያ የጀግና የደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁን ጀብዱ «ሊጋባው በየነ» ሲል በሰራው ትዕይንታዊ ዘፈን ሊዘክራቸው ሞክሯል።
የዘፈኑ መልዕከት አንድነታችንን የሚፈታተነንን፣ አብሮነታችንን የሚንድ፣ በኢትዮጵያችንና በኢትዮጵያዊነታችን የሚመጣውን ማናቸውንም ነገር ልንታገሰው አንችልም በማለት የደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁ መንፈስ ለመድገም ያለመ ይመስላል።
ድምጻዊው ግዛቸውም የደጃዝማች በየነን መንፈስ  በማሲንቆ እየከረከረ. . .
ኸረ ምነው… ምነው ! ኸረ ምነው ምነ!
ከሞተልሽ በላይ የወደደሽ ማነው ?!
ባንች የተነሳ ያልሆነው ምን አለ ?!
አንሸሽም ከፍቅርሽ ይምጣ ሌላም ካለ?!
እንሞታለን እንጅ እንደተዋደድነ!
እንደ ኩሩው ጀግና ሊጋባው በየነ!
የጎን ሕመም ቁስሉን በይቅርታ አልብሶ፣
ስለ ክብርሽ ሲባል መጣልሽ ገስግሶ፤
ሊጋባው በየነ ፣ አሉት ኩራተኛ፣
አንቺን ብሎ ቢቆም ፣ ለሆዱ ባይተኛ
ዛሬም ቢሰፋ እንጂ ፣ ሆድ ካገር አይበልጥም
አንቺን ያለ ጎበዝ ፣ ጦሙን ያድራል የትም፤
በማለት ዛሬም ለክብራቸው ሲሉ ወያኔ ጠባብ ማሰቃያ  ቤት ውስጥ ሲማቅቁ ለከረሙቱ ለኮለኔል ደመቀ እና ጓደኞቹ፤ ሲታገሉ ሕይወታቸውን ለሰውት ለእነ አርበኛ ጎቤ መልኬና የትግል ጓደኞቹን አይነት አገር አውል ወያኔን እምቢ ያሉ ጀግኖችን ያወሳል።
ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁን አይነት እውነተኛ አርበኞች በፈለቁባት ድንቅ ምድር፣ ምቾታቸውን ያልፈቀዱ፣ በዱር በገደሉ ለሐገር የነፍስ መስዋእትነት የከፈሉ፣ ስማቸው ግን የተረሳ አገር የሚያውሉ ጀግኖች አልፈውባታል።
ጸረ ሰው አስተሳሰብ ይዘው አብዮት  አካሄድን ባሉን የግራ ፖለቲከኞች  ጨለማ ተደርጎ የተሳለው ያ ዘመን እንዲህ እንደዛሬው የነውረኞቹ የመለስ ዜናዊና የመንግሥቱ ኃይለማርያም ፍላጎት ያለገደብ የሚፈጸምበት ዘመን ላይ ሳንደርስ  የሕግ የበላይነት ነበረበት። ደጃዝማች የሚለው የኢትዮጵያ ማዕረግ ጀኔራል ከሚለው የፈረንጆቹ ማዕረግ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚያ ዘመን በደጃዝማችነት ማዕረግ ያሉ ሰው ያላግባብና  ያለ ፍርድ ሰው በድለሃል ተብለው ፍርድ ቤት ቀርበው  ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል። በወያኔና በደርግ ዘመን ግን ድሃ የዘረፉና ያለ ፍርድ ንጹሐንን በግፍ የሚገድሉ ጀኖራሎች ሹመትና ሽልማት ሲጎርፍላቸው ነው ያየነው። ባለፈው ሰሞን  ባለ አራት ኮከብ ሙሉ ጀኔራል የሆኑት ሶስት የወያኔ አገልጋዮች ሙሉ ጀኔራል የሆኑት ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ የአማራና የኦሮሞ እንቦቀቅላዎችን በትዕዛዝ ስለጨፈጨፉ ነው። አብዮት አካሄደ ተብሎ የደረስነው  ዛሬ እንደምናየው ለፍትሕ ምንም ታህል ቅንጣት ደንታ በማይሰጣቸው ነውረኞች እጅ ያለ ፍርድ በነጻ እርምጃ በጅምላ  መረሽን ነው።
በርግጥ ይህ ነገር የተጀመረው ከመንግሥቱ ንዋይ ጀምሮ ራሳቸውን ተራማጅ አድርገው የሚቆጥሩት ወፈፌዎች ነው።  እንደ ጀግናው ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁ ሁሉ   ራስ አበበ አረጋይና ራስ መስፍን ስለሺም  ምክራቸው አገር የሚያውልና  ጥሊያንን የተፋለሙ ጀግኖች ነበሩ። ራስ አበበን ያህል ጀግና የተረሸኑት ለውስጥ አመጣለሁ ብሎ በተነሳው መንግሥቱ ንዋይ ነው። ከመንግሥቱ ንዋይ ጭፍጨፋ የተረፉትን እነ ራስ መስፍን ስለሺን  ጀግሞ የፈጃቸው የመንግሥቱ ንዋይ «አልጋ ወራሽ» መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነው። መለስ ዜናዊ የሚባለው የትግራይ ሽፍቶች አለቃም የሁለቱ አረመኔዎች ታናሽ ወንድምና  በአማራ ጥላቻ ጨጓራው ተቃጥሎ የሞተ ነውረኛ ነው። የሶስቱ ነውረኞችና የመንፈስ ወንድሞቻቸው የሕይወት ፍልስፍና  የሚበልጧቸው ሰዎች ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው። ፋሽስት ጥሊያንን ሲዋጉ በጀግንነት የወደቁት አርበኛው በየነ ወንድማገኘሁ በሕይወት ቢተርፉ ኖሮ እንደ ራስ  አበበ አረጋይ ሁሉ  በመንግሥቱ ንዋይ፣ ወይንም  በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አልያም በመለስ ዜናዊ ይረሸኑ ነበር።
ለውጥ መጣ ተብለው ያተረፍነው የነበረንን መብት ነጥቀው  ተራውን ዜጋ ብቻ ሳይሆን ከሁላችን በላይ  አገራቸውን ከጠላት ወረራ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው የተፋለሙ አርበኞችን ጭምር ያለ ፍርድ  በጥይት ደብድበው  የሚረሽኑ ምህረት የለሽ አረመኔዎች የአገዛዝ ቀንበር ስር መውደቅ ነው። ደጃዝማች በየነ የጎንደር አገረ ገዢ ተደርገው ሲሾሙ ሹመቱን አልቀበልም ያሉት ሰዎች በመነግሥት ላይ ጥገኛ ስላልነበሩ፤ እሳቸውም  በጥረታቸውና በልፋታቸው  ራሳቸውን ችለው መኖር እንደሚችሉ  ስለሚያውቁና   የራሳቸው  የሆነ መሬትና  ንብረት ስለነበራቸውም ነው። ላለፉት 44 ዓመታት የታጫኑብን ሁለት ስታሊናዊ አገዛዞች ግን የአገዛዛቸውን የጭቆናና[የአስተዳደር ላለማለት ነው] የስለላ መዋቅር ሁሉ በሰፊው ዘርግተው  በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ የሚወሰኑ የእለት ተእለት የኑሮ ውሳኔዎቻችንን ብቻ ሳይሆን  ሕይወታችንንም ጭምር  በአገዛዞቹ   መልካም ፈቃድና  ይሁንታ ስር እንዲወድቅ አድርገውታል።
እያንዳንዱ ሰው  በመንግሥት ላይ ጥገኛ እንዲሆን ተደርጎ በተዘረጉት  የሁለቱ  ዱርዬ  አገዛዞች መዋቅርና የግራ ፖለቲከኞቻችን በሙሉ   የመንግሥት  ጥገኛ እንድንሆን ላለፉት አርባ አራት አመታት  በሰሩት ሴራ የተነሳ ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁንና እልቆ ቢስ መሰሎቻቸው  ያፈራች አገር እንደ ደመቀ መኮንን አይነት  አመርማሮ ያወጡና  ምንም የግፍ ቀንበር  ለመሸከም ትክሻቸውን ያመቻቹ፣  ሕሊና ቢስ  ሆድ አደር እልፎች መፈልፈያ  ጎረኖ ሆናለች። የነጻነት ቀናችን እየተራዘመ ያለው በአገዛዞቹ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን እንደ ደመቀ መኮነን አይነት የባርነት ዘመን የሚያራዝሙ  የፊደል ሽፍቶች ጭምር   እንዳሸን እየፈሉ  ወደ ነጻነት በምናደርገው መንገድ  ላይ ደንቃሮች ሆነውብን ነው።
Filed in: Amharic