>

በይግባኝ ችሎት በነፃ የተሰናበቱት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ሰበር ሰሚ ችሎት ቅጣታቸውን አፀናው

በሙስና ወንጀል ተከሰው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት አራት ዓመታት ከስምንት ወራት ፅኑ እስራትና 60,000 ብር የገንዘብ ቅጣት የተወሰነባቸው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በይግባኝ ሰሚው ችሎት በነፃ የተሰናበቱ ቢሆንም፣ የሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ ሰሚ ችሎቱን ውሳኔውን ውድቅ በማድረግ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አፀናው፡፡

ዶ/ር ፍቅሩ ለእስራትና ለገንዘብ ቅጣት የዳረጋቸውን ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው ጥቅምት 12 ቀን 2003 ዓ.ም. የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸውንና ገደብና ቁጥጥር የሚደረግባቸውን 32 ዓይነት የተለያዩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ኢትዮጵያ ከማስገባታቸው ጋር በተያያዘ መሆኑን የቅጣት ውሳኔው ያስረዳል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉት የሕክምና አገልግሎት መሣሪያዎች አምስት በመቶ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎባቸው ወደመጡበት አገር (ስዊድን) እንዲመለሱ፣ ኅዳር 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ተወስኖና ታግ ተለጥፎባቸው ቤልት ውስጥ ገብተው እንደነበርም ውሳኔው ያብራራል፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ፍቅሩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎቹ ወደመጡበት አገር ሳይመለሱ ደብቀው ሲያስገቡ በመያዛቸው፣ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91(1)ን (አዋጁ አሁን ተለውጧል) በመተላለፋቸው የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው እንደነበርም በውሳኔው አስታውሷል፡፡

ተከሳሹ የተመሠረተባቸው ክስ ክርክር ተጠናቆና ለፍርድ ተቀጥሮ በነበረበት ወቅት፣ ያለበቂ ምክንያት በወቅቱ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዳይሬክተር አማካይነት ክሱ እንዲቋረጥ መደረጉንም አክሏል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ (አሁን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተጠረጠሩትን የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና ነጋዴዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ባሰረበት በ2005 ዓ.ም. ግንቦት ወር ዶ/ር ፍቅሩ ማሩም ተካተው መታሰራቸው ይታወሳል፡፡ ለአራት ዓመታት ያህል በተደረገ ክርክር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት እሳቸው የተካተቱበት የክስ መዝገብ ተከሳሾች ‹‹ተከላከሉ›› ሲባሉ ዶ/ር ፍቅሩ የመከላከያ ምስክር እንደሌላቸው በመናገራቸው፣ በወቅቱ በሕመም ምክንያት ተኝተው በነበሩበት ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ችሎቱ ተገኝቶ የጥፋተኝነት ውሳኔ አንብቦላቸው መመለሱ ይታወሳል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ ጥፋተኛ በመባላቸው ፍርድ ቤቱ በአራት ዓመት ከስምንት ወራት ፅኑ እስራትና 60,000 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ፍርድ ሰጥቶ ነበር፡፡

ቅጣቱን የተቃወሙት ዶ/ር ፍቅሩ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርበው ነበር፡፡ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የቀረበለትን ይግባኝ ተቀብሎ የግራ ቀኙን ማከራከሩን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው አንደኛ ምስክር የዶ/ር ፍቅሩ ክስ በባለሥልጣኑ ኃላፊዎች እንዲቋረጥ የተደረገው ያለበቂ ምክንያት መሆኑንና ክሱ ሊነሳ እንደማይገባ ለባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ማስረዳቱን መስክሮለት እንደነበር ማስረዳቱን ውሳኔው ይገልጻል፡፡ ሁለተኛው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ደግሞ የስሚ ስሚ ምስክር መሆኑ ገልጾ፣ ዶ/ር ፍቅሩ የባለሥልጣኑ ዋናና ምክትል ዳይሬክተር ለነበሩት ለእያንዳንዳቸው 200,000 ብር ጉቦ እንደሰጡ እንደነገሩት ገልጾ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳለትና እንደመሰከረለት መግለጹን ውሳኔው ያብራራል፡፡ ነገር ግን ይግባኝ ሰሚው ችሎት ከወንጀል ባህሪ አንፃር ዶ/ር ፍቅሩ ጉቦ ሰጥቻለሁ ብለው ለምስክሩ ይነግራሉ ማለት አጠራጣሪ መሆኑንና ‹‹ክሱም መነሳት የለበትም ብዬ ለዋና ዳይሬክተሩ ነግሬያቸዋለሁ›› ያለው ምስክርም ‹‹የክሱን መነሳት ይደግፋል ከሚባለው በስተቀር፣ ክሱ ባልተገባና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ተነስቷል ብሎ ሊመሰክር አይችልም›› በማለት የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር፣ ዶ/ር ፍቅሩ በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ መስጠቱን የሰበር ሰሚው ውሳኔ ያሳያል፡፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ቅሬታ ያሳደረበት ዓቃቤ ሕግ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙን በመዘርዘር ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን አስገብቶ ነበር፡፡ ሰበር ሰሚው ችሎት፣ ‹‹ዶ/ር ፍቅሩ የተከሰሱበት የሕግ አንቀጽ ጥፋተኛ ሊያስብላቸው ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚለውን የክርክሩን መሠረታዊ ጭብጥ ዓይቶ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመኑ፣ በሥር ፍርድ ቤት የተሰሙት ምስክሮች ቃል ይዘትን መመልከት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል፡፡

ሰበር ሰሚው ችሎት የምስክሮቹን ቃል ሲመረምር አንደኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር በወቅቱ የባለሥልጣኑ የዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ኃላፊ መሆኑን አስረድቶ በሰጠው ምስክርነት እንደገለጸው፣ ዶ/ር ፍቅሩ ከስዊድን ይዘዋቸው ስለመጡት 32 ዓይነት የሕክምና መሣሪያዎች በሚመለከት አስረድተዋል፡፡ ሁለተኛው ምስክርም ከላይ የተዘረዘረውን ዶ/ር ፍቅሩ ነገሩኝ ያለውን ጉቦ ስለመስጠታቸው የሰማውን መመስከሩን ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ምስክሮቹ በሰጡት የምስክርነት ቃል ማረጋገጥ የሚቻለው የዓቃቤ ሕግ አንደኛ ምስክር የሰጠው የቃል ምስክርነትና የሰነድ ማስረጃ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር መሆኑን ችሎቱ ገልጿል፡፡

ሁለተኛ ምስክርም ለቀድሞ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለእያንዳንዳቸው 200,000 ብር ጉቦ መስጠቱን መመስከሩ፣ ዶ/ር ፍቅሩ የጥቅም ግንኙነት እንደነበራቸው የሚያረጋግጥ መሆኑን አክሏል፡፡ በሌላ በኩል በወንጀል ሕግ አንቀጽ 403 እንደተደነገገው ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር (ዶ/ር ፍቅሩ መከላከያ ምስክር የለኝም ማለታቸውን ያስታውሷል) የሙስና ወንጀሎች የተፈጸሙት የማይገባ ጥቅም ለማግኘት፣ ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘትና ለመጉዳት መሆኑ በዝርዝር ተገልጾ መደንገጉን ችሎቱ አስታውሷል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ ከቀድሞ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት እንዳለና እንደሌለ የማስረዳት ኃላፊነት የነበረባቸው ቢሆንም፣ ‹‹መከላከያ ምስክር የለኝም›› ብለው ማለፋቸው ከቀረበባቸው ክስ በነፃ ለመሰናበት የሚያስችላቸው የሕግ ምክንያት እንደሌለ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከሕጉ አግባብነት ጋር ማየት ሲገባው ‹‹ከተጠሪ ባለሥልጣናት ጋር የጥቅም ግንኙነት እንዳለው አልተረጋገጠም›› በማለት በነፃ እንዲሰናበቱ የወሰነው ውሳኔ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸም መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ‹‹በነፃ ይሰናበቱ›› ውሳኔ በመሻር የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን የአራት ዓመታት ከስምንት ወራት ፅኑ እስራትና የ60,000 ብር የገንዘብ ቅጣት አፅንቷል፡፡

Filed in: Amharic