>

ቀላል ስሌት ግን ደግሞ ግልፅ እውነት የሆነ ነገር እናውራ እስኪ!!! (ሞሀመድ ኤ እድሪስ)

ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች ጥምረት ነው፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ቢያንስ ሁለቱ ድርጅቶች የራሳቸውን እጣፈንታ ያለጣልቃ ገብነት የመወሰን ፍላጎት እና አቅም እያሳዩ ነው-ህዝቡም በዚህ ደስተኛ ይመስላል፡፡ አሁን በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እግር የሚተካውን ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጥ ሂደት ውስጥ ሊገባ ሲሆን የኦፒዲኦ እጩ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ግምቱ ግን በአራቱ ድርጅቶች እጩዎች መካከል በሚደረግ ዴሞክራሲያዊ ፉክክር አሸንፎ የመውጣት አቅም ላይ የተመሰረተ አካሄድን ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን በኢህአዴግ የውስጥ ፖለቲካ ላይ ተስፋ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ተተኪው ጠቅላይ አብላጫ ድምፅ እንዲያኝ አባል ድርጅቶቹ ወይ እጩ አያቀርቡም ወይንም ከራሳቸው እጩ ሌላ የሌላ ድርጅትን እጩ የሚመርጡ አባላት ይኖራሉ፡፡ ይሄ የሚታሰበው የውስጥ ዴሞክራሲ በሳል የሚባልበት ደረጃ በደረሰበት ሁኔታ እንጂ የብሄር ወገንተኝነት የድጋፍና ተቃውሞ ብቸኛ ምንጭ በሆነባት በኛዋ ኢትዮጵያ አይታሰብም፡፡ ሌላ ምክንያት ከሌለ በስተቀር አንዱ ፓርቲ ለሌላው ድምፅ አይሰጡም እያልን መሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ አማራጮቹ ሶስት ናቸው ፡፡ አንደኛው ኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አባል ድርጅቶቹ በጋራ ሊያፀድቁለት በሚያስችል ደረጃ የውስጥ መግባባት ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ይሄ ለኢህአዴግ እና ደጋፊዎቹ መልካም ዜና ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አሁንም በኢህአዴግ ቤት እከሌን አውጡ እና እከሌን አውርዱ የሚሉ ስውር እጆች ሁሉም ፓርቲዎች ጋር መድረሳቸውን ቀጥለዋል ማለት ነው፡፡ ፈተናውም እዚህ ጋር ነው፡፡ የምንፈልገውን ሰው በየትኛው መንገድ ወደስልጣን እንዲመጣ ነው የምንመኘው?  የምንመኘውን ለማግኘትስ  እውታውንስ አምነን የመቀበል ወኔያችን የት ድረስ ነው? ሶስተኛው አማራጭ ህዝቡ የሚጠብቀው ጠቅላይ ካልተመረጠ አገሪቱ አትረጋጋም የፓርቲዎቹም ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል በሚል ፓርቲዎቹ በተናጠል ለራሳቸው ህልውና እና በራሳቸው ፍቃድ ድምፃቸውን ለሌላ ፓርቲ እጩ ይሰጣሉ፡፡ ይህ እድሉ ጠባብ ከመሆኑጋር ለዘላቂ መተባበር የሚበጅ አይሆንም፡፡ ስለዚህ የምንፈልገው መሪ ሊመረጥ የሚችለው ወይ በጠንካራ ኢህአዴግ ወይንም በስውር እጅ አባል ድርጅቶች በሚያስገድድ ኢህአዴግ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ከቀዳሚው ቢመርም ስንመርጠው የመርህ ጥያቄን ሳናነሳ ነው፡፡ በአንደኛው መንገድ የምንፈልገው ከተመረጠ ደግሞ ቀጣዩ ጉዞ ከጠንካራው ኢህአዴግ ጋር ነው ማለት ነው፡፡
እነዚህ መንገዶች ሳይሰሩ በአገሪቱ ዳግም አመፅ ከተነሳ ጥያቄው ግልፅ እና ግልፅ ነው-መንግስት ይውረድ የሚል! ወደዚህኛው የአመፅ እርከን ለመሻገር ደጋግሞ ለክቶ መቁረጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ እርከን እደከዚህ ቀደሙ የተበደሉ ሁሉ የሚሳተፉበት ሳይሆን መጪው ግዜ ከባለፈው የከፋ አለመሆኑን እርግጠኛ የሆኑና አቅሙ ያላቸው ብቻ የሚከተሉት መንገድ ነውና! በዋናነነት ደግሞ አንድ ጠላት ላይ የሚደረግ አመፅ መሆኑ ቀርቶ ቀጣዩን ግዜ ታሳቢ በማድረግ የጎንዮሽ ፉክክሩ አትራፊ እና ከሳሪውን ከወዲሁ እየለየ የሚሄድበት እርከን ነውና!
ጨፌው ጉባኤውን አራዝሟል-በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚለው በምክንያትነት ይጠቀስ እንጂ አባላት በአንድ መንፈስ በጉባኤ የሚሰየሙበት የውስጥ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም ከሚለው የተለየ ምክንያት አይኖርም፡፡ የእሁዱ የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተሳትፎም አጠራጣሪ የሚሆንበት እድል አለ፡፡ ወይንም በስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ላይ በጨፌው ላይ አቋም የተያዘበት የጋራ ነገር ይዘው መግባት አይችሉም፡፡ የአቶ ሽፈራው ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጅታቸው በፓርላማ ውስጥ በራሱ ተመራጮች የገጠመውን ተቃውሞ ‘ተገቢ አይደለም’ ሲሉ መግለጻቸው በዚያው መግለጫቸው ሊያስተባብሉት ከሞከሩት የፓርቲዎች ሽኩቻ አለመኖር ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ግልፅ የሆነ የመስመር ልዩነት አለ የሚለውን ያሲዘናል፡፡ ለገዢ ፓርቲ ደግሞ ከህዝባዊ አመፅ በላይ የሚያሳስበው የውስጥ ድርጅቱ ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ የውስጥድርጅት ፖለቲካውን ሲቻል በመግባባት ካልሆነ በአሸናፊነት የሚወጣ ሀይል መኖሩ አይቀርም፡፡ ይሄ ለህዝባዊ ትግሉ አዎንታዊም አሉታዊም ተፅእኖ አለው፡፡ መድረሻው የሚታወቀው ግን በኦህዴድ እንደ ፓርቲ በሚያደርጋቸው ቀጣይ እንቅስቃሴዎች ነው-እስካሁን እንደሆነው ሁሉ፡፡
ያለህዝባዊ ጫና የዛሬው ኦህዴድ ሊወለድ አይችልም ነበር፡፡ ያለ ኦህዴድ ደግሞ የዛሬው ኢህአዴግ ሊታሰብም አይችልም ነበር፡፡ ፓርቲው እና አመራሮቹ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ አስተሳብ እና አካሄድ አስተዋውቀዋል፡፡ ኢህአዴግ በፈቃደኝነት ሊያመጣው ከሚችለው ተሀድሶ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥረት ከሚመጣ ለውጥ የተሸለ እና የፈጠነ ውጤት ማሳየት ችሏል-በህዝባዊ ትግል ወደፊት መውጣት የቻለው ኦህዴድ፡፡ ከገዢ ድርጅት ውስጥ እንደመውጣቱ ኦህዴድ ሌሎች ብሄራዊ ፓርቲዎችን ወደጎን እኩል የመገዳደር እና ተቃዋሚውን ደግሞ ከላይ ሆኖ አስተሳሰቡን እንዲቀበል ማድረግ ችሏል፡፡ የድርጅቱን ውሳኔ ሲያራዝምና ሲያስቀለብስ ቆይቷል፡፡ ስልጣኑን ተጠቅሞ አገራዊነት እና የታሪክ አረዳድ ላይ አዲስ ብይን እስከመስጠት ሲደርስ ታይቷል፡፡ በብሄር ጭቆና ዲስኮርስ ስልጣን ላይ ለ27 አመት ተቀምጦ የመደብ ጭቆና ዲስኮርስ አቀንቅኖ ማስጨብጨብ የቻለው ክፍል ቀላል ግምት አይሰጠውም፡፡
ከክልላዊ ጉዳይ ወጣ ብሎ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ለመወሰን ኢህአዴግ ውስጥ የሌሉ ግን ደግሞ ትልቅ ሚና ያላቸው አጋር ፓርቲ የሚባሉት ከኦህዴድ አንፃር አሰላለፋቸውን መረዳት ጠቃሚ ነው፡፡ ያለነርሱ ይሁንታ አገራዊነት አይታሰብምና ፡፡ በሌላ በኩል ለሰብአዊነት እና ለፖለቲካ መስመር ሲባል መተባበር ያልተለመደበት የፖለቲካ ባህላችን ምርኮኛ የሆኑ የፖለቲካ ተዋናዮች በአንፃሩ ስለተሸለ ለውጥ ሲባል የቀደመ ዳተኝነታቸውን ተወት አድርገውታል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በፖለቲካ መርህ ላይ ብቻ የሚያጠነጥን አካሄድ ባልተከተሉበት ሁኔታ የተሸለ የፉክክር ፓለቲካ ቢመጣ እንኳን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅቡልነት የማያገኙ አስተሳሰቦች አሁን ማግኘት ችለዋል፡፡  ይህ ግን ዘላቂ አይደለም፡፡ የኦፒዲኦ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው አቅም እየታየ የሚከለስ ነው፡፡ ኢህአዴግን ማደስ ወይንም ማዳከም እስከቻለ ድረስ ብቻ ነው ኦፒዲኦ ከሌላው ወገን ድጋፍ የሚቸረው፡፡ ከዚያ ውጭ አንድ የክልል ፓርቲ እንጂ ምንም መሆን አይችልም፡፡ ከጨፌው እስከቀበሌ ያለውን መዋቅር ለተሸለ ፖለቲካዊ ለውጥ መጠቀም የሚችለው ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ስለሆነ እንጂ ህዝባዊ ፓርቲ ስለሆነ አይደለም፡፡ እንደክልል ፓርቲ ደግሞ በክልሉ ካሉ ሌሎች ፓርቲዎችም ሆነ በአገሪቱ ካሉ የፖለቲካ ሀይሎች ፈተና የሚጠብቀው ነጠላ ፓርቲ ነው፡፡
የኦህዴድም ሆኑ የተቀሩት ሶስት ፓርቲዎች የመጫወቻ ሜዳ የእናት ድርጅታቸው ሜዳ ነው፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ለግዜው ሌላ መዋኛ የላቸውም፡፡ ከገንዳቸው ውጭ ከውሀ የወጣ አሳ ናቸው፡፡ መዋኘት የለመዱትም ባደጉበት የዋና ህግ እና ገንዳቸው ውስጥ ነው፡፡ የመዋኛውን ሙቀት እና ሙላት መቆጣጠር የሚችሉትም በዚያው ውስጥ እስካሉ ድረስ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ከገዥ ፓርቲ ውስጥ አፈንግጦ የሚወጣ አካል ለተሸለ የዴሞክራሲ ሽግግር አጋዥ የሚሆነው በርእዮተ አለም አልያም በአካሄድ መለያየት ምክንያት ሲፈጠር እንጂ አንድ ብሄርን የሚወክል ፓርቲ በሚፈጥረው መሰንጠቅ አይደለም፡፡ የአሜሪካ አንፃራዊ የሆነ ቸልተኝነትም ለግዜው በኢህአዴግ ውስጥ ከመጫወት ውጭ አማራጭ የለም የሚለውን የሚያጠናክር ነው፡፡ ህዝባዊ ትግሉ እና ፓርቲው የህዝብ ፍላጎትን የማስጠበቅ አላማቸው እንጂ ሙሉ ጋብቻ መፈፀማቸው ተገቢ ስለማይሆን ፓርቲው በፓርቲ ሜዳ ይጫወት ህዝቡም ህዝባዊ ጫናውን በስሌት መቀጠሉን የጨዋታውም ህግ ግድ ይላል፤ እርከኑን ለጠበቀ ፖለቲካዊ ለውጥም የቀረበ ነው፡፡
Filed in: Amharic