>
5:13 pm - Sunday April 19, 8303

"ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ትመስለኛለች ..." (ተመስገን ደሳለኝ- ክፍል 2)

 ወዴት እየሄድን ነው? የሚለው ኮርኳሪ ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጎማ በህዝብ ግፊት የተነሳ ከፍጥነት በላይ መሽከርከር በመጀመሩ እና ከፖለቲካ መዘውሩ ተለዋዋጭ ባህሪይ አኳያ ጥያቄውን በደፋር እርግጠኝነት መመለስ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም መስመር ያልያዘ የአብዮት ጉዞ ላይ ነን፡፡ የአብዮት መልህቅ የት ላይ እንደሚዘረጋ አልለየለትም፡፡ለዓመታት የፖለቲካ ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ እንደሰራ ጋዜጠኛ የኢትዮጵያን ነገ በአምስት ቢሆንም ዕድሎች (scenarios) አስቀምጠዋለሁ፡፡
ቀዳሚው የቢሆን ዕድል ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አደገኛ ከመሆኑ አኳያ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ወደማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ የሶሪያ መከራ በሚስተካከል መልኩ የህዝብና መንግስት ብሎም ዘውጋዊ መስመርን የዘረጋ የለየለት ጦርነት ያሰጋናል፡፡ በነገራችን ላይ ቀዳሚው የቢሆን እድል እንዳያጋጥመን በፍርሃት ተሸብበን ቅጥ ያጣው አምባገነናዊ ሥርዓት ለተራዛሚ ጭቆና እንዲቀጥል መፍቀድ የተገባ አይደለም፡፡ ለዚህ ሁላችንም ዋጋ መክፈል ይጠበቅብናል፡፡ ከራሳችን በላይ ለማሰብ የምንገደድበት ጊዜ ላይ ምድረሳችንን ልብ ማለት ይገባናል፡፡
ሁለተኛው የቢሆን እድል ከቀዳሚው የቢሆን ዕድል በተለየ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነትን የመበታተን ጠርዝ የመገፋቷን ያኸል እኩል በሆነ ዕድል አገዛዙ እንደአውሬ የሚናከስበት ጥርሱ በህዝብ ተጋድሎ እየረገፈ በመሆኑ የአብዮቱን መስመር በጋራ አጀንዳ መቀንበብ እስከተቻለ ድረስ ታሪኳን ማደስ የምትችን፤ሁሉንም ዜጎቿን አቃፊና ደጋፊ የሆነች አዲሲቷ ኢትዮጵያን በማዋለድ ሕዝባዊ መሰረት ያለው ዴሞክራሲያዊ መንግስት በሕዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን እንዲወጣ ማድረግ የሚቻልበት መደላደል መፍጠር ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ሁለተኛው የቢሆን እድል ይኼ ስርዓት በታላቅ ህዝባዊ ቁጣ መዳከም ነፃነታችንን በቅርቡ እናዋልዳለን፡፡ ልቤም የሚያምነው ይኼንን ነው፡፡ እናደርገዋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ብዙ ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ከእስርና ስደት እንግልት ባለፈ ቁጥሩ የበዛ የሕይወትን የአካል መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ነው፡፡ የታሰርነውስ ተፈታን፤የሞቱት ግን ደግመው አይነሱም፡፡ ወጣቶች የወደቁለትን ዓላማ የምናሳካው የኢትዮጵያን የነፃነት ትግል በአዲስ ሥርዓት ማዋለድ ሲቻል ነው፡፡ ይኼን ለማድረግ ሰፊ ዕድል አለን፡፡ ሁለተኛውን የቢሆን ለማጠናከር፤ኢትዮጵያ ውስጥ ያለማቋረጥ እየታየ ያለውን ተቃውሞ በአገዛዙ ቅጥ ያጣ አምባገነንነት ከተከፋው ሕዝብ ባቻ አይደለም፡፡ ለራሱ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መዋቅራዊ ግንኙት መካከል ተቃርኖ ወደለየለት ጠርዝ እየገፋ ነው፡፡ የውስጥ መረጃዎቻችን እናቆያቸው እና አሁን በአደባባዩ ፖለቲካዊ አውድ ላይ እየታየ ያለው የአገሪቱ ብሔራዊ ድርጅት የአርስ በእርስ ግንኙነት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀኖን የሆን ዴሞክራሲያ ማዕከላዊነት አፈር ልሷል፡፡ በተለየ መልኩ ከዚህ በኋላ ሕዋሓት እና ኦሕዴድ ጌታና አሽከር ሆነው የሚቀጥሉበት ፖለቲካዊ ድባብ የተሰበረ ይመስላል፡፡ ኦሕዴድ ከአሽከሩነት ወጥቶ የኦሮሞን ህዝብ ለመወከል የጀመረውን መንገድ የሚያቆም አይመስልም በግንባሩ ውስጥ ጎልቶ እየታየ ያለው  የእርስ በእርስ መጠራጠርና አለመተማመን  ወደ መጠፋፋት ጠርዝ እየተገፋ ይገኛል፡፡ ይኽን ተከትሎ ውስጣዊ ሚስጥሮችና ድርጅታዊ መረጃዎች ያለማባራት እያፈተለኩ ነው፡፡ ጎራ መደበላለቅ የበዛበት የግንባሩ ፖለቲካዊ ዝማሜ የማዕከላዊ መንግስቱን ፖለቲካዊ መዋቅራዊ ኃይል ጉልበት አሳጥቶታል፡፡ በግንባሩ ውስጥ ጎልቶ የወጣው ፖለቲካዊ ተቃርኖ ለአብዮት ሞተር ለሆነው ህዝብ ተደማሪ ጉልበት እየሆነው ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ዋነኛው ጉዳይ አለ፡፡ እነርሱም የሕዝብ ሀይልና ግፊት እየበረታ የመጣው በመለኮታዊ ጣልቃገብነት ሳይሆን ሞት በማይፈሩት በብዙሀን ኢትዮጵያ (በተለየ መልኩ ለኦሮሞ፤ለአማራና ከፊል ደቡብ ኢትዮጵያ) ወጣቶች መስዋዕትነት ነው፡፡ ሕዝባዊ አብዮቱን መስመር በማስያዝ በአቃፊና ደጋፊ አጀንዳዎች መግራት ከተቻለ አዲስ አገር፤አዲስ ሥርዓትና ሕዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት ለማየት የማንታደልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለዚህ የቢሆን ዕድል መሳካት የለውጥ መስመሩን አቅጣጫ የሚገራ ከአካባቢው ስሜት የተሻገረ አገራዊ የአብዮት መዳረሻ አጀንዳ ሊኖር ይገባል፡፡
ወደ ሦስተኛው የቢሆን እድል ስንሻገር፤ግንባሩ ወደ ስልጣን ከመጣበቅ ሁነትና ድርጅታዊ ባህሉ ጋር ይያያዛል፡፡ ዐስራ ሰባት ዓመታት በትጥቅ፣ ሃያ ሰባት አመታት ደግሞ በመንግስትነት የቆየ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መዋቅር በብረት መዳፍ ጠቅልሎ የመያዝ ልምድ ያለው አምባገነን ድርጅት ነው፡፡ በሴራ የታጀበ ብልጣብልጥነት እና ብልህነት የድርጅታዊ ባህሉ መታያዎች ናቸው፡፡ ብልህነቱ ግን እኛን ከአስከፊ የድህነት አረንቋ ለማውጣት ዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ስርዓት በማብቃት ረገድ አይደለም፡፡ ብልህነቱ ጠቅማዊ የፖለቲካ ትስስር በመፍጠር የአገዛዝ ዘመኑን በማራዘም ላይ ነው፡፡ በመሆኑም በኦህዴድ በኩል ያለውን ፖለቲካዊ ፍንገጣና ከፊል የብአዴን አመራሮችን የኦሕዴድ ፈለግ ተከታይነት በስምዊ ሥልጣን ወደ ማዕከላዊ መንግስቱ በመሳብና ከግምት በላይ በሆነ የገንዘብ ጥቅም በመደለል ከዚህም አልፎ የሴራ ፖለቲካዊ በመጎንጎን ያጋጠመው ፖለቲካዊ ቀውስ በመፍታት ለተራዛሚ የጭቆና ዓመታት አዲስ ጉልበት የሚያገኝበት ፖለቲካ ዕድል ፍፁም የተዘጋ አይመስልም፡፡
ሦስተኛው የቢሆን እድል ሕውሓት የለመደው የሴራና የጥቅመኝነት ፖለቲካውን በማፈራረቅ በስማዊ ስልጣንና በጥቅም ትስስር በግንባሩ ውስጥ እየታየ ያለውን የለውጥ ኃይሎች ፍላጎት በመግታት ወደ ተለመደው የአዛዥ ታዛዥ ፖለቲካዊ ተዋረድ የዕዝ ሰንሰለት ለመክተት አይቦዝንም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሺፈራው ሽጉጤ የግልቢያ ሜዳ የሆነው ዲኢሕዴን አለለት ዲኢሕዴን ጥርሳቸው የወለቀውን የፖለቲካ አመራሮችን (አምባሳደር ተሸመ ቶጋ) ሳይቀር ከአውሮፓ የዲፕሎማት ሥራቸው ነቅሎ አገር ቤት በፓርቲ ስራ አስፈፃሚነት ማዕረግ እስከመትከል ድረስ ረዘም ያለ ርቀት ለመጓዝ ያለመ ይመስላል፡፡
አራተኛው የቢሆን ዕድል ደግሞ፤በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል የተለየ መከፋፈል ከመኖሩና የሁኔታዎች ቀጣይነት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ዕድሉ የጠበበ ቢሆንም ከኢህአዴግ ውስጥ ዕድሉ በሰፋ መልኩ ደግሞ ከሕወሓት ውስጥ የተወሰኑ ኃይሎች ተሰባስበው ወታደራዊውን ክንፍ ይዘው ወደ መፈንቅለ መንግስት ሊያመሩ የሚችሉበት ዕድል አላቸው፡፡ የሕውሓት አመራርና በሙሉ መዳፋቸው ከጨበጡ የማዕከላዊ መንግስት ኃይል በመጠኑም ቢሆን መገፋት (ቦታ መስጠት )የማይፈቅዱ በመሆን አሁን ባለው ሁኔታ ተቃርኖ እያየለ ከቀጠለ መፈንቅለ መንግስት የተዘጋ እድል ነው ማለት አይቻልም፡፡ ጥንቃቄ ካተደረገ በስተቀር ፖለቲካዊ ስልጣንን ከበረሃ ተጋድሎ ጋር አስተሳስረው የሚያዩት የሕውሓት ነባር አመራሮች ተገንጥለው በመውጣት ከፊል የግንባሩን ተንሸራታች  አመራሮች በማቀፍ ወታደራዊ ኃይሉ ክንፍ መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂዱ ይችላሉ፡፡
እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር፤በእኔ እምነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መፈንቅለ መንግስት ሊያደርግ አይችልም፡፡ሁላችንም እንደምናውቀው መከላከያ ኃይሉን የሚመሩት ጀነራሎች ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው የጦፈ ንግድ ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡ ለፖለቲካ ዝንባሌ በጣም ሩቅ ናቸው፡፡ ከትጥቅ ትግል መጥተው ትምህርታቸውን በለብለብ የርቀት ትምህርት ‹‹ተከታትለው›› የወረቀት ረኀባቸውን በመጠኑ ካስታገሱ በኋላ፤በአለም ታዋቂ ከሆኑ ወታደራዊ አካዳሚዎች ወታደራዊ ሳየንስ ያጠኑት እነ ሜጀር ጄነራል ፋንታ በላይ፤መርዕድ ንጉሤና ደምሴ ቡልቱ ወዘተ.. የመሩትን የኢትዮጵያን ሠራዊት አፍርሰው በሌላ በመተካት ‹‹እየመሩት›› ይገኛሉ፡፡ አንድ አንድ ሰዎች እንደሚሉት ጀነራል እከሌ፣ ኮሎኔል እንትና መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉ ይችላሉ የሚለው ግምት ነባራዊ አውድ ያላገናዘበ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ከንባብ ተሞክሮ እንደምረዳው መፈንቅለ መንግስት በባህሪው የወታደራዊ ሳይንስ ዕውቀትና የሕዝብ አስተዳደር (የሕዝብ ግንኙነት) ዕውቀትና ክህሎትን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ የጀነራሎች አቅም ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ እነዚህ ጀነራሎች አገር የመምራት ስነ ልቦናዊ ዝግጅትና አዕምሯዊ ብስለት የሌላቸው በመሆኑ በቀጥታ ራሳቸውን ችለው እንደ መንግስቱ ንዋይ የ1953 መፈንቅለ መንግስት፣ እንደ 1981 የፋንታ በላይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ በጭራሽ አያደርጉትም፡፡ የጠመንጃ እንጂ የዕውቀት ኃይል የላቸውም፡፡ ምናልባት የኢሕአዴግ ውስጥ በተለየ መልኩ ሕውሓት ውስጥ ነጥሮ የሚወጣ አምባገነናዊ ቡድን የጀኔራሎቹን ክንድ ይዞ የዳግማዊ ምኒሊክ ቤተ መንግስት መንገድ ጠራጊ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ የክልሎችን የፖለቲካ አመራር ሚና ሽባ ያደረገው የአሁን የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ  አያያዝም በግንባሩ ውሰጥ ያቆጠቆጡ የለውጥ ኃይሎችን ለመድፈቅ፣ ሁኔታዎች ከከፋም የአዝጋሚ መፈንቅለ መንግስት ጥንስስ መጣያ አድርጌ እወስዳለሁ፡፡
ወደ መጨረሻው የቢሆን እድል ስንሻገር በአምስተኛው የምናገኘው የዓለም አቀፍን በተለይም የምዕራቡን ዓለም ግፊትና ጫና የተንተራሰ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ ለተወሰኑ ተቃዋሚ ኃይሎች ሥልጣን በማጋራት የጊዜአዊ መንግስት መሥርቶ ትውልዱ ሊወድቅለት የነበረውን የሥርዓት ለውጥ ዓላማ በመድፈቅ ሥልጣኑን ሊያስቀጥለው ይችላል፡፡
Filed in: Amharic