>
2:32 pm - Friday May 20, 2022

ግድያ ካልቆመ ሞት አይቆምም!  (ኡስታዝ አቡበከር አህመድ)

በሞያሌ መሳሪያ ባልታጠቁና ምንም አይነት እንቅስቃሴ ላይ ባልነበሩ ንፁሀን ላይ የተካሄደው ግድያ በጥብቅ የሚወገዝና ምንም ማስተባበያ ሊቀርበለት የማይችል ነው፡፡ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወትን ለመቅጠፍ ‘ስህተት’ የሚል ምክንያት ማስቀመጥ ለአዕምሮም የማይገጥም ለአንድ ትልቅ የአገር የመከላከያ ሰራዊት የአሰራር ሰንሰለትም የሚመጥን አይደለም፡፡ መንግስት ስህተቴን ተቀብያለሁ የሚለው ትርጉም የሚሰጠው በጎ እርምጃ ሲያስከትል በመሆኑ ህዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች ፍትሀዊ ምላሽ መስጠትና የመንግስት አካላት ላጓደሉት ፍትህ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ብቸኛው መፍትሄ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ስህተትን መቀበል ብቻውን ከሌላ ስህተት የሚያድን አይደለም፡፡
_
አላህ (ሱ.ወ) ሰማያት እና ምድርን የሚያስተናብረው በፍትህ እና ሁሉም ሂደቶች በተስተካከለ ፍሰት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ ነው፡፡ ልክ በዚሁ መልኩ አላህ (ሱ.ወ) በምድር ላይ በህዝቦች እና በህዝቦች ላይ በተሸሙት ላይም ፍትህን እና የተስተካከለ መስተጋብርን ማየት ይሻል፡፡ የበደል፣ ኢፍትሀዊነት፣ ቀውስ እና አለመረጋጋት በህዝቦች ላይ መንሰራፋት ከአላህ ፍላጎትና ከህዝቦች በሰላም የመኖር ዋስትና ተቃራኒ ናቸውና ከፍተኛ ሊባል በሚችል መልኩ የሚወገዙ ናቸው፡፡
በአንድ አገር ውስጥ የተረጋጋ የህዝቦች መስተጋብር እንዲሰፍን ሁሉም ኃላፊነት ቢኖረውም የገዢዎች እና የአስተዳዳሪዎች ኃላፊነት ግን ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በየእለቱ የምንሰማቸውና የምናያቸው ጉዳዮች ስለህዝባችን እና አገራችን እንድነሰጋ እንጂ ተስፋ እንድናደርግ የሚያደርጉ እየሆኑ አይደሉም፡፡ የፍትህ እና የመብት ጥያቄ ያነሱ ህዝቦች በፍትህ ሊዳኙ ሲገባ መንግስት ችግሬ ናቸው ብሎ የተቀበላቸውን መሰረታዊ ክፍተቶችን ከመሙላት ይልቅ ተደጋጋሚ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡
በየትኛውም አካባቢ ያለአግባብ የሚጠፋ የሰው ልጅ ህይወት በሁሉም የሰው ልጆችና በሁሉም አካባቢ ያንዣበበ የሞት አደጋ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሞት ደግሞ ሊቆም የሚችለው ገዳይ መግደሉን ሲያቆም ነውና መንግስት መሳሪያን በዜጎች ላይ አማራጭ አድርጎ መቁጠርን እስከመጨረሻው እንዲያቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ህዝባችንን እና አገራችንን እንዲጠብቅልንም እማፀነዋለሁ፡፡
Filed in: Amharic