>
5:13 pm - Saturday April 19, 5502

ለማ ኦህዴድ ክልላቸውን እያስተዳደሩ አይደለም መፈንቅለ ድርጅት ተካሂዷል!!! (መሳይ መኮንን)

ጦርነት ታውጆበታል። አስቸኳይ ጊዜ ተደንግጎበታል። ባለስልጣናቱ መናገር አይችሉም። ከተናገሩ ይታሰራሉ። የታሰሩትን የሚከታተላቸው የለም። ዋናዎቹም በትግራይ ደህንነቶችና በሳሞራ ቅልብ ወታደሮች ዓይን ስር ናቸው። መፈናፈኛ ለጊዜው የለም። ድምጻቸው ጠፍቷል። የትግራይ ገዢ ቡድን ባለስልጣናት በየመድረኩ ሲያስካኩ ሲፎክሩ፡ የለማ ኦህዴድ ሰዎች ግን ትንፋሻቸው እንኳን የለም። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን ድረስ ያለው የለማ ኦህዴድ መዋቅር በትግራይ ደህንነቶች እየተበረበረ አመራሮቹ በኮማንድ ፖስቱ ሰራዊት እየታደኑ ወደ ግዞት እስር ቤቶች እየተወረወሩ ናቸው። የአቶ ለማን የተስፋ መልዕክቶችና ቆራጥ ንግግሮች መከታ ጋሻ አድርገው ለለውጥ የተነሱ ባለሀብቶችም በአባዱላና በአቶ ድንቁ ጠቋሚነት እየተለቀሙ ወደ ማዕከላዊ በመወሰድ ላይ ናቸው።
የትግራዩ ገዡ ቡድን ጥድፊያ ላይ ነው። ጊዜ መስጠት አልፈለገም። እነለማንና አብይን በስብሰባና ግምገማ አፍኖ መዋቅራቸውን በማወላለቁ ዘመቻ ላይ ተጠምዷል። በመካሄድ ላይ ያለውን የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በተመለከተ ከባልደረቦቼ ኤርሚያስ ለገሰና ምናላቸው ስማቸው ጋር በኢሳት እፍታ ፕሮግራም ላይ ውይይት ባደረኩበት ጊዜ የተገለጠልኝ እነ ለማ መታገታቸውን ነው። መግለጫ መስጠት አይችሉም። ክልላቸውን እያስተዳደሩ አይደለም። ካቢኔያቸውን መገናኘትም አይችሉም እየተባለ ነው። ከጨዋታ ውጪ ተደርገዋል። ኤርሚያ ለገሰ መፈንቅለ ድርጅት ተካሂዷል ይላል። ውይይቱን ብታዳምጡ አትከስሩም። በማዳመጥ ለምታጠፉበት ጊዜ የሚቆጫችሁ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ማስፈንጠሪያውን ከዚህ ጽሁፍ ግርጌ አኖርላችኋለሁ።
እናም የእነለማ ኦህዴድ በጅቦች ተከቧል። ከህግ ውጭ፡ አሰራሩ በማይፈቅድ ሁኔታ የትግራዩን ገዢ ቡድን ከሞት ለማዳን በቀቢጸ ተስፋ የተሰለፉት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ነባር አመራሮች ከያሉበት ተለቃቅመው ገብተዋል። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አይደሉም። ምንም ውስጥ ምንም የላቸውም። ነገር ግን ጊዜው ቀውጢ ነው። የሞት ሽረት ትግል የሚካሄድበት ነው። 11ኛው ሰዓት ላይ የሚገኘውን የትግራይ ገዢ ቡድን ህልውና ለማትረፍ መረባረብ አለባቸው። የሚቧጠውን ቧጠው፡ የሚነከሰውንም ነክሰው ማፊያ ድርጅታቸውን ለማዳን ከስብሰባ አዳራሽ ገብተዋል። ይሉኝታን ከነመፈጠሩም የማያውቁት፡ ህሊናቸውን ገና ተከዜን ተሻግረው ሲዘልቁ በእንዶድ አጥበው የተገላገሉት፡ ከዕውቀትም፡ ከዕውነትም የተጣሉት፡ የዘመኑ ጎልያዶች፡ ተጠራርተው ተሰይመዋል። የመጨረሻ ሙከራ ነው። ይህ ስብሰባ ሁሉ ነገር ይለይለታል። ጀጋኑ፡ ተጋዳላይ፡ ወዲዎች!
እርጅናና የአልኮል ሱስ የተንኮልና ሴራ አቅሙን ያላዳከመው ስብሃት ነጋ ያጉረጠርጣል። የማይድን በሽታ የሚያሰቃየውና በመድሃኒት ጉልበት ቆሞ የሚሄደው ስዩም መስፍን ለዚህ ስብሰባ የሚሆን አቅም አላጣም። ቴድሮስ ሀጎስ ከመቀሌ  ገብቷል። አለቃ ጸጋዬ በርሄ ከቴልሃቪቭ በሮ መጥቷል። የስብሃት ነጋ ምርኩዝ ጠባቂ የሚባለው አባዲ ዘሙም አልቀረም። የሙስናው ባላባት ወዲ አባይ ጸሃዬ ፊት ወንበር ላይ ጉብ ብሏል። እነዚህ ስድስት የትግራይ ገዢ ቡድን ነባር አመራሮች በህውሀትም ሆነ በኢህ አዴግ ስራ አስፈጻሚ ውስጥ የሉም። ግን ተሰይመዋል። በወሳኙ ስብሰባ ላይ ወንበር ይዘው ተቀምጠዋል። ኤርሚያስ እነዚህን ሰዎች በዱር እንስሳ መስሏቸዋል። የትግራይ የበላይነት ላይ አደጋ የደቀኑትን ሰልቅጠው ለመብላት የተሰለፉ አውሬዎች።
ስብሰባው ሀገ ወጥ ነው። የእነዚህ ሰዎች መገኘት ብቻውን ጨዋታውን ያፈርሰዋል። ሳይጀመር ውጤቱ የታወቀ ስብሰባ ላይ እነለማ ምን ይሰራሉ? ምን ይጠብቃሉ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በእርግጥ ጥያቄው ተገቢ ነው። እነዚህ የትግራይ ቡድን ነባር አመራሮች የተገኙት ለምን እንደሆነ ይታወቃል። ከየብሄራዊ ድርጅቶቹ ዘጠኝ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ በሚሳተፉበት ስብሰባ ላይ ያለስልጣናቸው፡ ያለወንበራቸው ወንበር ይዘው የተቀመጡት እነስብሃት ምን እያሸተቱ እንዳለ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ለማጣፈጫነት ከሌላውም ድርጅት ነባር የሚባሉ አመራሮች መግባታቸው አልቀረም። እንደነካሱ ኢላላ ዓይነት ህወሀትን በጉርምስናው ዘመኑ የተጠመቀ የደኢህዴን አመራርም በስብሰባው ላይ ተገኝቷል። ዓላማው የእነስብሃትን መገኘት ምክንያታዊ ለማድረግ ነው። ደግሞም ካሱ ኢላላ ከስብሃት በላይ ህወሀት መሆኑን ለሚያውቁ የቅርብ ሰዎች ጉዳዩ በሚገባ ግልጽ ይሆንላቸዋል።
እንግዲህ እነስብሃት ተሰባስበው የገቡበት ስብሰባ በዝግ እየተካሄደ ነው። የትግራይ ገዢ ቡድንን ህልውና በማይናወጥ መሰረት ላይ ተክሎ ዳግም የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦና ጨፍልቆ ለመግዛት የሚያስችል አቋም ላይ ለመድረስ እንደሆነ አያያዙ ይመሰክራል። ከአዳራሹ ውስጥ እነስብሃት የለማን ቡድን ወጥረው ይዘዋል። ከአዳራሽ ውጪ ኮማንድ ፖስቱ የለማን መዋቅር እየመታ ነው። እነለማ ከውስጥም ከውጭም እየተጠቁ ናቸው። የትግራይ ገዢ ቡድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የፈለገበት ምክንያት ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍንትው ብሎ የታየበት ሆኗል። በረከት ስምዖንን ጨምሮ መላው የደኢህዴን አመራር እነለማ ላይ የጭቃ ጅራፍ እየሰነዘረ እንደሆነም ይሰማል። እነስብሃት ሂሳብ ሰርተው የገቡበትን ትወና በረከት፡ ካሱና ሌሎች በሚገባ እየተጫወቱት ነው።
የአጋች ታጋች ድራማው ቀጥሏል። እነለማ በአውሬዎች ተከበዋል። ጥያቄው በዚህ ሁኔታ እነለማ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚል መሆን አለበት። ምን ምርጫ አላቸው? ከካቢኔው የተቆራረጠ፡ አፉ የተሸበበ፡ መተንፈስ ብቻ የተፈቀደለት የለማ አመራር በዚህ ወቅት ላይ ተስፋው ማን ነው? በእርግጥ ከስብሰባው አዳራሽ ምን እየተካሄደ እንዳለ ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም። ሽፈራው ሽጉጤ የሚባል ሰው ብቅ ጥልቅ እያለ ከሚወረውራት ቁራጭ መረጃ በቀር ሌላ ነገር የለም። ጭምጭምታዎች የሚያመላክቱት እነለማ በተከላካይነት መስመር ላይ መሆናቸውን ነው። አቅም እያጡ የመጡ ይመስላል። ጓዶቻቸውን ከጅቦች መንጋ ማስጣል ያልቻሉት እነለማ የታዬ ደንደአ፡ የአምስት ከፍተኛ የኦህዴድ አመራሮች እስር ላይ ዝምታቸው የሚነግረን ያሉበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ መሆኑን ነው።
በእርግጥ እነለማ በመጨረሻ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናቸው። ሁለት ምርጫዎች ግን አላቸው። አንደኛው የአውሬዎቹን የሚያፏጭ ጥርስ አንበርክኳቸው፡ እጅ ሰጥተው ኦህዴድን ወደ ቀድሞው የአሽከርነት ዘመኑ በመመለስ በአሳፋሪ የታሪክ ገጽ ላይ ስማቸው ትተው ማለፍ ነው። ሁለተኛው ምርጫ የአወሬዎቹን ጥርስ ለማራገፍ ቆርጦ የተነሳውን ህዝባቸውን ተስፋ አድርገው መፈንቅለ ስብሰባ ከተካሄደበት አዳራሽ ውልቅ ብሎ መውጣት ነው። ሁለቱም ምርጫዎች ዋጋ ማስከፈላቸው አይቀርም። የመጀመሪያው ምርጫ ለእነለማ የቁም ሞት ነው። የእነስብሃትን የተሳለ ቢላዋ በመፍራት በተዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ ዘው ብሎ መግባትን ምርጫቸው ካደረጉ የእነለማ ታሪክ በክህደት መዝገብ ላይ ሰፍሮ ሲወቀሱ ይኖራሉ። እየሰጠመ ካለው መርከብ ጋር አብረው ሰጥመው ከትውልድ ትውልድ እየተረገሙ ይነሳሉ።
ምርጫቸው ሁለተኛው ከሆነ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ በመክፈት ሲወደሱ ይኖራሉ። ህዝባቸው ተነስቷል። የትግራዩን ገዢ ቡድን እያንቆራጠጠ ነው። በማያቋርጥ ህዝባዊ ማዕበል እያላጋው ነው። ይህ የህዝብ ሃይል እነዚህን የዘመኑ ጉግማንጉጎችን ጠራርጎ የታሪክ ቆሻሻ በምድረግ ሊቀብራቸው ከጫፍ ደርሷል። እነለማ ሁለተኛውን ምርጫ ከተከተሉ የሚከፍሉት ጊዜያዊ ዋጋ ነው። ምናልባትም እስር። ይሄው ጓዶቻቸው እየታሰሩም አይደል?! እነታዬ ደንደአ የታሰሩት ሰርቀው አይደለም። ነፍስ አጥፍተው አይደለም። ለቆሙለት መርህና የህዝብ ወገኝተኝነት እስከመጨረሻው ቃላቸውን በመጠበቃቸው ነው። ታዲያ እነለማ ምን ያስፈራቸዋል? እነታዬ እየከፈሉ ካሉት መስዋዕትነት በላይ ምን ዋጋ ሊከፍሉ እጅ ይሰጣሉ?
ይህ ሳምንት የለማ ኦህዴድ ቁርጡ ይለይለታል!!!!!
Filed in: Amharic