>

ተዋዶ ተዋልዶ የሚኖረው የሀረርጌ አማራ እንዲህ ነው!! (ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ)

እኔ “አማራ የለም” ከሚሉት ጋር አልስማማም፡፡ “አማራ” የሚባል የራሱን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ ያለው ትልቅ ብሄር አለ፡፡ የአኗኗር ብሂሩ እንደአካባቢው ይለያያል፡፡ ታዲያ እኔ በደንብ የማውቀው እዚሁ ሀረርጌ ውስጥ ከኔ ጋር ለዘመናት ሲኖር የነበረውን የሀረርጌ አማራ ነው፡፡
በጽሑፎቼ በአብዛኛው የምዳስሰው የምሥራቁን የሀገራችንን ክፍል ነው፡፡ በእስከ ዛሬው ቆይታዬ ስለ ሀረሪ እና ስለ ምሥራቁ ኦሮሞ በስፋት ጽፈናል (ይኸው! እንደ ጃንሆይ “እኛ” ማለታችንን ጀመርን እንግዲህ!!)፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለሀረርጌው አማራ እንድንጽፍ ዘንድ ልባችን ቆስቁሶናል፡፡ መነሻ አለው፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ሐዘን ቤት ሄደን ነበር፡፡ እዚያ ተሰይመን ያገኘነው አንድ “መለሳይ” (ጨዋታ አዋቂ) ታሪካዊና ባህላዊ ጉዳዮችን በመጽሐፍና በመጣጥፎች እንምንጽፍ ሰምቶት ነው መሰለኝ “አቦ ሸጎዬ ኒፌታ” በማለት ጠየቀን፡፡ “ሸጎዬ ትወዳለህን?” ማለቱ ነው (“ሸጎዬ” የሀረርጌው ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን ነግረናችሁ ነበር)፡፡
“አዎን” አልነው ጓዳችንን፡፡ ሰውዬውም ጀመረው የሸጎዬውን ግጥም በኦሮምኛ!!
Afaan Amaaraatiin dhadhaan qibee qibee (በአማርኛ ቋንቋ “ደዳ” ቅቤ ነው)
Nuti wal-jaalannaan amba maaltu dhibee (እኛ ብንዋደድ ሌላው ምን ጨነቀው)
በድንኳኑ ያለው ጀመዓ በሳቅ ፍርስ አለ፡፡ እኛ ደግሞ ሌላ ነገር ልንሰማ ልባችን ስቅል አለ፡፡ “አቦ እስቲ ቀጥልበት ጓድ” አልነው፡፡ ሰውዬውም አላቅማማም፡፡
Galamsottin deemaa deebbii na hinyaadinii (ወደ ገለምሶ እየሄድኩ ነውና ስመለስ ጎራ እላለሁኝ)
Warra keessan dhufee sareen na hinynaatinii (ወደናንተ ቤት ስመጣ ግን ውሻችሁ እንዳይበላኝ)
ሌላ የሳቅ ጎርፍ!! እኛ ግን የገለምሶ ስም በመጠራቱ እኛነታችንን ትተን “እኔ” ሆነን ቁጭ አልን፡፡  “እኔ”ም ውስጥ ውስጡን  ደነገጥኩ፡፡ “ከገለምሶ መሆኔን ሁሉም ሰው አውቆታል ማለት ነው?” እያልኩ ወደ ግራና ወደ ቀኝ አማተርኩ፡፡ ደግነቱ በድንኳኑ ያለው ጀመዓ ልቡ ከሰውዬው ጋር እንጂ እኔ ጋ አልነበረም፡፡
ጀመዓው “ሦሥት ይሁን” እያለ ሰውዬውን ነካካው፡፡ ሰውዬውም በህይወቴ ከሰሟኋቸው ተአምራዊ ግጥሞች አንዱ የሆነውን እንዲህ በማለት አወረደው፡፡
Halasnaa jijigoo haaloo ganda barii (የጅጅጋው ውቃቢ የገንደ በሪ አዋጅ)
Maazajaan haammatee kan duriin gargarii (ማዘዣው ጠንክሯል እንደ ድሮው አይበጅ)
Nama sinjaalatiin “imbii… “ashaffarii” (ያልወደደሽን ሰው አሻፈረኝ እምቢ በይ)
Nuura samii kessaa yaa Shamsal-Qamarii (አንቺ “ሙሉ ጨረቃ” ያለሽው በሰማይ ላይ)
የሳቅ ነጎድጓድ ድንኳኑን አዳረሰው፡፡ ስቄ ማቆም አቃተኝ፡፡… (ቂቂቂቂቂቂቂቂ)
ይህ ሰው በብሄሩ አማራ እንጂ ኦሮሞ አይደለም፡፡ ነገር ግን እድሜ ልኩን ሲኖር የነበረው ከኦሮሞዎች ጋር በመሆኑ የኦሮሞን ባህል ልቅም አድርጎ ይዞታል፡፡ በዚህ ሰውዬ አስታዋሽነት ሌሎች ደጋግና ልብ ብርቱ ሀረር-በቀል የአማራ ወዳጆቻችንና የሀገር ሀብቶች አንድ በአንድ ወደ አዕምሮዬ መጡ፡፡ እነ ሚሊዮን ለማ፣ ሚሊዮን አየለ፣ መምሬ ይፍሩ፣ መምሬ ሙላቱ፣ ረ/ፕሮፌሰር ሰይፉ መታፈሪያ፣ ወጋየሁ ደግነቱ፣ ቢተው ወርቁ፣ ሁሉም ታወሱኝ፡፡ ምን ይሄ ብቻ!! ያ ጣፋጭ የልጅነት ጊዜያችንም እንደገና ወደ ተመልሶ መጣ፡፡
*****
“ኦነግ እና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት” የሚለውን ተከታታይ ጽሑፍ አንብባችኋል? አዎን!! ጦርነቱ የተካሄደው የአያቴ መንደር በሆነው በልበሌቲ (ጭረቲ) ነው፡፡ ውጊያው አብቅቶ በሶስተኛው ቀን (ቅዳሜ ሰኔ 20/1984) “የሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ልጆችና ዘመዶች መትረፋቸውን ማረጋገጥ አለብን” በሚል በርካታ ሰዎች ወደ መንደሩ መጥተው ነበር፡፡ በቅድሚያ ወደ ሰፈሩ የገቡት ደግሞ “ገቦ” በሚባለው ተራራ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ነበሩ (ገቦ ከበልበሌቲ በስተሰሜን ምዕራብ በኩል ነው ያለው፤ ርቀቱ አራት ኪሎሜትር ያህል ይሆናል)፡፡ እነዚያ ሰዎች በእጃቸው እንቁላል፣ ዶሮ፣ የሆጃ ቅጠል፣ ወተት፣ ወዘተ.. እየያዙ ነበር የመጡት፡፡ እናም ብዙዎቹ በሰፈሩና በነዋሪዎቹ ላይ ጉዳት አለመድረሱን ሲያዩ የደስታ እምባ ነበር የረጩት፡፡
ከነዚያ ሰዎች መካከል አንዱ “እንግዳ” ይባላል፡፡ እንግዳ የሼኽ ሙሐመድ ረሺድ የልጅ ልጅ መሆኔ ሲነገረው ወደራሱ አስጠጋኝና ስለከተማው ይጠያይቀኝ ጀመር፡፡ እኔም በከተማው ስለነበረው ግርግር ከነገርኩት በኋላ “ለምንድነው እንዲህ ተሰብስባችሁ መጣችሁት?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ “እንዴ! ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ከመሞታቸው በፊት ልጆቼንና ሰፈሬን አደራ ብለውናል እኮ፤ እሳቸው በነበሩበት ዘመን የዋሉልን ውለታ ቀላል መሰለህ? የኛ ዳኛ፣ የፍርድ ቤት ጠበቃ፣ ሐኪማችን፤ ገላጋይ ሽማግሌ፣ አስተማሪ፣ ይሄንን ሁሉ ነበሩ፡፡ እኛ ራሳችን የምናርስበት መሬት ጥንት የርሳቸው ርስት ነበር እኮ!! “ያለኝ መሬት ይበቃኛል” ብለው ግማሽ ጋሽ ሙሉ ለኛ አከፋፍለው ሰጡን” አለኝ (በቅርቡ እንደሰማሁት “እንግዳ” አርፏል፤ ነፍሱን ይማረውና)፡፡
*****
  እንዲህ ሐቁን የሚናገር ነው የሀረርጌው አማራ፡፡ ጊዜ ተለወጠ ብሎ የማይገለበጥ፤ መሬት ላይ ያለውን ሐቅ የማይክድ ቀጥተኛ ህዝብ ነው፡፡ ከሌላው ጋር መኖርን በተግባር ያስመሰከረ፣ የሌላውን ባህልና ወግ እንደራሱ የሚወድ፣ ለሌላው መብት ጭምር የሚቆረቆር፣ አስመሳይነት የሌለበት እውነተኛ ህዝብ ነው፡፡ ይህንንም በተግባር አሳይቷል፡፡
ታዲያ የሀረርጌ ኦሮሞም ዋዛ አይደለም፡፡ ለአማራው ወገኑ ያለውን አክብሮትና ተቆርቋሪነት በተለያዩ ጊዜያት አስመስክሯል፡፡ ለዚህ ምሳሌ ለመስጠት ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም፡፡ ከላይ የጠቀስኩትን የሸጎዬ ግጥም የለቀቀብንን ሰውዬ ውሰዱት፡፡ ትክክለኛ ስሙ ግርማ ታደሰ ነው፡፡ አቶ ግርማ በ1968 ከሀረር መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም (ቲቲአይ) ተመርቆ በጃርሶ ወረዳ (ኤጄርሳ ጎሮ ከተማ አጠገብ) በመምህርነት ሙያ ያገለግል ነበር፡፡ ከርሱ ጋር የሚሰራው ሌላኛው መምህር ኢብራሂም ሙሳ ይባላል፡፡ ኢብራሂም ሙስሊም ኦሮሞ ነበረ፡፡ ሁለቱ ሰዎች በ1970 በአንዱ ቀን በስራ ላይ እያሉ ወራሪው የሶማሊያ ጦር በድንገት ወደ ጃርሶ ገባ፡፡
የሶማሊያ ጦር በጊዜው ሲቪሎችንም ያጠቃ የነበረ ሲሆን በጥቃቱ ቀዳሚ ዒላማ ያደረገው ደግሞ ክርስቲያኖችን በተለይም የአማራ ተወላጆችን ነበር፡፡ እንግዲህ ግርማ ክርስቲያን የአማራ ተወላጅ ነውና ያለምንም ጥፋቱ “የመንግሥቱ ሰላይ” ተብሎ ታሰረ፡፡ በአጠገቡ የነበረው የስራ ጓደኛው ኢብራሂምም “አረ ወላሂ! ይሄ ሰውዬ ሰላይ አይደለም፤ እኔና እርሱ ልናስተምር ነው ከዚህ የመጣነው፤ ምንም ጥፋት የሌለው ሰላማዊ ሰው ነው” በማለት ተከራከረለት፡፡ በዚህ የተበሳጩት የሶማሊያ ጦረኞች “አንተን ምን አገባህ” በሚል ኢብራሂምንም አሰሩት፡፡ ሁለቱም በአንድ ላይ እንደ ጦር ምርኮኛ ተወስደው ለአስራ አንድ ዓመታት ታሰሩ (ሁለቱ ሰዎች በ1981 ነው የተለቀቁት)፡፡
ኢብራሂምና ግርማ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ወደ ሀረር ከተማ ተመልሰው ኑሮአቸውን ተያያዙት፡፡ ሁለቱም በአንድ አካባቢ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ሁለቱም በተቀራራቢ ወቅት ሚስት አገቡ፡፡ በቅርቡ የሁለቱም ልጆች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል፡፡
*****
የሀረርጌው አማራ ጣጣ አያውቅም ይባላል አይደል?…. እውነት ነው፡፡ ነገር አያካብድም፡፡ ሁሉንም ነገር ቀልል አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ ምሳሌ እንስጣችሁ!!
ደሳለኝና ምንተስኖት የጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተማ ነዋሪ ነበሩ፡፡ በቦታ ጉዳይ ተጣሉና ተካሰሱ፡፡ ከሳሽ ምንተስኖት ሲሆን ተከሳሽ ደሳለኝ ነው፡፡ እናም ሁለቱም በቀጠሮው እለት ወደ ችሎቱ ገቡ፡፡ ደሳለኝ ምንተስኖትን ገና እንዳየው “አቦ! አንድ አምስት ሺህ ብር ብለቅብህ ያንን ቦታ አትተውልኝም” አለው፡፡ ምንተስኖትም “አቦ ይበቃኛል፤ አሁኑኑ ፈርምልሃለሁ” ብሎት ነገሩን ወዲያው አቆመው፡፡ በችሎት ውስጥ ተሰይሞ የሚያስተውላቸው ዳኛ “አንድ ጊዜ! አካሄድ መጣስ የለባችሁም፤ በመዝገብ የተከፈተ ክስ እንደዚህ አይዘጋም” ሲላቸው ምንተስኖት ወደ ዳኛው ዞሮ “አቦ ጣጣ አታብዛብን አቦ!! እኛ ተስማምተናል” አለው አሉ፡፡ ምንተስኖት ከሳሽነቱን ትቶት ለተከሳሹ ተከራከረለት (ቂቂቂቂቂቂ)፡፡
——
አፈንዲ ሙተቂ
ሀረር-ምሥራቅ ኢትዮጵያ
ታሕሳስ 8/2007
Filed in: Amharic