>

አንድን ቋንቋ በሁለት ፊደል (በሳባ እና በላቲን) ማስተማሩ ለማግባባት ወይስ ግራ ለማጋባት!?! (በላይነው አሻግሬ)

ምሁራን ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጻፉት የተባለውን ደብዳቤ በተለያዩ ገጸ-ድሮች ተደምሮ ተቀንሶ አየነው፡፡ በዚህ ላይ ተመርኩዘው አረጋዊው የቀድሞው ርዕሰ-ብሔር የመቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የጻፉትን የልመና ደብዳቤም ተመልከተነዋል፡፡ አጃኢብ ነው፡፡
መንደርደሪያ፡- በሕግ ትምህርት ፍሬ ነገር (fact) የሚባል መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ ፍሬ ነገር ማለት በስሜት ህዋሳት ሊታወቅ የሚችል ማናቸውም ነገር፣ የነገሮች ሁኔታ፣ ወይም ደግሞ የነገሮች ዝምድና (ግንኙነት)፣ እና ማናቸውም የአእምሮ ሁኔታ ማለት ነው፡፡ አጠር ያለ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡ “አበበ ወደ ከበደ ድንጋይ ወረወረ፡፡” ይህ ድንጋይ መወርወር ፍሬ ነገር ይባላል፡፡ ፍሬ ነገር አንድ ክርክር እልባት እንዲያገኝ መጣራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ፍሬ ነገር በትክክል ካልተለየ ወይም ከተጣመመ ፍርድ ይዛባል፡፡ ለምሳሌ አበበ ወደ ከበደ የወረወረው ኳስ ነው ብንል ፍሬ ነገሩ ተስቷል፡፡ ይህንም የፍሬ ነገር ስህተት (mistake of fact) እንለዋለን፡፡ ፍሬ ነገር ከተሳተ የክርክሩ ውጤት እንዳልሆነ ይሆናል፡፡
ይህን ጉዳይ ያነሳሁበት ምክንያት ሰሞኑን ምሁራን ለአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ ኦሮሞኛ በአማራ ክልል ት/ቤቶች እንዲስጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጻፉ የተባለውን ካየሁ በኋላ ነው፡፡ በመሠረቱ ይህ ደብዳቤ መጻፍ የነበረበት ለአቶ ለማ እንጅ ለአቶ ገዱ አልነበረም፡፡ ቢያንስ በአንድ ዋና ነጥብ ላይ እነዚህ ምሁራን ዋና ፍሬ ነገር ስተዋል፡፡ በባእዳን ፊደል መጻፍ ያለውን ውርደት ለአማራ ክልል አይደለም ማስረዳት ያለባቸው፤ በአማራ ክልል በባእድ ቋንቋ የሚጻፈው የባእድ ቋንቋ የሆነው እንግሊዝኛ ብቻ ነው፡፡ የግእዝ ፊደላትን ሳይሸራርፍ ጠብቆ እየተጠቀመ ካለው ሕዝብ አንደኛው አማራ ክልል ነው፡፡ የራሱን ፊደላት እየተጠቀመ ያለን ክልል፣ ስለማያውቀውና ስለማይጠቀምበት ባእድ ፊደል ነውርነት ልምከርህ ማለት በጣም አስቂኝ ነው፡፡ እና የተከበራችሁ ምሁራን ሆይ! ይህ ምክር የሚገባው ግእዝን አሽቀንጥሮ ከላቲን ፊደላት ጋር ለተጋባው ለኦሮሚያ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ደብዳቤው የፍሬ ነገር ስህተት አለበት ማለቴ፡፡
ምሁራን ሆይ “የአማራ ክልል የአገርን ቅርስ በማስጠበቅ አንጻር የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ በአክብሮት እንጠይቃለን” ብላችኋል፡፡ ይበል ነው፤ ከዚህ ላይ ልክ ናችሁ፡፡ ከዚህ ላይ ያቀረባችሁት ልመና በጣም ከበድ ያለ እንደሆነ፣ አማራ ክልል ኦሮሞኛን እንዲታደግ ግልጽ የሆነ ተማጽኖ ነው፡፡ አዎ! አማራ ክልል ያባቶቹን ቅርስ ጠብቆ ለትውልድ እያስተላለፈ ነው፡፡ አይደለም የራሱን የሌሎችንም ጠብቆ አቆይቷል፡፡ በዚህስ አይታማም፡፡
የአሁኑ የሀገራችን የጎሳ ፖለቲካ ትሩፋት መሬት ሸንሽኖ ከመቀራመት ባለፈ አንዱ ክልል በሌላው ክልል ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ሚና እንዳይኖረው ማድረጉ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ለዚያም እኮ ነው አንድ አማራ ስለ ኦሮሞ ወይም ስለ ትግራይ ወይም ስለ ሐረሪ ጉዳይ ወይም በግልባጩ፣ ሲናገር “ምን አገባህ ስለ እኛ ክልል?” “በክልላችን ተውን፣ እንደፈለግን እንሁን” ሲባል የምንሰማው፡፡ እና ምሁራን ሆይ! አማራ ክልል የኦሮሞኛን ቋንቋ ከባእዳን ፊደላት ይላቀቅ ዘንድ እንዲታደገው ያቀረባችሁት ልመና በጎ ነው፡፡ ምናልባትም ኦሮሚያ ክልል የግእዙን ፊደል መጠቀምን በተመለከተ ተሥፋ አስቆራጭ ነገር ሳይናገራችሁ የቀረ አይመስለኝም፡፡ ዋና ችግሩ ግን እናንተ ለአማራ ክልል ያቀረባችሁት ተማጽኖ የእናንተ ምኞት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የጎሳ ፖለቲካችን ይህን አንዱ ክልል ለሌላው የሚያደርገውን በእናትና በልጅ መካከል የሚታየውን ዓይነት ትድግና ይጸየፈዋል፡፡ እናማ መጀመሪያ ኦሮሚያ እንዲህ ዓይቱን ትድግና በግልጽ እንደሚሻ ቢያሳውቅ ሁላችንም በተረባረብነ፡፡ ግን እንደዚያ ዓይነት ፍላጎት እንደሌለ የናንተ ደብዳቤ ፍንጭ ይሰጠናል፡፡
አዎ! የምሁራኑ ደብዳቤ ገጸ-ንባቡን ስንመለከተው ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት፡፡ አንደኛው ኦሮሞኛ በአማራ ክልል መሰጠቱ ለአማሮች ይጠቅማል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኦሮሞኛን በግእዝ ለመጻፍ አማራ ክልል ላይ ይሞከር የሚል ነው፡፡
ሰምና ወርቅ አስማምተን የምንፈትል፣ ቅኔ አዋቂዎች፣ ነገር ከሥሩ የሚገባን አይደለን፡፡ እናማ የምሁራኑ ደብዳቤ ከዚህ ያለፈ ሌሎች ዓላማዎችም እንዳሉት እናመሰጥራለን፡፡ አንድም ኦሮሞኛን የፌዴራል ቋንቋ ለማድረግ የሚደረገው ትግል አንደኛው ክፍል ነው ብለን እንተረጉመዋለን፤ ይህን ጉዳይ ሌላ ጊዜ በስፋት እመለስበታለሁ፡፡ ዳግመኛም የበላይነትን ለመያዝ የሚደረግ ትግል ገጽታ ነው ብለን አንድምታውን እንፈታዋለን፡፡ ይህን ነጥብ ደግሞ ለፖለቲካ ተንታኞች እተወዋለሁ፡፡
ወደ ዋናው ክርክር ልግባና እስኪ የምሁራኑ ደብዳቤ የያዘውን ዓላማ እንፈትሽ፡፡
1. ብሔራዊ መግባባት የጠፋው ኦሮሞኛ በአማራ ክልል ት/ቤቶች ባለመሰጠቱ አይደለም፡፡ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ መቼም ከአማርኛ ቋንቋ የሚደረግ ሽሽት ብዙ ነገር አሳይቶናል፤ ብዙ ዝቅታ አድርሶብናል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ከተጸነሰበት ጊዜ ጀምሮ አማርኛን መሸሽ ከአማራ ተጽእኖ መላቀቅ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ግን እውነታው እንደዚያ አይደለም፡፡ ከአማርኛ መሸሽ ከአማራ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብሔርች ጋር ያለን መስተጋብርም መሸሽ እና በሩን ማጥበብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም የሚያስተሳስረን አንደኛው ገመድ እርሱ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላ የሚያስተሳስር ገመድ ለመዘርጋት፣ ቀድሞ የነበረውን ገመድ መበጠስ ወይም ማላላት አያስፈልግም ነበር፡፡ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠረው አንዱን ቆርጦ አንዱን በመወጠር አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በኔ ሙያ ያጋጠመኝን ነገር ከሁለት ዓመታት በፊት ሁለት ተከታታይ ጦማሮችን አሰናድቼ ነበር፡፡
ሌላው ሰሞኑን በብዙኃን መገናኛ እንዳየነው በኦሮሚያ ክልል በአማርኛ የተጻፉ ማስታወቂያዎች ሲሰረዙ፣ ሲገነጠሉ አይተናል፡፡ በርግጥ ማስታወቂያ የመሰረዙ ጉዳይ ቀደም ብሎ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራበት እንደነበር እኔ አውቃለሁ፡፡ ክልሉ ባህሉን፣ ቋንቋውን ለማሳደግና የክልሉን ሕግ የበላይነት ለማስፈን የሚያደርገውን ትጋት አደንቃለሁ፡፡ እንዲያውም በ2005 ይህን ድርጊት በቀድሞው ኦሮሚያ ቴሊቪዥን ስመለከት የክልሉን ድርጊት አድንቄ ከዚሁ መንደር ላይ መጻፌን አስታውሳለሁ፡፡ የሰሞኑ ግን ቀደም ካለው ለየት ያለ ነው፡፡ የፌዴራል ተቋማት ሳይቀሩ የሚጽፉትን ማስታወቂያና ታፔላ ሳይቀር መገንጠሉ ከቀድሞው ለየት ያደርገዋል፡፡ የማስታወቂያ ሕግ ከማስከበር ይልቅ በሃይል ወደ መጨፍለቅ ያዘነበለ ሂደት ነው፡፡ እንዲህ ሃይል የተቀላቀለበት መንፈስ ይዞ ለብሔራዊ መግባባት ይጠቅማል ማለት የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡
2. ሌላው አስገራሚው ምናልባትም ምሁራኑ ሂሳቸውን መልሰው ሊውጡት፣ ወይም ባልጻፍነው ብለው ሊያፍሩበት የሚገባው ነገር ለአማራ ክልል ባቀረቡት ሃሳብ መሠረት ኦሮሞኛ በግእዝ ፊደላት ይጻፍ የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን እንመልከት፡፡
አንደኛ፣ ለኦሮሞኛ ቋንቋ አስበው ከሆነ በዋናነት ሊያሳድገው፣ የሚጻፍበትን ፊደል ሊመርጥ የሚገባው ኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ እና ይህን ክልላዊ ሉአላዊነት አሳልፎ መስጠትና አማራ ክልልን በኦሮሞኛ ቋንቋ ላይ ሚና እንዲኖረው ማድረግ የጎሳ ፖለቲካችንን የሚያቅረው ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ኦሮሞኛን በግእዝ ለመጻፍ በአማራ ክልል ይሞከር የሚለው ሲሆን በጣም አሳፋሪ ሃሳብ ብዬዋለሁ፡፡ እንዲያው አማራ ክልል የስንቱ ቤተ-ሙከራ ይሁን!?1
ሙከራው ለኦሮሚያ አዋሳኝ በሆኑ የአማራ ክልል ወረዳ ት/ቤቶች ይጀመር አላችሁ፡፡ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ይላል ያገሬ ሰው፡፡ ኦሮሚያ ለሙከራ እምቢ ሲላችሁ አማራ ላይ ይሞከር ማለት ነውር አይደለም?? ነገሩማ ሙከራውን በዋናነት ከሚመለከተው ቦታ ላይ አድርጋችሁ ውጤታማነቱ ታይቶ ከዚያ ሃሳቡን ማቅረብ በተገባ ነበር፡፡ እስኪ በግልባጩ ለአማራ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የኦሮሚያ ክልል ወረዳ ት/ቤቶች ሙከራው ይካሄድ፤ ውጤቱንም አብረን እናያለን፡፡ ይችን ኦሮሚያ ላይ ብታሞክሩ ቄሮ ትልቅ አቧራ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ እና ምኑ ላይ ነው ዋና የተማጽኖ ዓላማችሁ?
እና ምሁራን ሆይ! እውነት ለኦሮሞኛ ቋንቋ እድገት አስባችሁ ከሆነ እስኪ መጀመሪያ ኦሮሚያ ክልል በጉዳዩ ላይ እንዲመክርበት፣ ኦነግ የሰራውን ስህተት እንዲያርም አድርጉት፡፡ እንደሚታወቀው የላቲን ፊደላትን ለኦሮሞኛ ቋንቋ መጠቀም የኦነግ ሃሳብ እንጅ የመላ ኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ ነግራችሁናል፤ ከአማርኛ ለመራቅ የተደረገ ሽሽት እንጅ ትክክል እንዳልነበር ጨምራችሁ በጥናታችሁ ነግራችሁናል፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደም፡፡ አደሬኛ በላቲን ፊደላት ሞክረው ስላልተሳካላቸው ወደ ግእዙ ፊደላት ተመልሰዋል ብላችሁ አብነት ነግራችሁናል፡፡ እና ኦሮሞኛም ተመሳሳይ ፈለግ እንዲከተል ብትመክሩ አይሻልም ነበር?
እንደው ይህን ደብዳቤ ስትጽፉት ለኦሮሞኛ ቋንቋ እድገት አስባችሁ ነው?? ለብሔራዊ መግባባት ነውን?? አይመስለኝም፡፡ አንድ ቋንቋ በሁለት የተለያዩ ፊደሎች እየተጻፈ (ግእዝ እና ላቲን)፣ አይደለም የቋንቋ እድገትና መግባባት ቀርቶ ወደ ግራ መጋባትና መዛነቅ ነው የሚያደርሰው፡፡ እንዲያው በግእዝ ፊደላት ይሰጥ ብለን መላምት እንምታ፤ ማን ነው ግን ኦሮሞኛን በግእዝ ፊደላት በአማራ ክልል ት/ቤት የሚያስተምረው? አማራው ኦሮሞኛውን አያውቅም፤ ኦሮሞውም (በተለይ የአሁኑ ትውልድ) የግእዝ ፊደላትን አያውቃቸውም፡፡ እና ማን ማንን ያስተምር? ምሁራን ሆይ አሁንስ የፍሬ ነገር ስህተት እንደሠራችሁ ታወቃችሁ?
በመጨረሻ ግን አንድ የማምንበትን ሃሳብ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ቋንቋ ማወቅ ማንንም ጎድቶ አያውቅም፡፡ በተለመደው አባባል “ባይጠቅምም፣ አይጎዳም” የሚባል ተራ ነገር እንኳ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ኦሮሞኛ ብችል በሙያዬ የሰፋ እድል፣ ብዙ ቦታዎች ተንቀሳቅሶ የመስራት እድሌን ያሰፋልኛል፡፡ ሌላው ቢቀር የኦሮሚያ የጥብቅና ፈቃድ አውጥቼ በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች እንደፈለኩ መሥራት እችል ነበር፡፡ ታዲያ አሁን በቀረበው ዓይነት መንገድ ቋንቋው ሲሰጥኝ ግን አይደለም፡፡
—————————————————————————-
1. አማራ ክልል ለኦሮሞኛ ቋንቋ እድገት ጥሩ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት መመልከት ለዚህ በቂ ምስክር ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ኦሮሞኛ እንደ ሌሎች የክልሉ ቋንቋዎች ሁሉ ተገቢውን ቦታ ተሰጥቶት ተፈጥሯዊ ኑሮ እየኖረ ነው፤ ድርጅቱም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
Filed in: Amharic