>

ይድረስ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፤ (ከውብሸት ሙላት)

ይህ ጽሑፍ  “አንቀጽ 39” የሚለው መጽሐፌ ላይ ተካትቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም እንዲሁ በማኅበራዊ ሚዲያ ተቆራርጣም ቢሆን ወጥታለች፡፡ በእኔ መጽሐፍ የተጠቀሰው ከእርስዎ መጽሐፍ “የክህደት ቁልቁለት” ከሚለው ላይ ነው፡፡ አሁንም በመጽሐፍዎ ላይ ተመሳሳይ መከራከሪያ በማቅረብ በፌስ ቡክ ላይ ስለ አማራ ጉዳይ ስለጻፉ እኔም በድጋሜ አስተያየት ለመሥጠት ነው፡፡
አንድ ከግምት እንዲገባልኝ የምፈልገው ቁምነገር አለ፡፡ ይኸውም በርካታ ሐሳቦችን ከተለያዩ ድርሳናት ወስጃለሁ፤ምንጫቸውን ለፈለገ መጽሐፌ ላይ ገልጫለሁ፡፡ ለፌስ ቡክ እንዲመች ሲባል እንጂ የራሴ አስመስዬ ነጥቄ ለማቅረብ አይደለም፡፡
የእኔ ጽሑፍ ሁለት ክፍሎችን ይዟል፡፡ የመጀመሪያው አማራ የሚባል ብሔር መኖሩን ለማሳየት የሚሞክር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አማራ የሚባል ብሔር ካለ ስለምን የአማራ ብሔርተኝነት ሳይፈጠር ኖረ? ሳይፈጠር ኖረ ያልኩት ቀድሞ የነበረው የአማራ ብሔርተኝነት ሁኔታ አሁን ካለበት የሚለይ ስለሆነ ነው፡፡ ሁለቱንም በአጭሩ እናያቸው፡፡
የአማራ  ብሔር ኅልውና ጉዳይ፤
የፕሮፌሰር መስፍንን አሁንም ቢሆን አማራ “የለም” ባይ ናቸው፡፡ በማስረጃነት የሚያቀርቡትም ሊቃውንት አማራ ለሚለው ቃል፣ ከሥርወ-ቃሉ በመነሳት “ነጻ፣ የተመረጠ፣ መገዛትን የማይወድ” ወዘተ ሕዝብ ነው በማለት የሰጡትን ትርጓሜ መነሻ ያደርጋሉ፡፡
በግዕዝ-“ዐም”፣በዕብራይስጥ-“ዐሚ” ማለት ‘ሕዝብ’ ሲሆን፣ “ሀራ” ማለት ደግሞ ሁለት ትርጉም አለው፡፡ የመጀመሪያው ‘ነጻ’ ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘ሰራዊት፣ወታደር’ እንደማለት ነው፡፡ አማራ ማለት ነጻ ሕዝብ ማለት ነው የሚለው ብዙም ትርጉም የማይሰጥ ቢሆንም፣ ነጻነትን የሚወድ ለማለት ነው ከተባለም ነጻነትን የሚጠላ ሕዝብ ያለ ስለማይመስለኝ ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ብዙም ስለብሔሩ የሚገልጸው ነገር ያለ አይመስልም፡፡
በአለቃ ታዬ “አማራ ጥሩ የላስቶች ወታደር የነበረ ሕዝብ ነው” የሚለውን ሐሳብም እንደአስረጂ ያቀርባሉ፡፡ “ሀራ” የሚለው ቃል ሁለተኛው ትርጉም ‘ሰራዊት፣ወታደር’ ማለት ስለሆነ የአለቃ ታዬና ሌሎች ምሁራንም አማራ የላስቶች ወታደር የነበረ ሕዝብ ነው ሲሉ ይህንን ወታደርነቱን ለመወከል የተሰጠ ቃልም ይመስላል-አምሀራ፡፡ ይህ አጠራር ሕዝቡ ከተፈጠረ በኋላ የተሰጠ፣ አመጣጡን አይቶ ስም የወጣለት ያስመስለዋል፡፡
አባ ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር በትግርኛ-አማርኛ መዝገበ-ቃላታቸው ደግሞ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም” ያሉትንና የንቡረ-እድ ኤርምያስን “የኅብረብሔር አጠቃላይ መጠሪያ” የሚሉትን ትርጓሜ እንደማጠናከሪያ በመውሰድ አማራ የሚባል የተለየ ጎሳ የለም በማለት ይደመድማሉ፡፡ የሁለቱ ሊቃውንት ስያሜ ከፕሮፌሰር መስፍን መደምደሚያ ጋር ይስማማል ማለት ይቻል ይሆናል፡፡
ይሁን እንጂ የአባ ዮሐንስ፣ መዝገበ ቃላታዊ ፍቺ በመሆኑ እና ብዙም ማብራሪያ ስለሌለው ለክርክር አይመችም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ነው ማለት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ “አማራ ነው” የሚል አንድምታ ስላለውና ይህ እውነት ለማለት ደግሞ የሌሎች ብሔረሰብ አባላት ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ መፍትሔ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ አማራ ነን ካሉ አባ ዮሐንስ ትክክል ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የአንዱ ሕዝብ ስም ነው የሚል ትርጓሜ ከያዘ የፕሮፌሰርን ክርክር ያፈርሳል፡፡
የንቡረ እድ  ኤርምያስ፣ የኅበረ ብሔር አጠቃላይ መጠሪያ የሚለውም ቢሆን፣ የአማራ ሕዝብ እንደ ብሔር፣ አፈጣጠሩንና አመጣጡን በተመለከተ ከሆነ በትክክል ይገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ብሔሮች ውጤት በመሆኑ፡፡ ነገር ግን ሌሎችንም ብሄሮች አካትቶ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ አንድ ቡድን ለመግለጽ ከሆነ ኢትዮጵያዊነትና አማራነት አንድ ናቸው የሚል ትርጉም ያመጣል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን፣ ቀጥለውም የተለያዩ ሰዎች “አማራ ነኝ” ሲሉ “ክርስቲያን ነኝ” ማለታቸውም እንደሆነ በመግለጽ ክርስቲያን ከሚለው ጋርም ያመሳስሉታል- በመጽሐፋቸው፡፡ እርግጥ ነው ይህን አጠራር ብዙ ሰው ሲጠቀምበት ይስተዋላል፡፡
የአማራነትና የክርስቲያንነትን “ተመሳስሎሽ” በተመለከተ አንድ ክርስቲያን የሆነ ትግሬ ወይንም ኦሮሞ “ሃይማኖትህ ምንድን ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ መቼም ቢሆን “አማራ” ሊል አይችልም፡፡ ለነገሩ በአማራ ክልል ውስጥም የሚገኙ ክርስቲያኖች “ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው?” ሲባሉ በተለይ አሁን አሁን “አማራ ነኝ” አይሉም፡፡ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ሙሉወንጌል ወዘተ ይላሉ እንጂ፡፡ በመሆኑም እየተቀየረ መሔዱንም መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ለማጠቃለል ሊቃውንት ከሥርወ-ቃሉ በመነሳት ትርጉም የሰጡት አማራ የሚባል ቢያንስ ሕዝብ በመኖሩ ነው፡፡ የአለቃ ታዬም የአማራን ሕዝብ ከየት መጣነት (ከላስቶች ወታደር እንደተገኘ) አስረዱ ከማለት ውጭ “የለም” አላሉም፡፡ ሊቃውንት አማራ የሚባል ብሔር ወይንም ሕዝብ “የለም” አላሉም፡፡ትርጉምን የሰጡት ቢኖር ይመስለኛል፡፡
ታዲያ አብዝሃኛው አማራ ስለብሔሩ ሲጠየቅ ‘አማራ ነኝ’ ማለት ለምን አይቀናውም ለሚለው ጥቂት ምክንያቶችን ላቅርብ፡፡
የአማራ ብሔርተኝነት ጉዳይ፤
ለአማራ እንደብዙዎቹ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጥንት አባትና እናት/የጋራ የዘር ግንድ የለውም፡፡ የጋራ አፈታሪክና ተረት የለውም፡፡ አማራዎች የጋራ የዘር ግንድ አለን ብለው ሲያወሩ አይሰማም፡፡ ጎሳ፣ ነገድና የመሳሰሉትም ቅድመ-ብሔር ዝግመተ-ለውጣዊ እድገት እንደሌሎቹ  በርካታ ብሔሮች በዚህ ሂደት ውስጥ አላለፈም፡፡
ይህ ሁነት አለመኖሩ ወይንም አለመከሰቱ፣ አማራ እንደ አንድ የተለየ ብሔር የብሔርተኝነት ስሜትና የአንድነት መንፈስ እንዳያሳድግ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡
ለብሔርተኝነት ሌላው ምንጩ ጭቆና ነው፡፡ እንደሌሎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች፣ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተራዘመ ጭቆና ስላልደረሰበት ይህ ስሜቱ አላደገ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናውኑ ካሉት አድራጎቶች ይህንን ለውጥ መኖሩን ማጤን ይቻላል፡፡ ከአርሲ፣ በደኖ፣ ወተር ጭፍጨፋ፣ ከጉራፋርዳና ከቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በተከሰተው መፈናቀል ምክንያት የትውልድ ቀዬው የትም ይሁን የት፣ ሁሉም አማራ እንደ ብሔር የሀዘን ስሜቱን መግለጹ ብዙ መልዕክቶች አሉት፡፡ ለነገሩ መአህድ (የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት) የተባለው የፖለቲካ ፓርቲም የተመሠረተው እነዚህ አድራጎቶችን ተከትሎ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የተከሠቱትን ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ የብሔርተኝነቱ ደረጃ ምን ላይ እንደደረሰ ለማንም ግልጽ ነው፡፡
ሦስተኛው ምክንያት አማራ ባለፈው መቶ ዓመት በተለይም በባህል ረገድ ሌሎች ላይ ባህሉን ጫኝ እንጂ ተጫኝ ባለመሆኑ  በሌሎች ሀገራት እንደተስተዋለው ባህላቸውን ጫኝ ብሔሮች እራሳቸውን እንደነጠላ የሰው ልጅ (ዜጋ) እንጂ እንደ ቡድን አለማሰባቸው፣ እንደ ዜጋ እንጂ እንደ ብሔር ወይም ነገድ በመሰባሰብ ዘር ባለመምዘዛቸው ምክንያት ነው ፡፡
አማራም ልክ እንደሌሎች በዚህ ሂደት ውስጥ እንዳለፉ ብሔራት ተመሳሳይ ታሪክና እሳቤ አለው ማለት ይቻላል፡፡ አማራ በዘር አይሰባሰብም፤ ዘሩን ሳይሆን ርስቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ሚስቱን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ የክተት ነጋሪት ሲጎሰም ወደኋላ ብሎ የማያውቅ ሕዝብ ነው፡፡ ደግሞም የትም ዘምቷል፤የትም ለምዷል፡፡
አራተኛው ምክንያት አማራ የሚባል ብሔር ወይም ሕዝብ ሳይኖር አማርኛ  ቋንቋ ብቻ የተፈጠረ መሆኑም ነው፡፡ ቋንቋው መቼና እንዴት እንደተፈጠረ ስምምነት ላይ መድረስ ባይቻልም አማራ የሚባል ጎሳ ወይም ነገድ ወይም ዘር ነበር ባይ ምሁራን ስለመኖራቸው አላውቅም፡፡ አላውቅም ማለቴ የለም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑት ሕዝቦች ከብዙ ብሔርና ብሔረሰቦች የመነጩ በመሆናቸው ጥብቅ የሆነ የጋራ ማንነት እንዳያሳድጉ አድርጓል፡፡
ሌላው ስለብሔር ስናነሳ የብዙሃኑ ስለብሔሩ ያለውን ንቃት እንጂ የልሂቃኖች መንቃት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ የብዙሃኑን ንቃት ለማምጣት ደግሞ በተለያዩ ኩታገጠም ቦታዎች እያረሱ ከብት እያረቡ በዚያው አካባቢ ባለ የገበያ ቦታ እየተገበያዩ በአንድነት በሚኖሩ፣ ባልተማሩ ኅብረተሰቦች ዘንድ፣ ትራንስፖርትና ሌሎች መገናኛ ዘደዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በቀላሉ የሚፈጠር አይመስልም፡፡ የራሱን ማንነት እየተረዳና እያወቀ የሚመጣው ከሌላው ጋር በሚፈጥረው ግንኙነትና መስተጋብር ነው፡፡ እርስ በርሱ ብቻ የሚገናኝ ኅብረተሰብ ብሔርተኝነት መሰባሰቢያው አይደለም፤ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ፈረንሳይ ናት፡፡
በ1870ዎቹ ፈረንሳይ ውስጥ የፈረንሳዊነት ስሜት አልነበረም፡፡ እራሳቸውን በአካባቢያቸውና በመሳሰሉት ነገሮች ነበር የሚለዩት፡፡ ከናፖሊዎን ወታደርም ቢያንስ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የውጪ ቅጥረኞች ነበሩ፡፡ ገበሬው የፈረንሳይ ሕዝብ የፈረንሳዊነት ስሜት ስላልነበረው “ለእናት ሀገሬ ፈረንሳይ” ብሎ የሚዋጋበት ደረጃ ላይ እንኳን አልደረሰም ነበር፡፡  ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ነው ፈረንሳዊነት እያደገ የመጣው፡፡
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሁኔታ ከፈረንሳዮቹ ጋር የሚለያይ ይመስላል፡፡ አንድም የአድዋን ጦርነት  ያስታውሷል፡፡ ወቅቱ ዐጼ ምንሊክ የተለያዩ ንጉሦችንና የአካባቢ ገዥዎችን እያስገበሩ የነበሩበት ወቅት ቢሆንም ቅሉ የክተት አዋጅ ሲታወጅ የሁሉም ብሔር ተወላጆች ‘ደረታቸውን ለጦር እግራቸውን ለጠጠር’ መስጠታቸው እሙን ነው፡፡ ይህ ከፈረንሳዮቹ ለየቅል መሆኑ ነው፡፡ ሁኔታው ሰፋ ባለ ቦታ/ክልል ለሚኖሩ ለማንኛውም ብሔር የሚሠራ ቢሆንም ከላይ ከ1-5 ተጠቀሱት ምክንያቶች ሲታከሉባቸው ግን ለአማራ የበለጠ ይሰራል ባይ ነኝ፡፡
ብዙ ሰዎች (ከላይ የተገለጹትን ንቡረ-እድ ኤርምያስና ምንአልባትም እንዳገላለጻቸው ከሆነ አባ ዮሐንስም) አማራነትና ኢትዮጵያዊነትን አንድ የማድረግ አዝማሚያ ይታያል፡፡ ዋናው ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ መጠናትም የሚገባው ይሔው ነው፡፡ አብዝሃኛው የአማራ ልሂቃን ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ አስተዳደር ለምን ይቃወማሉ? ለምንስ ብሔራቸውን ሲጠየቁ  “ኢትዮጵያዊ” ማለት ይቀናቸዋል? በሌላ አገላለጽ ለምን “አማራ ነኝ” ማለት አይፈልጉም?
ሀገር ማቅናት ወይንም አንዲትን ሀገር አሁን የያዘችውን ቅርጽ እንዲኖራት አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብሎ የሚያስብ ብሔር እራሱን የሚጠራው በሀገሪቱ ስም፣ ራሱን የሚቆጥረውም እንደዜጋ እንጂ፣እንደ ብሔር አይደለም፡፡ በስፔን የሚኖሩ ካስቲሊያን፣ ስፔን የአሁን ይዘቷን እንድትይዝ ፊታውራሪዎች ስለነበሩ ራሳቸውን እንደካስቲሊያን ከመውሰድ ይልቅ ስፓንያርድ (ስፔናውያን) ማለት የሚቀናቸው ሲሆን ብሔርነታቸው ሳይሆን ዜግነታቸው ይቀድምባቸዋል፡፡ ካታሎንያን፣ ባስኮች፣ ቫሌንሽያዎች እራሳቸውን በብሔራቸው ሲጠሩ ካስቲሊያኖች ለፍተን እዚህ ያደረስናትን ስፔንን ሊገነጣጥሉ ነው ብለው ያስባሉ፡፡
የእንግሊዞችም የብሔርተኝነት ስሜት ከአማራ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ዌልስና ስኮትላንዶች ራሳቸውን ዌልሳዌና ስኮትሽ በማለት ሲጠሩ እንግሊዞች ግን የላላ ብሔርተኝነት ስላላቸው እራሳቸውን ከታላቋ ብሪታኒያ ነጥለው እንግሊዛዊ ማለትን አይፈለጉም ነበር፡፡ ይሔንን ንጽጽር ክርስቶፎር ክላፕሃም ጥሩ አድርጎ ጽፎታል፡፡ በኢትዮጵያም ብዙዎች “አባቶቻችን ለፍተው ለፍተው መና ቀሩ፤ አንቀጽ 39 የእነሱን ልፋት ከንቱ ማድረጊያ ስልት ነው” ብለው ያስባሉ፡፡
ሲጠቃለል፣ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አሁንም ቢሆን አማራ እንደሌለ የቀረቡትን መከራከሪያ አሳማኝ አልመሰለኝም፡፡ ብሔርን መሠረት አድርጎ መደራጀት ተገቢ ነው ወይስ አይደለም አገራችን የብሔርና በቋንቋ መለኪያነት የፌደራል ሥርዓት መከተሏ ተገቢ መሆን አለመሆኑ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡
እስኪ ከእንደገና ዘርዘር አድረገው እንዲያስረዱን ለመጠየቅ ሲባል የቀረበ ነው፡፡
#Mesfin Wolde-mariam
ዕድሜና ጤና ይስጥዎ!
ከታናሽዎ እና ፍጹም አክባሪዎ!
#Engida Kebede
Filed in: Amharic