>

ዝርው ዓመፃ እና ከዋናው ጉዳይ የተናጠበ ጽሑፍና ንግግር (ከይኄይስ እውነቱ)

 

አገራችን ኢትዮጵያ በለየለት ቅጥረኛ የወታደራዊ እዝ ሥር ከሆነች ውላ አድራለች፡፡ የወያኔ አገዛዝ ሕገ ወጥ
በሆነ ዓዋጅ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሽብር የመፈጸሙን ተግባር ዋናው ተልእኮው፣ ግቡም ዕድሜውን በመቀጠል ባለበት የ‹‹ጠላት ወረዳ›› ላይ የግል ደኅንነቱንና በጎሣ ያደራጀውን ‹‹ተናካሽ ውሻ/ሠራዊት›› በመጠቀም እስከተቻለ ድረስ በደም የተጨማለቀ ሥልጣኑን እና ዝርፊያውን ማደላደል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ሕዝባችን ግፍና መከራውን የማይሸከምበት ደረጃ በመድረሱ በተበታተነ (ዝርው)፣ መሪና
አደራጅ በሌለው ትግል የሕይወት መሥዋዕትነት በመክፈል ላይ ይገኛል፡፡ ያለተቀናጀውና ብልጭ ድርግም የሚለው ‹‹ሕዝባዊ›› ተቃውሞ ለአገዛዙ ጭራቆች ሰይጣናዊ ዱለታ ፋታ ሰጥቷቸዋል፡፡ ዛሬ ከምንጠቀምበት ቋንቋ ጀምሮ ዘረኛውን የወያኔ አገዛዝ ለመጣል እሰከሚደረገው ትግል ወያኔ ባቆመልን የጎሣ ጣዖት ላይ የተመሠረተ ሆኗል፡፡ ዛሬ ለዚህ ጣዖት ያልተንበረከከ ሰው በአገር ቤትም ሆነ በውጭ በዝርወት በሚገኘው ኢትዮጵያዊ መካከል ማግኘት ግመልን በመርፌ ቀዳዳ የማሾለክ ያህል ከብዷል፡፡ ይህ የት እንደሚያደርሰን ፈጣሪ ይወቀው፡፡ አገርን ለመታደግ፣ ከባርነት ተላቆ አርነት ለመውጣት በፈረቃ (ጎሣንና አካባቢን መሠረት አድርጎ)የሚካሄደውን እምቢ ባይነት፣ የሚገበረውን ሕይወት፣ በእስር የሚፈጸመውን እንግልት፣ ባጠቃላይ የወንበዴዎቹን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት የሚደረገውን ማናቸውም ዓይነት የትግል እንቅስቃሴ በፈጣሪ የምሕረት ዓይን እንዳይጎበኝ ከወያኔ በተቃራኒው የቆምን ኹላችን ሰብአ ባቢሎንን መስለናል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመዘገበው እግዚአብሔር በመለያየት ውስጥ የቸርነቱን ሥራ አይሠራም፡፡ እስኪ ወደ ልቡናችን ተመልሰን ማስተዋልን ገንዘብ እናደርግ እንደሆን፣ ለአብነት ያህል መሰናክል የሆኑንን የድንቁርናችንን ጥግ መገለጫዎች አነሳለሁ፡፡

1. በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ፤

እግዚአብሔር ጤንነት ያለበት ረጅም ዕድሜ ይስጣቸውና ኢትዮጵያዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ የፖለቲካል
ሳይንስና የሕገመንግሥት ሕግ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም በቅርቡ ባገራችንና በሕዝቧ ላይ ግልጽ ሽብር ለመፈጸም ሕገ ወጥ ፈቃድ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን ቅጥረኛ የወታደራዊ እዝ (mercenary military command post) እና ሌሎችንም የወያኔን አገዛዝ እውነተኛ ባህርይ የሚገልጹ ቃላት አጠቃቀምን በሚመለከት በውጭ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛዎች ጠበቅ ያለ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ሌሎችም እንደ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ ያሉ ለውጭ ብዙኃን መገናኛ፣ እንዲሁም ዶ/ር ተስፋዬ ደመላሽ ለምሁራን ያቀረቡት ተማጽኖ (የኢትዮጵያ ህዝብ ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል ለመደገፍ ከቋንቋ አጠቃቀም ጀምሮ ሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳብን፣ ፍልስምናን፣የበሰለ ትንተናን ወዘተ. መሠረት አድርገው አገዛዙ ሕዝብንም ሆነ የውጭውን ዓለም ለማጭበርበር የሚጠቀምባቸውን የማስመሰያ ሃሳቦች/‹ርእዮት› በማምከን ረገድ ሊኖራቸው ስለሚገባው ጉልህ ሚና ማንሳታቸው) በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ስለሆነም የወያኔ የጡት አባት የሆኑ የውጭ መንግሥታትና የግፍና የዝርፊያ ተባባሪው የሆኑት ሆዳም አድርባዮች እንደ ብጤታቻው ቢሆኑም፣ የተቀረነው ግን አካፋን አካፋ ብለን መጥራቱ ለሕዝባችን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ ከብዥታና ውዥንብር በመጠበቅ ለ‹ሕዝባዊ› ትግሉ የማይናቅ አስተዋጽኦ እናደርጋለን፡፡ በዚህም መሠረት፣
1.1. የወያኔ/ሕወሓት አገዛዝ ጭርሱኑ ከሰብአዊነት የተረቆተ ተራ የማጅራት መቺዎች ስብስብ በመሆኑ ‹ሕገ
መንግሥት›ም ሆነ ‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት› የሚባሉት የከበሩ ሃሳቦች ከዚህ ሽብርተኛ ቡድን ጋር
ተያይዘው ሊነሱ አይገባም፡፡ በዚህም ምክንያት የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› (façade constitution)
ወያኔ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማጥፋት ለተማማለበት የደደቢት መግለጫ ሽፋን በመሆኑ በዚህ የግል
‹ወረቀታቸው› ውስጥ ያካተቱት ዝባዝንኬ ነፃነት፣ ፍትሕና ርትዕ፣ እኩልነት እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት
መንግሥተ ሕዝብ ለማቆም ለሚታገሉ ወገኖች በሙሉ ትርጉም የላቸውም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በምትባል
አገር ያለ (ባህላዊ፣ ቋንቋና እምነት ወዘተ. ዝንጉርጉርነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ወያኔ
በልቦለድ የፈጠረው ግዑዝ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› አይደለም፡፡ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ በዘር፣
በታሪክ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በጋራ ሥነ ልቦና፣ በጋብቻ፣ በንግድ፣በሰላምም ሆነ በጦርነት ወቅት
በመተጋገዝ ወዘተ. ስር የሰደዱ የጋራ እሴቶች ያላቸው ማኅበረሰቦች ተዋሕደው በሚኖሩባት አገር ቀርቶ የጎላ ልዩነት ኖሯቸው በታሪክ አጋጣሚ በአንድ አገርና መንግሥት ጥላ ስር የሆኑ ማኅበረሰቦች ሕዝብ እንጂ ሕዝቦች
አይባሉም፡፡ ‹ፌዴሬሽን›፣ ‹ክልል› ወዘተ. የተባሉ ማጭበርበሪያዎችም እንዲሁ፡፡ ወያኔ ከፋፍሎ
ለመግዛትና ቅጥ ላጣ ዝርፊያው እንዲያመቸው 9 ቦታ የሸነሸናቸው ግልጽ ወህኒ ቤቶች (ክልሎች)
የአስተዳደር ክፍላተ ሃገራት ወይም ግዛቶች ሳይሆኑ ትክክለኛ የሕዝብ ማጎሪያ ‹ጋጣዎች› በመሆናቸው
በርካታ አገር ወዳድ ምሁራን እንዳሳሰቡት በቀድሞ ስማቸው ወለጋ፣ ሸዋ፣ ከፋ፣ ሲዳሞ፣ ኢለባቦር፣ ትግራይ፣
ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሐረርጌ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ኦጋዴን፣ ወዘተ. ወይም ሌላ አመቺ በምንለው አጠራር
መጠቀም የወያኔን አፍራሽ የመረጃ ዘመቻ ለመዋጋት ከመርዳቱ በተጨማሪ የእምቢ ባይነት መገለጫ ነው፡፡
በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ የጥቂት ነጮች የአፓርታይድ አገዛዝ “Bantustan/black homeland” አምሳል ወያኔ የቀረፀውና ‹‹ክልል›› የተባለው የአትድረሱብኝ አጥር እስከነ ስያሜው በወደፊቷ ኢትዮጵያ ቦታ
እንደማይኖረው አልጠራጠርም፡፡
1.2. ኢትዮጵያ አገራችን በወያኔ አገዛዝ ‹መንግሥት› የላትም፡፡ የምንታገለውም ከሥርዓተ አልበኝነት ወጥተን
መንግሥተ ሕዝብ ለማቆም ነው፡፡ በመሆኑም የ‹ኢሕአዴግ መንግሥት› የሚባል የለም፡፡ ሲጀመርም
ኢሕአዴግ የሚባል ነገር የለም፡፡ ወያኔ/ሕወሓት (ትሕነግ) የተባለ አገዛዝ እንጂ፡፡
1.3. የወያኔ አገዛዝ የሽፍቶች ስብስብ እንደመሆኑ ግልጽነትና ተጠያቂነት በመዝገበ ቃላቱ ውስጥ የሉም፡፡ ስር
በሰደደ የበታችነት ስሜት የሚንፀባረቅ ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ ጭካኔ እና ዕርቃኑን በሚታይ ውሸት/ቅጥፈት
የሚመራ፤ በደባና ሴራ የተተበተበ፤ እኩይነትንና እቡይነትን ድርና ማጉ ያደረገ ቡድን ከሚባል በቀር ይህ ነው
የሚባል የሚገዛበት ርእዮተ ዓለምም ሆነ ፍልስምና ያለው አገዛዝ አይደለም፡፡ ሕውሓትና አሽከሮቹ በድብቅ
ይሰበሰባሉ፣ ሕወሓት ይወስናል፣ የሚጋልባቸው አሽከሮቹ ይፈጽማሉ ያስፈጽማሉ፡፡ ግለሰቦች ከፈጣሪ
የተሰጣቸው የማሰብ (የመጠየቅ፣ የመመራመር፣ የመተንተን ወዘተ.) ጸጋ ሙሉ በሙሉ ተገፎ
‹በፈቃዳቸው› የሚናገሩ፣ የሚበሉና የሚጠጡ ‹አጋሰሶች› የሆኑበት ስብስብ ነው፡፡ አገዛዙ በወረቀት
‹‹ፌዴራላዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነፃ/ገበያ-መር ኢኮኖሚ›› እያለ የ27 ዓመት ውሎ አዳሩ በተግባር
የሚያሳየን ግን የአንድን ጎሣ ‹ፓርቲ›ያሰፈነ አሐዳዊ አገዛዝ ሲሆን፣ እርስ በርሱ በሚጣረስ አስተሳሰብ
የታጀለ – ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ›/የዲሞክራሲያዊ ማዕከልነት/፣ ልማታዊ መንግሥት›› ወዘተ. –
ፀረ እውቀት/ፀረ ጥበብ ቡድን ነው፡፡ ይህንን የሃሳብ ተፋልሶውን ለማራመድና ሕዝብን ለማሳሳት
የሚጠቀምባቸውን የማምታቻ ቃላት እኛም እንደ በቀቀን የምናስተጋባ ከሆነ በወያኔ ወጥመድ ውስጥ
ላለመግባታችን ምንም ዋስትና የለም፡፡ በነገራችን ላይ አገዛዙ ለተለመደ ቅጥፈቱ የሚፈበርካቸውን ካድሬያዊ
ቃላቶች ሥራ ላይ በማዋሉ ረገድ ከተራው ሕዝብ ጀምሮ፣ ፊደል ቆጥሬያለሁ እንዲሁም ምሁር ነኝ የሚለውን
እንደሚጨምር ለመታዘብ ችዬአለሁ፡፡

2. ዐቢይ ከሆነው አገራዊ ጉዳይ መናጠብ

በመደበኛ ብዙኃን መገናኛዎች፣ በበይነ መረቦች፣ በገጸ-ድሮች እና በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ከወያኔ አገዛዝ በተቃራኒ ቆመናል የሚሉ ኃይሎች የሚያወጧቸውን መረጃዎች (በጽሑፍም ሆነ በድምጽ) ስንከታተል በአመዛኙ ከፍሬ ጉዳዩ ይልቅ ጭፍጫፊ ሃሳቦች ላይ ያተኮረና የጎንዮሽ መጎሻሸም ያየለበት ሆኖ አግቼዋለኹ፡፡ ለአብነት ያህል ለማንሳት፣
2.1. አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች አገዛዙ ዋሻ አድርጎ የተደበቀበትን ማኅበረሰብ በምን መልኩ ሲቀርፀው
እንደቆየና እየቀረፀው እንዳለ ለመስማት ጆሮን ጭው የሚያደርግ ዘግናኝ ዘገባ በማቅረብ ተጠምደዋል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ መረጃ (እውነት ከሆነ) ያለመው ተስፋ ማስቆረጥ ይሁን፣ ለቂምና በቀል ማነሳሳት ይሁን፣
ወያኔ የሄደበትን ርቀትና ‹አይበገሬነት› ማሳየት ይሁን ግልጽ አይደለም፡፡ አገርን ለመታደግ እንዲሁም ለነፃነት
ትግሉ የሚኖረው አንደምታ አልገባ ብሎኛል፡፡
2.2. ሌላው የወየኔ ጠ/ሚኒስትር ‹ሹመት› ላይ ያተኮረው አስተያየትና ‹ትንተና› ነው፡፡ ይህ ርእሰ ጉዳይ በምን መመዘኛ ይሆን የኢትዮጵያና ሕዝቧ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሊሆን የቻለው፡፡ በሰለጠነ መልኩ የሕዝብ ድምጽ አስተያየት (public opinion poll) ተሰብስቦ የሚተነተንበት አገር ውስጥ ባለመሆናችን እንጂ ሕዝባዊ ዓመፁን በእጅጉ እንደጎዳው ጥርጣሬ የለኝም፡፡ መደበኛ ሥራቸው ዜናን ማወጅ በሆኑ ብዙኃን መገናኛዎች እንደ አንድ ወሬ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከዛ ባለፈ ወያኔ በተከታታይ ዝግ ስብሰባዎች ተጠምዶ ህልውናውን ለማስቀጠል የሚዶልትበት ‹የአይሁድ ጉባኤ› አገራችንን የምንታደግበት፣ ነፃነታችንን የምናውጅበት የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ ማየቱ ግን የጤንነት አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያሻማ መልኩ ላቀረበው ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ወያኔ በራሱ አምሳል ጠፍጥፎ ከሠራቸው ድኩማኖች መካከል ከሚሰይመው አሻንጉሊት ጠ/ሚኒስትር መልስ መጠበቅ አንድም በተበታተነው ሕዝባዊ ትግል የተፈጠረ ቅሬታ፤ አሊያም አገርን በማዳን አጀንዳ ዙሪያ ስምምነት አድርገው በኅብረት ቁም ነገር ሊሠሩ የሚችሉ ተቃዋሚ ‹ፓርቲዎች› ላይ ተስፋ ከመቁረጥ የሚሰነዘር እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ በጣም የሚገርመውና በወያኔያዊ አስተሳሰብ መበከላችንን የሚያሳብቅብን ደግሞ አሁን የጠ/ሚኒስትርነቱ ተራ የእገሌ ጎሣ ነው ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ጥቂት የማይባሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ፡፡ ይህን ዓይነት አመለካከት ያላቸው ወገኖች ለወደፊቷ
ኢትዮጵያ የሚያስቡት የአገር መሪ መሥፈርቱ ብቃት/ችሎታ ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይስ የጎሣ ተዋጽኦ?
ተጨማሪ ዝቅጠት፡፡ ኧረ እናስተውል ጎበዝ!!
በቅርቡ ከወያኔ አሽከሮች መካከል ከተለመደው የመንጋ አስተሳሰብ አፈንግጠው ጥያቄ ማንሳት የጀመሩ
ቢኖሩም በጥርጣሬ የታጀበው ተቀባይነታቸው (በትልቁ ዓሣ/ሕወሓት ካልተዋጡ) እስከምን ድረስ
እንደሚዘልቅ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡
ከፍ ብሎ የተገለጸው ሃሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዚህ አስተያየት አቅራቢ አሽከርነት በቃን ብለው ከአገዛዙ
ያፈነገጡ፣ (ፍንገጣው እውነት እሰከሆነና ዘላቂነት ካለው)፣ ከመንደርተኝነት ተላቀው ወደኢትዮጵያዊነት እና
ሰብአዊነት (ወደላቀ የሃሳብ ልዕልና) የተሸጋገሩ፣ በአንፃራዊነት ‹ብቃት› ያላቸው ግለሰቦች (በጅምር
መልኩ እንደታየው) ለሕዝባዊ ትግሉ ብሎም ለሰላማዊ ሽግግር የመንገድ ጠራጊነት (በሁለተኛ ደረጃ
የሚታይ) ሚና እንደሚኖራቸው ያምናል፡፡
2.3. በትጥቅ ትግል ተሰማርተናል የሚሉ አንዳንድ የተቃዋሚ ኃይሎች በስራቸው ያሰለፏቸው ወገኖች ሕይወት ማጣት፣ አካል መጉደል፤ በሚከፈለውም መሥዋዕትነት አገርንና ሕዝብን ከሚቤዠቱ ታላቅ ዓላማ ይልቅ እዚህም እዚያም የሚገኙ ትናንሽ ድሎችና ታሪክ ሽሚያ ላይ ተጠምደው ሲጠላለፉ መስማት እጅግ
የሚያሳምም ጉዳይ ነው፡፡
2.4. ጎሣዊ ማንነትን መሠረት አድርገው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ስብስቦች ውሳጣዊ መቆራቆሳቸው ሳያንስ ከጎሣ ኢምንትነት ወጥተው ከፍተኛ የልዕልና ሠገነት ላይ የሚገኙትን፣ ነገረ ኢትዮጵያን በሰብአዊነትና በኢትዮጵያዊነት መነፅር የሚመለከቱትን፣ ሃሳባቸውን ምክራቸውንና የዘመናት ተሞክሮአቸውን ያለስስት በሚለግሱ የተከበሩ ወገኖች ላይ የሚያሰሙት ብልግናና ዘለፋ ሌላው ለወያኔ ጊዜ መግዣ ዳረጎት ሆኗል፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ኩራት፣ የአገር ሀብትና ቅርስ፣ እውነተኛ ምሁርና ሽማግሌ፣ መምህር ወመገሥጽ ኢያደልዎ
ለገጽ (ፊትን አይቶ የማያዳላ እውነተኛ መምህር) የሆኑት ጋሼ መሥፍን ላይ በጥራዝ ነጠቅ አክራሪ ጎሠኞች
የታየውን ብልግናም ለአብነት ያህል ያስታውሷል፡፡ ዋናዎቹን የማያከብር ትውልድ መጨረሻው ምን ይሆን? ገንቢ የሆነ ትችትን በሠለጠነ መንገድ መረጃን፣ ማስረጃን እውቀትን ገንዘብ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹ኹሉ ተፈቅዷል፤ የተፈቀደ ኹሉ ግን አይጠቅምም፡፡›› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ስለፈቀደ ብቻ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት አለኝ በሚል የምንናገርና የምንጽፈው የሚያስከትለውን ውጤት ሳናቅ መዘባረቅ
ቢያንስ የኅሊና ወቀሳንና የታሪክ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ለምንናገረውን ለምንጽፈው ጉዳይ ኃላፊነት
እንዳለብን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በተከበሩበትም አገር መብትና ነፃነት ልቅ
አይደለም፡፡ የሕግ ፣የጨዋነትና የሞራል ገደብ አለው፡፡ የምናፍርበትንና የምንጸጸትበትን ነገር ቢቻል
አለማድረግ፡፡ ካደረግንም ቀዳሚው ትምህርት ሆኖን አለመድገም አስተዋይነት ነው፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ወደድንም ጠላንም አንድ የፖለቲካ ማኅበር በጎሣ ሲደራጅ ውጤቱ የጎሣ
ፖለቲካ ማራመድ ነው፡፡ የጎሣ ጉዳይ ይዋል ይደር እንጂ ወርዶና ዘቅጦ ወደ መንደር ከዚያም ቤተሰብ ውስጥ
ይወሸቃል፡፡ ‹ፊደል ቆጥረናል› ያሉ በአሜሪካ ሳንሆዜ፣ ኮለምበስ፣ ሚኔሶታ የሚገኙ አብዛኛው ‹የኛው
ጉዶች› ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ናቸው፡፡ የድንቁርናውን ጥልቀት የበለጠ ያከፋው ደግሞ ጎሠኞቹ ጠባብነቱን
የሚያራምዱት በክርስትና ስም መሆኑ ነው፡፡ የጎሣ ቡድኖች ትልቁን አገራዊ ሥዕል ከሚያስተውለው
ኢትዮጵያዊ የበለጠ ተቆርቋሪነት አለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ በእጅጉ ተሳስተዋል፡፡ ይህ ቢሆንማ ኖሮ ለአንድ
ጎሣ ጥብቅና ቆመናል/ጎሣውን እንወክለዋለን የሚሉ ለቁጥር የሚያታክቱና እርስ በርሳቸው በበጎ የማይተያዩ
ቡድኖች ባልተፈለፈሉ ነበር፡፡

የጎሣ አደረጃጀት በባህርይው አግላይ በመሆኑ እጅግ አስከፊ የሆነ ገጽታውን (አገርንና ሕዝብን በማዋረድ፣
ለዘመናት የተገነቡ መልካም እሴቶችን በማጥፋት፣ ኹለንተናዊ ድቀትና ውድቀት በማስከተል፣ ለርስ በርስ
ግጭት መንስኤ በመሆን ብሎም የአገር ህልውና ራሱ በቋፍ እንዲሆን በማድረግ ወዘተ.) አገር-በቀል አሸባሪ
በሆነው የሕወሓት አገዛዝ እስኪያቅለሸልሸን አይተነዋል፡፡ ሌላ ዙር በባለወር ተረኞች እንሞክረው ካልተባለ?
በስመ አብ በል አትሉኝም፡፡ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ይህንን ምድራዊ ገሃነም በኢትዮጵያ ምድር ለመድገም
አድፍጠው የሚጠባበቁ እንዳሉ ግን መዘንጋት የለብንም፡፡ የጎሣ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያዊነት ያደርሳል ማለት
ከወያኔ ‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ› ያልተለየ መካን አስተሳሰብ ነው፡፡ ጉምን እንደመዝገን ነፋስን እንደመጐሰም
ያለ፡፡
ማስተዋሉን ይስጠን፡፡

Filed in: Amharic