>
5:01 pm - Tuesday December 2, 5490

"የለማ ቡድን ሳይዘናጋ ያልተቋረጠ የህዝብ እምቢተኝነትን እንደ ነዳጅ እየተጠቀመ ትግሉን ማፋፋም ይኖርበታል" (ኤርሚያስ ለገሰ)

“ጠቅላይነት” ለምን አላማ??
የዶክተር አቢይ በኢህአዴግ ሊቀመንበርነት መመደብ ከተሰማ በኃላ ስሜቴን እንዴት ልግለፅ ብዬ ሳስብ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ የለማ ቡድን ያደረገውን ተጋድሎ አለማድነቅ የሚቻል አይደለም። ስልጣኑን ለማግኘት ረጅም መንገድ ተጉዟል። ይህ በህውሓት ታሪክ ውስጥ ያልተለመደ ክስተት ነው። የውስጠ ዴሞክራሲው በበሰበሰበት ሁኔታ የተደረገው የሞት ሽረት ትንቅንቅ በፓርቲው ታሪክ ላይ ትልቅ አሻራ የሚያሳርፍ ነው።
አሁን ጥያቄው “የለማ ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትርነትን የፈለገበት ዋነኛ አላማ ምን ሊሆን ይገባል?” የሚለው  ነው። የለማ ቡድን ሽንጡን ገትሮ እሰጥ አገባ ውስጥ የገባው መቋጠሪያውን ምን ለማድረግ አስቦ ነው። የተካሄደው የአልሞት ባይነት ተጋድሎ ቀጣይ ተግባራት ምን ሊሆኑ ይገባል የሚለው መነሳት ይኖርበታል። ይህ የለውጥ ሂደት የፈጠረው የኃይል አሰላለፍ አዎንታዊ እና አሉታዊ ጐኖቹ ምን እንደሆኑ መተንተን ያስፈልጋል። የሚካሄደው ለውጥ መሰረታዊ የፓሊሲና የመርህ ለውጥ ያመጣል ወይ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል። ለዛሬው በዚህ አጭር መጣጥፍ የለውጥ ዋነኛ አላማ ሊሆኑ ይገባሉ ካልኳቸው ውስጥ ሶስቱን በቅደም ተከተል ለማንሳት እሞክራለሁ።
                     ***
#አላማ አንድ:- ከኢህአዴግ ጋር በህጋዊ መንገድ ፍችውን መፈፀም
ለማንም ግልፅ ሆኖ እንደሚታየው በህዉሃትና በራሱ አምሳያ በፈጠራቸው ድርጅቶች ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ምክንያት የፓርቲዎቹ ውስጣዊ ትስስር ብቻ ሳይሆን በጋራ የመኖሩም ሁኔታ እየተፍረከረከ ሄዷል። በለማ ቡድን የሚመራው ኦህዴድ “የመደብ እንጂ የብሔር ጭቆና የለም!” በማለት የርዕዮተ-ዓለም ለውጥ ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በቤተመንግስት ግምገማ ተወጥሮም ቢሆን 28ኛ አመት  የልደት በዓሌ ብሎ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ የብሔር ጭቆና የሚለውን እርግፍ አድርጐ ትቶታል። በዚህ የፖለቲካ አቋሙ ከሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች ጋር የሐሳብ አንድነት እንደሌለው በግልጽ አመላክቷል።
በዚህ ተከታታይ አቋሙ በለማ ቡድን የሚመራው ኦህዴድ በኢህአዴግ ዣንጥላ ውስጥ የሚቆይበት አንዳችም መተክላዊ መሰረት እንደሌለው አሳይቷል። በዚህ ምክንያት ኢህአዴግ የሚባለው የውሸት ዣንጥላም በአንድ አስደንጋጭ እሳተ ገሞራዊ ፍንዳታ ዋዜማ ላይ እንዲገኝ አድርጐታል። በመሆኑም ይህ አፋኝ የሆነ የአገዛዙ ስልት የሚሽቀነጠርበት ጊዜ እየመጣ ነው። በህውሓት የሚመራው ግንባር ጊዜውን ጠብቆ ተፈጥሮአዊ ሞቱን ሊሞት መቃረቡን አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ያመለክታሉ።
 ከዚህ በተጨማሪም ቲም ለማ ሌሎች የበታችነት ስሜት የሚፈጥሩ ትርክቶችንም አሽቀንጥሮ በመጣል ለሩብ ክፍለ-ዘመን እንደ መንገድ ላይ ጭቃ ሲረግጡት የነበሩትን ህዉሃቶች ኩምሽሽ አድርጓል። በፈጣሪው ህውሓት እና በሁለቱ ተፈጣሪዎች  ላይ የሞራል የበላይነት መጐናፀፍ ችሏል። እርግጥ ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ የብአዴንና ደኢህዴን አባላት የለውጥ ሀይል ሆነው ከህውሓት በተቃራኒ መቆማቸው ተረጋግጧል።
 ይሄ የለማ ቡድን ውሳኔ የህውሃት ደጃፍ በተለይም በፌዴራልና በመቀሌ የሚገኘውን ካድሬ ወጥ በወጥ አድርጓል። ካድሬዎቹና የፌስቡክ አለቆቻቸው ቋንቋ ቀይረው እርስ በራስ መናጨትና መፅናናት ጀምረዋል። አልፎ ሄዶም አንዳንዶቹ የገቡበትን እንካ ሰላንቲያ ተተርጉሞ በመኮምኮም ላይ እንገኛለን።
በሌላ በኩል የለማ ቡድን አብዛኛው ኢትዬጲያዊ በተስፋና በተከፈተ ልብ መቀበሉ የአገዛዛቸው ፍፃሜ መዳረሱን ስለተረዱ የስም ማጥፋት ዘመቻውን በተቀነባበረ መንገድ ቀጥለውበታል። “ፕሮፌሰር ጄኔራል” ሳሞራ የኑስ ባለቤት በሆነበት ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ) ሙሉ ወጪ የሚንቀሳቀሰው ዛሚ ሬዲዬ “ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ፓርላማ ተገኝቶ ማፅደቅ ያልፈለገ ህዝበኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን እንዴት የግብፅን ተጽእኖ ሊቋቋም ይችላል?” በማለት የጠነሰሱትን ሴራ ግላጭ አውጥተዋል። በአሮጌ ጨርቅ ላይ አሮጌ እራፊ ለመለጠፍ ያላቸውን ፍላጐት በአደባባይ ቢገልጡም ለጊዜው አልሳካላቸውም። ርግጥም አሁን ዶክተር አቢይ የድርጅቱ ሊቀመንበርና  ጠቅላይ ሚኒስትር መሆኑን ሲያውቁ ምን እንደሚውጣቸው ክልተ ብቻ ድምፅ ያገኘው ደብሪጽ ብቻ ነው የሚያውቀው።
                          ***
#አላማ ሁለት: ህውሓትን ገዝግዞ መጣል
ህውሓት የጠቅላይነት ቦታውን አሳልፎ የሰጠው ከውስጣዊ ፍላጐት በመነጨ እንዳልሆነ ይታወቃል። በዋናነት የሕዝቡ እምቢተኝነትና ተቃዉሞ ከቁጥጥሩ ውጪ በመውጣቱ ነው። በማስከተል ምእራባውያን በተለይም አሜሪካ ያሳደረችበት ጫና መዘዙ የማያልቅ መሆኑን በመረዳት ፍራቻ የወለደው ነው። የምስራቅ አፍሪካ ጂኦፓለቲካዊ ሁኔታ በመቀየሩ አሜሪካኖቹ በቀላሉ እንደሚከዷቸው ወለል ብሎ ታይቷቸዋል። በግልፅም እየታየ ያለው አቋም ህውሓትን አደጋ ላይ የሚጥል ሆኗል።
መደጋገም ባይመስልብኝ የለማ ቡድን ጠቅላዩን የሚይዘው ህውሓትን ለመለወጥ ከሆነ መሰረታዊ ስህተት ይሰራል። የሕዝቡን ትግል ማፈን የማይወጣው ድጥ ውስጥ ተነክሮ በአፍጢሙ ሊደፋ ይችላል። ህውሓት የሚለወጥ ድርጅት አይደለም። የማይለወጥበት መሰረታዊ ምንጩም ፓርቲው የማይማር ድርጅት መሆኑ ነው።ያረጀው አገዛዝ ሁለንተናዊ እይታ በሌላቸው ዘረኞች የተሞላ ስብስብ ነው።
 እንደ ልምዱ ቢሆን ኖሮ በአንድ አገር ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ሲመጣ ለውጡ አስቀድሞ መንካት የሚገባው ስልጣኑን የተቆናጠጡት መሪዎችን ነው። በመጀመሪያ መሪዎች መለወጥ አለባቸው። በህውሓት ሁኔታ ግን “ ህዝባዊ ማእበሉ” የአገዛዙን መሪዎች አለወጠም። ለመማር ዝግጁ ሳይሆኑ ደግሞ መለወጥ አይቻልም። ጠመንጃ የስልጣን ማግኛና ማቆያ ያደረገ ስርአት የሚማር ከሆነም በመቃብሩ ላይ ነው።
 ስለዚህ የለማ ቡድን ፓለቲካዊ ሞቱን የተጐናፀፈውን ህውሓት ገዝግዞ በመጣል አወዳደቁን ማሳመር አለበት። ዋና ዋና ከሚባሉ ፓለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ የደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ስልጣኖች የህውሓት ካድሬዎችን ማንሳት ይኖርበታል። በተለይም የኢታማዦር ፣ የደህንነት ፣ የፌዴራል ፓሊስ፣በፓርላማው የመንግስት ዋና ተጠሪ፣ የውጭ ጉዳይ፣ ኢኮኖሚና ፋይናንስ የበላይ ሹመትና ሚኒስትርነት የህውሓት ካድሬዎች ደጃፉ እንዳይደርሱ ማድረግ ያስፈልጋል። የቻይና እና የአሜሪካ አምባሳደር ሹመትም በለማና ገዱ ቡድን ቁጥጥር ስር መዋል ይኖርበታል።
እርግጥ እንደ ቆሰለ አውሬ ሁሉንም ለመንከስ የሚሯሯጠውን ህውሓት በአንድ ጊዜ ከስልጣኑም ከሀብቱም ማባረር ከባድ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የተወሰኑ ስልጣኖችን ማካፈሉ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ፕሬዝዳንትነቱን ከዶክተር ሙላቱ ተሾመ በማንሳት ለዶክተር አርከበ እቁባይ አሊያም አባይ ፀሀዬ መስጠት ተገቢ ይሆናል። የባህልና ቱሪዝም፣ የወጣቶችና ስፓርት፣የሴቶችና ህፃናት፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም የአሳ ሃብት ሚኒስትርነትን ለህውሓት እስከ ዛሬም ተሰጥቶት ስለማያውቅ አሁን ቢሰጠው ቅሬታ የሚያስነሳ አይሆንም።
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የደብረጺዬን ለጠቅላይነት ሲወዳደር ሁለት ድምፅ ማግኘት በጥናት የተሰራ መሆኑን አምናለሁ። ህውሓቶች በሙት መንፈስ ውስጥም ሆነው ዛሬን ተሻግረው የነገን ስልጣን እየተመለከቱ በመሆኑ መጥፎ ሁኔታ (ፕሪሲደንስ) ትተው ማለፍ አልፈለጉም። አንዳንድ የዋህ ታዛቢዎች እንዳሰቡት ህውሓቶች ባለማወቅ የተነሳ የሚፈፅሙት ከመሰላቸው ተላላ ከመሆንም አልፈው አውቆ አጥፊ ሆነዋል። አገዛዙ ከአነሳሱ ጀምሮ በተንኮል ተጠንስሶና በተንኮል ስራ ተክኖ የተወለደ ሸረኛ ስርአት መሆኑ አልገባቸውም። በተጨማሪም ህውሓቶች ተንኮልና ሸር የሚያስቡትም ሆነ የሚፈፅሙት በቡድን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
                        ***
#አላማ ሶስት:- ሕዝባዊ ትግሉን አጠናክሮ ማስቀጠል
ባለፈው መጣጥፌ እንደገለጥኩት የለማ ቡድንን ከላይ እና ከታች በሚነድ እሳት የገና ዳቦ ለማድረግ የሚደረገው መቀናጆ ፊት ለፊት ወጥቷል። በእኔ እምነት ቡድኑ ለሚፈለገው አላማ ትክክለኛ ስትራቴጂ እና ስልት እስከተከተለ ድረስ ዳቦው የበለጠ በስሎ ይወጣል እንጂ የሚቃጠልበት ነባራዊ ሁኔታ የለም።
ተደጋግሞ እንደተገለጠው ህዝባዊ ማእበል የፈጠረውንና የሚመራውን ሐይል በቀላሉ “አስብቶ ማረድ” የሚቻል አይደለም። አልፋ እና ኦሜጋው የሕዝብ አልገዛም ባይነት እና እምቢተኝነት በመሆኑ ነው። የህውሓትን ፍልስፍና፣ የፓለቲካ እምነትና ፕሮግራም ህዝቡ ላለመቀበል ያሳየው ህዝባዊ ማዕበል በውስጡ ዳብሮ የኖረው የሞራል እሴት የፈጠረበት ጠንካራ እምነት ነው።
 አንዳንድ ሀይሎችም የውስጣቸውን ጥላቻ አምቀው እንደ እስስት የሚለዋወጡት የለማ ቡድንን የፈጠረው ህዝባዊ ማእበሉ መሆኑን ጠንቅቀው በመረዳታቸው ነው። ከለማ ቡድን ጋር መላተም ጭላንጭል ተስፋ ከሰነቀው ሕዝብ ጋር መጋጨት እንደሆነ ጠንቅቀው አውቀውታል። ውስጥ ለውስጥ አንድ ጊዜ ከሀይማኖት ጋር ሌላ ጊዜ ከትምህርት ማስረጃ ጋር አያይዘው የከፈቱት ዘመቻ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
 አሁን በደረስኩበት ደረጃ ልሰማው የማልወደውና ለግንዛቤዬ እንደ ስድብ የምቆጥረው የሰዎች ክርክር “ የለማ ቡድን የትግራይ ነፃ አውጪ ተልእኮ ፈፃሚ ነው” የሚለው ነው። መልሼ ልድገመውና የለማ ቡድን  የሕዝቡን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመድፈቅ ከህውሓት ጋር እያሴረ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ራሳቸው ከህውሓት በላይ በሴራ ፓለቲካ የታመሙ  ናቸው።
በሌላ በኩል የለማ ቡድን ስልጣን አገኘሁ ብሎ ሕዝባዊ ትግሉ እንዲቋረጥ አሉታዊ ሚና ከተጫወተ በራሱ ጊዜ እድሜውን እያሳጠረ ነው። ቡድኑ ከሕዝብ ፍላጐት በተቃራኒ ማሰብ ከጀመረ በፍርሃት ስጋት ይዋጣል። በፍርሃት መዋጥ ከጀመረ ደግሞ ሕዝብን በጠላትነት ማየት ይጀምራል። ይህም ባልተጠበቀ ሁኔታ አለመደማመጥን በማምጣት እልቂትን ሊጋብዝ ይችላል። በሂደትም በቡድኑ እና ሕዝቡ መካከል የባቢሎን ግንብ ተገንብቶ አሳዛኝ ሁኔታ ይፈጠራል። በመሆኑም የለማ ቡድን ያልተቋረጠ የህዝብ እምቢተኝነትን እንደ ነዳጅ እየተጠቀመ ትግሉን ማፋፋም ይኖርበታል።
Filed in: Amharic