>

የአክሱም ሙስሊሞች ሰቆቃ (በአህመዲን ጀበል)

የአክሱም ሙስሊሞች ሰቆቃ

(የሙስሊሞች ጉዳይ መጽሄት የመጀመሪያ እትም በአህመዲን ጀበል የተጻፈ የጉዞ ማስታወሻ)

  በየጊዜው የምሰማውን የሙስሊሞች ሮሮ ምን እንደሚመስል ለመታዘብ እየጓጓሁ ወደ ሙስሊሞች መስገጃ ሥፍራዎች ሄድኩ፡፡ በከተማው መስጊድ መስራት እንደተከለከሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የማርያም ሀገር ነች፣ የሙሴ ጽላት አለባት፣ ታሪካዊቷ የጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያንም አለባት›› በሚል ሰበብ መስጊድ መስራት እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ከተራ ሙስሊሞች አንስቶ እስከ የዞኑ መጅሊስ መሪዎች ገለፃ አደረጉልኝ፡፡
በከተማው ትናንሽ ወቅፍ የተደረጉ መስገጃዎች 13 አካባቢ ይደርሳሉ፡፡ እነዚህም ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው አንዱን አልያም ከሱቃቸው አንዱን ክፍል በመስገጃነት ሰጥተው ይሰገድባቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በሼኽ መሀመድ ሀጎስ ወቅፍ የተሰጠው መስገጃ አንዱ ነው፡፡ ሀያ ሰው አካባቢ ያሰግዳል፡፡ በራሳቸው ግቢ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ሌላኛው ጁሙዓ የሚሰገድበት ‹‹ሱቅ መስጊድ›› የሚሉት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ እንዲሰገድበት ወቅፍ ሰጥተው ነው የሚሰገድበት፡፡
ቢበዛ 60 ሰዎችን ብታስተናግድ ነው፡፡ ስለምትሞላ በበረንዳዋና በሱቆቹ መካከል ባለ ቦታ በኮሪደር ላይ ይሰገድባታል፡፡ አሰጋጁ ወጣት ሼኽ ሙሐመድ አወል ያቀራል፤ ያሰግዳል፡፡ ከአሊፍ እስከ ኪታቦች ያቀራል፡፡ ጠዋት ከሱብሂ በኋላና መግሪብና ዒሻ መሀል ጥቂት ሰዎችን ኪታብ ያቀራል፡፡ ጠዋትና ከሰዓት ህፃናትን ቁርአን ያቀራል፡፡ ከአስር በኋላ ሴቶችን ያቀራል፡፡ የጀመዓ ሶላትንም የሚያሰግደው ራሱ ነው፡፡ የሚገርመው ሙሉ ቀን እንደዚያ እየታገለ የአካባቢው ሙስሊሞች አዋጥተው በወር ሦስት መቶ ብር ነው የሚከፍሉት፡፡ ዳዕዋ ማድረግ እንደምፈልግ ፈቃድ ጠይቄ ጥቂት አደረግኩ፡፡ ሰዉ የዳዕዋ ጥማት እንዳለው ይታያል፡፡ ኢስላምን ሲወዱ ለጉድ ነው፡፡ አንድ አባት እያለቀሱ መጥተው እጄን ሳሙኝ፡፡ ‹‹ህዝቡ ጃሂል ነው፡፡ ምን ያውቃል? እባካችሁ ኑና አስተምሩን! ከቻልክ በመግሪብና ዒሻም መሀል ድገም›› አሉኝ፡፡ ሰው በሰልፍ እጄን ሊስም ተሰባሰበ፡፡ ሳላስበው ለዝየራ መከበቤ አስገረመኝም፤ አስደነገጠኝም፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞኝም አያውቅም፡፡
በመግሪብና ዒሻ መሀልም ዳዕዋ አደረግኩ፡፡ ከቅድሙ ሰው ሞልቷል፡፡ ከዩኒቨርስቲ ጥቂት ተማሪዎችም ነበሩ፡፡ ከሶላት በኋላ ስላሉበት አስደንጋጭና አሳዛኝ ሁኔታ ሲነግሩኝ ወላሂ ሆዴ ባባ፡፡ ከሱብሂ በኋላ በሼኽ ሙሐመድ ሀጎስ ወቅፍ ወደተደረገው መስጊድ አመራሁ፡፡ አምስት ሰዎች ኪታብ ይቀራሉ፡፡ ሽማግሌዎች ደግሞ ዱዓ ያደርጋሉ፡፡ የዞኑ መጅሊስ ፀሐፊ ሼኽ ሙሐመድ ሐሰንም እዚያው ነበሩ፡፡ ስለ አክሱም ሙስሊሞች አሳዛኝና አሳማሚ ችግር ተረኩልኝ፡፡ በሀገሪቷ ህገመንግስት ቢኖርም መብት ብሎ ነገር ማግኘት እንዳልቻሉ ነገሩኝ፡፡ ቤተክህነት ብዙ ጫና እንደምታስደርግባቸው ተረኩልኝ፡፡ የአክሱም ከተማ ሙስሊም ብዛቱ አስራ አምስት ሺ እንደሚደርስ ነገሩኝ፡፡ በ 2005 የስታቲስቲክስ ባለስልጣን ያወጣው መጽሐፍ የአክሱም ህዝብ 47,320 እንደሆነ ይተርካል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሆነው 75% (35,490) እንደሆነ ይናገራል፡፡
በደጋ ሀሙስ ሰፈር ወይዘሮ ሸምሲያ ሼኽ ሷሊህ የኢቢዩ ሕጻናትን ቁርአን እንደሚያቀሩ ወዳጄ ተረከልኝ፡፡
ከ 120 በላይ ሕጻናትን ቁርአን እንደሚያቀሩና ተማሪዎቹ በወይዘሮዋ (ዑስታዟ) ቤት ዉስጥ የራሳቸውን ቁርአንና ወንበር ይዘው እንደሚመጡ ሰማሁ፡፡ ከደርግ ዘመን በፊት ሙስሊሙ መሬት መያዝ እንደማይችልና ቤት እንደሌለው፤ ሙስሊሙ ቤት ሊይዝ የተቻለው በደርግ ዘመን እንደሆነ ሽማግሌዎች አብራሩልኝ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ሙስሊሙ መሬትም ቤትም እንዳይኖረው ይቃወሙ የነበሩትን የቤተክህነት ቀሳውስት በወቅቱ ይፈራ የነበረው የደርጉ መሪ አፈወርቅ አለምሰገድ ጠራቸው፡፡ ለሙስሊሙ የቤት መስሪያ ቦታ ቢሰጣቸው ይቃወሙ እንደሆነም ጠየቃቸው፡፡ በጣም ይፈራ ስለነበር እንደማይቃወሙ ገለጹለት፡፡ ‹‹ብትቃወሙ ኖሮ በአደባባይ ነበር የምሰቅላችሁ›› ሲል ተናገራቸው፡፡ ከዚያም ለሙስሊሞቹ በ 30 ብር መሬት መራላቸው፡፡ ከዚያም መሬት መያዝ ቻሉ፡፡
የንግድ ቦታውን ደግሞ ጣሊያን ነበር ለሙስሊሞች የሰጠው፡፡ አሳዛኙን የአክሱም ቅኝቴን ጨረስኩ፡፡ በአንድ መስገጃ ቦታ ሳለሁ አንድ አባት መጡና ‹‹ቶሎ ከአክሱም ውጣ፣ በኋላ ይይዙሃል፣ መረጃ እንድታወጣ አይፈልጉም›› አሉኝ፡፡ የበረራ ሰዓቴ ስለደረሰ ወደ አፄ ዮሐንስ 4ኛ አየር ማረፊያ በባጃጅ አመራሁ፡፡ አውሮፕላኑ የሚነሳው 2፡50 ላይ ነበር፡፡ እቃዎቼን አስፈትሽ ጀመር፡፡ ሁሉንም ከፍተው አዩ፡፡ ፈታሿ ወክማንና ካሴቶች አየችና ወክማኑን አወጣች፡፡ ‹‹ምንድ ነው?›› ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ለጉብኝት እንደመጣሁ ነገርኳት፡፡ ወክማኑን ከፈተችው፡፡ በሁሉም ቦታ ስጎበኝ በወክማን እየቀዳሁ ነበርና እንዳጋጣሚ ሆኖ የአክሱም ሀውልት ጉብኝቴ ግቢ የተቀዳው ሆነ፡፡ ገባሁና መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ በአየር ማረፊያው የሚሸጡት በጠቅላላ የቤተክርስቲያን መገልገያዎች ናቸው፡፡ በአንድ ጎን ላይ ተምርና ማር አየሁ፡፡ ተምሩ የደረቀ ነው፡፡ የታሸገውን በ10 ብር ገዛሁ፡፡ ማሩ ግን በጣም ነጭና ወተት የመሰለ ነበር፡፡ ኪሎውን በ70 ብር ገዛሁና ጥበቃዬን ቀጠልኩ፡፡
2፡50 አለፈ፡፡ አንድ የአየር ማረፊያው ደህንነት ሰራተኛ መጣና ‹‹ውስጥ ትፈለጋለህ!›› አለኝ፡፡ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ ውስጥ ‹‹በኤክስሬይ ስናየው ሻንጣህን ደግመን መፈተሸ እንዳለብን ስለተሰማን ነው፡፡ ይቅርታ፡፡ ሻንጣህን ክፈት›› አለኝ፡፡ ግርም አለኝና ያቺ ወክማን ደግሞ ልትደመጥ ነው ብዬ በልቤ አሰብኩ፡፡ ሁሉንም አወጡና በጥንቃቄ ፈተሹና አመስግነው መለሱልኝ፡፡
Filed in: Amharic