>

የገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣... ደበበ ሰይፉ 18ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ (አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ 18ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ

ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ያረፈው ከዛሬ 18 ዓመታት በፊት (ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም) ነበር፡፡
ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ከበጅሮንድ ሰይፉ አንተንይሥጠኝ እና ከወይዘሮ የማርያምወርቅ አስፋው ባለውለታው፣ የማንነቱ መገኛ፣ የዕውቀቱ መፍለቂያና መድመቂያ መሆኗን በግጥሙ ባሞካሻት ይርጋለም ከተማ ተወለደ፡፡
ደበበ ፊደል የቆጠረው በቄስ ት/ቤት ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም መዝሙረ ዳዊትን አጠናቆ ወደ ዘመናዊ (‹‹አስኳላ››) ት/ቤት ገባ፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ይርጋለም ከተማ በሚገኘው ራስ ደስታ ት/ቤት ተማረ፡፡
ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮከበ ፅባህ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ት/ቤት አጠናቀቀ፡፡ በትምህርቱ የላቀ ውጤት እያስመዘገበ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (ያሁኑ Addis Ababa University) ገባ፡፡ የጀመረውን የቢዝነስ ትምህርት ትቶ ወደ ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ተዛወረ፡፡
በ1965 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ተቋም በመጀመሪያ ዲግሪ በማዕረግ ተመረቀ፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላም በእንግሊዝኛ ስነ-ጽሑፍ (English Literature) ሁለተኛ ዲግሪውን (MA) በማዕረግ ተመረቀ፡፡
ደበበ በልጅነቱ መጽሐፍትን አንብቦ አይጠግብም ነበር ይባላል፡፡ እስከ ግንቦት 1985 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግሏል፡፡ ከምርምር ስራዎቹም መካከል …
– የትያትር ጥበብ ከጸሐፊ ተውኔት አንፃር
– ደራሲው በአብዮት አውድ
– ዋዜማ ጦርነት ግጥሞች
– ሕዝባዊ ስነ-ግጥም
– Profile of Peasantry in Ethiopian Novels
– A Critical Analogy of Ethiopian Novels
– Foreign Scholars on Amharic Novels
– A Critical Analogy to Amharic Poetry
– The Need for Marxist Approach in the Teaching of Literature
– Post-Revolution Ethiopian Theaters … የሚሉትና ሌሎች ስራዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡
ከተውኔት ስራዎቹ መካከል ደግሞ … 
• እናትና ልጆቿ
• ከባህር ወጣ ዓሳ
• ሳይቋጠር ሲተረተር
• የሕፃን ሽማግሌ … ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ክፍተት፣ እድምተኞቹ፣ ጋሊልዮ ጋሊሊ፣ ማክቤዝ እና ፓሪስ ኮሚዬን የተባሉ ስራዎቹ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትያትር ዘርፍ ያበረከታቸው የትርጉም ስራዎቹ ናቸው፡፡
ለሕትመት ከበቁት የደበበ መጽሐፍት መካከል ደግሞ ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮች (1971)፣ የትያትር ጥበባት ከጸሐፊ ተውኔት አንፃር (1973)፣ ፅጌሬዳ ብዕር (ከሌሎች ደራስያን ስራዎች ጋር – 1977)፣ የብርሃን ፍቅር ቅጽ 1 (1980) እንዲሁም ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ (የብርሃን ፍቅር ቅጽ 2) ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ከግንቦት 1985 በኋላ የማስተማር ስራውን አቁሞ ለሰባት ዓመታት ያህል ከቤት ዋለ፡፡
ሲያሰቃየው የነበረው የመገጣጠሚያ አካላት ያለመታዘዝ ችግር በተወለደ በ50 ዓመቱ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ለሕልፈት ዳረገው፡፡ ስርዓተ ቀብሩም ሚያዚያ 17 ቀን 1992 ዓ.ም በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፀመ፡፡ በወቅቱም በርካታ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ስለደበበ ታላቅነት ደጋግመው ጽፈዋል፡፡
[ማሳሰቢያ … ይህን ታላቅ የጥበብ ሰው ‹‹አንተ›› ብዬ መጥራቴ ለስብዕናውና ለስራዎቹ ባለኝ የስሜት ቅርበት ምክንያት እንጂ ደበበን ካለማክበር እንዳልሆነ ይታወቅልኝ!]

ጠብቄሽ ነበረ …

መንፈሴን አንፅቼ፣
ገላዬን አጥርቼ፣
አበባ አሳብቤ፣
አዱኛ ሰብስቤ፡፡
ጠብቄሽ ነበረ
ብትቀሪ ጊዜ …
መንፈሴን አሳደፍኩ፣
ገላዬን አጎደፍኩ፡፡
አበባው ደረቀ፣
አዱኛው አለቀ፡፡
ብትቀሪ ጊዜ …
የጣልኩብሽ ተስፋ፣
እኔን ይዞኝ ጠፋ፡፡ (ደበበ ሰይፉ – 1962 ዓ.ም)
✍️✍️✍️
ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic