>

ዶ/ር አብይ እና ህወሓቶች፡ ለይቶ ማስር ወይስ አብሮ መስራት? (ስዩም ተሾመ)

ኢህአዴግ ውስጥ ስለተደረገው አመራር ለውጥና ለውጡ የተካሄደበትን ሁኔታ አስመልክቶ የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ ያደረገው በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ለመግታት እንደሆነ ሲገልፁ ይሰማል፡፡ በሌላ በከል አንዳንድ የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎች የአመራር ለውጡ የተካሄደው በተለመደው የፓርቲው ደንብና ስርዓት እንደሆነና የአዲሱ ሊቀመንበር ምርጫ በአባል ድርጅቶች የጋራ መግባባት የተመሠረተ እንደሆነ ሲገልፁ ይሰማል፡፡ ነገር ግን፣ ሁለቱም አመለካከቶች በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ አስተያየቶች፤ አንደኛ፦ የለውጡን መነሻ ምክንያት በጥልቀት ካለመረዳት፣ ሁለተኛ፦ የአመራር ለውጡ የተካሄደበትን ሁኔታ በግልፅ ካለመገንዘብ የመነጩ ናቸው፡፡

ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ እንዲያደርግ ያስገደደው ምንድነው? በመጀመሪያ ደረጃ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ቀድሞ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተመሣሣይ ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ የአመራር ለውጥ ያደረገው ኦህዴድ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በመቀጠል ኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ ግንባር-ቀደም ሚና የተጫወተው አዲሱ የኦህዴድ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡

በመጨረሻም የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር የሆነው የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ በመሆኑም በኢህአዴግ ውስጥ የተደረገውን የአመራር ለውጥ ለመገንዘብ፤ በኦህዴድ አመራሮች እና በክልሉ ህዝብ፣ እንዲሁም በኦህዴድ እና በተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች መካከል የነበረውን ግንኙት በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት በቄሮዎች እና በኦህዴድ አመራሮች መካከል የነበረው ግንኙነት በጠላትነት ስሜት የሚመራ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም አጋማሽ በተለይ በቀበሌ፥ ወረዳና ዞን ደረጃ ላይ የሚገኙ የኦህዴድ ባለስልጣናትና የፀጥታ ሰራተኞች ህይወትና ንብረት ጠፍቷል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት መሠረት በስድስት ወር ውስጥ ብቻ 14 የፀጥታ ሰራተኞች እና 14 የመንግስት ባለስልጣናት ተገድለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በወረዳና ዞን ደረጃ የሚገኙ የኦህዴድ ባለስልጣናት ቤትና ንብረት ወድሟል፡፡ ቄሮዎች በወሰዱት ቀጥተኛ የሃይል እርምጃ የክልሉ ባለስልጣናትና የፀጥታ ሰራተኞች የህዝቡን ጥያቄ እንዲቀበሉና ከቄሮዎች ጎን እንዲቆሙ አስገድዷቸዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም መጨረሻ በዞንና ወረዳ ደረጃ የሚገኙ ኦህዴዶች ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ የቄሮዎችን ጥያቄ በመቀበል ከህዝቡ ጎን ከመቆም በስተቀር ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው በግልፅ ተናግረዋል፡፡ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ይህን ማድረግ ከተሳናቸው የድርጅቱ ህልውና ያከትማል፣ የባለስልጣናቱ ህይወትና ንብረት ይወድማል፡፡ ስለዚህ ኦህዴዶች በወቅቱ የነበራቸው አማራጭ የመኖር ወይም የመጥፋት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ኦህዴድ ከክልሉ ህዝብ ጎን ከቆመ ድርጅቱ ህልውናውን ያረጋግጣል፣ የህወሓት የበላይነት ያከትማል፡፡ ነገር ግን፣ ኦህዴድ እንደቀድሞው ተገዢ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ የህወሓት የበላይነት ይቀጥላል፣ የኦህዴድ ህልውና ግን ያከትማል፡፡

በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ነው እንግዲህ አዲሱ የኦህዴድ አመራር ወደ ስልጣን የመጣው፡፡ የኦቦ ለማ አመራር ወደ ስልጣን እንደመጣ ቀዳሚ ተግባሩ ከክልሉ ህዝብ ጎን በመቆም እንደ ፖለቲካ ድርጅት ህልውናውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ኦህዴድ ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚወስደው እርምጃ የህወሓትን የበላይነት የሚፃረር ነው፡፡ ምክንያቱም ህወሓት ከአመሠራረቱ ጀምሮ ዓላማው የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚወስደው ማንኛውም ዓይነት የለውጥ እርምጃ በህወሓት ላይ ቀጥተኛ የህልውና አደጋ ይጋርጣል፡፡

ጠ/ሚ አብይ አህመድ

በአጠቃላይ በኦህዴድ እና ህወሓት መካከል ያለው ግንኙነት የመኖር ወይም የመጥፋት ነው፡፡ ኦህዴድ ካሸነፈ የህወሓት የበላይነት ያከትማል፣ ህወሓት ካሸነፈ ደግሞ የኦህዴድ ህልውና ያከትማል፡፡ ስለዚህ አዲሱ የኦህዴድ አመራር እና ህወሓት ያላቸው አማራጭ ከመጥፋታቸው በፊት አጥፊያቸውን ቀድሞ ማጥፋት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ህወሓት በህዝቦች መካከል ያለመተማመን መንፈስና ግጭት በመፍጠር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ገድሏል፣ አፈናቅሏል፡፡ በዚህ መሠረት ዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማሳጣት ህወሓት ተቀባይነት ለማግኘት፣ ኦህዴድን ደግሞ ለማሳጣት ከፍተኛ ጥረት አድርጏል፡፡ ኦህዴድ ደግሞ በብሔሮች መካከል ያለውን ግንኙነትና የትብብር መንፈስ በማጠናከር በሀገር-አቀፍ ደረጃ ያለው ተቀባይነት ለማሳደግ፣ ህወሓትን ደግሞ ተቀባይነት ለማሳጣት ከፍተኛ ትግል አድርጏል፡፡

ህወሓት በዚህ አመት የመጀመሪያ ወራት ባደረገው 35 ቀናት የፈጀ ስብሰባ ዋና የመወያያ አጀንዳ የነበረው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ዳግም በማወጅ፣ “ህዝበኞች – Populist” ያሏቸውን የኦህዴድና ብአዴን መሪዎች ማሰርና የለውጡን ንቅናቄ መቀልበስ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት፣ በመጀመሪያ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ላይ ብቻ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ ሞከሩ፡፡ ይህ ሙከራ ከኦህዴድና ብአዴን ባጋጠመው ጠንካራ ተቃውሞ ውድቅ ተደረገ፡፡ በመቀጠል “ብሔራዊ የደህንነት ምክር” በማቋቋም በእጅ አዙር የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ ሞከሩ፡፡ በተለይ ከኦሮሚያና አማራ ክልል መስተዳደሮች ተቀባይነት በማጣቱ ምክንያት ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ፡፡

በመጨረሻም በ17ቱ ቀን የኢህአዴግ ስብሰባ ህወሓት ስልታዊ ማፈግፈግ አደረገ፡፡ በዚህ መሠረት፣ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ በአንፃሩ ‘ሁከትና ብጥብጥ ከተነሳ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ ከስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ በድርድሩ ወቅት የህወሓት መሠረታዊ ዓላማ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማወጅ ፀረ-ህወሓት አቋም የሚያራምዱና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች በማሰር የለውጡን እንቅስቃሴ መቀልበስ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከህወሓት ፍላጎትና ምርጪ ውጪ ከደኢዴን እና ብአዴን ጋር በፈጠረው ጥምረት ኦህዴድ የጠ/ሚኒስትርነት ቦታውን ያዘ፡፡

የዶ/ር አብይ መመረጥ የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን በማሰር የለውጡን እንቅስቃሴ መቀልበስ ለሚሻው ህወሓት የህልውና አደጋ ነው፡፡ የአዲሱ አመራር የመወሰን አቅምና ነፃነት የሚረጋገጠው ደግሞ የህወሓትን የበላይነት በማስወገድ ነው፡፡ በመሆኑም የዶ/ር አብይ ውጤታማነት የሚወሰነው የህወሓት ልሂቃን በፖለቲካና ኢኮኖሚው ውስጥ የነበራቸውን አድራጊ-ፈጣሪነት እንዲያከትም በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የዶ/ር አብይ አፈፃፀም ብቃት የሚለካው የህወሓትን የበላይነት በማስወገድ ሲሆን የህወሓት ህልውና ደግሞ በፖለቲካና ኢኮኖሚው ረገድ የነበረውን የበላይነት በማስቀጠል ነው፡፡

ህወሓቶች በተለያዩ ብሔሮች መካከል ግጭት በመፍጠር የለውጡን ንቅናቄ ለማኮላሸት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህን የማድረጉ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ ላይ የፍርሃትና ስጋት ድባብ በመፍጠር በተለይ አዲሱን የኦህዴድ አመራር ተቀባይነት ማሳጣት ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ሲሳናቸው ደግሞ በተለይ በቀድሞ ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አማካኝነት፣ እንዲሁም በመከላከያ፥ ደህንነቱ እና የፍትህ ተቋማት ላይ ያላቸውን የበላይነት ተጠቅመው አዲሱን የኦህዴድ አመራሮችን በማሰር የፖለቲካ ስልጣናቸውን እና በህዝቡ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት ለማሳጣት ጥረት አድርገዋል፡፡

የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ ህወሓቶች በሥራ አስፈፃሚው ላይ የነበራቸውን ስልጣን አጥተዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ በመከላከያና ደህንነት መዋቅሩ ላይ የነበራቸውን ስልጣን ሙሉ በሙሉ አጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት ያላቸውን የበላይነት ተጠቅመው በዜጎች ላይ የፍርሃትና ስጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መልኩ አዲሱ አመራር በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለማሳጣት ከመንቀሳቀስ ወደኋላ አይሉም፡፡ በሌላ በኩል፣ ዶ/ር አብይ ያለውን የፖለቲካ ስልጣን በመጠቀም በህዝብ ላይ ፍርሃትና ሽብር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን የህወሓት አመራሮችና ልሂቃን ማሰር ይችላል፡፡

በዚህ መሠረት ህዝቡን ከህወሓቶች እኩይ ተግባር በመከላከል ተቀባይነቱን ማሳደግ ይችላል፡፡ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ከተሳነው ግን ተቀባይነቱንና የመወሰን ስልጣኑን ያጣል፡፡ ህወሓቶች የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን ማስር የተሳናቸው፤ አንደኛ፦ አመራሮቹ በህዝብ ዘንድ አንፃራዊ ተቀባይነት ስለነበራቸው፣ ሁለተኛ፦ አመራሮቹን ለማሰር የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ ስላልነበራቸው ነው፡፡ ቀንደኛ በሆኑ የህወሓት አመራሮች ላይ ማስረጃ ማግኘት ግን በጣም ቀላል ነው፡፡ በመሆኑም አፍራሽ በሆኑ ተግባራት የተሰማሩና ሊሰማሩ የሚችሉት የህወሓት አመራሮች በማሰር ለፍርድ ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህን በማድረግ የህወሓትን የበላይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ማስወገድ ይችላል፡፡

Filed in: Amharic