>

ኩ ን ታ ፡ ኪ ን ቴ — እ ና — አ ፍ ሪ ካ ዊ ነ ት ! (አሰፋ ሀይሉ)

…… በመጨረሻ ባርያ ፈንጋዮቹ  ያወጡለትን  ስሙን  ተቀበለ ፡፡ ‹‹ቶቤ ነኝ!›› አለ፡፡ እና ግርፋቱ ቀረለት…..  ተዘረረ፡፡
 ዋ አንቺ አፍሪካ!
 ዋ እማማዬ አፍሪካ!
 ዋ አንቺ ያልታደልሽ ምድር! ተፈንጋይሽ የራስሽ ልጅ፡፡ ፈንጋይሽ የራስሽ ልጅ፡፡ አስጠርናፊሽ የገዛ ራስሽ ልጅ፡፡ ገራፊሽ የራስሽ ልጅ፡፡ ባርነትሽ ችግርሽ ሰቆቃሽ የራስሽ፡፡ አ ፍ ሪ ካ ዬ ፡ እ ማ ማ ፡ ሆ ይ – ሠላም፣ እና ምህረት፣ አንድነት እና አይበገሬነት፣ ታላቅነት እና ወገንተኝነት – ባንቺ ዘንድ ይሁን!!!
                        **********
‹‹ሠረሠርህን ያውጣው!›› ተብዬ መሰደቤን አልክድም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ አፍሪካዊ ነኝ፡፡ ተሰድቤም፣ ተረግሜም፣ ተመዝልጌም፣ ተገርፌም ያደግኩ – ንፁህ ኢትዮጵያዊ፡፡ ግን ኢትዮጵያዊ የሚገረፈው ለራሱ ነው፡፡ ጨዋነትን እንዲላበስ ነው፡፡ እንዲያከብር ነው፡፡ ባህሉን እንዲላበስ ነው፡፡ እንዲኖርበት እንዲጠቀምበት ነው፡፡ ‹‹አሣዳጊ የበደለው!›› ወይም ‹‹ያልተቆነጠጠ›› ማለት እኮ ‹‹ሥድ አደግ›› ማለት ነበር እኮ በቋንቋችን፡፡ እና ግርፋትም ሆነ እርግማን – ለእኛ ለአፍሪካውያን – ምርቃታችን ነው፡፡ ጥሩ የተመኙልን የሚሰጡን – የማይረሳ የህይወት ስጦታ፡፡ ልጅህን ባጠፋ ጊዜ ከመግረፍ ቸል አትበል – ኋላ በጎለመሰ ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም – እንደተባለ፡፡
ይሄኛው ግን ‹‹ሠረሠርህን ያውጣው!›› የሚለው እርግማን እንደክፉ ንግርት ሆኖ አንድም ጠብ-ሣይል የደረሰበት የአፍሪካ ልጅ ነው፡፡ ይሄ – የኩንታ ኪንቴ ታሪክ ነው፡፡ እውነተኛ የአፍሪካዊነት ማንነት አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ ማሳያ ነው፡፡ የኩንታ ኪንቴ ታሪክ ለሁላችን አፍሪካውያን የተደበቀ ታሪክ አይደለም፡፡ የማንነታችን ጥቁር ነጥብ ነው፡፡ ይሄም የኩንታ ኪንቴ ታሪክ የእኔ፣ የአንተ፣ የእሱ፣ ወይም የእሷ አፍሪካውያንና አፍሪካውያት ሁሉ ታሪክ ነው፡፡ የኪንታ ኪንቴ ታሪክ – በአንድ ወይም በሌላ መልኩ – እኛን ሁላችንን ይነካል፣ ይወክላል፣ ይመስላል፣ ነውም፡፡
ይሄን አሁን ታሪኩን የምናነሳለት – እውነተኛው የአፍሪካውያን አሳዛኝ ታሪክ – ከ250 ዓመት በኋላ – ህያዋን ያለፉበትን ያውቁት ዘንድ እና ለማንነታቸው ክብር ይሰጡት ዘንድ  – እውነተኛ አፍሪካዊ ማንነታቸው የጠፋባቸውም ይፈልጉት፣ ያገኙትና ይሆኑት ዘንድ – ዳግመኛ – በደራሲው አሌክስ ሄሊ ብዕር – ‹‹ሩትስ›› በሚል ርዕስ በመጽሐፍ ታትሞ . . . እና በተመሣሣይ ርዕስ ወደ ፊልምነት በተቀየረ – ‹‹ሩትስ›› በሚለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ አማካይነት – ስላወቅነው – ስለእውነተኛው – ግን ስለምናባዊው ኩንታ ኪንቴ ነው አሁን የምናወሳው፡፡
የኩንታ ኪንቴ ታሪክ ‹‹ሩትስ›› በሚል ርዕስ በቀረበልን ፊልም ያገኘነውመ፣ ያየነው፣ ያነባንበት፣ የነካን፣ ያሳወቀን እውነተኛ የአፍሪካውያን ታሪክ ነው፡፡ ‹‹ሩትስ›› ያው ‹‹ሥሮች›› እንደማለት ነው፡፡ ወይም ‹‹ኬት-መጤነቶች››፣ ወይም ‹‹የማንነት መሠረቶች››፣ ወይም ‹‹የአንተነትህ መፍለቂያ ምንጮች››፣ ወይም ‹‹አንተን ያበቀለች የማንነት ቅንጣት››፣… እንደማለት፡፡
ኩንታ ኪንቴ አፍሪካዊ ነው፡፡ በታላቅ የውሃ ፏፏቴ ሥር የመነጨ አፍሪካዊ፡፡ ኩንታ ኪንቴ ከአራት ወንድምና እህቶቹ ጋር – በጋምቢያ ጄፉሬ በተሰኘች ትንሽ መንደር – ሶስት ሃገራትን ሰንጥቆ በሚያልፍ የጋምቢያ ወንዝ በተሰኘ ታላቅ ወንዝን በተጎራበተ ለምለም ሥፍራ – በ17መቶዎቹ አጋማሽ ላይ ተወለደ፡፡ ጁፉሬ የምዕራብ አፍሪካ ጠረፋማ መንደር ስትሆን – እስልምናን ከባህላዊ አፍሪካዊ ዕምነት ጋር ቀላቅለው የሚያራምዱ አፍሪካውያን ነዋሪዎች የሚመላለሱባት ምድር ነበረች፡፡ ኩንታ ኪንቴም እንደ ማናቸውም የጁፉሬ መንደር ነዋሪ ጀግና መሆን ይጠበቅበት ነበርና – በ15 ዓመቱ – በሃገሩ አፍሪካዊ ባህል – ራሱን ችሎ አደን እንዲያከናውን – ተፈትኖ፣ ተመርቆ፣ ወጣ በጀግንነት፡፡ ወፍን – ያለ መሣሪያ አድን ተባለ፡፡ እና አደነ፡፡ በባዶ እጁ፡፡ ያ ነበር ፈተናውው፡
አፍሪካውያን እኮ የሚያስገርም ጥበብ ነበራቸው፡፡ ገና ወደጦረኝነት የተቀላቀለን ሳተና – በሚቀልህ መሳሪያ ግደል አይደለም ይሉ የነበሩት፡፡ በባዶ እጅህ ጥረህ ግረህ በወዝህ ብላ ነው፡፡ ክፋቱ ከሌላኛው ይሻላል ይመስለኛል፡፡ ለተፈጥሮ በመቅረቡ፣ ህልውናን ለማትረፍ ዓላማ የመነጨ ከመሆኑ፣ ለተፈጥሮ ከመሳሳቱ፣ እና አንተን ከማጀገኑ ላይ ነውና ዋናው ዓላማ፡፡ እና ኩንታ ኪንቴም እንደዚያ ዓይነቱ አፍሪካዊ ጀግና ነበር፡፡ ሥነምግባርን፣ ከተፈጥሯዊነትና ከጀግንነት ጋር የተላበሰ – አይበገሬ – ትኩስ – አፍሪካዊ ጀግና ነበር – ኩንታ ኪንቴ – በ17 ዓመቱ ላይ፡፡
አዎ ነበር፡፡ ነበር ያልኩት – ወድቆ ባይሰበር ለማለት ነው፡፡ ያ የኩነታ ኪንቴ ጀግንነት አንድ ቀን – ባልተጠበቀ ሁኔታ የማይወጡበት ተከርቸም ውስጥ ገባ እና የሚያንገፈግፈው፣ የማይወደደው ነገር ሆነ፡፡ ኩንታ ኪንቴ – ልክ ለሞፈርና ቀንበር የሚሆን ሁነኛ እንጨት ሊፈልግ በተፍጥሮ ደን ውስጥ እንደሚሰማራ ያገራችን ጀግና – በጁፉሬ ጫካ ውስጥ – ይዘዋወራል – እንጨት ለመፈለግ፡፡ እንጨቱን ምን ሊያደርግበት ነው? – እንጨቱን የፈለገው – ለታናሽ ወንድሙ – ታምቡር ሊሰራለት ነው – ባህላዊ ከበሮ ሊሰራለት – ከምርጡ እንጨት፡፡
ኩንታ ኪንቴ እውነተኛ አፍሪካዊ ነው፡፡ ባህሉን ከታላላቆቹ የወረሰ፡፡ ትዑመ-ዜማውን ከወንዙ፣ ከምንጩ፣ ከራሱ አፈር ያበቀለ፣ የቀዳ፣ በክብር የተቀበለ እውነተኛ አፍሪካዊ፡፡ እና ደግሞ – ያን ነፍስ ያለው – ግን የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ፣ የማይቆጠር – አፍሪካዊ የጥበብ ትውፊት – በወረሰበት መንገድ – እርሱ ደግሞ – ለታናሽ ወንድሙ ሊያስተላልፍ ነበር – ወደጫካ የገባው – ኩንታ ኪንቴ፡፡
ግን በጫካ ያጋጠመው ምን ነበር? ኩንታ ኪንቴ የጀግንነትን ክብር ከምድሩ የተሸለም ጀግና ነው፡፡ በጫካ ውስጥ አውሬን አድኖ መያዝ የሚችል፡፡ እርሱን ያን ዕለት በዚያ ጫካ ያጋጠሙት ግን አደገኛ አውሬዎች አልነበሩም፡፡ አደገኛ ሰዎች ናቸው፡፡ እንደ እርሱ ዓይነት ጥቁር መልክ ያላቸው፡፡ እንደ እርሱ አይነት የተፈረፈረ ጥቁር ጎፈሬ ፀጉር ያላቸው፡፡ መጠሪያ ስማቸው እርሱን ካበቀለ ተመሣሣይ ባህል ተመዝዞ የወጣላቸው፡፡ እርሱኑ የመሠሉ የጋምቢያ አፍሪካውያን ናቸው – በዚያ ጫካ ያጋጠሙት፡፡
የእርሱና የእነርሱ ልዩነት ምንድነው? እርሱ ድንቅ ጥዑመ-ዜማ ለታናናሾቹ የሚሠራበትን ሁነኛ አፍሪካዊ ቅርንጫፍ ፈልጎ ጫካ የገባ መሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ ውቅያኖስን ተሻግረው ሰውን ለመፈንገል ለመጡ ነጭ የባርያ-ፈንጋዮች – ድንቅ ጉልበትና አቅም ያለውን – የሞከተ አፍሪካዊ ሰው አጥምደው – ሊሸጡ – እና ስጋቸውን በሚገኘው ቱሩፋት ሊያሞክቱ – ወደጫካ የገቡ – ከክፉ ተናካሽም አውሬ የከፉ – አደገኛ አዳኞች መሆናቸው ነበር – ብቸኛው ልዩነታቸው፡፡
አለበለዚያማ – ኩንታ ኪንቴም – አራቱም አዳኞቹም – ያው አፍሪካውያን መልክ ያላቸው ናቸው፡፡ እርሱ የአፍሪካዊነትን ኃይል አልካደም ነበር፡፡ እነርሱ ደግሞ ኃይሉን ክደዋል፡፡ እና የራሳቸውን ወገን አድነው – ይሸጡታል ለግፍ፣ በግፍ፡፡ አፍሪካውያን ናቸው – ለአፍሪካውያን መቅሰፍቶች የነበሩት፡፡ አፍሪካውያን ናቸው -ዛሬም ድረስ ወንድሞቻቸውን እህቶቻቸውን እናቶቻቸውን ወገኖቻቸውን የሚያስለቅሱት፣ አሳልፈው የሚሰጡት፡፡ እነዚህ አፍሪካውያን ናቸው – እንዲያውም የበዙት፡፡ ያሳዝናል፡፡ እጅግ በጣም፡፡ ሥራችንን መዝዘን ስንለመለከተው – አትድገሙት የሚል፣ የሚያሰቅቅ አፍሪካዊ ታሪክ ነው – ‹‹ሥሮች›› የሚለው የኩንታ ኪንቴ ታሪክ፡፡ እነዚያን እርኩሳን ደግሞ – እንዲያው ‹‹ሠረሠራቸውን ያውጣው!›› ማለት ይነስብን??!!!
ብቻ እናሳጥረው፡፡ ኩንታ ኪንቴ በቀላሉ እሺ አላለም፡፡ ጀግና ነው፡፡ ከሩ አፍሪካዊ ጀግና፡፡ በቀላሉ ለአጥቂዎቹ በጄ የማይል ጀግና፡፡ እና ታገላቸው፡፡ ሞከረ ጩኸቱና ብርታቱ – እንደ ራሔል – እንደ ዳዊት – እንደ ካሌብ – እንደ ቴዎድሮስ – መላውን አፍሪካን እስኪያዳርስ ድረስ፡፡ አልቻለም ግን ፡፡ የጭካኔ ኃይል – ከበጎነት ኃይል ይልቅ – እጀጉን በረታች፡፡ እና ለማራኪዎቹ እጁን ሰጠ፡፡ ለከሃዲዎቹ ተረታ፡፡ ተሸነፈ፡፡ እና ራሱን ሲያውቅ – ዓይኖቹ ተሸብበው፣ እጆቹ እግሮቹ ተጠፍንገው፣ ሰውነቱ በድብደባ ብዛት እየነደደ፣ ከሌሎች እንደእርሱ ሁሉ – ከሚወዱት ቤተሰባቸው፣ ከሚወት እናታቸው፣ ከሚወዷት አፍሪካ፣ ከሚወዱት ወንድማቸው፣ ከሚወዷት፣ ከበቀሉባት አፍሪካዊት ምድር – በሌሎች አፍሪካውያን አውሬዎች ታድነው – በነጮች የአጋሰስ ማጓጓዣ መርከብ ውስጥ – ወደ አሜሪካ የሜሪላንድ የጥጥ እርሻዎች ጉልበታቸውን እንዲያንጠፈጥፉ – በማያውቁት የህይወት ዕጣፈንታ ከተፈረደባቸው – ሌሎች 167 አፍሪካውያን የውቅያኖስ ምርኮኞች ጋር – ራሱን በባህር ላይ አገኘው፡፡
ኩንታ ኪንቴን ወደ አሜሪካ የወሰደው የባርያ ፈንጋይ ኩንታ ኪንቴን በገበያ መሐል ትርሱን እያሳየ፣ ታፋውን እየመተረ፣ ባቱን እየጨመቀ፣ ትከሻውን እየለካ፣ ባደባባይ ፣ በጨረታ፣ ጥዑም ሙዚቃ አምሮት በአፍሪካ ጫካ ውስጥ የተገኘውን ያን አፍሪካዊ ልጅ – ኩንታ ኪንቴን – ለባርነት – በገበያ መሀል – እንደከብት፣ እንደፈረስ፣ እንዳህያ፣ እንዳጋሰስ – ሸጠው፡፡ ግን የአንድ አፍሪካዊ ነፍስ ዋጋው ስንት ነው? የሌላውን አላውቅም፡፡ ኩንታ ኪንቴ ግን በ155 የእንግሊዝ ባውንድ ነበር የተሸጠው፡፡ አፍሪካዊነታችንን በዋጋ መቸርቸር የጀመርነው በእንደዚያ ያለ የሰው ልጅ ቅሚያ ነበር፡፡ በእንደዚያ ያለ የጉልበት ዝርፊያ ነበር፡፡ በእንደዚያ ያለ አውሬያዊ መንገድ ነበር፡፡ ዋ ሃገር! ዋ ሀገር! ዋ!
የኩንታ ኪንቴ ታሪክ ግን ያ ብቻ አልነበረም፡፡ ኩንታ ኪንቴ – ለማስተር ዎለር ተሸጠ፡፡ ግን ባርነቱን እምቢኝ አለ፡፡ ይኸውልህ ኩንታ – አንተ እኮ – በገናዦችህ፣ በገራፊዎችህ፣ በፈንጋዮችህ፣ በጌቶችህ፣ በፈላጭ-ቆራጮችህ እጅ የተያዝክ – የምትበላ ወፍ ነህ! – እና አትታገል – የማትጋፋውን ጉልበተኛ አውሬ ዝም ብለህ ተቀበል – ብሎ ያልመከረው አልነበረም፡፡ እርሱ ግን እምቢኝ አለ!!! ሊያመልጥ ሞከረ፡፡ ግን ተያዘ፡፡ የያዙት ማን ናቸው? እንዴ! እነዚያ አውሬያዊ አፍሪካውያን ያሉት እዚህ በጁፉሬ ጫካ ውስጥ ብቻ መሠለህ እንዴ? ኖኖኖ !!! አይምሰልህ! እነዚያ እኮ ሰዎች አይደሉም፡፡ ባህርይ ናቸው፡፡ እውን ገጸ-ባህርያት፡፡ ለገንዘብ፣ እና ለጥቅም ሲሉ – ማናቸውንም ጭካኔ ለማድረግ አይናቸውን የማያሹ የሰው ልጅ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ግን የምናነሳቸው አሁን ለኩነኔ አይደለም፡፡ ባለም ሞልተውልህ የለ እንዴ ለነገሩ? እንዳንደግመው ነው፡፡ እየደገምነውም ካለ እንድናቆመው ነው፡፡ ምክንያቱም አስፀያፊ ነውና፡፡ በጣም! ሲበዛ አሳዛኝ! አሳፋሪም!
እና ኩንታ ኪንቴ እዚያም የአሜሪካ ሠፊ የጉልበት ማጎሪያ – ማለትም የጥጥ ማሳ – ሊያመልጥ ሞክሮ በራሳቸው አፍሪካውያን ተይዞ – ለነጩ አሳዳሪው – ለሚስተር ዋለር ተላልፎ ተሰጠ፡፡ እና ሚስተር ዎለር – አንዳንዴ – ጲላጦስን ይመስለኛል – ደሙ በራሱ እጅ እንዳትሆንበት እየተጠነቀቀ ያለ፡፡ ግን አይደለም፡፡ አይምሰልህ፡፡ ቶርቸረር ነበር፡፡ አንተን በራስህ ሰው በማስገረፍ የሚረካ፣ ህሊናህን የሚያቆረቁዝ፣ አንተን ከአንተነትህ የሚከፍልህ፣ የሚከፋፍልህ፣ የሚያጣላህ፣ አፍሪካዊነትህን የሚያስጠላህ – ክፉ ጌታ ነበር – ያ የኩንታ ኪንቴ ገዢ – ሚስተር – ወይም ማስተር – ዎለር!!!
ማስተር ዎለር ከትልቅ ግንድ ጋር አሳሰረው – ኩንታ ኪንቴን – በሌሎች ባሮች፡፡ እና አዲስ ያወጣሁልህ የባርያ ስምህ ማነው? ብሎ ጠየቀው፡፡ ‹‹ዋት ኢዝ ዮ ኔም?›› ይለዋል፡፡ ኩንታ ኪንቴ ዝም ይላል፡፡ ከዚያ ማስተር ዎለር ወደታሰረበት ግንድ ጠጋ ይልና፡- ‹‹ዮ ኔም ኢዝ ቶቤ!›› ይለዋል – አዲስ ያወጣለትን የባርነት ስም – ሁሉም ባሮች በተሰበሰቡበት ፊት፡፡ እና ያን ብሎት – ገራፊውን አሁን አርባ ጊዜ – ቆዳው እስኪተለተል ግረፍልኝ – ይለዋል፡፡ ገራፊው ማነው? ብለህ አትጠይቅ፡፡ መልሱን ታውቀው የለ እንዴ! ገራፊውማ ‹‹ጄምስ›› የሚል የክርስትና ስም – በጌታ ዎለር የወጣለት – ከአፍሪካ ተፈንግሎ የተጋዘ – ሌላ አፍሪካዊ ባርያ ነው፡፡ እና ጄምስ ግረፈው ሲባል – ኩንታ ኪንቴን በያዘው አለንጋ ይገሸልጠዋል፡፡ ምክንያቱም እርሱ ባይገርፈው – ራሱ ጄምስ ከገራፊነት ወደ ተገርራፊነት ይሸጋገራልና፡፡ ባርነት እንዴት አስቀያሚ ነው? ህሊና የሚሉትን ታላቅ ነገር የከሰተስ አምላክ ምንኛ የተባረከ ነው? – ህሊና ሲኖር እኮ ነው ‹‹እምቢ!›› ‹‹አልገርፍም!›› የምትለው፡፡ ህሊና ሲኖር ብቻ ሳይሆን – ለህሊና ስትል ልገረፍ የሚል ታላቅነት ሲነግስ – እንደ ኩንታ ኪንቴ ያለ ታላቅ አይበገሬ የአፍሪካዊነት መንፈስ ሲሰርፅብህ!!! ዋ አፍሪካ! ዋ ህሊና! ዋ ባርነት!!
እና ኩንተ ኪንቴ – ቆዳው እስኪገሸለጥ – በባርያው ጄምስ አለንጋ ተገረፈ – እና ተጠየቀ፡፡ ማንነቱን፡፡ ስሙን፡፡ አዲሱን የባርነት መጠሪያውን፡፡ አፍሪካዊነቱን የሚሽረውን አዲሱን ስሙን ‹‹ቶቤ!›› ብሎ እንዲያምን፣ እንዲቀበል፣ እንዲጠራ! ማስተር ዎለር – ጄምስን አንዴ ግርፋቱን አቁምለት ይለዋል፡፡ ያቆምለታል በጣት ምልክት፡፡ ከዚያ በግርፋት ወደደከመው ኩንታ ኪንቴ ጠጋ ይልና ይጠይቀዋል ስሙን፡- ‹‹ዋት ኢዝ ዮ ኔም?›› ፡፡ የኩንታ ኪንቴ መልስ ደግሞ ሁሌም አንድ! ሁሌም ራሱ ሆኖ እርፍ!! ‹‹አይ ኧም ኩንታ ኪንቴ!›› ፡፡ ግርፋቱ ይቀጥላል፡፡ አሁንም ያው ጥያቄ ይቀጥላል፡፡ አሁንም ያው መልስ፡፡ ማነህ?‹‹ዋት ኢዝ ዮ ኔም?››፡፡ ‹‹ዩ አ ቶቤ!››፡፡ ‹‹ቴል ሚ ናው!›› ‹‹ዋት ኢዝ ዮ ኔም?››፡፡ ‹‹ኩ ን ታ ፡ ኪ ን ቴ !››፡፡ ስጋው እስኪስለመለም ድረስ፡፡ ማንነቱ እስኪሳሳ ድረስ፡፡ ገዢውና ገራፊው አከርካሪያቸውና ነርቫቸው አሻፈረኝ እስኪላቸው ድረስ፡፡ ነፍስና ስጋው እስክትላቀቅ ድረስ፡፡ ኩንታ ኪንቴ አፍሪካዊነቱን አልለቅም አለ፡፡ አልቀበልም፡፡ እምቢኝ፡፡ እኔ የሃገሬ አፍሪካ ድንቅ ልጅ ነኝ፡፡ እናቴ ያወጣችልኝ አፍሪካዊ መጠሪያዬም ኩንታ ኪንቴ ይባላል፡፡ ያ ነው የእኔ ማንነት፡፡ ሌላ ማንነት የለኝም፡፡ ለምን በራሴነቴ አትቀበሉኝም?! የሚል ታላቅ አፍሪካዊ ጩኸት – በራማ ተሰማ!!!
በመጨረሻ ተቀበለ ስሙን፡፡ ‹‹ቶቤ ነኝ!›› አለ፡፡ እና ግርፋቱ ቀረለት፡፡ እና ተዘረረ፡፡ ዋ አንቺ አፍሪካ! ዋ እማማዬ አፍሪካ! ዋ አንቺ ያልታደልሽ ምድር! ተፈንጋይሽ የራስሽ ልጅ፡፡ ፈንጋይሽ የራስሽ ልጅ፡፡ አስጠርናፊሽ የገዛ ራስሽ ልጅ፡፡ ገራፊሽ የራስሽ ልጅ፡፡ ባርነትሽ ችግርሽ ሰቆቃሽ የራስሽ፡፡ አ ፍ ሪ ካ ዬ ፡ እ ማ ማ ፡ ሆ ይ – ሠላም፣ እና ምህረት፣ እና አንድነት፣ እና አይበገሬነት፣ እና ታላቅነት፣ እና ወገንተኝነት – ባንቺ ዘንድ ይሁን!!!
‹‹ዋት ኢዝ ዮ ኔም?››፡፡ ‹‹አይ ኧም.. አሣፍ – ኃይሉ – ዶሰኛው – ጋሻውጠና – …. ኦፍ ኢትዮጵያ – ኦፍ አፍሪካ – ኦፍ ዘ ዎርልድ!!››፡፡ እኔ ኩ ን ታ ፡ ኪ ን ቴ ፡ ነኝ!!! አምላክ አፍሪካዊቱን ጥቁር አልማዝ – አይበገሬይቱን ኢትዮጵያዬን – አብዝቶ ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አበቃሁ፡፡ ‹‹ኦ አፍሪካዬ – ኦ አፍሪካዬ እማማ!›› የሚለውን ከቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ጥቁር ሰው›› አልበም ላይ የሚገኘውን – እና እጅግ የምወደውን፣ የማደንቀውን – ምርጥ ዜማ እየጋበዝኩ፡፡ ቻው፡፡
‹‹ኦ አፍሪካዬ – ኦ አፍሪካዬ እማማ!
‹‹ኦና አርጌው ታሪኬን – ዜግነቴን ሣሰላስል!
የማንነቴን የዕምነቴን ማተብ – ዜግነቴን ሣሰላስል!
ለካ አፍሪካዊነቴን ስቼዋለሁ – ዜግነቴን ሣሰላስል!
ውዬ አድሬ ስጀምር ማሰብ – ዜግነቴን ሣሰላስል!
ብርድ አይሞቅም – ፍቅር አይበርድም!
በቃ ማንነት አይለወጥም – ኦላ !
‹ዜግነቴን ሣፈላልግ – እግሬ ሲዞር ባቋራጩ!
ለካ እኔ ቤቴ አፍሪካ ነው – ቤቴ አባይ ላይ ነው!
ኦ አፍሪካዬ – ኦ አፍሪካዬ እማማ!
‹‹የዮቶር ልጅ ርስቱ – ዜግነቴን ሣሰላስል!
አባይ ሆነ ጣና ዳር ቤቱ – ዜግነቴን ሣሰላስል!
ጥበብ ርቄ ስቀዳ – ዜግነቴን ሣሰላስል!
እንዴት ልሁን ለወንዜ ባዳ – ዜግነቴን ሣሰላስል!
ጠምቶኝ ተኛሁ – ባባይ ዙሪያ – ከሰው መጀመሪያ መጥቼ – ኦላ!
‹‹ዜግነቴን ሣፈላልግ – እግሬ ሲዞር ባቋራጩ!
ለካ ኔ ቤቴ አፍሪካ ነው – ቤቴ አባይ ላይ ነው!
ኦ አፍሪካዬ – ኦ አፍሪካዬ እማማ!
ኦ አፍሪካዬ – ኦ አፍሪካዬ እማማ!
ኦ አፍሪካዬማ – ኦ አፍሪካ እማማ!››
— የከበረ ምስጋና ለቴዲ አፍሮ – (የጥቁር ሰው ግጥም ስንኞች፡- ‹‹ቤቴ አባይ ላይ ነው (ኦ አፍሪካዬ እማማ) አልበም)፡፡
— ለምስሉም (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር) – ‹‹kunta-chained1››፡፡
Filed in: Amharic