የአለማቀፍ ህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር በተደረጉ የቅኝ ግዛት ውሎች ለመዳኘት መስማማት አልበረባትም ብለዋል፤ ችግሩን በድርድር መፍታት ይቻል እንደነበርም ተናግረዋል። የዶ/ር ያዕቆብ አስተያየት ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። በጣም የሚገርመው የግልግል ፍርድ ቤት እንዲመሰረት ሃሳብ ያቀረበችው ኢትዮጵያ እንጅ ኤርትራ አለመሆኗ ነው። ኤርትራ የድንበሩ ጉዳይ በካርታ ስራ ባለሙያዎች ( cartographers) እንዲያልቅ ሃሳቧን ስትገልጽ ፣ ኢትዮጵያ አይሆንም ብላ የገላጋዮች ኮሚሽን እንዲቋቋም አደረገች። ከዚህ ብሶ ደግሞ፣ ዶ/ር ያዕቆብ እንዳሉት፣ እነዚያ በጫናና በማታለል የተፈረሙት የ1902 እና የ1908 ( እኤአ) ውሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ብዙ ጉዳዮችን አንስቶ መሟገት ሲገባ፣ ይህን ለማድረግ ፈቃደኝነት አለመታየቱ በመለስ ዜናዊ አዕምሮ ውስጥ ምን እንደነበረ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። የጣሊያን መንግስት ተወካይ የነበረው የኤርትራው ገዢ ፈርዲናንዶ ማርቲኒ እንኳን ብዙ ቦታዎችን ከኢትዮጵያ መውሰዳቸውን አልሸሸገም። ለዳኞች የቀረቡት ካርታዎች ብዙዎቹ ( ሲመስለኝ ከአንድ እንግሊዝ ሰራሽ ካርታ በስተቀር) በጣሊያን ካርታ ሰራተኞች የተሰሩ መሆናቸውና እነዚህን አምኖ ለማስረጃነት መቅረቡ ጅልነት ወይም በአገር ላይ የተሰራ ደባ ካልሆነ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ጣሊያን ኤርትራን ለቅቄ እወጣለሁ ብሎ መቼ አስቦ ያውቅና ነው ፍትሃዊ የሆነ ካርታ የሚሰራው? ለማንኛውም
ድሮ ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ
እንዲሉ ነውና ዜጎቻችን ከሁለት ሳይከፈሉ እንዲሁም የኤርትራና የኢትዮጵያ ዜጎች ከመሬት ባለፈ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር የሚያደርጉ ስራዎችን በመስራት ይህን ጊዜያዊ ችግር ማለፍ ይገባል እላለሁ። ለመጪዎቹ ትውልዶች እናስብ!