>

የጥፋት ሀይል ለሆኑት እብሪተኛ ልጆቹ ሰብአዊ ጋሻ እንዲሆን የተፈረደበት የትግራይ ህዝብ?!? (አሰፋ ሀይሉ)

የጥፋት ሀይል ለሆኑት እብሪተኛ ልጆቹ ሰብአዊ ጋሻ እንዲሆን የተፈረደበት የትግራይ ህዝብ?!?
አሰፋ ሀይሉ
* ‹‹ጥልቅ ወደሆነ ባህር ጠጠር ብትጥልበት ድምፅ ሣያሰማ ይቀበለዋል፤
 * በትንሽ ኩሬ ላይ ያንኑ ጠጠር ብትጥልበት ግን፡-
   ጭቃውን በቁጣ ይፈነጥቅብሃል፣ 
   ጠጠሩንም አፈናጥሮ ወደ መሬት ይተፋዋል፡፡››
     — የጥንታዊ ሂንዱዎች ‹‹ሳጋታ ሱታ›› የሠላም የፅሞና አስተምህሮት፡፡
ከ80 ዓመታት በፊት — ጣልያን ሀገራችንን ሲወርር ያነሣው የአክሱም ፎቶ ነው — ይሄ ፎቶ፡፡ ፎቶውን ካነሣ በኋላ ጣልያን — ‹‹የተራቆተችው የአቢሲንያ ንጉሦች መናኸሪያ!›› ከሚል ርዕስ ጋር — ለዓለም አሠራጨው፡፡ አንድም አባቶቹ ያጡትን ድል እርሱ መጨበጡን ለመመስከር፣ አንድም በእኛ ለመሣለቅ፡፡ ደግሞ ሆነ ብሎ ጎጆ ቤቶቹን አቅርቦ፣ ኃውልቶቹን ደግሞ የገብስ ዘለላ እንኳ እስካይመስሉ አርቆ ነው ያነሣቸው፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን አንዳንዶች ከፎቶው ባሻገር የጥንቱን አስበው አድንቀውናል፡፡ ሌሎች ደግሞ የጥንቱን እና የአሁኑን ጎን ለጎን አስተውለው ተሣልቀውብናል፡፡ ‹‹ይሄ ነው ወይ የምትደነፉበት ሥልጣኔያችሁ?›› በሚል፡፡
ዋናው እውነት — ሰው ያለው ወይም ያላለው ቃል አይደለም፡፡ እውነት እስከሆነ ድረስ.. — እውነት ተነገረም አልተነገረም — ምንግዜም —ያው ራሱ እውነት ነው፡፡ ብትሸሸው፣ አልይህ ብትለው — እውነት የሆነ ነገር — ያው ራሱ እውነት ነው — መልሶ ያፈጥብሀል፡፡ በእርግጥ ህይወት ሁልጊዜ እውነታን በግልጽ ላታስቀምጥልን ትችላለችና — አንዳንዴ — እንዲያውም ብዙ ጊዜ —እውነቱ የቱ እንደሆነ ለመለየት ራሱ — በጥልቅ ማስተዋል እንደሚያስፈልገን — ጥያቄ አያሻውም፡፡ እውነትን እንፈልግ፣ እውነትን እናግኝ፣ እና ካገኘነው እውነት ጋር በሃቅ እንጋፈጥ፡፡
የእኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች — ያ የጥንቱ ሠማይ ጠቀስ ሥልጣኔያችን — እንዴት ብሎ ገደል ገባ? በምንስ ምክንያት ይሆን — በምትኩ — ፀሐይ ጠልቃ እስክትገባ፣ ከዘመን ዘመን፣ በሣር ጎጆዎች ተቀብረን፣ አጎንብሰን ኑሮአችንን የምንገፋ ተመፅዋች የዓለም ሕዝቦች ሆነን ልንቀር የቻልነው? ራሳችንን በጥንት ዝናና ታሪክ ብቻ ሣይሆን — አሁን ከምንገኝበት እውነታ ጋር አጋፍጠን — በሀቅ መጠየቅ እና ያንንም በሀቅ ለመመለስ ፈቃደኛ መሆን ያሻናል፡፡ በአክሱምም ሆነ በአፋር፣ በሶማሌም ሆነ በጎንደር፣ በባሌም ሆነ በጋምቤላ… በአርሲም ሆነ በሞያሌ የምንኖር የኢትዮጵያ ሕዝቦች — ጥያቄያችን እና መልሳችን ሀቅ እና ሀቅ እስከሆነ ድረስ — እውነታችንም — ብዙ የሚራራቅ አይሆንም የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ይህ ራሱ ቀላል ሥራ አይደለም!! ምናልባትም የፈጣሪ እርዳታም ጭምር ሣያስፈልገን አይቀርም፡፡  እውነቱ ላይ ለመድረስ — እውነታውን — በሀቅ — ማየት — እና መቀበል — ያሻልና — ፈተናችን — ገና ብዙ ነው፡፡ ብዙ፡፡
ይህን ካልን ዘንድ — አሁን ወደተነሣሁበት ወደ ዋናው ጥያቄ ልመለስ፡፡ ሰሞኑን በማህበራዊም ሆነ በብዙሃን መገናኛ በተሠራጭ ዝግጅት ሳይቀር — ብዙዎችን እያወዛገበ የነበረ ርዕስ አጋጥሞናል፡፡ በአንድ በኩል… በአንዳንድ የሀገሪቱ መሪዎች.. (እና በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ) በህወኀት አስተዳደር የተጠቀሙት ጥቂት የህወኀት አመራሮችና ከእነርሱ ጋር ለጥቅማቸው የተቧደኑ ጥገኞችና ባለሀብቶች እንጂ… ሠፊው 5 ሚሊየኑ የትግራይ ህዝብ… ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ.. የተጠቀመው አንዳች ነገር የለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ እውነታ – ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እውነታ ጋር አንድ ነው፣ አይለይም፡፡ ነገር ግን በትግራይ ህዝብ ስም የተጠቀሙበት  – ‹‹ጥቂት›› ራሳቸውን ከሚሊየነርነትም፣ ወደ ቢሊየነርነት ያሸጋገሩ፣ በድርጅቱ ስም የመዘበሩ፣ በድርጅቱ ስም ያሰሩ፣ የገደሉ፣ የዘረፉ፣ ፀረ-ዲሞክራሲ ተግባራትን ሲያራምዱ የቆዩ… ‹‹ጥቂት›› የህወኀት መሪዎች ናቸው፡፡ እነርሱ ህዝቡን አይወክሉም፡፡ ባደረጉት መጥፎ ነገር ኃላፊነቱን ራሳቸውን ችለው ይወስዳሉ፡፡ በሠሩት ጥሩ ተግባር ራሳቸውን ችለው ይመሰገናሉ፡፡ እንጂ የትግራይ ህዝብ – ባልበላበት – የግፍ ፈጻሚዎችና የዕብሪተኞች መደበቂያ- በእነዚያም ምክንያት ከሌሎች የሚሰነዘሩ መጠላቶችና ክሶች ተጠያቂ ሊሆን አይገባውም — የሚል — አስገራሚ — አስታራቂም — ሀሳብ ነው፡፡
ይህንን ሀሳብ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንም ይደግፉታል፡፡ ብዙዎች ልጆቹን ለጦርነት የገበረው የዘመነ-ደርጉ የትግራይ ሕዝብ ደግሞ – እውነቱ ቢነገረው – ከእውነት ጋር እንደሚወግን — ጥርጥርም አድሮብን አያውቅም፡፡ ያ ነው እውነታው፡፡ ነገር ግን እውነት አንዳንዳንዴ አስቸጋሪ ነች ብለናል፡፡ እውነትን በብርቱ መፈለግ ነው መልሱ፡፡ እንጂ መነታረክ አይደለም፡፡ ማስፈራራትም አይደለም፡፡ የድሮ ሞትና ደም መፍሰስ እየጠቀሱ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለትም አይደለም መፍትሄው፡፡ ድንፋታና እንካ ሠላንቲያም አይደለም፡፡ መስከን፡፡ እና ፅሞና ነው መፍትሄው፡፡ እና እውነቱን መጋፈጥ፡፡
‹‹የትግራይ ህዝብና ህወሀት አንድ ናቸው? ወይስ አንድም ሦስትም ናቸው?›› 
ወደ እውነት የሚወስደን እውነተኛው ጥያቄ… ‹‹የትግራይ ህዝብና ህወሀት አንድ ናቸው? ወይስ አንድም ሦስትም ናቸው?›› የሚለው አይደለም፡፡ ጥያቄው የህወኀት መሪዎች ሕዝቡን ወደቀደመበት ሥልጣኔው መልሰውታል ወይስ አልመለሱትም? ነው፡፡ ጥያቄው የህወኀት መሪዎች ከጎጆ ቤት ወደ ፎቅ ቤት ሲሸጋገሩ ሕዝባቸውንስ ከዚያ ከተቀበረበት ከተጎናበሰ ጎጆ አውጥተውታል ወይ? የሚለው ነው፡፡ መሠረታዊው እውነት.. አሁን የትግራይ ህዝብ ወኪል ነኝ አይደለሁም የሚለው እሰጥ አገባና ኃላፊነት-የጎደለው የጦርነት ቁስቆሳም… አይደለም፡፡ ለዚያ ከሌላ ወገን የሚሠጠው በተመሣሣይ ኃላፊነት-የጎደለው መልስም ሊሆን አይችልም፡፡ ይሄ አይደለም፡፡
ይልቁንስ.. ዛሬ ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጅ ምሁራንና የህወኀት መሪዎች — ከግልፍታቸው ሠከን ብለው ማሰብና ማስተዋል ያለባቸው ዋናው እውነት — እና ዋናው ጥያቄ… — ይህ … ከዚህ ከምድራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አሣልፈው መንፈሣዊ ሐይማኖት ሊመሠርቱበት እስከሚመስል ድረስ… — አሁን እነርሱ እንደ ሥላሴ እንድነትና ሦስትነት— ሥጋ ወ ደሙ ጭምር እያሉ — የሚነታረኩበትና ለማሳመን የሚሰብኩበት የአሁኑ አካሄዳቸው… እውነት.. እውነት… ከሥልጣኔው ርቆ፣ ከሠላሙ ርቆ፣ ከሀብትና ከእፎይታው ርቆ… ላለፉት ሺህ ዘመናት የኖረውን.. ከአድዋ እስከ ባድመ… ጦርነት፣ ሥጋት፣ ሽብር እና የሦስቱ ሥላሴዎች አንድነትና ሦስትነት ሰበካ.. የየዕለት ቀለቡ ሆኖ ለኖረው… ሠፊው የትግራይ ህዝብ… ይህ የአሁኑ ‹‹አንድ ነን..›› እና ‹‹ሦስት ነን..›› እና ‹‹አንድም ሁለትም ነን..››፣ ወዘተ ወዘተ የሚል አስገራሚ ክርክርና ስብከት… እውን ይጠቅመዋል? ወይስ አይጠቅመውም? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄው ሊሆን የሚገባው፡፡
የትግራይ ህዝብ በአንድ አይን እንዲታይ የሚፈልገው የህወኀት አክራሪው ክንፍ ነው
ይህ የአንዳንድ ነባር ህወኀታውያን መሪዎች ስብከተ-ወንጌል-ወ-ትግራይ… የትግራይን ሕዝብ — እንደማንኛውም በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ቤተሰባዊ፣ አካባቢያዊ፣ ግላዊ ፍላቶጎች ተሰባጥሮ፣ በልዩነቱ ተስማምቶ፣ የማያምንበትን ትቶ፣ በሚያምንበት አግዞ፣ተጋግዞ የሚኖር ሠላማዊ ሕዝብ ሣይሆን — ከዓለም ሕዝብ ሁሉ የተለየ — ከሠማይ በእርግብ አምሳል የወረደለትን የህወኀት የሆነ ዘመን ብሶት አንግቦ ዕድሜ ልኩን እንደ ቀኖና ሐይማኖት ተቀብሎት የሚኖር — ፍፁም የማይለወጥ፣ የማይሰጥ፣ የማይቀበል — አንድ ወጥ የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንደሆነ በማስመሰል… — ላለፉት 27 ዓመታት — በሰው ዘንድ አምርሮ በተጠላው የህወኀት ፖለቲካ ሰበብ… — የትግራይም ሕዝብ አብሮ በተቀረው (እና የህወኀት ፖለቲካ ባንገፈገፈው) በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ — እስከምንጊዜም እንዲጠላ፣ እና እንዲፈረጅ፣ እና ማመዛዘንና እውነታውን መረዳት እንደሚችል ሰብዓዊ ፍጡር፣ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ፖለቲካ ምንደኛ አሊያም እንደ አንድ ሃይማኖተ-ፖለቲካ አርበኛ ተቆጥሮ… — የትግራይ ተወላጅ የተባለ ሁሉ — ከቄሱ እስከ ሊስትሮው… — ከመምህሩ እስከ መዘምሩ — ገዳም ከገባው ጀምሮ ቡና ቤት እስከገባው ጭምር — በአንድ ዕይታና በአንድ መነፅር… — በሌላው ሕዝብ ዓይን እንዲታይ የሚፈለግ የህወኀት አመራር ወይም አክራሪ ክንፍ ያለ ይመስላል፡፡
ግን በሀገራችን ለተፈጠሩት እና እየተከናወኑ ላሉት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ሁሉን-አቀፍ እንቅስቃሴዎች ሀገሪቱን በበላይነት እየመሩ የቆዩት የህወኀት መሪዎች — አሁን — እየሰጡት ያለው መልስ — እየተከተሉት ያሉት አማራጭ — ወደ የት ነው የሚወስደን?  ብሎ ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህ እኔና ትግራይ አንድም ሦስትም ነን የሚል ተደጋጋሚ መፈክር — ህዝብን የመቀስቀሻ ሥልት ሊሆን ቢችልም — በተለይ አሁን በሀገራችን አፍጦ ከወጣው እውነታ አንፃር — የህወኀት መሪዎች ድንፋታ — ውጤቱ — የትግራይ ሕዝብ በአንድ ወጥ የፖለቲካ አስተሳሰብና አርበኝነት ተፈርጆ — በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የጎሪጥ እንዲታይ — ከፍ ሲልም እንዲጠላ… — አሊያም የጥቃት ዒላማ እንዲሆንና እንዲገለል የሚያደርገው አካሄድ አይደለም ወይ?? ብለው ማሰብ — እና ራሳቸውን መጠየቅ — እጅግ ተገቢ ተግባር ነው፡፡ እውነት ነው — የተነሡበት ሕዝብ መሸሻ፣ መሸሸጊያ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከመሸሽ በፊት፣ እውነታን እንጋፈጥ፡፡ እና ፀብን ከመዝራት ይልቅ በኃላፊነት ሥሜት — ችግራችንን እና የችግራችንን ምንጭ ተነጋግረን — የመፍትሄው አካል እንሁን፡፡ ወይም በአሁኑ ቋንቋ — እንደመር — እና ሕዝባችንንም ከሌላው ሕዝብ ጋር ለበጎ ህልም እንዳይደመር አናግደው፡፡
የትግራይ ህዝብ ለምን የሰብአዊ ጋሻ አድርገው  መሸሸጊያ ሊያደርጉት ፈለጉ?
ዛሬ ዛሬ እኮ — በየሥርቻውና በየአደባባዩ የሚወራው እኮ — ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ በሠፊው የሚወራው እኮ — እነዚያ የትግራይ ህዝብ በአንድ ወቅት ለአንገቱ የሚያምንባቸው፣ ራሳቸውም በአንድ ወቅት አንገታቸውን የሠጡ የጦርሜዳ አዋጊዎች — ዛሬ በሠላሙ ዓየር — በሠፊው የሀገሪቱ መስክ — ሥልጣን በሚያመጣው ጦስ ባልገዋል ነው እኮ እየተባሉ የሚታሙት፡፡ መታማት ብቻም ሳይሆን በግልጽ ብዙ ሥሞታ የሚቀርብባቸው፡፡ እና ታዲያ — ይህን አይቶ ነቅሶ ማውጣትና ራሱን ወደቀደመ ሥፍራው መመለስ የሚጠበቅበት በህዝብ ስም እና ለህዝቦች የተቋቋመ — የአሁኖቹን ዲታ ባለሥልጣናት አቅፎ የያዘ — የፖለቲካ ድርጅት — ለምን አምንበታለሁ የሚለውን ፖለቲካውን.. እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ በእውነት እና ስለ እስነት ቀርቦ፣ ሰብኮም ሆነ አሳምኖ.. ለምን ከራሱ ተስማምቶ አይኖርም?? የአሁኖቹ የህወኀት ግንፍልተኝነትን የተላበሱ መሪዎች — ስለምን ራሳቸውን ችለው አይቆሙም?? ስለምን ከሕዝቡ ጫንቃ አይወርዱም?? ለምን ከጥንት እስከ አሁን ያላለፈለትን የትግራይን ሕዝብ… እውነትን ላለማመን ሲሉ.. ስርየትን ከልብ ላለመጠየቅ ሲሉ፣ ጥፋትን ለማደባበስ ሲሉ.. እንደ መጨረሻ ሰብዓዊ ጋሻ ይጠቀሙበታል..?
ዛሬ ላይ ቆመን ‹‹የህወኀት አባላት 750 ሺህ ናቸው፣ እያንዳንዱ 5 ቤተሰብ አባል ቢኖረው፣ ህወኀት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው፣ የትግራይ ህዝብ ማለት ደግሞ ህወኀት ማለት ነው፣ አይነጣጠልም›› እያልን ዛሬ ላይ — የህወኀት መሪዎች — ሀቀኞቹን እና እስከዛሬም ለሀቅ የቆሙትን ሳይሆን — በተለይ በሥልጣን ብልሹነትና በሀገር ሀብት ምዝበራ ስማቸው በህዝቡ ዘንድ የሚነሳባቸው ነባር አባላት — እንደጥንቱ አንገቱን ደፍቶ፣ ሱቅ እየቸረቸረ፣ እርሻውን እየቆፈረ፣ ሊስትሮውን እየጠረገ፣ የጉልበት ሥራውን እየሠራ፣ በውትድርና እያደረ፣ በተላላኪነት፣ በዘበኝነት፣ በቅስና በድቁና፣ በሸቃይነት፣ ሌላ ቀርቶ በልመና ራሱ ተሰማርቶ — እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ የዚህችን ሀገር የኑሮ መቅሰፍት እየተቋደሰ አንገቱን ደፍቶ የሚኖረውን ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ — ዛሬ እውነትን ላለመጋፈጥ ሲሉ — ለምን እንደ አይነተኛ የሰብአዊ ጋሻ ቆጥረው ህዝቡን መሸሸጊያ ሊያደርጉት ፈለጉ
ዛሬ በሰፊው እንደሚደመጠው፣ በግልጽም ወጥቶ እንደሚታው… የብዙው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ… እንደ ማንኛውም የትግራይ ሕዝብ ሁሉ… የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ የብዙው ሕዝብ ጥያቄ እኩል እንጠቀም፣ እኩል እንብላ፣ እኩል እንናገር፣ እኩል እንሙት የሚል የእኩልነት ጥያቄ ነው፡፡ የብዙው ሰው ጥያቄ የነፃነት ጥያቄ ነው፡፡ የብዙው ሰው ጥያቄ የፍትህ ጥያቄ ነው፡፡ የብዙው ሰው ጥያቄ ለሕዝብ ተጠያቂ የሆነ መንግሥት የመፈለግ ጥያቄ ነው፡፡ የብዙው ሰው ጥያቄ – የምርጫ ቦርድን ድምፅ ይዞ ጠፋ ተብሎ እየተሳቀቀ አንገቱን ደፍቶ ከመኖር የመገላገል የእውነት ጥያቄ ነው፡፡ የብዙው ሰው ጥያቄ የመደመጥ ጥያቄ ነው፡፡ የመደመር ጥያቄ ነው፡፡ እንጂ የማድማት እና የመደማማት ጥያቄ አይደለም፡፡ የመጥላት እና የመጠላላት ጥያቄ አይደለም፡፡ የመበቀልና የመተላለቅ ጥያቄም በፍፁም አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብ — ባለፈው ዘመን ስለሞተ፣ ልጆቹን ስለሰጠ፣ መራራውን የሠላም እጦት እየመረረው ስለተጋተ፣ ለምን ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ ጥርስ ይነክስበታል? ይታዘንለታል እንጂ ስለምን እናንተ የምታስቡትን የሰቆቃ ቅዠት ይታለምለታል???
እናስ ዛሬ ላይ ለምንድነው የህወኀት ምሁራንና መሪዎች – የጥንቱ የሕዝባችሁን ሥልጣኔ እንዴት ጠፋ? የራቀውንስ ለቀረው ኢትዮጵያ የተረፈውን ታላቅ ሰሜናዊ ጥበብና ሥልጣኔ.. ለሕዝባችን እንዴት እናላብሰው፣ እንዴት አድርገን እንመልስለት? ብለው መመራመር፣ ማሰብና መተግበር ያልተቻላቸው? እና በተቃራኒው የጥፋት ቁልቁለት ህዝቡን እየመሩ ሊያንደረድሩት የሚፈልጉት??? እና የህወኀትን አንድነትና ሦስትነት ነጋ-ጠባ የሚሰብኩን??!! — መልሱን የሚያውቀው ሰው የተገኘ አይመስልም፡፡
የትግራይን ህዝብ ዳግም ለማያባራ ሰቆቃና ሰቀቀን ከሚጋብዘው አካሄዳችሁ ተቆጠቡ
ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ግን — አንድ ቁልጭ ብሎ የሚታይ — አንድ ትልቅ እውነታ አለ፡፡ ያም እውነት… በደንብ ካሰብንበት… እንዲያውም ለሀገራችን ሥልጣኔ መንኮታኮት.. ዋነኛው ምንጩ.. ለሕዝባችን የሚበጀውን ሥልጣኔ በጋራ ከመፍጠርና ከመገንባት ይልቅ… በውስጣችን የሰፈነውን ጭፍን የዘረኝነት እና የጥላቻ እና የፍርሃት እና ያለመተማመን … ኋላ ቀር አመለካከት በማስተጋባት ወደፊት መሄድ ስንችል ወደኋላ እየተሰናከልን መቅረታችን ነው — ዋናው የችግራችን ምንጭ የሚል — ብዙ ተሞክሮ የወለደው — መላምት ግን አለኝ፡፡ መላምት ግን በቂ አይደለም፡፡ የቱንም ያህል እሣት ባልነደደበት ጭስ ጨሶ ባይገኝ.. የቱንም ያህል ግምቱ ለእውነታው የቀረበ ቢሆን… እውነቱን ሞክሮ፣ ፈትሾ፣ አንጥሮ፣ አስተውሎ፣ ሰክኖ እንደመለየት እና እንደማወቅ የመሰለ ነገር ሊኖር አይችልም……፡፡
እና…… እስቲ ፡ እባካችሁ – የዘር-ጥላቻንና የዘር-ፍራቻን የሚሰብክ… የማይረባ.. ወደኋላ የሚመልስ… ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ – እና በተለይ በመላ ኢትዮጵያም ሆነ በትግራይ ምድር ለሚኖረው.. እና ላለፉት ረዥም ዘመናት ሠላሙን ተነስቶ ለኖረው… ሰቆቃን እስከጥጉ ለዘመናት እያወራረደ ለኖረው ሰፊው ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ስትሉ….. አሁን የያዛችሁትን…. የትግራይን ህዝብ ዳግም ወደማያባራ ሰቆቃና ሰቀቀን ከሚጋብዝ አካሄዳችሁ ተቆጥባችሁ – ከልብ የመነጨን የእውነትን የአባቶችን የሕዝብን ምክር ሰምታችሁ – ሀገርንና ህዝብን ወደሚያድን — ሁላችንንም ወደ እውነት ለሚያስጠጋ፣ ወደ እውነት ለሚመራ፣ በዕውቀትና በሰብዓዊነት ለሚመራ የወደፊት ተስፋ — እጃችሁን እንድትሰጡ፣ አዕምሮአችሁን እንድታውሉ፣ ልሳናችሁን እንድትከፍቱ፣ ታሪካችሁን እንድታወሱ — ሁኑ?!!!
እስቲ እባካችሁ — ወደ ሠላም የሚያመራ፣ ዘመንን የሚሻገር፣ ሩቅ የሚመለከት፣ ሥልጣኔን ማቅ የሚያለብስ ሳይሆን ሥልጣኔን ዳግም የሚሞሽር — ለሕዝብ የሚጠቅም የጥናት ግኝታችሁን፣ የሠላምና የእርቅ ሃሳባችሁን፣ የመተቃቀፍ እጅ ለእጅ ተያይዞ አብሮ በሠላም የመጓዝ ፅኑ ራዕያችሁን፣ እና ባለፉት 27 ዓመታት የፈፀማችሁትን በጎም የሚያስመሰግናችሁንም ሆነ፣ ክፉ ሕዝብን ያስቀየመውን እውነት  — እስቲ ለመላው ኢትዮጵያውያን — እንዲሁም — ወንድማችን እና እህታችን፣ አባት እናታችን፣ ልጃችን ወዳጃችን እና ባለውለታችን ጭምር ለሆነው — ለሠፊው የትግራይ ሕዝብ ጭምር — ጀባ በሉን፣ አሳውቁን፣ አሣዩንማ — እያልኩ — ከልብ ከመነጨ ጥልቅ አክብሮትና ልመና ጋር — ለመላው የህወኀት ምሁራን፣ ልሂቃንና ፖለቲከኞች — በትህትና አቀርባለሁ!!!
በመጨረሻ ፅሑፌን የምደመድመው ከህንዶች ዘንድ ባገኘሁት አንድ አስተምህሮተ-ታሪክ ነው፡፡ የዛሬ 5,000 ዓመት ገደማ — ህንዳዊው መንፈሣዊ መሪ — ጎታማ ሲዳርታ — ወደኖረበት ቤተመንግሥት ድንገት ቤተሰቦቹ ትዝ ብለውት — በተመለሰ ጊዜ — ንግሥቲቱን ቬዳሂን ያገኛታል፡፡ ሲያገኛት ግን ያ ከ12 ዓመታት በፊት አብሯት የነረበው ደስታና ውበት ፍፁም ርቋት — ፍፁም ተክዛና በእንባ እየታጠበች ነበር፡፡ እና ከልቡ አዝኖ ትከሻዋን ይዞ አንገቷን ቀና ሲያደርገው… ጎታማን አየች፡፡ እና እርሱ ከዚያ በእርሷ ላይ በቤተመንግሥት ከወደቀባት መከራ በደህና ጊዜ ማምለጡን እያሰበች ምነው እሱን ባረገኝ እያለች ሁሌ ታስበው ነበርና ፊቷ ላይ የተስፋ ፍንጥቅታ ታየ፡፡ እንዴት ነሽ የተከበርሽ ልዕልት ቬዳሂ ሲላት፤ እንዲህ የሚል ምላሿን ትቸረዋለች፡— ‹‹ህይወት በሥቃይ የተሞላች ነች፤ ከሥቃይ ውጭ የሆነ ሥፍራ የለም እንዴ ግን? ቢኖር ብርር ብዬ በዚያ ሥፍራ እርፍ ብል እንዴት ደስ ባለኝ?!›› (“Life is filled with suffering. Is there not a place without suffering? I wish to live in such a world!”)፡፡ እርሱም ባሳለፈችው የአበሳ ህይወት ከልቡ አዝኖ እና በውስጧ ባሳደረችው ፅኑ ምኞትም ራርቶላት.. ለእርሱ የአዕምሮ ሠላም የሆኑትን አብርሆታዊ ጥበቦቹን ለንግሥት ቬዳሂ ይገልጥላታል.፡፡ እና ከቤተ መንግሥቱ አውጥቶ.. ራቅ ወዳለው ወደ ምዕራቡ ነፋሻማ ኮረብታ ያኖራታል፡፡ እና እፎይ ትላለች፡፡ የራቃት ሠላምና ደስታም ወደ እርሷ ህይወት ይገባል፡፡
በውስጧ ደስታና እርካታ መስፈኑን እና የጠፋው ሠላሟም ማበቡን ያስተዋለው ሲዳርታም ሊሰናበታት ወደ ንግሥቲቷ ቀረበ፡፡ እና ከመሄዱ በፊት እነዚህን ሶስት የምክር ቃላት ለገሣት፡፡ እስከዛሬም የሠላምና የፅሞና አስተምህሮዎች እየተባሉ ይታወቃሉ፡፡
ዛሬ የትግራይ ሕዝብ፣ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ — ልክ ከ5ሺህ ዓመት በፊት የኖረችውን — የጎታማን እህት ንግሥት ቬዳሂን ሆኖ የተገኘበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ የምኞቱን የሚፈጽምለት ቢያገኝ — ቤተመንግሥቱም ቀርቶበት — ምቾቱም ቀርቶበት፣ ድሉም ሆነ ሽንፈቱም ቀርቶበት፣ ታላቅነቱም ሆነ ታናሽነቱም ቀርቶበት — ከምንም በላይ በሠላምና ደስታው ነፋሻማ ከፍታው ላይ የሚያወጣውን ተስፋ እየተመኘ ያለ — አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ምስኪን ሕዝብ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ላይ ያሉ — የህወኀት ፣ እና ሌሎችም የፖለቲካ መሪዎች ደግሞ — ያኔ ጎታማ ሲዳርታ እህቱን ሲሰናበት የተናገራቸውን — እና እኔም አሁን ወገኖቼን ስሰናበት የመረጥኳቸውን — እነዚያን የሠላምና የፅሞና ቀኖናዎች እንድናስተውል — እና ሁላችንም ሰከን እንድንል — የፈጣሪ ረዳትነት የፈጣሪ በረከት አይለያችሁ እላለሁ፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን — እና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ — አንድም ሣያስቀር — አብዝቶ ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያችን — በፍቅር፣ በሠላም፣ በፅሞና፣ በፅናት፣ በህብረት — ለዘለዓለም ትኑር፡፡ በንግሥት ቬዳሂ የሠላምና የፅሞና አስተምህሮዎች ተለየሁ፡፡ መልካሙን ሁሉ እየተመኘሁ፡፡
1ኛ/ ለእናትና ለአባቶቻችን፣ ለተጧሪዎቻችን ሁሉ እንዘንላቸው፣ እናሣርፋቸው!
 
2ኛ/ ላስተማሩን፣ በዕድሜ ለሚበልጡን፣ ለወገኖቻችን፣ በየረገጥንበት ሥፍራ ላገኘናቸው ሁሉ ልባዊ አክብሮት ይኑረን!
 
3ኛ/ ለሁሉም ሰው አዛኝና ወዳጅ እንሁን፣ የየትኛውንም ህይወት ያለውን ፍጡር ነፍስ አንቅጠፍ!   
አበቃሁ፡፡ ቻው፡፡ ፎቶው (ከከበረ ምስጋና ጋር)
‹‹The sacred city of Axum in Abyssinia was captured and plundered by the Italians. In the photo there are royal tombs, 1936.››
Filed in: Amharic