>
5:09 pm - Thursday March 3, 0078

ፀረ-ማሠቃየት (ቶርቸር) ሕግ አስፈላጊነት [ውብሸት ሙላት]

ፀረ-ማሠቃየት (ቶርቸር) ሕግ አስፈላጊነት
ውብሸት ሙላት
ይህ ጽሑፍ የሚያጠነጥነው በ”ሥቃይ” (torture) ዙሪያ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ‘ቶርቸር’ የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በአማርኛ ለመተካት ‘ኢሰብኣዊ የድብደባ ድርጊት’ የሚል ሐረግ ተጠቅሟል፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ ደግሞ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 424 ላይ የተቀመጠውን ‘physical and mental torture’ የሚለውን ሐረግ ‘የአካልና የመንፈስ ሥቃይ’ ይለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በእዚህ ጽሑፍ፣ በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው ሐረግ  ይልቅ በወንጀል ሕጉ ላይ ያለውን፣ ሥቃይ፣ የሚለው ተመርጧል፡፡ ይህን ለማድረግ ያስገደዱት ምክንያቶች ደግሞ አምስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ‘ኢሰብአዊ የድብደባ ድርጊት’ የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው አካላዊ የሆነን ብቻ እንጂ ሥነ-ልቦናዊ ወይም አእምሯዊን አለመሆኑ ነው፡፡ ‘ቶርቸር’ ግን ሁለቱንም ያካትታል፡፡
ሌላው ምክንያት፣ ‘ኢሰብኣዊ የድብደባ ድርጊት’ የሚለውን ሐረግ ከተጠቀምን ከ’ቶርቸር’ ውጭ ያሉት ሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶች ሊሆኑ ነው፡፡ ሰብአዊ የድብደባ ድርጊት የሚባል፣በሕግ የተፈቀደ አድራጎት ስለሌለ አደናጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ ምናልባት በጅራፍ መግረፍ የቅጣት ዐይነት በነበረበት ዘመን ሕጋዊ ነው ሊባል ቢችልም  ድብደባውን ሰብኣዊ ነው የሚያሰኘውም ነገር አይኖርም፡፡
ሦስተኛው፣ ‘ቶርቸር’ ከኢሰብኣዊ አያያዝና ቅጣት የተለየ ስሆነ ከእነዚህ ጽንሰ ሐሳብም ለመለየት ጭምር ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ፣ የ’ቶርቸር’ን ድርጊቱን፣ አድራጊዎቹን፣ አስደራጊዎቹን፣ አደራራጊዎቹን ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት  በአንድ ቃል መጠቀሙ ቀላል ስለሆነ ነው፡፡
የመጨረሻው ደግሞ ‘ሥቃይ’ የሚለው ቃል የ‘ቶርቸር’ን ጽንሰ ሐሳብ ሊተካ ስለሚችል ነው፡፡  ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ‘ሥቃይ’ን የሚለውን ቃል “ጭንቅ መከራ መቅሠፍት፤ግፍ ቅጣት” በማለት ይተረጉሙታል፡፡ ይህ ትርጉም አካል ላይ  ከሚደርሰውም በተጨማሪ አእምሯዊ (ሥነ-ልቦናዊውንም) የሆነውንም ጉዳት ያካትታል፡፡
ምንነቱ
ስለሥቃይ ስናነሳ ለምርመራ የተያዙ፣ የተከሰሱ፣ የተፈረደባቸውን (ታራሚዎችን) ሁሉንም በማጠቃለል ሲሆን  ለአገላለጽ እንዲመች ሁሉንም እስረኞች በማለት እንጠቀማለን፡፡ በሕጎቻችን ላይ እስረኞች ላይ ለሚደርስ ሥቃይ ምንነት የተሰጠ ብያኔ የለም፡፡
በሁሉን አቀፍ የሰብኣዊ መብት መግለጫ እና በዓለም አቀፉ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ ማንም ሰው ሥቃይ እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለው የተረጋገጠ ነው፡፡ ሁለቱም ሰነዶች በኢትዮጵያ ላይ የአስገዳጅነት ኃይል እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሕግ ሆኗል፡፡ ሁለተኛውን ተቀብለን ያጸደቅነው በመሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣እነዚህ ሁለት ሰነዶች ሰዎች ከእነደዚህ ዓይነት ድርጊቶች የመጠበቅ መብት እንዳላቸው ከመግለጽ ያለፈ ብያኔ አይሰጡም፡፡
ማሠቃየትን በተመለከተ ሰፊ ተቀባይነት ያለው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እ.አ.አ. ታሕሳስ 10 ቀን 1984 ዓ.ም. ‘ከሥቃይ እና ከሌሎች ጭካኔ ከተሞላባቸው፣ኢሰብኣዊ ወይም አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ለመጠበቅ የወጣው ስምምነት’ ላይ የሰፈረው ትርጉም ነው፡፡ ኢትዮጵያም በመጋቢት 1984 ዓ.ም. ላይ ተቀብላ ስላጸደቀችው በዚሁ ስምምነት ላይ የተቀመጠውን ብያኔ እንጠቀማለን፡፡
በእዚህ ስምምነት ላይ በተሰጠው ብያኔ መሠረት አንድን ድርጊት ማሠቃት ነው ለማለት ቢያንስ የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች ማሟላት አለበት፡፡ የማሠቃየት ድርጊት መኖር፣ ድርጊቱ ለከፍተኛ ሕማምና ሰቆቃ የሚዳርግ መሆኑ፣ የሥቃዩ ዐይነት   ደግሞ አካላዊም አእምሯዊም ሊሆን መቻሉ፣ ሆን ተብሎ መፈጸሙ፣ማሠቃየቱ ዓላማ ያለው መሆኑ፣ እንዲሁም የመንግሥት ሰዎች (ባለሥልጣናት) ተሳትፎ ማድረጋቸው ናቸው፡፡
ስለሥቃይ በሚነሳበት ጊዜ አሠቃዮቹ የሚያደርሱት የሥቃይ ድርጊት (act) መኖር አለበት፡፡ ‘ድርጊት’ የሚያመለክተው አንዱ ሰው ሌላው ላይ የሚፈጽመውን ቢሆንም በተለይ በወንጀል ሕግ ከመታቀብ ወይም ከመተው የሚከሠተውንም ያካትታል፡፡ ስለሆነም፣ማሠቃየት በሚባልበት ጊዜ አሠቃዮቹ በራሳቸው የሚያደርጓቸውንም ሆነ በመተው የሚመጡትንም ያካትታል፡፡ ጥፍር መንቀል፣ የወንድ ብልት ላይ ዕቃ ማንጠልጠል፣በኤሌክትሪክ መግረፍ ወዘተ በማድረግ ውጤት እንደሆኑት ሁሉ ምግብና መጠጥ አለመስጠት፣ሲታመሙ ሕክምና ወደሚገኝት ቦታ አለመውሰድ ደግሞ በመተው የሚመጡ ናቸው፡፡
በሥቃይ ድርጊት መሞትም ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ማሠቃየቱ በዝቶ ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የአገዳደል ሁኔታው በራሱ ማሠቃየት ሊሆን ይችላል፡፡ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሰው አሟሟቱ ሥቃይ የበዛበት እንዲሆን በማድረግ ለምሳሌ በስቅላት የሚገደል ከሆነ የገመዱ ቋጠሮ ከፊት ለፊቱ በማድረግ፣በጣም አንገቱን እንዳያጠብቀው በማላላት የሚፈጸሙ የማሠቃየት ድርጊት ሊሆን ይችላል፡፡
ማሠቃየት ከሌሎች ተቀራራቢ ድርጊቶች የሚለይባው መገለጫዎች አሉት፡፡ ማንኛውም ኢሰብኣዊ እና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ሁሉ ማሠቃየት አይሆንም፡፡ በእርግጥ ማሠቃየት ኢሰብኣዊም፣ክብርን የሚነካና የሚያዋርድ ነው፡፡ ነገር ግን ማሠቃየት ከእነዚህ የከፋ እና የሚያሳቅቅ ድርጊት መሆኑን ከላይ የጠቀስነው ዓለም አቀፍ ስምምነት ያመለክታል፡፡ በጣም የጨለመ ቤት፣ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለው፣ርጥበት ያለበት ቤት ማሰር ማሠቃየት ነው፡፡ አንድን ሰው እጁንም እግሩንም ለየብቻ በማስር በድጋሜ እንዳይንቀሳቀስ ከብረት ጋር ማሳር የድርጊቱን ደረጃ ማለትም የሥቃዩን መጠን እና የደረሰውን ሰቆቃ ያመለክታል፡፡ (ይህ በደርግ ዘመን አቡነ ቴዎፍሎስ ወድያውኑ እንደታሠሩ የተፈጸመባቸው ነው፡፡) በቴሌቪዥን ያየነው ከላይ ከተዘረዘሩት የከፋና የባሰ ነበር፡፡
የሚደርሰው ሥቃይ አካላዊም አእምሯዊም ሊሆን ይችላል ብለናል፡፡ የማሠቃያ ዘዴዎቹ በየዘመኑ፣ በየአገራቱ እንዲሁም  በማሠቃየት ይገኛል ተብሎ እንደሚፈለገው ውጤት ሊለያዩ እንደሚችሉ ስለጉዳዩ የተጻፉ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
አካላዊ ከሆኑት በተጨማሪ የሰዎችን እጅና እግራቸውን በማሰር አካላቸውን ማር፣ቅቤና ሌሎች ተመሳሳይ ቅባቶችን በመቀባት ፀሐይ ላይ በማስቀመጥ ዝምብና ሌሎች ነፍሳት እንዲወርሯቸው ለአይጥና መሠል ተባዮች እንዲጋለጡ ማድረግ፣ ሆን ብሎ ለረጅም ጊዜም ሰውነታቸውን እንዳይታጠቡ በመከልከል ተሠቃዮቹ ላይ የሚደርሰው  የሥቃይ ዓይነት በዋናነት አእምሯዊ ነው፡፡ በአጭሩ፣ማሠቃየት አካላዊ ብቻ ሳይሆን አእምሯዊም ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡
በእስረኞች ላይ የሚፈጸም የማሠቃየት ተግባር ምንጊዜም ቢሆን ሆን ተብሎ እንጂ በቸልተኝነት  አይደረግም፡፡ ከአያያዝ ጉድለት፣ጥንቃቄ ማድረግ ሲገባ ባለማድረግ ወዘተ የሚከሠቱ የሥቃይ ድርጊቶች ሊኖሩ ቢችሉም እንዲህ ዐይነቶቹ በዚህ ሥር አይወድቁም፡፡ አሠቃዩ አካል የሚፈጽመውን ድርጊት አስቦበት፣በማሠቃየቱ የሚመጣውንም ውጤት ተቀብሎት መሆን አለበት፡፡
ማሠቃየት የሚፈጸመው የሆነ ዓለማን ወይም ግብን ለማሳካት ነው፡፡ በማሠቃየት መረጃ ማግኘት፣ስለሌሎችም ሆነ ስለራስ ለማናዘዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ብሔርን፣ሃይማኖትን፣የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት በማድረግ አድሏዊ በሆነ መልኩ ለማዋከብ፣ ለመቅጣት፣ ለመበቀል ሊሆን ይችላል፡፡ በአማራ ቲቪ ከተላለፈውም ብሔርን መሠረት ያደረገ እንደነበርም መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይ ኦሮሞና አማራን ነጥሎ የማሰቃየት ድርጊት እንደነበር ይታወቃል፡፡
የሆነው ሆኖ፣ማሠቃየት የራሱ የሆነ ግብ ያለው መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ለማሠቃየት ምክንያቶቹ በርካታም የተለያዩም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቅጣት፣ብቀላ፣ ማስተማር፣መቀጣጫ ማድረግ፣መረጃ ለማግኘት፣እውነትም ይሁን ውሸት እንዲናዘዝ ለማድረግ ወይም በስቃዩም ለመደሰት ሊሆን ይችላል፡፡
አንድ ድርጊት ማሠቃየት ለማለት መጨረሻው መለያ ደግሞ የመንግሥት ሰዎች ወይም ባለሥልጣናት በገቢርም ይሁን በዝምታ ተስማምተው የሚፈጽሙት፣ወይም ፈጻሚው በራሱ በመንግሥት የተሠጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ ያረገው፤ አልበለዚያም የማሠቃየት ድርጊቱን ማንም ይፈጽመው ማን መንግሥት እንዲህ ዐይነቱን ጥቃትና ሥቃይ ሳያስቆም ሲቀር ነው ማሠቃየት ተፈጽማል የሚባለው፡፡
አሠቃዩ በመንግሥት የተቀጠረ፣የሥቃይ ድርጊቱም የሚፈጸምበት ቦታ በመንግሥት እጅ ሥር ያለ ከሆነ፣የሚፈጸምበት ተቋም ኃላፊ የሥቃይ ድርጊቶችን አለማስቀሙ ወይም ‘ጆር ዳባ ልበስ’ ማለቱ የማሠቃየት ወንጀልን ሊያቋቁም ይችላል፡፡
ማሠቃየትን ለማስቆም የአገራት ግዴታ
የማሠቃየት ምንነት በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ድርጊቱን ለማስቆም አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ የ1984ቱን ማሠቃየትን ለማስቆም የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት የፈረሙ አገራት በርካታ ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው እስረኞችን ሥቃይ እንዳይደርስባቸው ለማድረግ የሚያግዝ እና አሠቃዮችን የሚቀጣ ብሔራዊ ሕግ ማውጣት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የፀረ-ማሠቃየት ሕግ የላትም፡፡ በሕገ መንግሥቱም ላይ በግልጽ ማሠቃየትን የሚከለክል አንቀጽ የለም፡፡ ማንኛውም የማሠቃየት ተግባር ኢሰብኣዊ፣ጭካኔ የተሞላበት እና ክብርን የሚያዋርድ በመሆኑ፤ በአንቀጽ 18 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ዕውቅና ተሰጥቶታል ማለት ቢቻልም ማሠቃየትን ልዩ የሚደርጉት ነጥቦች ስላሉ እንዲሁም የተጠያቂዎቹን ኃላፊነት በግለሰብ ደረጃ ብቻ ስለሚያስቀረው ተጨማሪ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ይህ አንቀጽ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡
እንደውም ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ2014 ዓ.ም. ወቅቱን ጠብቆ በሚቀርበው ሁሉን አቀፍ የሰብኣዊ መብት ሪፖርት (Universal Periodic Review) ስታቀርብ የፀረ-ማሠቃየት ሕግ እንድታወጣ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ተቀብላዋችም፡፡
ይሁን እንጂ፣ በአገር ደረጃ ማሠቃየት እንዳይኖር የሚከታተል ኮሚቴ የማቋቋም እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚገኝ የፀረ-የማሠቃየት ኮሜቴ እስር ቤቶችን በመጎብኘት ማሠቃየት መኖር ወይም አለመኖሩን እንዲመረምር ሥልጣን የሚያሰጠውን አማራጭ የፀረ-ማሠቃየት ፕሮቶኮል እንድትፈርም የተሰጣትን አስተያየት አልተቀበለችውም፡፡
ማሠቃየትን ለማስቆም የተለያዩ መፍትሔዎችን በአንድነት መጠቀም ግድ ነው፡፡ የተለያዩ ተቋማትን ርብርብም ይጠይቃል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ይህንን ለማስቆም በዋናነት ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡
በሽግግር መንግሥቱ ዘመን (በ1984 ዓ.ም.) የተቀበልነውን የፀረ-ማሠቃየት ስምምነት በመከተል በአገር ደረጃ ሕግ ማውጣት ይጠበቅ ነበር፡፡ እንዲህ ዐይነት ሕግ መኖሩ መንግሥት በተለያዩ ተቋማቱ አማካይነት ዜጎች ላይ የሚያደርሳቸውን ጥቃቶች እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ አጋዥ ነው፡፡
ዜጎችና ድርጂቶች በሽብር ድርጊት  መንግሥት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ፣ ካደረሱም ለመቅጣት ሲባል የፀረ-ሽብር ሕግ እንዳለውና እንደሚኖረው ሁሉ በተቃራኒው ለሚደርሱት ደግሞ የፀረ-ማሠቃየት ሕግ ይኖር ዘንድ ግድ ነው፡፡ በተለይም የሽብር ድርጊቶችን ለመመርመር በሚል ሰበብ በበርካታ አገራትም ጭምር  የታሰሩ ሰዎች ላይ ማሠቃየት እንደሚፈጸም ይታወቃል፡፡
ይህንን እጅግ አሠቃቂ ድርጊት ለማስቆም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት በፀደቀው ስምምነት መሠረት ያልፈጸመውን የቤት ሥራ መቋጨት አለበት፡፡ ከእዚህ በተጨማሪም፣የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን በቦታው በመገኘት በተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት እንደሚጎበኘው ሁሉ እስረኞች የሚገኙባቸውን ማእከላት ሊጎበኝ ይገባዋል፡፡
ከሕዝብ ተዋካዮችም ምክር ቤት በታች ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቋቋማቸውን መሥሪያ ቤቶች በሕጋዊ መንገድ ተግባራቸውን መወጣታቸው መከታተል ይጠበቅበታል፡፡ የፀረ-ማሠቃየት ስምምነቱን አማራጭ ፕሮቶኮል እንዲፈረም ማድረግም የማሠቃየት ድርጊትን ለመቀነስ ቁርጠኝነት መኖርን ያሳያል፡፡ ማሠቃየት እስካልቀጠለ ድረስ ይህንን ፕሮቶኮል ማጽደቅ የሚያስፈራ ሊሆን አይችልም፡፡
ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀጥሎ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ የወንጀል ምርመራን ሒደትን እና የተመርማሪዎችንንም ሆነ የታራሚዎችን አያያዝ በሚመለከት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በርካታ ሥልጣኖች እንዳሉት ከተቋቋመበት ከአዋጁ ቁጥር 943/2008 መገንዘብ ይቻላል፡፡ የተመርማሪዎችን ሁኔታ መከታተል አለበት፡፡ ምርመራው በተገቢው መንገድ ካልተመራ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ይህ እንግዲህ የፖሊስ እና የማረሚያ ቤቶቹ ኃላፊነትና ግዴታ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 210/1992 አንቀጽ 5 ላይ እንደተገለጸው ሦስት ዋና ዓለማዎችን እንዲያሳካ የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡ እነዚህም ስለሰብኣዊ መብቶች ግንዛቤ እንዲጨምር ማስተማር፣ መብቶቹ እንዳይጣሱ መጠበቅና ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ ማድረግ፣ እንዲሁም ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ናቸው፡፡ ማሰቃየትን በተመለከተ ሊያሰቃዩ ይችላሉ ተብለው ለሚገመቱ ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ሰዎች ትምህርት መሥጠት አለበት፡፡ ግንዛቤያቸውን ማዳበር ይጠበቅበታል፡፡
በወንጀል ምርመራ ቦታዎች፣በማረሚያ ቤቶች በመገኘት እስረኞችን በመጎብት አያያዛቸውን በመከታተል የተጠርጣሪዎች፣ የተከሳሾች፣ የፍርደኞች መብት አለመጓደሉን የማረጋገጥ ሕጋ ግዴታ አለበት፡፡ በተጨማሪም፣እንኳንስ በማሰቃየት ይቅርና በሌላ በማናቸውም ሁኔታ የሰብአዊ መብታቸው የተጣሱ የተያዙ ሰዎችን በሚኖርበት ጊዜ ተገቢውን እርምጃ ማስወሰድ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
እነዚህ ተቋማት እንዳሉ ሆነው የእስረኞችን ሥቃይ በመቀነስ ረገድ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሚናም ከፍ ያለ ነው፡፡እንደ አገሪቱ ርእሰ ብሔር በበዓላት፣በሳምንቱ የእረፍት ቀናት ወዘተ በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን መጎብኘት ባህላችን ነው፡፡ ባህላችን የነበረው በእርግጥ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ነበር፡፡ ከእዚያ ወዲህ አልቀጠለም፡፡ በዓላትን ሰበብ በማድረግ፣በሳምንቱ መጨረሻ ቀን እስረኞችን እና ታካሚዎችን መጎብኘትና ማጽናናት ልማድ ነበር፡፡ የሃይማኖታዊም ጥሩ የሞራል ድርጊትም ነው፡፡
እስረኞችን ማሠቃየት መተው የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ውሎ አድሮም ለአገራዊ መግባባት ይጠቅማል፡፡ በተለይ ማሠቃየቱ የፖለቲካ ባላንጣን (ተፎካካሪን) ሲሆን ዴሞክራሲን ለማስፈን ትልቅ እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በአሠቃዮቹ እና በተሠቃዮቹ መካከል የብሔር ልዩነት ኖሮ እንዲሁ የብሔር ቅርጽ እየያዘ ከሔደም አደጋው ቀላል ሊሆን አይችልም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት ሚናቸው ማሠቃየትን ለመከላከልና ለመቀነስ ነው፡፡ ድርጊቱ ተፈጽሞ ሲገኝ ደግሞ ተገቢውን የወንጀል፣የፍትሐ ብሔርና የአስተዳደር እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ የፀረ-ማሠቃየት ሕግ ቢኖር ለተሠቃዮች ቢያንስ ካሳ እንዲያገኙ፣በይፋና በዐደባባይ ይቅርታ እንዲባሉ ማስደረግ የእነዚህ ሕጎች መለያ ስለሚሆን፤ ቢኖረን ኖሮ የተሠቃዩትን ሰዎች ለአካላቸው ጉዳት ሕክምናና ካሳ ለመንፈሳቸው ስብራት ደግሞ መጽናናትንና ማገገም እንዲችሉ ያግዝ ነበር፡፡
አሁን ባለው አሠራር ግን ተሠቃዮቹ ክስ ቢመሠርቱም ለማሸነፍ አዳጋች እንደሚሆንባቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አንድ ብቻ ምሳሌ እናንሳ፡፡ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ከላይ በጠቀስነው ጉዳይ ላይ ምርመራ ማድረግ ሲጀምር ማረሚያ ቤቱ እስረኞቹን ሲቀበል ያደረገውን የጤና ምርምራ እንዲያቀርብ በሚጠይቅበት ጊዜ ምርመራውን አለማድረጉን አሳውቋል፡፡ ማረሚያ ቤቶች ይህንን የማድረግ ግዴታ ግን በሕግ ተጥሎባቸዋል፡፡
እስረኞቹ ሲገቡ የነበሩበት የጤና ሁኔታ እና ከገቡ በኋላ የተፈጠረውን ልዩነት ማሳየት፣ ተሠቃዮቹ አቤቱታቸውን ለማስረዳት ወሳኝ ማስረጃ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወስ ያለበት እንዲሁም የአገራትም ልማድ የሚያረጋግጠው የማሠቃየት ድርጊት ላይ በተሳትፎም አንዳንዴም በአሠቃይነት የሚወሰዱት የሕክምና ተቋማት መሆናቸውን ነው፡፡
 በብዙ አገራት የእስረኞችን ሥቃይ በሚመለከት የሕክምና ውጤቶችን የሚያዛቡ በተባባሪነትም በዋና ወንጀል አድራጊነትም ተቀጥተዋል፡፡
የአሠቃዮቹ የወንጀል ተጠያቂነት
ስለማሠቃየት ወንጀል በቀጥታ የሚመለከተው የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 424ን ነው፡፡ ይህ አንቀጽ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ሆነው ሥራቸውን በተገቢው መንገድ ማከናውን ሲገባቸው ሳያከናውኑ ሲቀሩ የወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው፡፡
በተለይም እስረኞችን ማለትም የተያዙ፣የተከሰሱም ይሁኑ ታራሚዎች ላይ የአካል ወይም የመንፈስ ሥቃይ ያደረሱ እንደሆነ ፣እንደሌሎች ኢሰብኣዊ ድርጊቶችን እንደፈጸሙ ሁሉ፣ በወንጀል ያስጠይቃል፡፡ እስከ አስር ዓመት የሚደርስ እስራትም ያስቀጣል፡፡ ይህ ማለት ግን በማሠቃየቱ ምክንያት የደረሱት ጉዳቶች በራሳቸው ወንጀል ከሆኑ በእነዚያም ጭምር በወንጀል ያስጠይቃል፡፡ ድርጊቱ የበላይ ኃላፊዎች ይሁንታ ወይም ትእዛዝ ካለበትም ኃላፊውንም ጭምር በወንጀል እንዲጠየቅ ለማድረግ ያስችላል፡፡ እስከ አስራ አምስት ዓመትም ያስቀጣል፡፡
ሦስት ነጥቦችን መነሳት አለባቸው፡፡ አንደኛው አሠቃዮች ብዙውን ጊዜ የበላይ ኃላፊዎችን ትእዛዝ ተቀብለው መፈጸማቸው ከተጠያቂነት የማያድናቸው መሆኑን ነው፡፡ መቼም ቢሆን ማሠቃየት ወንጀል መሆኑን የማያውቅ ሰው ስለማይኖር አሠቃዮቹን ማንም ይዘዛቸው ማን ከተጠያቂነት አያድናቸውም፡፡ የበላይ ኃላፊዎችም በሚሰጡት ትእዛዝም ይሁን ሲፈጸም ባለማስቆማቸው፣እርምጃ ባለመውሰዳቸው የወንጀል ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡ እራሳቸው አለመፈጸማቸው ብቻውን ተጠያቂ እንዳይሆኑ መከላከያ አይሆንም፡፡
ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፣ እስረኞችንም ይሁን ሌላ ማንኛውም ሰው ላይ በሚፈጸም የማሠቃየት ወንጀል ምክንያት ክስ ለማቅረብ የጊዜ ገደብ የለውም፡፡ ማሠቃየት፣በሰብኣዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች (crimes against humanity) አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ደግሞ ይርጋ እንደሌላቸው፣ምሕረትም ይሁን ይቅርታ እንደማይሰጣቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ላይ ተቀምጧል፡፡
ስለሆነም፣አሠቃዮች ለሚፈጽሙት ድርጊት በሕይወት እስካሉ ድረስ ሊጠየቁ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 424 ላይ የተገለጸውን የማሠቃየት የወንጀል ድርጊት በፈፀሙ ላይ መቼም ቢሆን ክስ ሊቀርብባቸው ይችላል፡፡ ይርጋ ስላለመኖሩ ሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
ሦስተኛው፣ የማሠቃየት ድርጊት የፈጸመ ሰው ጉዳዩ በየትኛውም አገራት ሊታይ መቻሉ ነው፡፡ በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ድርጊቱ የተፈጸመባቸው አገራት ብቻ ሳይሆኑ የየትኛውም አገር ፍርድ ቤት የመዳኘት ሥልጣን አለው፡፡ በደርግ ዘመን ጎጃም ውስጥ በፈጸመው ወንጀል በቅርቡ በአገረ ኔዘርላንድ ጥፋተኛ ተብሎ የተፈረደበትም በዚሁ አግባብ መሆኑን ያጤኗል፡፡ የሥቃይ ድርጊቱን የፈጸመው ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ተጎጂው ቢሞትም እንኳን የወንጀል ድርጊቱ በሚሄድበት አገር ጥላ ሆኖ ይከተለዋል ማለት ነው፡፡
ለማጠቃለል ያው አገራችን ውስጥ ሲከሠት የቆየውን በደል በተለያዩ ሚዲያዎች ዐይተናል፤ሰምተናል፡፡ በተለይ በአማራ ቲቪ የተላለፈው እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ እነዚህን ሥቃይና በደሎች ረዘም ላለ ጊዜ በርካታ ሞት አይፈሬ ወጣቶች ይህንን ግፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲያስተላልፉ ኑረዋል፤መንግሥት በዝምታ ይሁንታውን ለግሶ ሥቃይ ሲፈጸም ከረመ፡፡ ምክንያቱም ሆን ተብሎ የተዘጋጀ የገራፊ ቡድን በየቦታው ያቋቋመው መንግሥት (ህወሃት) በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከ1997 በኋላ ሲፈጸም የነበረው ድርጊት ለመስማትም ለማየትም እጅግ ሰቅጣጭ ነው፡፡
ለመስማትና ለማየት እንዲህ የሚዘገንን ከሆነ የሚሠቃዩት ምን እንደተሰማቸውና እንደደረሰባቸው መገመት ለኅሊናም ይከብዳል፡፡  አሁን ላይ የመንግሥት ሚዲያዎች መዘገባቸው፣ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርም በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ሰዎችን ለፍትሕ ለማቅረብ ቃል መግባቱ ጥሩ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን ሥርዓት ማበጀት፣ሕግ ማውጣት፣ እስረኞች ላይ የአካልና የመንፈስ ሥቃይ እንዳይፈጸምባቸው ለማድረግ የሚረዳ የፀረ-ማሠቃየት ሕግ (Anti-torture law) ማውጣት እና አማራጭ ፕሮቶኮሉን ማጽደቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሕግ ሳይወጣ የቀረውና አማራጭ ፕሮቶኮሉም ያልጸደቀው ገራፊዎችና አሰቃዮች በራሳቸው ላይ ሰይፍ መምዘዝ ስለሆነባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቢያንስ ከዚህ ወቅት መጀመሩ ተገቢ ነው፡፡
(ይህ ጽሑፍ ማእከላዊ እንዲዘጋ መወሰኑን ተከትሎ በጥር ወር የተጻፈ ሲሆን መጠነኛ ማሻሻያ ብቻ ተጨምሮበታል፡፡ )
Filed in: Amharic