>

የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ 71ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ 71ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ
ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
ባለቅኔ፣ ደራሲና ገጣሚ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ያረፉት ከዛሬ 71 ዓመታት በፊት (ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም) ነበር፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ከአባታቸው ቄስ ገበዝ ንጉሤ ወልደ ኢየሱስና ከእናታቸው ወይዘረ ማዘንጊያ ወልደኄር በ1887 ዓ.ም. ጐጃም ውስጥ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም የቤተ ክህነት ትምህርት በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የአማርኛ፣ የግዕዝና የግብረ ገብ መምህር ሆነው እያስተማሩ፣ ለብርሃንና ሰላም ጋዜጣ አጫጭር ጽሑፎችን ያቀርቡ ነበር፡፡
‹‹ወላድ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹የኛማ ሀገር›› እና ‹‹ድንግል አገሬ ሆይ›› የተሰኙትንና በሕዝብ ዘንድ በዋናነት የሚታወቁላቸውንና የሚወደዱላቸውን የመጀመሪያ የድርሰት ስራዎቻቸውን የፃፉትም በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ ትያትር ስራ ለመግባት እንደገፋፋቸውም ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በዚህም ‹‹ምስክር›› የተሰኘ የመጀመሪያ የትያትር ስራቸውን አበረከቱ፡፡
የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ በአምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ›› የሚለውን የደረሱት ቀኝጌታ ዮፍታሔ፣ ስለአገር ፍቅርና ጀግንነት የሚያወሱ በርካታ ድራማዎችንና መዝሙሮችን የደረሱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ‹‹አፋጀሽኝ››፣ ‹‹እለቄጥሩ›› ወይም ‹‹ጎበዝ ዐየን›› ይገኙበታል። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከ1935 ዓ.ም እስከ ሕልፈታቸው (1939 ዓ.ም) ድረስ አገልግለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ተአምራዊው ዋሽንት››፣ ‹‹ጥቅም ያለበት ጨዋታ››፣ ‹‹ሙሽሪት ሙሽራ››፣ ‹‹ያማረ ምላሽ››፣‹‹የሆድ አምላኩ ቅጣት››፣ ‹‹ዳዲ ቱራ››፣ ‹‹የህዝብ ጸጸት››፣ ‹‹ሙሾ በከንቱ››፣ ‹‹አባት ንጉሳችን ጠረፍ ይጠብቅ››፣ ‹‹የደንቆሮዎች ቲያትር››፣ ‹‹ዓለም አታላይ››፣ ‹‹ዕያዩ ማዘን››፣ ‹‹ንጉሡ እና ዘውዱ›› የተሰኙና ሌሎች የድርሰት ስራዎችን አበርክተዋል፡፡
በ19 ዓመታቸው የቀኝ ጌትነትን ማዕረግ ያገኙት ይህ ታላቅ ሰው፣ የታሪክ መምህር፣ ዲፕሎማትና አርበኛም ነበሩ፡፡ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም መደበኛ ስራቸውን ሲያከናውኑ ውለው በተኙበት አርፈው ተገኙ፡፡ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የምትታወቀው ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› የተሰኘችው ስንኝ በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የድርሰት ስራ ውስጥ የምትገኝ ስሜት ቀስቃሽ ስንኝ ናት፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በመተባበር ጳጉሜ 2 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የተመረቁትን እና የቀኝ-ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤን እንዲሁም የደራስያን አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ እና አቶ ተመስገን ገብሬ ምስል የተቀረፁባቸው ቴምብሮችን ገበያ ላይ አውለዋል።
በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ሕይወትና ስራዎች ላይ መጽሐፍ የፃፈው ደራሲ ዮሐንስ አድማሱ፣ ስለ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጠቃላይ ማንነት ‹‹ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ብሔረ ነገዱ፣ አገረ ውላዱ፣ ጐጃም፤ ቅኔ የተቀኘበት፣ ድጓና ምስጢር የተማረበት፣ ደብረ ኤልያስ ነበር፡፡ ጠይም ረዥም፣ ጠጉረ ሉጫ፣ መልከ መልካም፣ ቀጭን-ዠርጋዳ ጣተ መልካም፣ ሽቅርቅር፣ ጥዩፍ፣ ኮከቡ ሚዛን ነፋስ ነበር›› በማለት ገልጿቸዋል፡፡
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አፅም ያረፈው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነበር፡፡ ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም  አፅማቸው ከአዲስ አበባ ፀሎተ ፍትሐት ተደርጎ፣ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት መድረክ ‹‹አፋጀሽኝ›› የተሰኘው የትያትርና ሌሎች ስራዎቻቸውን የሚዘክር አጭር ትርኢት ቀርቦ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተሸኝቷል፡፡ በዚያም በርካታ ሰው በተገኘበት አፅማቸው በክብር አርፏል፡፡
[ማሳሰቢያ – ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ ያረፉበትን ጊዜ በተመለከተ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተለያዩ ዓመተ ምህረቶችን አግኝቻለሁ፡፡ ነገር ግን በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ሕይወትና ስራዎች ላይ መጽሐፍ የፃፈውን የደራሲ ዮሐንስ አድማሱ መረጃ የተሻለ ነው ብዬ በማመን ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም የሚለውን ተጠቅሜያለሁ፡፡]
ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic