ከታሪክ አንጓዎች እምየ ምኒልክ
እንኳን በቁመናው ዛሬ እንኳ በሙቱ
በምኒልክ ሲባል ይረጋል መሬቱ!!!
መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ እንደፃፉት
… ታህሣሥ 3 ቀን1906 ዓ.ም በዕለተ ዓርብ ሞቱ፡፡ ወዲያው እንደሞቱ የግቢ ስራ ቤቶች ልቅሶ ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን የልጅ እያሱ ባለሟሎች አገር እንዳይሸበር ሰግተው በቶሎ ዝም አሰኟቸው፡፡
ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱና ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ አስከሬናቸው ከተቀመጠበት ሆነው ያለቅሱ ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ከተነገረው የልቅሶ ግጥም ጥቂቱን በሚከተለው እጽፋለሁ፡፡
ወይዘሮ ዘውዲቱ የተናገሩት የግጥም ቃል
.
ቀድሞ የምናውቀው የለመድነው ቀርቶ፣
እንግዳ ሞት አየሁ ከአባቴ ቤት ገብቶ፡፡
እጅግ ያስገርማል ያስደንቃል ከቶ፣
ከሁለታችን በቀር እሚያውቀው ሰው ጠፍቶ፡፡
ምልክቱ ይህ ነው የንጉሥ ሞት ሀዘን፣
ጣይቱ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትሆን፡፡
ወልደውኛል እንጅ አልወለድሁዎ፣
አንጀቴን ተብትበው ምነው መያዝዎ፡፡
እጅግ አዝኛለሁ አላቅሰኝ አገሬ፣
የሁሉ አባት ሞቶ ተጎድተሃል ዛሬ፡፡
ድርቅ ሆኖአል አሉ ዘንድሮ አገራችሁ፣
ዝናሙ ሲጠፋ ምነው ዝም አላችሁ፡፡
አሻግሬ ሳየው እንዲያ በሰው ላይ፣
መከራም እደ ሰው ይለመዳል ወይ፡፡
ያች የሰጡኝ በቅሎ መጣባት ባለቤት፣
አልገዙም መሰለኝ ሊገለኝ ነው ዕፍረት፡፡
……………………
እቴጌ ጣይቱ
.
እምቢልታ ማስነፋት ነጋሪት ማስመታት ነበረ ስራችን፣
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን፡፡
……………………
… አፄ ምኒልክ ምንም ቢሞቱም በሕይወት አሉ እየተባለና እየተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ድረስ ሁለት ዓመት ከዓስር ወር የሞታቸው ወሬ ተደበቀ፡፡ ስማቸውም ሕያው ሆኖ በምኒልክ አምላክ እየተባለ እንደ ቀድሞው ሕጋዊ ማስተዳደሪያ ሆኖ ቀረ፡፡ በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንገስት ሁሉ ሳይገለፅ ተደብቆ ኖረ፡፡ ሆኖም ወሬው መሰማቱና መታወቁ አልቀረም ነበርና የምንጃር ገበሬ በጤፍ ውቂያ ላይ እንዲህ ብሎ ግጥም ገጠመ፤
.
እምየ ምኒልክ ገንዘብ ስጠኝ ብየ አላስቸግርህም፤
አምና ነበር እንጂ ዘንድሮስ የለህም፡፡
……………………
… በደብረ ታቦር ከተማ ጥር 7 ቀን ስለ አፄ ምኒልክ ሞት ውሎ ተዋለ፡፡ የጎንደር መኳንንትና ሊቃውንት ጃንሜዳ በሚባላው ስፍራ ተሰብስበው ልቅሶ እየተለቀሰ የጉዞ ፍትሐት ሲፈታ ሳለ አንዲት አልቃሽ እንዲህ ብላ ግጥም ገጠመች፤
.
አባባ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥቱ
እንኳን የሰውን ልጅ አውሬውን የገዘቱ
ልጄን ያለ አንቀልባ ያሳደግሁበት
ቤቴን ያለመዝጊያ የተኛሁበት
እንኳን በቁመናው ዛሬ እንኳ በሙቱ
በምኒልክ ሲባል ይረጋል መሬቱ፡፡
……………………
… በዚሁ ጊዜ የንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስ ብዙ ድግስ አስደግሰው የአጼ ምኒልክን ተዝካር አወጡ፡፡ በደብረማርቆስም ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማት ስለ አጼ ምኒልክ ሞት ውሎ አውለው የጉዞ ፍትሐት አስፈቱ፡፡ እንዲሁም ብዙ ድግስ አስደግሰው የጎጃምን አድባራት ካህናት ሁሉ ጠርተው በጥር 15 ቀን የአጼ ምኒልክን ተዝካር አበሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የጎጃም አልቃሽ እንዲህ አለች፤
.
ታስሮ ተደብቆ የቀረ ምነው፣
ሕልም ነው ምኒልክ ጊዜ የፈታው፣
አልሞተም ይላሉ ሰዎች ንጉሡን
ሸዋን ቢጠይቁት ምኒልክ ይሆን፡፡