አቶ ኦባንግ ሜቶ
አዲስ አድማስ
• ዘንድሮ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጐች የተፈናቀሉት በዘር ፖለቲካ ነው!
• በዓለም ላይ በዘር የተቧደነ ሃገር የለም፤ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ነች!
• ሰው በሰውነቱ ብቻ ሰብአዊ ክብሩ ሊጠበቅ ይገባዋል!
• ጥላቻን የሚዘሩ ፖለቲከኞች፣ እውነቱ ሊነገራቸው ይገባል!
ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ በዘር ፖለቲካ የተዘራውን ጥላቻ፣ ፍሬውን እያየን ነው የሚሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹና ኢትዮጵያዊነትን አቀንቃኙ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ ጥላቻውን ማርከሻው ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ክልልን በዘር መከለል ተገቢ አይደለም ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ፤ ሰው ሰው በመሆኑ፣ ከሁሉም ጋር ያለ ክልል ገደብ መኖር አለበት ብለዋል፡፡ ዛሬ በየአካባቢው ለሚታየው ዘር ተኮር ጥቃትና መፈናቀል ሰበቡ ኢትዮጵያዊነት እንዲጨልም መደረጉ ነው ሲሉም፣ የዘር ፖለቲከኞችን ይነቅፋሉ፡፡ ላለፉት 28 ዓመታት ኑሮአቸውን በውጭ ሃገራት ያደረጉት አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን “የጋራ እንቅስቃሴ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ” በተሰኘው ድርጅታቸው አማካኝነት በሰብአዊነት ላይ ኢትዮጵያዊነትን እንገነባ በሚል እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡
ከሃገርዎ የወጡበት ምክንያት ምን ነበር? መቼስ ነው የወጡት?
ከሃገሬ ከወጣሁ 28 ዓመት ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ ሳይገባ በፊት ነው የወጣሁት፡፡ ግን በፖለቲካ ምክንያት አይደለም፡፡ በቤተሰብ ምክንያት ነው፡፡ ከ17 ዓመቴ ጀምሮ የኖርኩትና ያደግሁት ካናዳ ነው፡፡ ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ የተማርኩት እዚያው ነው። ከዚያ በኋላ ወደ ሃገሬ የተመለስኩት በ1992 ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱ ጋምቤላ ነበር የሄድኩት፡፡ ጋምቤላን ስመለከት በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ልማት የሚባል ነገር አልነበረውም፡፡ ህዝቡ በጨለማ ውስጥ ነበር የሚኖረው ማለት ይቀላል፡፡ አንድ ሆስፒታል ብቻ ነበር ያለው፡፡ በዚያ አንድ ሆስፒታል ውስጥ ደግሞ አንድ ዶክተር ብቻ ነው የነበረው፡፡ ሰዎች በንፁህ ውሃ እጦት ታመው ሲሞቱ ተመልክቻለሁ፡፡ ህክምና የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ ይሄንን የህዝቡን ጉስቁልና ስመለከት ብዙ ነገር ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ያየኋቸው ነገሮች በጣም ነው መንፈሴን የጐዱት፡፡ እነዚህን ሰዎች በምን መልኩ ልርዳ ብዬ ማሰብ የጀመርኩት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ እናም የጋምቤላ ልማት (Gambela Development) የሚባል ድርጅት አቋቋምኩ ማለት ነው፡፡
ድርጅቱ ዓላማው ምን ነበር?
የተለያዩ ለጋሾችን በማስተባበር በሚገኝ ገቢ ሆስፒታሎችን ለመስራት፣ ት/ቤቶችን ለመገንባትና ለጋምቤላ ህዝብ ልማት አጋዥ የሆኑ ተግባራትን አቅም በፈቀደ ሁሉ ለማከናወን ተንቀሳቅሰናል። ይሄን እንቅስቃሴ እያደረግን ባለበት ወቅት ደግሞ በ1994 ዓ.ም በጋምቤላ ግጭት ምክንያት ሰዎች ተጨፈጨፉ፡፡ 424 ሠዎች በግፍ ተገድለዋል፡፡ ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ እኔ በአካል የማውቃቸው ናቸው፡፡ እኔን ያስተማሩኝ ሰዎችና ዘመዶቼ ናቸው በብዛት የተገደሉት፡፡ በኋላም ይሄን ግፍ ለዓለም ለማጋለጥ መንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡ ወዲያው ለልማት በሚል ያቋቋምነውን ድርጅት ትተን፣ ሌላ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጋልጥ ተቋም መሰረትን፡፡ ለሞቱት 424 ሰዎች ፍትህ ለማግኘት “አኝዋክ የፍትህ ጉባኤ” (Agnwak Justice Council) የተሰኘ ተቋም መሠረትን፡፡ በዚህ ተቋም አማካኝነት የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ለሂውማን ራይትስ ዎች፣ ለአሜሪካ ኮንግረንስና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አጋልጠናል – ድምፃችንን አሰምተናል፡፡ ይህን እያሰማን ባለንበት ሰዓት ደግሞ በ1997 የተደረገውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ፣ በርካቶች መገደላቸውን አወቅን። ይሄን ስናውቅ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭፍጨፋ የሚፈፀመው በጋምቤላ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ነው በሚል ድምፃችንን ለሁሉም የግፍ ሰለባዎች ማሰማት እንዳለብን ወስነን መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡
ሁሉንም አካትተን ለአጠቃላይ ሠብአዊ መብቶች መከበር ካልተንቀሳቀስን የጋምቤላ ህዘብ ብቻውን ፍትህ ሊያገኝ አይችልም በሚል መንፈስ፣በኢትዮጵያ ያለውን ችግር በሥርዓቱ ገምግመን መሥራት ጀመርን። በኢትዮጵያ ያለው ችግር የዘር ፖለቲካ ነው። የአስተሳሰብ ችግር ነው ብለን ነው እንቅስቃሴያችንን እንደገና የጀመርነው፡፡ የዘር ፖለቲካ ጠቃሚ አይደለም። ሰው በሰውነቱ ብቻ ሰብአዊ መብቱ መጠበቅ አለበት ብለን ነው፣ አላማ አድርገን የተነሳነው። በብሔር መቧደንና መደራጀት ስህተት ነው ብለን ነው የተነሳነው፡፡ ክልልን በዘር መከለል ተገቢ አይደለም። በክልል ከብት እንጂ ሰው አይከለልም። ሰው ሰው በመሆኑ፣ ከሁሉም ሰው ጋር ያለ ክልል ገደብ መኖር አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ በኋላም ይህ የዘር አከላለል፣ ብዙ ጣጣ ይዞ ሲመጣ ነው የተመለከትነው፡፡ የአማራዎች ከጉራ ፈርዳና ከተለያዩ አካባቢዎች በግፍ መፈናቀል የሚታወቅ ነው፡፡ በወቅቱ ቤተ መንግስት የተቀመጡ ሰዎች፤ ለጉዳዩ የሰጡት ምላሽ ደግሞ የበለጠ አናዳጅ ነበር፡፡ በዓለም ላይ በዘር የተቧደነ ሃገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ነች፡፡ ያውም በክፉ መንገድ ነው በዘር የተደራጀነው፡፡ እኔ የበርካታ ሃገራትን ሕገ መንግስት ለማየት ሞክሬያለሁ፤ “የ……… ሃገር ህዝቦች….” ብሎ ነው የሚጀምረው። የእኛ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እና “ብሔር ብሔረሰቦች” ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ ይሄን እነ አቶ መለስ የሰሩበት ምክንያት፣ ለራሳቸው የከፋፍለህ ግዛ ታክቲክ እንዲመቻቸው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አስበው አይደለም፡፡ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ብለው ከከለሉ በኋላ ደቡብን በአንድ ጨፍልቀው ነው በአቅጣጫ ያካለሉት፡፡ ይሄ ትልቅ የአመለካከት ችግር ማሳያ ነው። ኢትዮጵያዊነትን ማዳከሚያ ነው፡፡ ይሄን ስገነዘብ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር ድምፃችንን ለማሰማት ከምናደርገው እንቅስቃሴ ጐን ለጐን፣ ሌላ ድርጅት ማቋቋም አለብን በሚል፣ “የጋራ እንቅስቃሴ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ”ን አቋቋምን፡፡
ይህ ድርጅታችሁ ከቀድሞው በምን ይለያል? ዋና ስራዎቹ ምንድን ናቸው?
ኢትዮጵያዊ ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ በዘሩ መታየት የለበትም የሚለውን እሳቤ ይዘን ነው የተነሳነው፡፡ በመጀመሪያ ሰው በሰውነቱ ብቻ ሰብአዊ ክብሩ ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ማምጣት ከተፈለገ፣ በመጀመሪያ ሰው በሰውነቱ ብቻ መከበር አለበት፡፡ ብሔር መጥቀስ ይቁም፡፡ ሰው በሰውነቱ ብቻ ከታየ፣ ዛሬ የምንታዘበው “ከክልሌ ውጣ” የሚለው ነገር አይኖርም፡፡ የፈለገበት የመረጠው ቦታ መኖር ይችላል፡፡ እኛ አሁን ከሰውነት ወርደን፣ ብሔር ላይ ነው የተንጠለጠልነው፡፡ በደርግ ጊዜ፣ በአውራጃ በክፍለ ሃገር የወሎ፣ የጐጃም፣ የወለጋ፣ የባሌ፣ የአሊባቦር ልጅ ነበር የምንባባለው እንጂ ብሔሩ አይጨንቀንም፡፡ አሁን ግን የአማራ ልጅ፣ የትግሬ ልጅ፣ የኦሮሞ ልጅ፣ የጉራጌ ልጅ—እየተባባልን ነው፡፡ ይሄ አስተሳሰብ አሁንም ለወደፊትም ለሃገር አይጠቅምም። በሂደት መለወጥ አለበት፡፡ ሰው በሰውነቱ የሚከበርበትን ሁኔታ ምሁራኖቻችን መፍጠር አለባቸው፡፡ በብሔር ተቧድኖ ሃገር ማስተዳደርም አዳጋች ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ እኮ ትግራይን ነፃ ለማውጣት በተደራጀ የፖለቲካ ድርጅት (የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት) ነው ስንመራ የነበረው። ነፃ አውጪ ደግሞ የፍቅር ፖለቲካ አያመጣም፤ የጥላቻ መከፋፈልና የነፃ መውጣት ፖለቲካ ነው የሚያመጣው፡፡ ዛሬ በህወኃት የስልጣን ዘመን ወንጀል የሰሩ በክልላቸው ይደበቃሉ፡፡ ይሄ ለምን ሆነ ካልን፣ በሌላው የሃገሪቱ ክፍል ለመኖር የሚያስችል፣ በሰውነት ላይ የተመሰረተ መተማመን የላቸውም፡፡ የእኛ ድርጅት በዋናነት ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጐ ነው የሚመራው፡፡ ከተቋቋመ ጀምሮ በተለይ በችግር ውስጥ ላሉ በውጭ ሃገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የአደጋ ጊዜ ደራሽ ለመሆን ጥረት ያደርጋል፡፡ ወደ 34 ሃገሮች ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ተንቀሳቅሰናል፡፡ ሊቢያ፣ ጓቲሟላ፣ ጃፓን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ደቡብ ኮርያ፣ እስራኤል—የመሳሰሉ ሃገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይቶችን እያዘጋጀን ነው፡፡ በመጨረሻም ያሰብነው፣ የሃገራችን ትልቅ ችግር ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራው ጥላቻ ስለሆነ፣ጥላቻውን የሚያሽር እርቅ ያስፈልጋል በሚል የእርቅ ሁኔታን ለማመቻቸት ነው፡፡ የእርቅ ሃሳቡንም ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አወያይተናቸው፣ “ጥሩ ስራ ነው፤ የኛም ሃሳብ ይሄው ነው፣ እንደግፋችኋለን” ብለውን ነው፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በአሜሪካ ስትገናኙ፣ በምን ጉዳዮች ላይ ነበር የተነጋገራችሁት?
በሃገሪቱ እርቅ ያስፈልጋል በሚለው ላይ ነው፡፡ እሳቸውም ሃሳቡን ተቀብለዋል፡፡ እንዲያውም የአንተን በጐ ሥራ፣ ከ8 ዓመት በፊት ነው ያወቅሁት ብለውኝ ነበር፡፡ “ለስራህ ክብር አለኝ፣ ወደ ሃገር ቤት ብትመጣና ተግባርህን ብታስፋፋ ጥሩ ነው” አሉኝ፡፡ ከመጣሁ በኋላም በቢሮአቸው ተቀብለውን አስተናግደውናል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ 16 ሰዎች አለን፡፡ ሁላችንም ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሰባሰብን ነን፡፡ በዚህ ስብስብ ምክንያት “ቲም ኢትዮጵያ” ነው የምንባለው። በዘር አናምንም፡፡ በኢትዮጵያዊነትና በሰውነት ነው የምናምነው፡፡ የምናራምደውም ይሄንኑ ዓላማ ነው። ወደዚህ ስንመጣ አላማችን፣ እርቅ ማመቻቸት በመሆኑ፣ አሁን “ለመተማመን እንነጋገር” በሚል የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ጀምረናል። ወደተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች መንቀሳቀስም ጀምረናል፡፡
የመጀመሪያ ጉዟችሁን ወደ ጋምቤላ አድርጋችኋል፡፡ ጋምቤላ ምን ጠበቃችሁ?
ጋምቤላ እንደደረስን የአካባቢው ባለስልጣናት ተቀብለውናል፡፡ ከተማ ከገባን በኋላ በአዳራሽ ስብሰባ አደረግን፡፡ በስብሰባው ላይ በ1992 የሞቱ 424 ሰዎችን ስም ዝርዝር በቪድዮ በመታገዝ ለህዝቡ አሳየን፡፡ እነዚህ ሰዎች በግፍ የተገደሉ ናቸው፡፡ መታሰቢያ ያስፈልጋቸዋል በሚል ውይይት አደረግን። በሞቱት ሰዎች ስም፣ 424 ዛፎች እንድንተክል መንግስትን ጠየቅሁ፡፡ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል፡፡ ዛፎቹ የተተከሉበት ቦታ መታሰቢያ ፓርክ እንዲሆን ተስማምተናል፡፡ በየዓመቱ ታህሳስ 4 ቀን የመታሰቢያቸው ቀን እንዲሆን ተነጋግረናል። በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እንዲመጣ የሚፈለገው እርቅም ከጋምቤላ እንዲጀምር ተወያይተናል። ከዚህ የጋምቤላ ጉብኝቴ ያወቅሁት ነገር ቢኖር፣ ጋምቤላ ከእነ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር አለመደመሩን ነው። ይሄን በግልፅ አይቻለሁ፡፡ አመራሮቹ ዐቢይን መደገፍ አይፈልጉም፡፡ በጠ/ሚኒስትሩ እርምጃዎች፣ ሥልጣናችንን እናጣለን የሚል ስጋት አላቸው፡፡ በአካባቢው መሬት ከወሰዱ ባለሃብቶች ጋር አንድ ላይ ነው እየሰሩ ያሉት፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር አንድ ላይ ለመቆም ብዙም ፍላጐት የላቸውም፡፡ እስካሁንም የድጋፍ ሰልፍ አለመደረጉ በዚህ ምክንያት መሆኑን ተረድቻለሁ። እኔንም ተቀብለው ያስተናገዱኝና ህዝቡን በአዳራሽ እንዲሰበሰብ የፈቀዱት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትዕዛዝ ፈርተው እንጂ ከልባቸው አይመስለኝም፡፡ ልማት የሚባል ነገር የለም፣ መንገድ፣ ሆስፒታል የለም። ሁሉም ነገር ኋላ ቀር እንደሆነ ነው ያየሁት፡፡ እኔ ራሴ በእውነት ግራ ነው የገባኝ፡፡ ለምን እንዲህ እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ህዝቡ ከልማት ጋር አልተገናኘም፡፡ አካባቢው የዘረፋ ቦታ እንጂ የልማት ቦታ አይደለም። ገንዘቡም፣ መሬቱም የጥቂቶች መጠቀሚያ እንጂ ህዝቡ ከልማቱ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ ህዝቡ ታፍኖ ነው ያለው፡፡ ጋምቤላ አለመደመሩን አውቄያለሁ። አመራሮቹ፤ የዐቢይን አሰራር የማይደግፉ ከሆነ፣ ለህዝቡ በግልፅ መናገር አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ነው የምንሰራው ብለዋል … ይሄን እውን ለማድረግ በምን መንገድ ነው የምትንቀሳቀሱት? አክራሪ ብሄርተኝነቱን እንዴት ታሸንፉታላችሁ?…
እኔ ጠ/ሚኒስትሩ ያሳዩን ነገር ተስፋ ሰጥቶኛል። በዚያው ልክ እንዳልከው ጐሰኝነት ሰፊውን ቦታ እየያዘ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ በቡራዩ የተከሰተው ጥቃት በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ በዚህ ዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጐች ተፈናቅለዋል፡፡ እነዚህ ዜጐች የተፈናቀሉት በዘር ጥላቻ ምክንያት ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ የፍቅር አይደለም፡፡ የእኔ እበልጥና የግድያ ፖለቲካ ነው፡፡ ይሄን የዘር ፖለቲካ ፊት ለፊት መዋጋት አለብን፡፡ በቡራዩ፣ ሻሸመኔ፣ በሶማሌ- ኦሮሞ የተፈጠረውን ሁሉ ያመጣው ባለፉት ዓመታት የተሰበከው የዘር ጥላቻ ነው፡፡ አሁን የተዘራው ጥላቻ ፍሬውን እያሳየን ነው፡፡ ይሄን ፍሬ የማምከን ኃላፊነት አለብን፡፡ በየቦታው ከህዝባችን፣ ከወጣቶቻችን ጋር መነጋገር አለብን፡፡ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችን፣ እናቶችን፣ ወጣቶችን አግኝተን ማወያየትና ማነጋገር እንፈልጋለን፡፡
ዘር እየቆጠሩ፣ በዘር ፖለቲካ፣ ጥላቻን የሚዘሩ ፖለቲከኞች፣ እውነቱ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ የጥላቻ ምንጮች እነሱ ናቸው፡፡ ገንዘብ ያላቸው የተደራጁ ሰዎች ደግሞ በገንዘባቸው የዶ/ር ዐቢይን አላማ እንዳይሳካ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እነዚህን መጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡ ጥላቻን የሚነዙ ሰዎች ወደ ሰውነታቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ይሄን እንዲያደርጉ በፍቅር ማስተማር አለብን፡፡ አሁን በየቦታው በማየው ነገር በጣም አዝኛለሁ፡፡ ልቤ ተሰብሯል፡፡ ምክንያቱም እኔ ልጆቻችን እንደዚህ አውሬ ሆነዋል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ የዘር ፖለቲካ ሰውን አውሬ ያደርጋል። ይሄን በማስተማር መቀየር አለበን፡፡ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ቀጣይ ቀጠሮ አለኝ፡፡ ስንገናኝ ይሄን ነገር በሰፊው እንነጋገርበታለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የጥላቻ፣ የዘር ፍሬ የሚዘሩ ሰዎች፣ ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ መንግስትም ጉዳዩን በቸልታ ማየት አይገባውም፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ድርጅታችሁ ምን ተግባራትን ነው የሚያከናውነው?
አሁን ውይይቶች እያዘጋጀን ነው፡፡ በቀጣይ በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች ቢሮ እንከፍታለን፡፡ ከሃገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በቅርበት እንሰራለን፡፡ ለምሳሌ በጋምቤላ ካሉት ሽማግሌዎች ጋር እየተመካከርን ነው፡፡ ትልቁ አላማችን ህዝቡን ማስተማር ነው፡፡ ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰብአዊነትን አብዝቶ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ በሚዲያዎችም የአየር ሠዓት ይዘን ለማስተማር እቅድ አለን። ካስተማርን የኅብረተሰባችንን፣ የወጣቶቻችንን አስተሳሰብ ማስተካከል እንችላለን የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ በቀጣይም የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ የጉራጌ፣ የጋምቤላ፣ የሌላውም ወጣቶች አንድ ላይ የሚመክሩበትን ጉባኤ ለማዘጋጀትም ሃሳቡ አለን፡፡ ትልቁ ስራችን ሰብአዊነትን መስበክ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ በየደረጃው ሰብአዊነትን ማጐልበት ያስፈልጋል። ልጆቻችን ሰብአዊነትን ተላብሰው ማደግ አለባቸው፡፡ በሰብአዊነት ላይ ኢትዮጵያዊነትን መገንባት አለብን፡፡ ለዚህ በሰፊው እንንቀሳቀሳለን፡፡
የእርቅ ሥራ እንሠራለን ብለዋል፤ ማን ከማን ነው የሚታረቀው? እርቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
በመጀመሪያ ከራሳችን ጋር መታረቅ አለብን። አስተሳሰባችን ከሰውነታችን መታረቅ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ዘረኛ ከሆነ፣ እንደ ማኅበረሰብ ዘረኝነት ያብባል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ከሰውነት ጋር እንዲታረቅ መሆን አለበት፡፡ ከራሳችን የምንጀምረው እርቅ በቀጣይ ለመተማመን በመነጋገር፣ የተፈፀመውን ሁሉ ግልፅልፅ አድርገን ተወያይተን፣ ተራርመን መሄድ መቻል አለብን፡፡
ለሃገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
መወያየት፣ መነጋገር ነው፡፡ ሰውነትን ታሳቢ አድርጐ መነጋገር፡፡ ይሄን ካደረግን መፍትሄው በእጃችን ነው፡፡ አሁን ያለን ተስፋ እንዳይቀለበስ ሁላችንም ድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡ አሁን ቀደም ሲል እኛን አሸባሪ የሚለን መንግስት የለም፤ስለዚህ ወደ ሃገራችን ገብተን ማገልገል አለብን ብለን መጥተናል፡፡ በየቦታው እየዞርን ሰብአዊነትን፣ አንድነትን እናስተምራለን፡፡ ችግሮች በመነጋገር፣ በመወያየት ነው የሚፈቱት፡፡
ለወደፊት በሃገርዎ ምን ተስፋ ያደርጋሉ?
ዘረኝነት ላለፉት 27 ዓመታት የተዘራ ክፉ ዘር ነው። ኢትዮጵያዊነት እንዲጨልም ተደርጓል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከመጣ በኋላ የተፈጠረውን ማኅበረሰባዊ መነቃቃት አይተናል፡፡ የዘረኝነት ፖለቲካ ትርፉ ግድያ፣ መፈናቀል፣ መለያየት መሆኑን ላለፉት 27 ዓመታት አይተናል። ያኔ በዘረኝነት ጥቃት የፈፀሙ፣ ኢትዮጵያዊነት ሲጐለብት ያፍሩበታል፡፡ ህዝቡ በኢትዮጵያዊነቱ ጠንካራ ነው፡፡ ምንም እንኳ በተለያዩ መንገዶች፣ በዘረኝነት ለመሸርሸር ጥረት ቢደረግም፤ ከህዝቡ ልብ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አልወጣም፡፡ ህዝባችንን ካጠናከርነው ጥሩ ውጤት እናገኛለን፡፡ ዘረኝነት ጠፍቶ ኢትዮጵያዊነት ያብባል። የኔ ተስፋ በህዝቡ ላይ እንጂ በፖለቲከኞቹ ላይ አይደለም፡፡ እያንዳንዳችን የዘር ጥላቻን፣ ድንቁርናን ለማሸነፍ መስራት አለብን፡፡ በዘር የሚያስብ ሰው፤ ራሱን የማይወድ ሰው ነው፡፡ ራሱን የማይወድ ደግሞ ሌላውን አይወድም፡፡