>

የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ወጣቶች – (ቄሮ፡- ተስፋና ስጋቱ፣ ፈውስና ሕመሙ) [እንዳለጌታ ከበደ]

የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ወጣቶች – 
(ቄሮ ፡- ተስፋና ስጋቱ፣ ፈውስና ሕመሙ)
 
እንዳለጌታ ከበደ
የእኔ ጥያቄ፣ ቄሮ የማን ነው? ራሱን የቻለ ነው? ወይስ በአንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ የሚመራ ቡድን? በኦሮሞ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ሁሉም ማለት ይቻላል፤ ‹ቄሮ የእኛ ነው!› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ኦህዴድም፣ ኦፌኮም፣ ኦነግም፣ ጃዋር መሃመድም፣ ሌላ ሌላውም የእኔ ናቸው ይላሉ። ‹እኛ ነን ለነውጥ ያሰማራናቸው፤ ላመጡት ለውጥ ሹመቱም ሽልማቱም ይገባናል› ይላሉ!!
  እንደ መንደርደርያ
ወጣትነት የልማትና የጥፋት ፍሬ የሚበቅልበት ዛፍ ነው፡፡ ለፍሬው መምረርና መጣፈጥ ዛፉ የተተከለበት ቦታ፣ ዛፉን የሚንከባከቡት ግለሰቦች ችሎታና ፍሬው የሚለቀምበት ጊዜ ይወስነዋል፡፡ፍሬውን ለመልቀም ማኅበረሰቡ ድንጋዩን ሽቅብ ሊወረውር ወይም ወቅቱ ደርሶ እስኪረግፍ ሊጠብቅ ወይም ዛፉ ላይ ወጥቶ ፍሬውን የራሱ ሊያደርግ ወይም ሌላ መላ ሊዘይድ ይችላል፡፡ ይህ የትም ያለ ነው፡፡ ዛሬ አልተጀመረም፡፡ ዛሬም አይቋጭም፡፡
ወጣትነት ለማዘዝ እንጂ ለመታዘዝ ዝግጁ የማይኮንበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ እንደ ፍም መጋል፣ መንበልበል፣ ጉልበተኛነት፣ አለመንበርከክ፣ ተራማጅነት፣ ለራስ ህልውና ቀናዒ መሆንና የለውጥን ፍሬ ለማጣጣም መቸኮል የዕድሜ ክልሉ መገለጫ ነው፡፡
ለዚህም ነው፣ በወጣትነት ዕድሜ የተለኮሰ እሳት ፍሙ በቀላሉ የማይበርደው፡፡ ተስፋና ስጋቱ፣ ሕመሙና ፈውሱ ተላላፊ ነው፡፡ ደስታውም ሀዘኑም በቀላሉ ይዛመታል፤ ይጋባልም፡፡
(‹THE ROOTS OF AFRIICAN CONFLICTS› የተሰኘው በ Alfred Nhema  እና በ Paul Tiyambe Zeleza የተሰናዳው መጽሐፍ፤ ይህንኑ ድምዳሜ አጽንዖት ሰጥቶ ይተነትነዋል፡፡)
                              …
ወጣት አማጺዎች በኢትዮጵያ
..
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የወጣትነት አኗኗር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከሰመ፣ እየዳመነና እየተቀየጠ መጣ እንጂ በአብዛኛው ‹ተቋማዊ› የሚመስል ነገር ነበረው ብዬ አምናለሁ፡፡
አሁንም አብዛኛው የገጠር ማኅበረሰብ ትውልዱን የሚኮተኩትበት፣ የሚያንጽበትና የሚያድንበት መንገድ አለው፡፡
የሴቶቹን ለጊዜው እናቆየውና፣ ወንዱ ቤተሰብ ከመመስረቱ በፊት የሚጠበቅበት፣ የሚፈተንበት፣ ሙሉ ሰው ለመሆን መቃረቡን የሚያሳውጅበትና ሊሻገረው የሚገባ ድልድይ (Rites of passage እንዲሉ ፎክሎሪስቶች) አለው፡፡ ድልድዩ ተወደደም ተጠላ መመዘኛው ነው፡፡
በሀገራችን፣ ወጣቱን ጋሻ አድርጎ፣ በተናጠልም ሆነ በቡድን፣ ባህላዊ በሆነ መልኩ፣ የራስን መብት ማስከበርና ሕዝባዊ ተቃውሞ ማሰማት የተለመደ ነው፡፡
እንደ ብርሃንና ጨለማ፣ እየተፈራረቁ፣ በገዢነት ስሜት ሌላውን ማፈናቀል፣ እየተፈራረቁ በዘርና በሃይማኖት እየወገኑ የማይመስላቸውን መበደል፣ እየተፈራረቁ ሌላውን እንደ ወገን አልባ ቆጥሮ ማስቆጠር፣ ትናንትም ዛሬም ያለ ልማድ ነው፡፡
ከሰማንያ ዘጠና ዓመት በፊት በተደረገው ‹የአማጺዎች› መንገድና አሁን እየተደረገ ባለው ተቃውሞ መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ ነው። ልዩነቱ የትናንቶቹ ማኅበራዊ ሚዲያውን ለቅስቀሳና መገናኛ አይጠቀሙበትም፡፡
መቀጣጠርያቸው፣ መፎከርያና መሸፈቻ ሜዳቸው ጫካው፣ ዱርና ገደሉ ነበር፡፡
ልጃገረዶችም፣ ለጎበዝ አራሽ ከዘፈኑት ይልቅ አውሬ አድኖ፣ጠላት ገድሎ፣ ንብረቱን አደርጅቶ ለተመለሰው ጉብል አሞካሽተው የዘፈኑት ይበዛል፡፡
ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፣ ‹ካየሁት ከማስታውሰው› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ፣ በየጊዜው ይነሳ ስለነበረ አመጽና ሁከት እና ሁከቱን ለማስወገድ ስለተሄደባቸው መንገዶች በብዛት ጽፈዋል፡፡
ለአብነት ያህል አንዱን ብናነሳ፣ ‹‹በዚያም ወራት ባዲስ አበባ ሰሜን ያለ አገር ራያ፣ አዘቦ፣ ዋጅራት የራስ ጉግሳ አርአያ የክፍል ግዛት አገር እራሱ አለቃ እያበጀ፣ አንድነት እየሆነ እየዘመተ፣ የወሎን ክፍል የአፋሩን አገር ግዛትና ከደጋውም ወረባቦ የሚባለውን የኦሮሞውን አገር ጭምር እየወረረ፣ ሰውን እየገደለና እየሰለበ፣ ከብቱን እየዘረፈ ይወስድ ነበር፡፡ (ገጽ 143)›› ይላሉ፡፡
በ1919 ዓ.ም ደግሞ፣ ‹ወያኔ› ተብለው የሚጠሩ ወጣቶች ደሴን አምሰዋት እንደነበር ‹ብርሃንና ሰላም›  ጋዜጣ ጽፎ ነበር፡፡ እነዚህ ወያኔዎች ‹ያባቶቻችን ልማድ ነው!› እያሉ በረባ ባልረባ ነገር ንብረታቸውን የሚያጡ፣ በጦር የሚገዳደሉ ነበሩ፡፡ ይህን የታዘበ የጋዜጣው ወዳጅ፣ ቅሬታውን ጽፎ ሲጨርስ፣ ‹‹እኝህን የመሰሉ ለደህና ቀን የሚሆኑ ልጆች ባልረባ በትንሽ ነገር እየተበላሹ መቅረታቸውን ተረዳሁት፡፡
ይህ ሁሉ መደረጉ የትምሕርት ማነስና መንግሥት አገሩን እየሰጣቸው የሚገዙ ሰዎች ለዕለቱ ከማሰባቸው በተቀር ለተወለዱባት አገራቸው ለመልካሚቱ ኢትዮጵያ ከሕይወታቸው የተረፈውን ባያስቡላት ይመስላል››
ወጣትነት ያኔም አሁንም ለለውጥ ብቻ ሳይሆን ለነውጥም የቀረበ ትጋት የሚስተዋልበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ወጣት፣ በወጣትነት ዕድሜው እንደ ጭልፊት ነጥቆ የሚበላበት፣ እንደ አንበሳ ጉልበቱን በሌሎች ብቻ ሳይሆን በራሱ ጎሳ ላይም ጭምር እንዲያሳይ የሚጋበዝበት፣(የሮናልድ ሌቪን Greater Ethiopia የተሠኘውን መጽሐፍ ልብ ይሏል)፣ ኅብረተሰቡን የሚፈትን መከራ ሲመጣ ቀዳሚ ሆኖ እንዲጋፈጥ የሚጠበቅበትና ይህን በመሰለ ተጋድሎ ራሱን ለማስተዋወቅ አሻራውን እንዲያሳይ የሚበረታታበት ነው፡፡አንዳንዴ ወጣቶቹ ከሚጠበቅባቸው በላይ ሲጓዙ፣ አንዳንዴ ደግሞ የሚፈትናቸው ነገር ጠፍቶ፣ የሌለ ጦርነት ያውጃሉ። ‹ጦር አውርድ› ብለው ይማጸናሉ፡፡በአብዛኛው ኢትዮጵያ ባሕል ውስጥ፣ወጣቱ ‹እራሱ አለቃ እያበጀ፣ አንድነት እየሆነ፣ እየዘመተ… ሰው እየገደለ፣ ከብት እየዘረፈ› ሕይወቱን ይመራል፡፡
ቄሮ/Qeerroo እና መሰሎቻቸው
…..
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ፣ የምስጋናው የበኩር ተቋዳሽ ወጣቱ ብቻ (ብቻ የሚለው ቃል ይሰመርበት) እየሆነ ነው።የለውጡ ጀማሪዎችም ፈጻሚዎችም ቄሮዎች፣ ፋኖዎችና ዘርማዎች ናቸው እየተባለ ነው፡፡ይህ አገላለጽ፣ በሌሎች ሕዝቦች መሐል ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች  ክፉኛ ‹መገለልና መድልዎ› እየደረሰባቸውና አንዳችም ዋጋ እንዳልከፈሉ የሚያስቆጥር ነው፡፡
ቄሮ፣ ፋኖና ዘርማ – ሦስቱም – ዘራቸውን/ ብሔራቸውን ከሚደርስበት ጥቃት ለመከላከል፣ ከመከላከልም ወደ ማጥቃት ለመሸጋጋር ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙ ወይም ውክልናውን ለራሳቸው የሰጡ የመብት ተሟጋቾች ናቸው፡፡ ሲሆን እንዳየነው፣ ጥብቅናቸው ለወጡበት ብሔር ብቻ ነው፡፡አልፎ አልፎ፣ እጅግ በጣም አልፎ አልፎ፣ የሌላውን ብሔር ስም እየጠቀሱ አጋርነታቸውን ለማሳየት ሲሞክሩ እንጂ፣ ተከታታይነት ያለው ሕብረት ሲፈጥሩ፣ በአንድ ቃል ሲናገሩ በአንድ ልብ ሲመክሩ አይታዩም።በጩኸታቸው ውስጥ ‹የጋራ ቤታችን› የሆነችው ኢትዮጵያን የማያት በጨረፍታ ነው፡፡ በ1960ዎቹ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ፣ ‹ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ፣ እንደነሆቺሚኒ እንደቼጎቬራ› ተብሎ ይዘመር ነበረ፡፡
መዝሙሩ ብሔራዊ ስሜትን እንዲቀሰቅስ የጥሪ ደወላቸውን የሚያስደምጡ ወጣቶች ተሳትፎ ያደርጉበት ነበር እንጂ፣ ‹አማራነትን› መሰረት አድርገው  የሚንቀሳቀሱ አልነበረም፡፡
እርግጥ ስለ ቄሮም ሆነ ስለ ለፋኖ እንዲሁም ስለ ዘርማ በቂ ዕውቀት – ማለትም ሃሳባቸውንና አደረጃጀታቸውን ለማቀፍም ሆነ ለመንቀፍ የሚያስችል፣ ለመውደድም ሆነ ለመጥላት የሚያበቃ በቂ ዕውቀት – የለኝም፡፡ አንድ ነገር ግን መመስከር እችላለሁ፡፡ ሦስቱም ሕብረት አፍቃሪዎች ናቸው።መሰረታቸው ባሕላቸው ነው፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ አንድ አባባል አለ – ‹ትናናሽ ናቸው ተብለው የሚናቁት ጉንዳኖች እንኳን በሰልፍ ሆነው ተቧድነው ሲመጡ አንበሳ ይፈራቸዋል፡፡› የሚል፡፡‹ድር ቢያብር አንበሳን ያስር› እንደ ማለት፡፡ የወጣቶቹ ድምጽና  ጩኸት የኢያሪኮን ግንብ ማፍረስ የሚችል ይመስላል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ቄሮ  ማለት ወጣት ነው። ያላገባ፣ ሌጣውን የሆነ፡፡ ቄሮ ቤተሰቡን ተጠግቶ የሚኖር፣ የሚፈነቅለው ድንጋይ እንዲበዛ የሚኳትን፣ ቢያንስ ቢያንስ በአካባቢው ዘንድ ተከባሪና ተፈሪ ለመሆን ከመሰሎቹ ልቆ ለመታየት ዝግጁ የሚሆን ነው፡፡ማደጉን፣ ለለውጥ መዘጋጀቱን፣ ለትዳር መድረሱን፣ በራሱ እግር ለመቆም መወሰኑን የሚያስታውቅበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡
እንደሚታወቀው፣ ቄሮ  ማለት ወጣት ነው። ያላገባ፣ ሌጣውን የሆነ፡፡ ቄሮ ቤተሰቡን ተጠግቶ የሚኖር፣ የሚፈነቅለው ድንጋይ እንዲበዛ የሚኳትን፣ ቢያንስ ቢያንስ በአካባቢው ዘንድ ተከባሪና ተፈሪ ለመሆን ከመሰሎቹ ልቆ ለመታየት ዝግጁ የሚሆን ነው፡፡ማደጉን፣ ለለውጥ መዘጋጀቱን፣ ለትዳር መድረሱን፣ በራሱ እግር ለመቆም መወሰኑን የሚያስታውቅበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡
እንዳነበብኩት፤ በአርአያነቱ ሊጠቀስ ይገባዋል በሚባለው፣ በገዳ ሥርዓት ውስጥ፣ በዕድሜ ተገድበው የተቀመጡ አስር እርከኖች አሉ፡፡ ከእነዚህ እርከኖች መካከል አንዱ – ሶስተኛው -‹ደበሌ› ይባላል፡፡ደበሌ ዕድሜያቸው ከ17-24 ዓመት ያሉ ወጣቶች ሲሆኑ፣ በኦሮሞ ባህል፣በዚህ እርከን ውስጥ ያለ ወጣት፣ ስለ ባህሉ፣ ስለ አንድነቱ፣ ስለ ነጻነትና ስለ መብቱ ሲቆረቆር ይታያል፡፡ በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ላይም ጉዳት እንዳይደርስ የሚሟገትበት ዕድሜ ነው፡፡
በሕዝቡ ላይ ችግር ሲደርስ ቀድሞ ቅሬታውን ማሰማት፣ ደስታ ሲሆንለትም በእልልታና ጭብጨባ ስሜቱን ማስተናገድ ይጠበቅበታል፡፡ የሕዝቡ የልብ ትርታ የሚደመጠውም በደበሌ አንደበት ነው ይባላል፡፡በእኔ መረዳት፣ ደበሌና ቄሮ የሚመሳሰል ነገር አላቸው፡፡ በእርግጥ ቄሮ ወንዶችን እንጂ ሴቶችን አያካትትም፡፡
ስለ ቄሮ ሳስብ ቅርም ግርምም የሚለኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካው መድረክ ላይ የምናያቸው ስመ-ጥር አክቲቪስቶች፣ ቄሮን አወድሰው አይጠግቡም፡፡የእኔ ጥያቄ፣ ቄሮ የማን ነው? ራሱን የቻለ ነው? ወይስ በአንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ የሚመራ ቡድን? በኦሮሞ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ሁሉም ማለት ይቻላል፤ ‹ቄሮ የእኛ ነው!› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ኦህዴድም፣ ኦፌኮም፣ ኦነግም፣ ጃዋር መሃመድም፣ ሌላ ሌላውም የእኔ ናቸው ይላሉ። ‹እኛ ነን ለነውጥ ያሰማራናቸው፤ ላመጡት ለውጥ ሹመቱም ሽልማቱም ይገባናል› ይላሉ፡፡
እነ ዶክተር መራራ ጉዲናም፤ ‹ቄሮን አንቅተን መንገዱን አሳይተን፣ እዚህ ያደረስነው እኛ ነን› ብለዋል፡፡በዚህች በ‹አዲስ አድማስ› ጋዜጣ እንኳን ስንቶቹ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ፖለቲከኞች ናቸው፣ ለቃለ መጠይቅ ተጋብዘው፣ (በዓላማም ሆነ በሌላ ሌላው ፈጽሞ የማይገናኙ) ቄሮን የልብ ወዳጃቸውና የቁርጥ ቀን ልጃቸው አድርገው  በስሙ ያጌጡት? በስሙ የማሉት? ይሄ ግርታዬ ነው፡፡
እንደኔ እምነት ቄሮ ፈረስ አይደለም፣ ሁሉም እየመጣ የሚጋልብበት፡፡ የራሱ አደረጃጀት ያለው፣ ፍትህ ግድ ከሚሰጠው ሕዝብ አብራክ የተከፈለ ነው።የሚታገለው፣ የወጣትነት ዕድሜውን የሚገብረው፣ የራሱን ብሔር ነጻነት ለማስከበር ብቻ ነው የሚል እምነትም የለኝም፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ አቃፊ ነው፤ ከአብራኩ ያልተከፈለውን ልጅ እንደ ራሱ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ የሌላውን ማኅበረሰብ ሃሳብ መቀበል የሚችል፣ ሕመሙንም ለመታመምና ጩኸቱን ለማሰማት ዝግጁ የሆነ ነው፡፡የፖለቲካ ድርጅቶቹና አክቲቪስቶቹ ግን ሃሳባቸውን በብርሃን ፍጥነት መለዋወጥና ለአንድ ብሄር ብቻ ማጋደል፣ እንደ ‹ፖለቲካ ስትራቴጂ› የሚቆጥሩ ናቸው፡፡
ቄሮና መሰሎቻቸው አስተዋጽኦ ያደረጉበትን ስለ ወቅታዊው ለውጥ ስናነሳ፣ወጣቶቹ የመብት ተሟጋቾች  አድርገውታል፤ እያደረጉትም ነው ከሚለው እንቅስቃሴ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ግንኙነት ያለው አንድ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ጉዳዩ ቅድም መጠቀሚያ የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ ብዬ ካስነበብኩት ጋር ግንኙነት አለው፡፡ የቅሬታዬም መነሻ ነው፡፡
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ፣ ‹ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 1922-1927›  በሚለው መጽሐፋቸው (ገጽ 134-136)፤ ራስ ኃይሉ በመንግስት ላይ አሲረዋል ተብለው ተሽረው፣ ራስ እምሩ የጎጃም  አስተዳዳሪ ተደርገው በተሾሙበት ዘመን ስለተፈጸመ ሽብር የሚተርኩልን አላቸው፡፡
ራስ እምሩ የጎጃም አገረ ገዥ ከሆኑ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ወደ አውሮጳ አቀኑ፡፡ ከንቲባ ማተቤ ተጠባባቂ ሆነውም ጎጃምን ማስተዳደር ሲጀምሩም የሚከተለው ሁነት ተፈጸመ ይላል መጽሐፉ፡፡‹…በዚህ ጊዜም የራስ እምሩ እንደራሴ ቀኛዝማች ወልደየስና የጦር አለቃው ቀኛዝማች ደምሴ በዛብህ የቤት አሽከሮችንና የቁጥር ወታደሮችን ይዘው በዳውንት ላይ ተጓዙና ወደ ጎጃም ተሻግረው በሐምሌ ወር ደብረ ማርቆስ ገቡ፡፡
የራስ ኃይሉ ልጅ ፊታውራሪ አድማሱም ከአቸፈር መጥቶ በሐምሌ ወር ደብረማርቆስ ገባ፡፡ ይህ ሰው በአባቱ መታሰር የተከፋ መሆኑን ለመግለጽ ከል የገባ የሀዘን ልብስ ለብሶ ይታይ ነበር፡፡ በከንቲባ ማተቤም ላይ አምባጓሮ ለማንሳትና የአባቱን ግምጃ ቤት ለማስዘረፍ፣ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ተመካክሮ ሲሰናዳ ከረመ፡፡ ከተዘጋጀም በኋላም፣ በመስከረም 20 ቀን 1925 ዓ.ም ዓርብ ጧት ከንቲባ ማተቤ ወዳሉበት ግቢ በስተጀርባ መጥቶ ተኩስ ከፍቶ ውጊያ ጀመሩ፡፡
ሕዝቡም ለዘረፋው ተባባሪ ሆኖ አብሮት ተሰለፈ፡፡… ከእኩለ ቀን በኋላ ፊታውራሪ አድማሱ በአንድ ወገን ጥሶ ወደ ግቢው ገባና ከፎቅ ላይ ወጥቶ የመትረየስ ተኩስ ከፈተ፡፡በዚህ ጊዜ ለዘረፋ የተሰበሰበው ሕዝብ ግምጃ ቤቱን ሰብሮ ገንዘቡንና ልብሱን፣ ዕቃውንና መሳርያውን ይዘርፍ ጀመረ፡፡ ይህ ዘረፋ የብዙዎቹን ሕይወት ለማስጠፋት ምክንያት ሆነ።አንዱ ዘርፎ ተሸክሞ ሲሄድ፣ ሌላው ጠብቆ እየገደለ ይወስድበት ነበርና፣ በአንድ ዕቃ እስከ አስር ወይም እስከ አስራ አምስት ሰው የተገደለበት ብዙ ሰው ነበር። ዕቃውን የሚወስደውም የመጨረሻው ዘራፊ ብቻ ነበር፡፡በግምጃ ቤት ተከማችቶ የነበረውንም አረቄ ዘራፊው ያለ ግምት ስለጠጣው ሁሉም ደፋርና ጨካኝ ሆኖ ዋለ፡፡… በዚያ አምቧጓሮና በዘረፋው ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 300  ሲሆን፣ የቆሰሉትም ከሺህ በላይ መሆናቸው ተነገረ››
በዚህ ተረክ ውስጥ አጋጣሚውን ይጠባበቁ የነበሩ፣ ላንዳፍታ ‹ወሳኙ ሰው› ገለል እስኪልላቸው ሲያደቡ የነበሩ፣ ሌሎች የጫሩትን እሳት መሰረት አድርገው ደግሞ “አባቴ/አባት ፓርቲዬ ተበድሏል” በሚል ሰበብ፣ በመንግሥት ላይ ሁከት ለማስነሳት ከፍተኛ ምኞት ያደረባቸው ነበሩ፡፡
በተፈጠረው ግርግር ጣልቃ ገብተው፣ በዘረፋው ራሳቸውን ለማበልጸግ የሚቋምጡ ወመኔዎችም ነበሩ፡፡ እልቂቱን ከፍ ያደረገውም ይሄ ነው፡፡ ዛሬም ያለው ሁኔታ ይኸው ነው፡፡
ተሸናፊው ‹ባልበላውም ጭሬ ልበትነው!› ማለቱ አይቀሬ ነው። የራስ ኃይሉ ልጅ፣ አባቱ ከስልጣን ተሽሮ በመታሰሩ አዝኖ አመጽ በመቀስቀስ፣ ለአማጺዎች ስንቅ በመስፈር፣ ጥይት በማቀበል እንደተጠመደው ሁሉ፣ አሁንም ‹የበፊቱን› ኢሕአዴግ የሚመርጡ፣ በራሳቸው ቋንቋ ልጠቀምና፣ ‹ያለፈው ሥርዓት ናፋቂዎች› አሉ፡፡ወጣቱ  የራሱን መዝሙር ለማሰማት ወደ አደባባይ ሲወጣ ‹ያለፈው ሥርዓት ናፋቂዎች› ሰልፉን ተቀላቅለው፣ የራሳቸውን አዝማች ደበላልቀው ሲያሰሙ መስማት አይቀሬ ነው፡፡
    ….
አሁን ምን መደረግ አለበት?
ለውጡም፣ ለውጡን ተከትሎ የመጣው ነውጥም በደስታና ሀዘን ካፊያ ብቻ ሳይሆን በወጀብና ውሽንፍር የተሞላ ነው፡፡
‹ለውጥ መጣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ ይህን ልኖረው ምኞቴ ነበረ› ብሎ የዘፈነውም፣ ‹እረኛ አልባ ሆነን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ልንጠፋ ነው!› ብሎ አንጎራጓሪውም አየሩንና ሚዲያውን ተቆጣጥሮታል፡፡የምሥራቹም መርዶውም በፍጥነት እየተደመጡ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ‹የሽግግር ጊዜ› የሚጠበቅ ሁከት ቢኖርም፣ አሁን እየሆነ ያለውና እየሆነ ባለው ነገር ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም።በምክር ብዛት፣ በመፈክር ብዛት፣ በማባበል ብዛት ሕግ አይጸናም፡፡ የመንግሥት ጥንካሬ የሚለካው አንዱ አካል እንዲናገር ብቻ ሳይሆን ከሚመለከተው አካል ጋር እንዲነጋገር በማድረጉ፣በጽኑ አቋሙና በፈጥኖ ደራሽነቱም ጭምር ነው፡፡
የሆነው ሆኖ፣‹መግደል መሸነፍ ነው› ስለተባለ ለውጥ አይመጣም፡፡ ‹መግደል መሸነፍ ነው!› የሚለው አባባል፣ ‹እዚህ አካባቢ መሽናት በሕግ ያስቀጣል› ከሚለውና በየግንቡ ላይ ከሚጻፈው ማስጠንቀቂያ እኩል እየሆነ ነው፡፡ መግደሉም በየግንቡ ስር መሽናቱም እየቀጠለ ነው፡፡
ግንብ ስር ሲሸና ተገኝቶ ለሕግ የቀረበ ሰው አላውቅም፡፡ የማስጠንቀቂያው መጻፍ ቦታውን ጽዱ አላደረገውም፡፡ ልክ ‹መግደል መሸነፍ ነው!› የሚለው አባባል፣ ገዳዮቹን፣ ‹እውነት እኮ ነው!› አሰኝቶ አደብ እንዳላስገዛቸው ሁሉ።እርምጃ መወሰድ አለበት። ከእርምጃው በፊት ግን፣ ወጣቶቹ ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ እንዲናገሩ፣ ከመንግሥት ሹማምንት ጋር እንዲወያዩበት፣ ወደ መፍትሄ በሚወስደው መንገድ በጋራ ሲጓዙ ማየት ቢቀድም ይበጃል፡፡ አለመነጋገር ነው ችግራችን፡፡
እንደኔ እምነት፣ ለወጣቱ እየተሰጠው ያለው ክብር አለቅጥ በዝቷል፡፡ አሁን ያለው ለውጥ፣ በባለፉት ሦስት አራት ዓመታት ጊዜያት በተነሳ ተቃውሞ ብቻ የመጣ ለውጥ ተደርጎ መቆጠሩ ተገቢ አይደለም።የብዙ ንብርብር፣ የብዙ ድምር ውጤት ነው፡፡ የሃያ ሰባት ዓመታት ልቅሶ፣ ሙግት፣ እንግልትም ጭምር እንጂ፡፡ ለውጡ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ነው፡፡ስንቱ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ታስሮአል? ተሰዷል? ስንቱ ተንከራቷል? ስንቱ ሀገሬን ኢትዮጵያን ብሎ በመዝፈኑ ነቀፌታን አስተናግዷል? አሁን ያለው ወጣት በመጨረሻው ሰዓት ዱላው እጁ ላይ ተይዞ ስለተገኘ፣ በዚህም የተነሳ ዋጋ በመክፈሉ ብቻ፣ በፍጥነት ሮጦም ሪቫኑን ስለበጠሰው፣ ‹ብቸኛ  አሸናፊ እሱ ነው› ማለት አይደለም፡፡
እነ ቄሮን በየሕዝባዊ ሰልፉ፣ በየዘፈኑ፣ በየጋዜጣዊ መግለጫው መሃል ማመስገን፣ ረዘም ያለ ጭብጨባ እንዲጎርፍለት ማድረግ፣ ፖለቲከኞቹ ካለፉት አምስት ስድስት ወራት ጀምሮ የተጠመዱበት ሆኗል፡፡መመስገናቸው ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ ተደርገው መቆጠራቸው ደግሞ አግባብ አይደለም፡፡ለምሳሌ፣ አክቲቪስቱ ጃዋር በአንድ ቃለ መጠይቁ ውስጥ ሁለት ዓይነት መንግሥት አለ ብሎ፣ አንደኛውን መንግሥት ቄሮ አድርጎ ሲቆጥረው መስማት ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ ቄሮ አዲስ አበባን መቆጣጠር እንደሚችል የተናገረውን መስማትና የተነገረበት ድምጸት ፈጽሞ ሊያሳምነኝና ልወድለት አልቻልኩም፡፡ጃዋር፣ በሻሸመኔ ከተማ በግፍ ስለተገደለው ወጣት ሲጠየቅ፣ ድርጊቱን የፈጸሙት ቄሮዎች እንዳልሆኑና ማን እንዳደረገው እንደሚያውቅም ጭምር ተናግሯል፡፡ ግን በወቅቱ እስፍራው የነበሩ፣ በእሱ አቀባበል ላይ ተሳታፊ የነበሩ ቄሮዎች፣ ግድያውን በዝምታ – የቃና ቴሌቪዥን ድራማዎችን እንደምትመለከት ሴት በተመስጦ – ለመከታተል መፍቀዳቸው፣ የኦሮሞ ባህል እንዳልሆነ ተናግሮ፣ ድርጊቱን ሲኮንነው ብሰማ አክብሮቴ ከፍ ይል ነበረ፡፡
ሲባል እንደምንሰማው፣የቄሮ መነሻና መድረሻ ግድ ሳይሰጣቸው የተቀላቀሏቸው አሉ፡፡ ‹አንዲት የሞተች ዝንብ ባጥሩ መዓዛውን ሽቶውን ሁሉ ታገማዋለች› እንዲሉ፣ ሽቶው እንዳይከረፋ፣ዝንቦችን ማራቅ ያስፈልጋል፡፡ሽቶው ለገዛ ውብ ጠረኑ ሲል፣ ራሱን ከሟች ዝንቦች ይጠብቅ፡፡ አንድ አለቦታው ትግሉን የተቀላቀለ ወጣት፣በገንዘብ ተደልሎም ይሁን በራሱ ተነሳሽነት ተቀላቅሎ ገብቶ፣ እንቅስቃሴውን ሊያዳምነው ይችላል፡፡ታናናሾቻቸውም እያዩአቸው ነው፡፡ እናም ሊኮረጅ የሚገባቸው ሰናያት ተግባራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሳጠቃልለው፣ የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ለመብታቸው ያላቸውን ቀናኢ ስሜት እያደነቅሁ፣ ይህ ቀናኢ ስሜታቸው በብሔራዊ ደረጃ እንዲያድግ እየተመኘሁ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከከንቱ ሆይ ሆይታ፣ ወይም ከባዶ ድንፋታ፣ ወይም ከአጉል ጀብደኝነት ተላቅቀው፣ በዕውቀት ለመጎልመስ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው መጠቆምም እፈልጋለሁ፡፡
ወጣቶቹ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ባለ ሥራ እንዲሆኑ፣ ‹በትምህርት ማነስ› ምክንያት ከላይ እንዳነሳናቸው ‹ወያኔዎች› ሀገራቸውን እንዳያጨልሙ፣ የወጡበትን ማኅበረሰብ አንገት እንዳያስደፉ፣ ከማን ጋር ምን መምከር እንዳለባቸው መንገድ መጠቆም የታላላቆቻቸው ፈንታም ጭምር ነው፡፡ይህ የመቧደን እንቅስቃሴ፣ አፍርቶና ጎምርቶ ለተጠቃ ሲደርሱ፣ የጎበጠውን ሲያቀኑ፣በዳዩን ወደ ፍርድ ተቋማት ሲያስረክቡ መታየት አለባቸው፡፡‹ለመልካሚቱ ኢትዮጵያ› አርአያ መሆን የሚገባውን ሥራ በሚሰሩበት ዕድሜ፣ የአንድ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሠራተኛ ከመሆን እንዲታቀቡ ምክርም ተግሳጽም ሊለገሳቸው ይገባል፡፡
(አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ መስከረም 12/2011 ታትሞ የወጣ)
Filed in: Amharic