አሰፋ ሀይሉ
ፕሮፌሰር አይራ ዊልያም ዛርትማን… ማንኛውንም በዓለማችን ላይ ባለ ሃገር ውስጥ የሚፈጠር… የእርስ-በእርስ… ወይም አካባቢያዊ ግጭት መነሻው ከሶስት ከሶስት ምክንያቶች አያልፍም፡፡
አንድም፡- የተለያዩ ፍላጎቶቻችን ታፍኖብናል የሚሉ ሰዎች የሚፈጥሩት የጋራ እንቅስቃሴ (ወይም አመፅ) ነው፤
ሁለትም፡- የእኛ እምነት ወይም የእኛ ብሔር ወይም ማንነት በተለየ መልኩ ተረግጦብናል የሚሉ የሆነ ብሔር ወይም እምነት አባላት የሚፈጥሩት ኃይል የታከለበት የጋራ (ወይም የጋርዮሽ) እንቅስቃሴ ነው፤ አሊያ ግን እነዚህን ሁለቱን ካልሆነ..
ሶስትም፡- ሊሆን የሚችለው… የብዙ የተለያዩ መልኮች ያሏቸው ግጭቶች አንድ ወይም ሁለት ወይም በርካታ የሆነ ስብስብን ያነሳሱ፣ ያበረታቱ ወይም መንገድ የቀየሱ ‹‹መሪዎች›› ግላዊ ስግብግብነትና.. የግል ዝና ጥማት.. ናቸው ለግጭት መባባስና በቶሎ ግጭቶች እንዳይፈቱ አብይ መንስዔ የሚሆኑት፡፡
አንደኛ የግጭት ምክንያት፡- የተጨቆነ ፍላጎት — Conflicts of Need
ፕ/ር ዛርትማን ሰውን ቀውስ ነው ብለህ አታስበው ይላሉ፡፡ ሁሉም ሰው ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ደግሞ… ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ግጭትና አመፅን እንደማያቀጣጥል ማሰብና መረዳት ያስፈልገናል ይላሉ፡፡ ስለዚህ የሆነ ግጭት ስታይ የሆኑ ፍላጎቶች እንዳሉ ማወቅ አለብህ፡፡ እንዲያውም ይላሉ ፕሮፌሰሩ… አብዛኛውን የዓለማችን የሃገር ውስጥ ግጭቶች የሚፈጠሩት… ‹‹የሆኑ አንድ ዓይነት የሚያመሳስል ባህርይ፣ ወይም ጠባይ.. ወይም ፍላጎት… ወይም አካባቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች… በቃ እኛ ብቻ ከሌላው ተለይተን የተከለከልነው ነገር አለ… ሆነ ተብሎ መብታችን ተገድቦብናል…. የሚል የጋራ ስሜት ሲሰማቸው — ሲደርስባቸው እኮ አይደለም… እንደዚያ ነው ብለው ካሰቡ ራሱ — በቃ ግጭትን ይቀሰቅሳሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ መብቶችን የተነፈጉ ሰዎችም በጋራ የሚያነሱትን ጥያቄ መልስ ሲነፈጋቸው… በግድ ለማስፈፀም ሲሉ… ግጭትንና ኃይልን… እንደብቸኛና ዓይነተኛ አማራጭ ይመለከቱታል፡፡
ሰዎች በምንም መልኩ ይሁን ሆን ተብሎ በሌሎች እየተሸረበባቸው ባለ ተንኮል፣ ክፋትና አድማ የተነሳ… የሆነ የጥቃት ሰለባዎች ሆነናል… ሆነ ተብሎ በደል እንዲደርስብን እየተደረግን ነው… አሊያም በህቡዕና በማሸመቅ… እኛን ለማጥፋት… ለማደህየት… ለመበደል.. ኃይል ለማሳጣት… ወይም ድምፃችንን ለማፈን… በዙሪያችን የተደራጀ ሴራ እየተሰራብን ነው… ሆነ ተብሎ እኛ ገፈት እንዲወርድብን እየተደረግን ነው… ወዘተ ወዘተ.. የሚል ስሜት ከተሰማቸው… በምንም መልኩ ይሁን — ይላሉ ፕሮፌሰር አይራ ዊልያም ዛርትማን — ይዋልም ይደርም… ይዘግይም ይፍጥንም… ብቻ… እንደዚያ አድርጎናል… ምንም መፍትሄም የለውም.. አውቀነዋል.. ነቅተንበታል… ከሚሉት አካል ጋር የከረረ ግጭት ይፈጥራሉ፡፡
እንግዲህ እነዚህ በፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶች ሦስት መሠረታዊ ማጠንጠኛ ነው ያላቸው፡፡ አንድ፡- ኃይለኛ በደል ደርሶብኛል፣ ተጨቁኛለሁ፣ ተረግጫለሁ ነው፤ ሁለት፡- ላገኝ የሚገባኝን.. የኛ የሆነውን ነገር.. ተከልክለናል፣ ለሌሎች የሚሰጠውን ዕድል እኛ ተነፍገናል፣ መንገዱ ተዘግቶብናል ነው፤ እና ሶስት፡- ልዩነትና መድልዎ ተደርጎብናል.. በምንም ጥቅም.. በምንም ሃብት.. በምንም ዕድል.. በምንም ፍትህ… ከሌሎች በተለየ በእኛ ላይ መድልዎና ልዩነት ይደረግብናል… ለኛ ሲሆን ይከፉብናል.. ከኛ ሲሆን አላግባብ ይነጥቁናል.. በኛ ላይ ሲሆን ይበረታሉ ነው የሚሉት፡፡
ግን ግን.. እሺ ይላሉ ፕሮፌሰር አይራ ዛርትማን… ግን ግን ሰዎች ለምንድነው እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው የሚችለው??? ለምን ጥቃትና ሸር እነርሱ ላይ የተነጣጠረባቸው መስሎ ይሰማቸዋል??? — ይሉና መልሱንም ያስቀምጣሉ፡፡ ምናልባት እነዚያ ሰዎች ያሉበት የማህበራዊ፣ የሥልጣኔ፣ የሃብት ወይም የክብር፣ ወይም ሌሎች ማህበራዊ እርከኖች… ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያሉ ከሆኑ… አሊያም ደግሞ… ዝቅ ያለ ደረጃ ላይ ያሉ ከሆኑ… በቃ… ሌሎቹ እኔ ላይ አነጣጥረውብኛል የሚል ስሜት ይፈጠርባቸዋል፡፡ ሌላም ምክንያት አለው ይሉናል – ፕሮፌሰር ዛርትማን፡፡
ሌላው እንዲህ ዓይነት ለግጭት የሚዳርጉ ስሜቶችን የሚቀሰቅሰው ትልቁ ምክንያት ደግሞ…
በቃ… ሰዎች በስኬታቸው.. በጥረታቸው… ራሳቸው ባፈሩት ነገር.. ወይም በተቀዳጁት እርከን.. ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሳይሆን… በቃ… ማንኛቸውንም እነዚህን ነገሮች የማይጠይቁ… ከሆነ ዘር መወለድ ወይም ከሆነ ብሔር መምጣት… ወይም በሆነ አካባቢ መወለድ ብቻ በቅድመ-ሁኔታነት ተቀምጦ በአባልነት የሚገባበት… ለሌሎች ዝግ.. ለራስ ብቻ ክፍት.. የሆኑ ስብስቦች.. መንበሮች.. ማህበራት.. ወይም ቡድኖች ሲፈጠሩ…. ሌሎቹ የዚያ ዝግ ስብስብ አባል ያልሆኑትና ሊሆኑም የማይችሉት…. በቃ ‹‹ታርጌትድ›› የመደረግ ስሜት ይፈጠርባቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ በ‹‹ፍላጎት›› ላይ የተመሠረቱ ግጭቶች ብቻ ሳይሆኑ ‹‹በማንነት›› ወይም ‹‹በዕምነት›› ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችም ራሳቸው…. የሚቀሰቀሱት በዚሁ መሠል አስተሳሰቦች.. ግምቶች… ወይም ስሜቶች… ወይም ዕምነት-ማጣቶች… ወይም መጠራጠሮች… ወይም ከስንት አንዴ (በጣም አንዳንዴ) በዚህን መሰል እውነታዎች የተነሣ ነው፡፡
ሁለተኛ የግጭት ምክንያት፡- የዕምነት ወይም የብሔር ማንነት ጥያቄዎች — Conflicts of Creed
የዚህ መሠሉ ግጭት ዓይነተኛ መገለጫ የሆነ ኃይማኖት ወይም የሆነ ዓይነት እምነት ያላቸው ሰዎች በሌላው ከዚያ በተለየው… ወይም በተለዩት ሰዎች ወይም ስብስቦች… የተለየጠ በእኛ ላይ ጫና አድሮብናል… የተለየ መገለል ደርሶብናል… በኃይማኖታችን ላይ በተለይ የተነጣጠረ ጥቃትና ሸር ተፈጽሞብናል… እኛ በዚህ ወይም በዚያ ኃይማኖት ተከታይነታችን የተነሣ.. ይሄ ወይም ያኛው አድልዎና ክልከላ ተደርጎብኛል የሚሉ እና ለብዙ የዓለማችን ሃገሮች የእርስ በርስ ግጭቶች መንስዔዎችም የሆኑ ናቸው እነዚህ ሰበቦች፡፡ ኃይማኖቶች ወደ ላይ ወደ እዝጌሩ ሳይሆን ወደ ጎን ወደ ሰዎች ማየት ሲጀምሩ የሚፈጠር ግጭት ነው ይሉታል ይሄን ዓይነቱ ነገር የወለደውን ግጭት፡፡
ከእነዚህ በመቀጠል ደግሞ ያለው የሆነ ብሔረሰብ አባላት የሆኑ… ወይም ደግሞ የሆነ የሚለዩበት የቆዳ ቀለም ያላቸው… ወይም ደግሞ በሆነ በተለየ ቋንቋ የሚገለገሉ… ወይም ደግሞ የሆነ ከሌላው የተለየ የአለባበስ… ወይም የሰውነት… ወይም የፀጉር… ወይም የተለያዩ የባህል ትውፊቶች ያሉት.. አንድ ማህበረሰብ.. ወይም የሆነ የሰዎች ስብስብ… ወይም የሆነ የአንድ አካባቢ ተወላጆችና ነዋሪዎች ስብስብ… በቃ…. ምን ብሎ ያስባል??? — (በነገራችን ላይ ‹‹ማሰብ›› ብቻ በቂ ነው — ለግጭት!!) — በቃ እኔ እንዲህ በመሆኔ… ወይም እኛ እንዲህ በመሆናችን… ወይም እነሱ እንደኛ ስላልሆኑ… ነው ይሄን ይሄን ያንን በደል እየፈፀሙብን ያሉት ብለው ነው ግጭቱን የሚቀሰቅሱት፡፡
በተለይ በተለይ ደግሞ… ምንም ከብሔሩ ገጽታ.. ወይም ከባህሉ.. ወይም ከማንነቱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው… ለምሳሌ ድህነት፣ ወይም በሽታ፣ ወይም ችጋር…፣ ወይም ማይምነት፣ ወይም በቃ እነዚህን የመሣሠሉት ነገሮች የዚህን ብሔር-ተኮር ማህበረሰብ ወይም የሆነን-አካባቢ ሕዝቦች ያጠቁ ወይም የተፀናወቱ ሆኖ ሲገኝ…. ይህ ሆነ ተብሎ የዚያን ብሔር አባላት ለማጥቃት፣ ለማጥፋት፣ ለመጉዳት፣ ለመቅሰፍት ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ.. እንዳይሻሻሉ ለማድረግ… ወይ ተነስተው ለራሳቸው ዘብ እንዳይቆሙ ለማድረግ…. ሆነ ተብሎ በሌላው አካል በረቀቀ ዘዴ እንዲደርስባቸው የተደረገ አድርገው ነው የሚወስዱገት፡፡ ወይም እንዲያ ዓይነቱ ሃሳብ በተደጋጋሚ ይንሸራሸራል፡፡ ይህ አንዴ ከተፈጠረ… አበቃ… ‹‹እኛ›› (ሰለባ እየተደረግን ያለነው!) እና ‹‹እነሱ›› (በእኛ ላይ ይህን ሁሉ እያደረሱብን ያሉት!) የሚሉ ‹‹አለያይ›› እምነቶች ወይም ስሜቶች ቦታ አገኙ ማለት ነው፡፡ ካገኙ ደግሞ አከተመ፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ዕምነት የለውምና፡፡
ፕሮፌሰር አይራ ዊልያም ዛርትማን… ለእንዲህ ዓይነቶቹ ብሔር-ተኮር ግጭቶች ዋነኞቹ መንስዔዎች ሶስት ናቸው ይላሉ፡-
1ኛ/ ፈጣንና ሥር-ነቀል የሆነ (ቀድሞ የነበረውን ከሥሩ የሚቀያይር) ለውጥ ሲኖር፡-
እንዲህ ካሉ ፈጣን ለውጦች ጋር ሁሉም እኩል የመጓዝ ብቃት የለውም፤ እና አንዳንዶች በእነዚህ ለውጦች ከበፊቱ የበለጠ ጥቅም ሲያገኙ.. ሌሎች ደግሞ የነበራቸውንም ሊያጡ ይችላሉ… ሌሎች ደግሞ እየተከናወነ ያለው ፈጣን ለውጥና የነገሮች መቀያየር.. የብሔራቸውን.. የሕዝባቸውን.. እና የባህላቸውን እሴቶች አንድ በአንድ እየሸራረፈ የሚጥልባቸው.. የሚበርዝባቸው… የሚያጠፋባቸው.. ለእነርሱ ማንነት ‹‹ፀር››! የሆነ አድርገው ሊቆጥሩትና… በዚህም የተነሳ.. ያን ለውጥ ሊያካሂዱ የሚሞክሩት አካሎች ላይ.. ኃይል የተሞላበት ‹‹ራስን የመከላከል›› እንቅስቃሴና አመፅ ይፈጥራሉ!!!
2ኛ/ ቀደም ሲል የተሞከሩ ‹‹የጋራ ማንነት!!›› መፍጠር ሙከራዎች ሳይሳኩ ሲቀሩ
ሲከሽፉ… ወይም ደግሞ.. የጋራ አንድነትና የጋራ እኛነት ለመፍጠር የሚደረገው ጉዞ.. ፈተናው እጅጉን ከበዛ… በቃ… ያ ‹‹ኮመን ናሽናል ፕሮጀክት ፌይል›› ያደርጋል!! እና ክፍተት ይፈጠራል!! እና ቀደም ሲል በዚያ የጋራ ሃገር.. እና የጋራ ሕዝብ ለመፍጠር በተደረገው ጥረት… ማንነታቸውን ሊያጡት ተቃርበው የነበሩ (ወይም የመሠላቸው) የተለያዩ ማንነቶች የቆየ የተጠራቀመ ኃይላቸውን አጠራቅመው.. በሙሉ ኃይል.. በብዙ አባሎቻቸው ድጋፍ.. ሆሆሆ!! ብለው ይወጣሉ!!! ሌሎችም እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ እና እኒህ ማንነት-ተኮር ኃይሎች የሚፈጥሩት ግጭት በዓለማችን በ20ኛው ክፍለዘመን በብዛት የተስተናገደ ነው ይሉናል — ፕሮፌሰር አይራ ዛርትማን — ሶቪየቶችን፣ ዩጎዝላቪያን፣ ሶማሊያን፣ ኢትዮጵያን፣ እና ሌሎችንም ያነሳሳሉም በምሳሌነት!!!!
3ኛ/ መድልዎ ማድረግ… ለአንዱ ያገኘውን ለሌላው መከልከል፡-
ይህ ነው ትልቁ እና በሁሉም ዓይነት የግጭት ምክንያቶች ውስጥ በውስጠት-አዋቂ ያለው ዋነኛ ጥያቄና የቅሬታ ምንጭ – ወይ ‹‹ቤሲክ ኤለመንት!››!! ይህ በትክክልም ሊኖር ይችላል፡፡ አሊያ ደግሞ በትክክልም ሳይኖር… እንዲህ የሚለው ሃሳብ ወይም ስሜት ብቻ ሊሆንም ይችላል ያለው፡፡ እና ይህ ዓይነቱ ልዩነትና መድልዎ (ዲስክሪሚናተሪ ፕራክቲስዝ) — ያነሳነውንና እጅግ አደገኛ የሆነውን ‹‹ኔጌቲቪቲ ፊሊንግስ›› በመፍጠር ‹‹እኛ!›› (የተበደልነው! ጊዜ-የጣለን! የእንጀራ ልጆቹ!) እና ‹‹እነሱ›› (ተጠቃሚዎቹ! ባለጊዜዎቹ! የስለት ልጆቹ!) የሚሉ ስሜቶች በከፍተኛ ሁኔታ ይስፋፋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ ሲጠራቀምም… ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትሉ… መስሚያ ጆሮ የሌላቸውን… አሰቃቂ ግጭቶች ይፈጥራሉ፡፡ ፈጥረዋልም ይሉናል — ፕሮፌሰር ዛርትማን — እዚሁ በአህጉራችን በአፍሪካና በአውሮፓ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ በዚህን መሠል ምክንያቶች የተፈፀሙ ጥፋቶችን — አንዳንዴም ምስሎችን እየከሰቱ — በምሳሌነት በመጠቃቀስ፡፡፡
ሶስተኛው የግጭት ምክንያት፡- የ‹‹መሪዎች›› ስግብግብነትና.. ዝና ጥማት.. — Conflicts of Greed
መሪዎች — ይላሉ ፕሮፌሰር አይራ ዊልያም ዛርትማን — ብዙውን ጊዜ ስለራሳቸው ደንታ የሌላቸው፣ የራሣቸውን ግላዊ ፍላጎትና ጉጉት ፍፁም ረስተው… የሚወክሏቸውን ሰዎች ወይም ሕዝቦች ፍላጎቶችና የጥቅም ጥያቄዎች በቀጥታ የሚያንፀባርቁ ሆነው ይገኛሉ ይሉናል፡፡ ነገር ግን ይላሉ — ፕሮፌሰር ዛርትማን — ያለመታደል ጉዳይ ሆኖ አንዳንዴ… ግጭትን እንዲፈታ ከመጣጣር ይልቅ… የወከሉት ማህበረሰብ ሰላምን እንዲያገኝ ከመርዳት ይልቅ… የሚመሩት ሕዝብ ብርቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ከማመቻቸት ይልቅ… ሁልጊዜም ግጭት እንዲኖር ሌት-ተቀን ተግተው የሚሰሩ… እና… ግጭቱ ከበረደ በቃ የእነሱ – የመሪነት – አስፈላጊነት እና ክብር እና ስልጣን.. እና መሪነት… አብሮ ከግጭቱ ጋር ስለሚያከትም… በምንም ተዓምር ግጭት እንዲመክን አይፈልጉም!! አንዱ ግጭት ቢያበቃ ሌሎችን ግጭት ይፈጥራሉ!! ወይም እንደሚፈጠር ለሕዝባቸው እያነቁ በተጠንቀቅ ያቆዩታል – ለምን?? እነርሱን ተሸክሞ እንዲያኖራቸው… ዕውቅናውን እንዳይነሳቸው…!!!!!
እኒህ ዓይነት መሪዎች — እነርሱ የግል ዝናና ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸው… ሁልጊዜ በሚመሯቸው.. እና ይበጁኛል ብሎ በመሪነት በተቀበላቸው… ሕዝባቸው ዘንድ… ሁልጊዜ… ግጭት ወይም የግጭት ሃሳብ.. መጠንሰስ አለበት! ግጭት የህልውናቸው ምንጭ ነው!!! አሊያማ ማን ይፈልጋቸዋል??? እንዲህ ዓይነቶቹ ‹‹ሎርድስ ኦፍ ኮንፍሊክት!!›› ‹‹የግጭት ጌቶች!!›› ቢባሉስ… ማዕረጉ በትክክል አይገልፃቸው ይሆን???!!! ፕሮፌሰር ዛርትማን በተለይ የሚያንገፈግፏቸውን አንዳንድ ‹‹እኔ-ብቻ!! የግጭት ጌቶች››ን በስም ሁሉ ይጠሯቸዋል!!! አንዳንዴ ደግሞ… የፀጥታ ኃይሎች ግጭትን ሊያበርዱ ሲመጡ ልብ ሊሉ የሚገባው — ይላሉ ፕሮፌሰሩ — የፀጥታ ኃይሎቹ መተኮስ የለባቸውም! ግጭቱን ለማብረድ ሲባል የግድ መተኮስ ካለባቸው ግን መተኮስ ያለባቸው… እነዚህ ስግብግብ የግጭት ጌቶች ላይ ነው እንጂ… በግጭቶቹ ላይ እየተሳተፈ… ያለው ሰው እኮ.. እርሱማ ራሱ የእነዚህ ስግብግቦች ገፈት ቀማሽ እኮ ነው – ሕዝቡ ሠለባ ነው – ሊታዘንለት እንጂ – ሊተኮስበት አይገባም!!!! ሲሉ ይመክራሉ!!!
ፕሮፌሰር አይራ ዊልያም ዛርትማን — በመጨረሻም ለግጭቶች (በተለይ ለብሔር-ተኮር ግጭቶ) ፍቱን መድኃኒቶች ብለው የሚጠቃቅሧቸው በርካታ መፍትሄዎች አሉ — መፍትሄዎቹ ከቦታ ቦታ አገልግሎታቸው እንደሚለያይ፣ በጊዜ ግጭቱ ሳይፈጠረር ቢሆኑ እንደሚሻል፣ እና ትልቅ ትዕግስት፣ ጥበብና ችሎታም እንደሚጠይቁ በመምከር ጭምር ነው የሚዘረዝሯቸው፡—
አንደኛ መፍትሄ፡- ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም.. ማንኛዎቹንም ብሔር-ተኮር ጥያቄዎች መናቅ አያዋጣም፡፡ አሁን አናሣ የሆኑት፤ ነገ የኔ ነው የሚለውን የትልቁን ሁሉ ነገር ነጥቀውት ጉብ ሊሉ ይችላሉና፡፡ ሁሉንም በሰፊ ጆሮ እና በሰፊ ልብ ማድመጥ!!!!
ሁለተኛ መፍትሄ፡- በምንም ዓይነት ቢሆን፣ በማንኛውም ቦታ ቢሆን ለእነዚህ ነገሮች ምትክ ማካካሻ ሊገኝላቸው አይቻልምና ሁልጊዜም ለሁሉም መዳረስ አለባቸው ይላሉ፡፡ መልካም አስተዳደር፣ ተጠያቂነት፣ ዲሞክራሲ፣ እና ከሸፍጥና ከጉልበተኝነት የፀዳ ፖለቲካ!!!
ሶስተኛ መፍትሄ፡- ‹‹ታሪክ አብሮ የሰፋውን፤ ጊዜያዊ ስሜቶች እንዲቀድዱት አይሁን!!›› “What history has joined together, let not momentary passions put asunder” ይላሉ በራሳቸው በፕሮፌሰር አይራ ዊሊያም ዛርትማን ቃላት!!!!! ሁልጊዜም ቢሆን… በዓለማችን የታየው እውነታ የሚሰክረው… ይላሉ… በታሪክ ለረዥም ዘመናት አብሮ ከኖረበት ተለይቶ ተገንጥሎ በመውጣት… ያሰበውን ያሳካ ሕዝብ እጅግ እጅግ ኢምንት ነው ይሉናል!! ብዙ በመነጣጠል ይገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ተስፋዎች ላም አለኝ በሰማይ ናቸው ይሉናል፡፡ ብዙ የዓለማችን መሰል ህዝቦች ከኖሩበት ማህበረ-ሰብ ተለይተው በመገንጠላቸው ያተረፉት ነገር የለም፡፡ አዲስ ሃገር የመመስረት… ህዝብን ለብቻ የማስተዳደር ፈተናው ብዙ፤ መንገዱ አስቸጋሪ፣ ግቡ እጅግ እጅግ ሩቅ ነው ይሉናል፡፡ እና ይላሉ ፕሮፌሰር አይራ ዊልያም ዛርትማን… ምንጊዜም ቢሆን ግጭት ሲፈጠር… ማናቸውም አደራዳሪም ይሁን ሽማግሌ… መዘንጋት የሌለበት እና ማረጋገጥም ያለበት ነገር… ተጋጪዎቹን ለመለያየት ሳይሆን… ተጋጪዎቹ… እንደቀድሞው አብረው በህብረትና በሠላም እንዲኖሩ የሚያስችል መፍትሄ ማምጣቱን ነው!!!!!!!
አራተኛ መፍትሄ፡- ‹‹ፍርድ ቤቶች የባልና ሚስት ፍቺን ለመወሰን ጥሩ ሥፍራዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ የብሔሮችን ወይም የሰዎች ስብስቦችን ግጭት ለመፍታት ግን — እመኑኝ — ፍርድ ቤቶች ጥሩ ተመራጭ አይደሉም!!››፡፡ እና ይላሉ ፕሮፌሰር አይራ ዊሊያም ዛርትማን… ግጭቶች ሲነሱ… መንግሥትም በቀጥታ አስታራቂ ሆኖ በይገባ.. መንግሥት ያቋቋማቸው አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ አካላትም በአስታራቂነቱ ሂደት ጣልቃ ባይገቡም ይመረጣል፡፡ እና እርቀ-ሰላሙን ከፖለቲካ ገለል ያለ አካል ቢያደርገው!!! ኦፊሺያል ያልሆኑ… ባለስልጣን ያልሆኑ ቢያደርጉት… ገለልተኛ አሸማጋይ ሰዎችና አካሎች ቢያደርጉት… እና ከምንም በላይ ደግሞ በሕዝቡ ውስጥ የኖሩ አንጋፋዎች ቢሳተፉበት ግጭትን በተሣካ መልኩ መፍታት ይቻላል!!!!
አምስተኛ መፍትሄ፡- ‹‹ቅሬታ ያላችሁ ብሔሮች.. ቡድኖች.. ወይም የሕብረተሰብ ክፍሎች፡-
ይህን ምክሬን ስሙኝ! ሁልጊዜም ቅር-የተሰኛችሁበት የእናንተ ሁኔታ የሚሻሻልበትን… የሚስተካከልበትን.. የሚቀረፍበትን ሙከራዎች ሁሉ አድርጉ!!! ነገር ግን በፍፁም! በፍፁም! በፍፁም! የእናንተን ለማሻሻል ስትጣጣሩ ግን… የሌሎችን ደፍጥጣችሁ አይሁን!!!!›› (‹‹Find ways to improve your own status that do not damage the status of others!››)፡፡
ስድስተኛ መፍትሄ፡- ‹‹መንግሥታት፣ የሃገር ውስጥና ዓለማቀፍ ተቋማት፣ እባካችሁ ዋነኛውን ነገር አታሳልፉት፡፡
መላ ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን… የብሔር-ተኮር ግጭቶች… ሣይፈነዱ በፊት… የብጥብጥና አመፃ ተግባራትን ሳያስከትሉ በፊት… አስቀድማችሁ ብሄር-ነክ ግጭቶችን ለመከላከል አውሉት!!!! ለግጭት — ሁልጊዜም — ከማዳን — መከላከል — ይበጃልና ! ! !
እጅግ የከበረ ምስጋናን እጅግ ለተከበሩት የጆን ሆፕኪንስ ፕሮፌሰር አይራ ዊልያም ዛርትማን እያቀረብን አበቃን፡፡ ከአውዳሚ ግጭት ነጻ የሆነች ዓለምን ለሰው ልጅ ማህበረሰቦች ሁሉ ተመኘን፡፡ መልካም ጊዜ ለሁላችን፡፡ ቻው፡፡
ለቀረበው ጽሑፍ በዋነኛነት የተጠቀምንበት የጥናት ጽሑፍ፡- Ira William Zartman፣ Mediating Conflicts of Need, Creed, and Greed, 2001 (2015).
Professor Ira William Zartman’s published works:]
• Rethinking the Economics of War: The Intersection of Need, Creed, and Greed (2005)
• Getting It Done: Post-Agreement Negotiation and International Regimes (2003)
• A Strategic Vision for Africa: The Kampala Movement (2002)
• Preventive Negotiation: Avoiding Conflict Escalation (2001)
• Power and Negotiation (2000)
• International Multilateral Negotiations; Approaches to the Management of Complexity (1999)
• International Negotiation: Actors, Structure/Process, Values (1999)
• Peacemaking in International Conflict (1997) Ed. United States Institute of Peace
• Collapsed States: The Disintegration and Restoration of Legitimate Authority (1995)
የመጽሐፍ ዝርዝር፡-