>

ቀድሞ የተሸነፈው የኢትጵያ ጦር ሰራዊት!!!  ክፍል ፪ (ሻለቃ ላቀው መንግስቴ)  ክፍል ፪

ቀድሞ የተሸነፈው የኢትጵያ ጦር ሰራዊት!!!
ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ
 ክፍል ፪
የደሤው ጠቅላይ ሠፈር★
 
ቆቦ ላይ የተከማቸው ሀይል እውነቱን ለመናገር የትግራይ ክልልን ውጊያ በሚገባ አጠናቆ ኤርትራ ቀን ከለሊት ለሚዋደቀው ሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት አለኝታ ሊሆን በበቃ ነበር፡፡ሥፓርታ ብርጌድ 2,81ኛ፡የ30ኛ ብርጌድና የ6ኛ ሜ/ብርጌድ፡የ1ኛ ክ/ጦር የተሠባሠበ ሀይል፡የአየር ወለድ ብርጌድ፡የ12ኛ ብርጌድ አባሎች፡የ1ኛ ክ/ጦር ቃኚ፡መሐንዲሥ፡የ17ኛ ክፍለጦር የተወሠኑ ብርጌዶች ፡እዚያው ጦር ግምባር ላይ ይለማመዱ ተብሎ ወደ ሁለት ብርጌድ የሚጠጋ ሀይል፡፡እጅግ የሚያሣዝን ለሌላ ውድቀት ያዘጋጀው ከፍተኛ ሐይል ዙሪያውን በተራራ በተከበበችው ወልድያ ይተራመሣል፡፡
ወያኔ እንኳን መሐላችን ገብቶ ተኩሥ ቢከፍት እርሥ በራሡ ከፊል ሀይሉ ሙትና ቁሥለኛ ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ ሠራዊቱ እንደሥጥ ተሠጥቶአል፡፡ያኔ ከመከላከያ ውጭ ሆኖ የራሥ እዝና ቁጥጥር አቋቁሞ እንደገና ወደ መቀሌ መገሥገሥ ቢቻል ዛሬ ቢያንሥ ወያኔን እጅ በመጠምዘዝ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም አሥገዳጅ ሁኔታ ውሥጥ ሊያሥገባ የሚችል ኢትዮጵያዊ ቁመና ላይ መሠንበት ይቻል ነበር፡፡ነባራዊዉ ሁኔታ መንግሥት ጦር መምራት ብቻ ሣይሆን ሐገር ለመምራት አቅም ማጣቱ ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነበር፡፡
መከላከያ ወታደራዊ ሥልቱን ጨርሦ አፈግፍጉ የሚለውን /ሽሹ/በግልፅ ቋንቋ የሚለውን ዜማ እየለቀቀ፡ወልድያ ላይ ከተምን፡፡እሥከ መሥከረም 5/1982ቆይቼ ወደ ጢጣ ጦር ሠፈር እንድመለሥ ተደርጌ  ወታደራዊ ሞራሌና ሠብእናየ ጎዶሎነት እየተሠማኝ በንዴትና በቁጭት የበገኑትን ጀነራል ጥላሁን አርጋውን ተሠናብቼ ለጉዞ ተዘጋጀሁ፡፡በእድሜ የሚገኝን ጀግንነት በራሣቸው ሀላፊነት ጦራቸውን መርተው በወታደራዊ እውቀታቸው ላይ የቀለደው የበላይ አመራር በትካዜ እየቆዘሙ በተሠበረ ልብ ወደ ጢጣ በመኪና በግል አፈገፈግሁ፡፡
★ደሤ ጥቅምት 1እና2/1982★
ከላይ ክንዱ የዛለው ሥርአትና ሀላፊነቱን ወሥዶ ውጊያ የሚመራ ቡድን ያጣው መከላከያ ወያኔን ቀልቡን ሥቶ የፈለገውን እንዲያደርግ  እድል ሠጠ፡፡የሠሜን ወሎ ቁልፍ ወታደራዊ መሬቶችና የትግራይ ክልል የውጊያ ቦታዎችን ሽሬ፡አክሡም ፡አዲግራትና፡መቀሌን በሐገር ፍቅር በነደዱ ጀግኖች መሥዋዕትነት የጦር ወንጀል እየተፈፀመባቸው ባለፉ እነጀነራል ለገሠ አበጀን የመሠለ ሐገር የሚያኮሩ ጀግኖችን መከላከያ አሥረክቦ ሥውር በሆነ ሤራ ጦርነቱ አሣዛኝ ሁኔታ ላይ ወድቋል፡፡
ያለምንም አጋዥ ሀይል ዙሪያቸውን ተከበው በጀግንነት ኪሣራ ሢያደርሡበት የቆዩት ጀነራል ለገሠ አበጀ፡ሀይል እንዲጨመርላቸው ሢጠይቁ ሂሊኮፕተር ይላክልሀል ውጣ ነው የተባሉት፡፡እኔ የምመራውን ጦር ጥዬ ከምወጣ አብሬው እሥከመጨረሻው የመጣውን ጠላት ጥዬ እወድቃለሁ፡፡የግል ችግር የለኝም፡፡
ቃል የገባሁት ለሐገሬ እሥከመጨረሻው የህይወት መሥዋእት ልከፍል እንጂ እኔ ለገሠ በሂሊኮፕተር ልሸሽ አልተፈጠርኩም ብለው ምንም አማራጭ በጠፋበት ጦራቸውም እሣቸውም የጀግንነት ታሪካቸው ማብቂያ ሆኖ የተቀደሠችው አክሡም ከተማ ላይ የታጠቋትን ሽጉጥ አውጥተው የመጨረሻ እርምጃ በራሣቸው ላይ ወሠዱ፡፡
ሩህ ሩህ ከጦር አዛዥነታቸውም በላይ በጦራቸው ዘንድ እንደ አባት የሚቆጠሩት ቁመተ ዘንካታው መልከመልካሙና የቀይ ዳማው ጀነራል ለገሠ አበጀ ለውሀ ጥሙም ለንዴታቸውም ማብረጃ በሽጉጣቸውየጀግንነታቸው ልክአሣዩ፡፡
ወያኔ በሠሜን ወሎም፡የአምባላጌን ፡የማይጨዉን፡የግራ ካሦን የዞብልንና የወልድያ መዳረሻ ከፍተኛ መሬቶችን ከተቆጣጠረ በሁዋላ ወደ ጎጃም ጎንደር እንደፈለገ ይፈነጭ ያዘ፡፡ደሤ ከመጣሁ በሁዋላ ጠቅላይ ሠፈሩ በአነሥተኛ ሀይል ከመጠበቁ ውጭ አሥተማማኝ ዙሪያ ጥበቃ አልነበረውም በኩታበር በሐይቅ በገራዶና በኮምቦልቻ መሥመር 17ኛ ክ/ጦር ኮምቦልቻ የሚገኘው 17ኛ መድፈኛ ሻለቃ የሦሠሥተኛው አብዮታዊው ሠራዊት የተለያዩ ክፍሎች ከኮምቦልቻ ጀምሮ በሣሣ መልኩ ተዘርግተዋል፡፡
በኮ /እንደግ የሚመራው 17ኛ ክፍለጦር ወለድያ ላይ ከአቅም በላይ የተከመረውን ሀይል ወደ ሁዋላ ለመበተን በሚመሥል መልኩ ወያኔ ጥቅምት 1/1982 ተኩሥ መክፈት ጀመረች እነደ ቀልድ የተጀመረው የሙከራ ውጊያ ሁኔታውን ሊከታተሉ ወደ ግምባሩ የወጡትን ጀነራል ጌታሁን ከክፍለ ሐገሩ አሊ ሙሣ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሢጨቃጨቁ በተነሣባቸው የሥኳር ሕመም ራሣቸውን ሊቆጣጠሩ ባልቻሉበት ሁኔታ ወያኔ የይምጡ ወደ እኔ አይነት አመራረክ ማርኳቸው ሁኔታው አሥገራሚ ሆነ ፡፡
ደሤን ለመያዝ  እርግጠኛ የነበረው ወያኔ በከፍተኛ ሀይል በተለያዩ አቅጣጫዎች ማጥቃቱን አሠፋ፡፡ጥቅምት አንድን ደሤ በገራዶ በኩታበርና በሐይቅ በተኩሥ ሥትናጥ ያደረችው ደሤ ጥቅምት 2/1982 ጠዋት ላይ ለኢትዮጵያ አብዮት ግንባራችን አይታጠፍም ብለው የገቡትን ቃል አጥፈው የቻሉትን ንብረት ቤተሠብና ሠራተኛ እየጫኑ ወደ መሐል አገር መሽሽ ያዙ፡፡አሥተዳደሩም በአሊ ሙሣ መሬነት የኮምቦልቻን መንገድ ተከትሎ ከእነ አጃቢዎቹ ነፍሥ ውላ የምታድርበትን መንገድ መርጦ ደሤን ለፍርደኛው ጦር ለቆ ሸመጠጠ፡፡
የደሤ ፖሊሥ መምሪያም በደሤ ወህኒ ቤት ያሉ እሥረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፈቶ ከለቀቀ  በሁዋላ ፍትህ ከጦርነቱ ውጤት በሁዋላ ብሎ እነ አሊ ሙሣን ተከተለ፡፡ሠራዊቱ ሢዋጋ ውሎ አድሮ ጥቅምት 2/1982እሥከ ረፋዱ ድረሥ የታሪክና የሐገር ሉአላዊነት እዳውን ለመክፈል ከአቅም በላይ ከገጠመው የወያኔ ሀይል ጋር መተጋተጉን፡ይዟል ሌላው ቀርቶ ውሀ እና ቀለብ እንኳን ለማሥጠጋት የተኩሡ ግለት አየጨመረ በመሄዱ ውሀ ጥሙና ርሐቡ የፈታቸው ጀግኖች ወደሁዋላ  ፊታቸውን ማዞር ጀምረዋል፡፡
★★ጥቅምት 2/1982 ወጊያው እንደቀጠለ ነው ከላይ በጠቀሥኩባቸው የደሤ ከተማ ዙሪያ ዐወታደራዊው ቀበቶ  የርሀቡን ግፊት አየታገለ፡የመጨረሻ ቃል ኪዳኑን በተግባር እየፈፀመ፡የጦርነቱም መርዘም በባሩድ ጭሥና ከባድ መሣሪያዎች የሚያሥነሡት በአውሎ ንፋሥ አይነት በሚያሥነሡት አዋራ ከማእድን ቁፋሮ የወጣ ሙያተኛ የመሠለው ጦር አረንጓዴ ፋቲክ ይልበሥ በማይለይበት ሁኔታ ራሡን ጥሎ ለወያኔ ተኩሥ እየመለሠ ይዋደቃል፡፡
ቀድመው በተፈናቃይ ሥም የገቡ የወያኔ ሢቪል ለባሽ ተፋላሚዎች የውጥር ተይዛ ደሤ የመከራ ቋት ሆናለች፡፡ሜጀር ጀነራል መርዳሣ ሌሊሣ አነሥተኛ ሥብሠባ አድርገው:-
1ኛ/የደሤ ሕዝብን አሥተዳዳሪዎቹና የፓርቲው ሠዎች በዚህ እውነትን በሚፈትን ወቅት ጥለውት ኮብልለዋል
2/ኛ ሠራዊታችንን የገጠመው የውሀና ችግር ሌላው የገጠመን ፈተና ነው ለዚህ አሥቸኳይ ሁኔታ ምን ይደረግ የሚል ጥያቄ አነሡ፡፡ሁላችንም ከደሤ ሕዝብ ጋር ችግሩን መፍታት እንዳለብን ተማምነን፡ሕዝቡንም በማረጋጋትና እየደከመው ወደ ሁዋላ የመጣውን ወታደር የሚችለውን ያህል የውሀና የምግብ ድጋፍ እየሠጠ ውጊያውን እንዲያግዝ ለማድረግ በግምባር ቀደምትነት የጀነራል መርዳሣን ትእዛዝ በሀላፊነት ተቀብዬ ሜጋፎንና ታጣፊ መሣሪያ ይዤ ወደ ደሤ ከተማ መሀል ፒያሣ ላይ ቆሜ ፡፡
የደሤ ሕዝብ ሆይ ሠራዊቱ በፅናት እየተዋጋ ወደ ድል እያመራ ነው፡፡ደክመው የመጡትን ተዋጊዎቻችሁን ውሀና ምግብ እየሠጣችሁ ወደ ዉጊያው መልሡ፡፡ወህኒ ቤቱም እሥረኞች ሥለቀቀ ራሣችሁን ጠብቁ እያልኩ በቀሠቀሥኩ በደቂቃዎች ውሥጥ የደሤ ሕዝብ በድጋፍ የመጀመሪያ የድጋፍ ጠርዝ ላይ ቆሞ የሠራዊቱን ሞራል ጫፍ አደረሠ፡፡
ሠራዊቱ ወደነበረት ተመመ፡፡እናቶች ማብላት ብቻ ሣይሆን ወደ ሚዋጋው ሀይል በቀረበ ሁኔታ ድጋፋቸው ዘለቀ፡፡በጥልቀት በገራዶ አቅጣጫ ሊገባ የነበረ ወያኔ በቀን ብርሀን በደሤ ሕዝብ እየታገዘ የሚዋጋውን ሀይል ሊቋቋም አልቻለም፡፡በኩታበር አቅጣጫም መሣሪያውን ቁሥለኛውን እየጣለ አፈገፈገ፡፡ሠራዊቱ ወደ ማሣደድና በእጁ በርካታ ምርኮኛ ሠብሠቦ ጀግንነቱን አረጋገጠ፡፡ ጥቅምት ሁለት ደሤን ወደ ነበረበት መልሠን ቀሪ ሥራዎቻችንን ማሥተካከል ጀመርን፡፡በሚቀጥለው ጋዜጠኞች ምርኮኞቻችንን የቲቪ ቀረፃ ተደርጎ ኢንተርቪዩም ሠጠሁ፡፡
በ3/2/82 ጠዋት ላይ ከወልድይ ጀነራል ጥላሁን ሬዲዮ ቤት ፈልገውኝ ተገናኘን ፡፡ላቀው ምንድን ያለው ሁኔታ ብለው ጠየቁኝ እኔም የወያኔ ማጥቃት ከሽፎ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ሁኔታ ተመልሠዋል፡፡የፓርቲውና የአሥተዳደሩ ሀላፊዎች በሄዱበት አኩሀን እየተመለሡ ነው፡፡ወያኔ ከደረሠበት ጉዳት አንፃር ደሤን መልሦ ለመያዝ ይሞክራል የሚል እምነት የለኝም አልኳቸው፡፡እሣቸውም ወልድያ ያለውን ሀይል ይዘህ ወደ ደሤ በአሥቸኳይ አፈግፍጋችሁ እንድትገቡ ተብለን ጉዞ እየጀመርን ሢሉኝ ሁሉም ነገር ማብቃቱ ተሠማኝ ፡፡
ሠራዊቱ በቂ ሀይል እያለው በአፈግፍግ ትእዛዝ ከላይ ሆኖ የሚፈታተነን የሐገርና የሕዝብ ጠላት ማን ይሆን ሊቀመንበሩሥ ምን እያደረጉ ነው ብዬ ራሤን መጠየቅ ያዝኩ፡፡የወልድያውም ጦር የወልድያን ሕዝብ ወየኔ እንዲያሥተዳድረው ገፀ በረከት ሠጥተው ወደ ደሤ በድል የተጠናቀቀውን የደሤን ጦር ሊያግዙ በሚገርም ፍጥነት አፈገፈጉ፡፡
★የደም ገበያ★
ሠኔ/15/1980
የወያኔ ሠራዊት ከምንጊዜውም በላይ በተዋጊ ሀይሉ ላይ ከፍተኛ መመናመን ደርሥበታል፡፡ተከታታይ የሆኑ ቀጣይ ውጊያዎች ታቅደው ቢሆን ሁኔታዎች መልካቸው ባለፉት ጊዜያቶች ሁኔታ እንደማይጠቃለል ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም ነበር፡፡ውጊያውን መቀጠል አለብን ወይሥ ማቆም አለብን በሚል ሁለት ፅንፍ ላይ ጊዜ አግኝቶ ውይይት የጀመረው የወያኔ ጦር ቀደምት የማጥቃት ውጊያ አቅዶ ለመነቃነቅ ተዋጊው የወያኔ ሀይል በተለያዩ የትግራይና የሠሜን ወሎ ውጊያዎች አቅሙ መቅኒው ከመፍሠሡም በላይ ትጥቅ ትግል ውሥጥ የገባንው የትግራይን ክልል ነፃ ልንወጣ እንጂ ከአሁን በሁዋላ አንታገልም ብለው አሻፈረን አሉ፡፡
ከትንሿ ተዋጊ ሀይል እሥከ ክፍለ ሠራዊት የተደረገው ሥብሠባ ሁሉ ውጤት አላመጣ አለ፡፡አሁን ባለው ሁኔታ ውጊያ ብናቆም ደርግ ውጊያውን አጠናክሮ ህልውናችን አደጋ ላይ ከመውደቁም  በላይ ለዲሞክራሢ ሥንታገል የቆየንበት አለማ ፍሬቢሥ ሊሆን ነው የሚለው የወያኔ መሪዎች ተማፅኖ ውጤት አጥቶአል፡፡ፍጥነት አይኑረው እንጂ ሐይል የማሠባሠቡ ሥራ በመከላከያ ሚኒሥቴር በኩል ጫና ከሌለበት ግንባር ወደ ትግራይ ግምባር የማዘጋጀቱ ሥራ በሦሥተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ግንባር ቀጥሏል፡፡
ጀነራል ረጋሣ ጂማ አንድም ቀን በሠላም ከቤተሠቦቻቸው ጋር ቀዝቃዛ ውሀ እንኳን ለመጠጣት ያልታደሉ፡ከኤርትራ የውጊያ በረሀ በነ ጓድ ለገሠ አሥፋው የሚመራውን ሠራዊት ከጀነራል መርዳሣ ሌሊሣ ጋር እንዲመሩ ቀጥታ ትግራይ ክልል የገቡ በውጊያ አመራር ባለ ከፍተኛው ልምድ ቁመተ ረጅሙ ሽበታሙና ፂማቸውን ከላይኛው ቀኝና ግራ በኩል ጎንና ጎን በረጅሙ አሣድገው ውሣኔ ከመሥጠታቸው በፊት ሁኔታዎችን ሢያጤኑ በገራ ጣቶቻቸውን የሚያፍተለትሉ ሢሆን ውሣኔ ላይ ሢደርሡ ደግሞ በቀኝ ጣቶቻቸው በቀኝ በኩል በረጅሙ ያሣደጉትን ፂም ካፍተለተሉ ጀነራሉ ወደ እርምጃ መግባታቸው አይቀሬ ነው፡፡
የኛ ሠራዊት ቀላል ተነቃናቂ ሆኖ እንደ ወያኔ አለመደራጀቱ ሁልጊዜ ተከታትሎ ወያኔን ፋታ ለመንሣት ችግሮች ነበሩብን፡፡ከቦታ ቦታ ሥንነቃነቅ የነፍሥ ወከፍ ጥይቶችና ለሀያ አራት ሠአት ማቆየት የሚችል ቀለብና ውሀ ብቻ ይዞ የመነቃነቅ ልምዳችን ችግር ያለው ሢሆን ውሀ በቦቴ ቀለብ በትላልቅ የጦር ተሽከርካሪዎች ሢቢል ሠራተኞችን ጭምር ሥለምናጓጉዝ ፍጥነታችን አዝጋሚ መሆኑ ብቻ ሣይሆን በየምንጓዝ መሥመር ሁሉ መረጃችን ቀድሞ ለወያኔ ይደርሥ ነበር፡፡
ሐይሉ የተመናመነው የወያኔ ክፍለ ሠራዊት በተለይም ካሁን በሁዋላ አልዋጋም ብሎ ፊቱን ያዞረው ሀይል የሚይዙት የሚጨብጡትን ያሣጣቸው እነመለሥ ከፍተኛ ሀይል ለገበያ የሚወጣበትን የሐውዜን ገበያ ባየር ለማሥደብደብና በዚያ ጥቃት ሐይል ለመመልመል ከፍተኛ ሤራ አሤሩ፡፡ረቡእ ግንቦት 15/1980 በሚውለው የሐውዜን ገበያ ላይ ያየር ድብደባ እንዲካሄድ ሚሥጥራዊ ፕሮጀክት ታቀደ፡፡ለነ ጓድ ለገሠ አሥፋው ሐውዜን ላይ ግንቦት 15/1980 ወየኔ ከፍተኛ ኮንፈረሥ የሚያደረግ መሆኑን በርካታ ገበያተኛም የሚሠባሠብበት ሠአት ሁሉ ተገልፆ መረጃው በትክክል ይደርሣል፡፡ በወያኔ በኩል ከአደጋ ሊሠውሩ የሚችሉ ቦታዎች ተመርጠው ፊልም መቅረጫው ተዘጋጅቶ የተወሠኑ ጋንታዎች ገበያተኛው አካባቢ መከታና ከለላ እንዲጠቀም ተደረገ፡፡
ለገሠ አሥፋው በደረሠው መረጃ እርግጠኛ ሆኖ ሐውዜን ላይ ሥብሠባ ላይ ነው ባለው ሀይል ላይ አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ከፍተኛ ፈንጂ የታጠቁትን የአየር ሐይል ሚጎችን በሐውዜን ገበያ ላይ በንፁሀን ህይወት ላይ ሞት አዘነበ፡፡እናቶች አባቶች ወጣቶች ህፃናት እንዳልነበሩ ሆኖ ደሣሣ ጎጆዎች ፈራረሡ የመሬት የላይ መልክ በሥረኛው ተተካ ፡፡ያ ዘግናኝ ድርጊት የትግራይን ሕዝብ አሥቆጥቶ አልዋጋም ያለውን ብቻ ሣይሆን በአዲሥ ሀይል ወያኔ ተጥለቀለቀ፡፡የተቀረፀዉ ፊልም የሠውን ልጅ ሁሉ በሐዘን አኮማተረ፡፡ድርጊቱ የቀድሞው ሠራዊትን አመራርና እነ ለገሠ አሥፋውን ጨፍጫፊ አሠኝቶ በእድሜ ልክ ፍርድ አሥፈርዶ ወያኔን ለድል አብቅቶ ሐውዜን ሥውር የሆነ ጭካኔ ተፈፅሞባት ሚሥጥርዋ ጊዜ ፈቶታል ፡፡፡፡፡፡፡፡ጠብቁኝ፡፡
፡፡፡እቀጥላለሁ
Filed in: Amharic