ማኅበር
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም (ቦስተን)
የፖሊቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ እኔን ክፉ ስጋት ውስጥ ጥሎኛል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊቲካ ፓርቲዎቹ ቁጥር ከሰማንያ አንድ ወደአራትና አምስት ቢወርድ እያለ መማጸኑ ይበልጥ አሰጋኝ! እኔ እንደሚመስለኝ የቋንቋም፣ የሀሳብም፣ አስተሳሰብም ነው፤ በምናውቀው ቋንቋ፣ በምናውቀው ባህል ውስጥ ሆነን ብንናገር ምናልባት ችግሩ የቀለለ ይሆን ነበር፤ ፓርቲ ምን ማለት ነው?
ማኅበር ማለት የጋራ ዓላማ ያላቸውን ሰዎች ተሰብስበው የሚፈጥሩት ድርጅት ነው፤ ማኅበር ዓላማ አለው፤ አለቃ አለው፤ ደንብና ሥርዓት አለው፤ አባሎቹ ለማኅበሩ ግልጽና የተወሰነ ግዴታ አለባቸው፤ ማኅበሩም ለአባሎቹ የተወሰኑ መብቶችን ያጎናጽፋል፤ በተጨማሪም አባሎቹ በማኅበሩ ዓላማ የተሳሰሩና የተዛመዱ ይሆናሉ፤ እኔ የማውቃቸውን መኅበሮች ምናልባት በሦስት መመደብ ይቻል ይሆናል፤ አንደኛ መንፈሳዊ ዓላማ ያላቸው፣ የገንዘብ ዓላማ ያላቸው፣ ማኅበረሰባዊ ዓላማ ያላቸው፤
መንፈሳዊ ዓላማ ያላቸው የምላቸው በአምላክ፣ ወይ በአንድ መልአክ፣ ወይ ሰማዕት፣ ወይም ጻድቅ ስም በየወሩ እየተሰበሰቡ ‹‹ጸበልና ጻድቅ‹‹ የሚካፈሉ ናቸው፤ የገንዘብ ዓላማ ያላቸው በተወሰነ ጊዜ እየተሰበሰቡ፣ የተወሰነ ገንዘብ እያዋጡ በእጣ ለእድለኛው የሚያስረክቡበት እቁብ የሚበል ማኅበር ነው፤ ሦስተኛው የማኅበር ዓይነት የማኅበረሰባዊ ዋስትና ልንለው የምንችል፤ ስለቀብርና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች መቋቋሚያና መረዳጃ ነው፤
በገጠር በተለይ ቋሚ ያልሆኑ የትብብር ሥራዎች አሉ፤ ለተለያዩ የግብርና ሥራዎች ገበሬዎች በኅብረት እየሠሩ ይረዳዳሉ፤ ከነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች የሚከተለውን እንገነዘባለን፡—
- ሰዎች ዓላማ ሲያገኙ ይሰባሰባሉ፤ ተመሳሳይ ዓላማ ያቀራርባል፤ መቀራረቡ ዓላማውን ለማራመድ ብልሃትን ይፈጥራል፤
- ዓላማውን ለማራመድ መደረጀት ግድ ነው፤ በዓላማው የሚያምኑ ሰዎች ይሰባሰባሉ፤ ግዴታቸውን ይመዘግባሉ፤ ጉልበታቸውን ያስተባብራሉ፤ ለተፈላጊው ነገር ሁሉ የማኅበሩ ኃይል የሚሆን መዋጮ ያዋጣሉ፤
- ለማኅበሩ ህልውና፣ መስፋፋትና ጥንካሬ፣ እድገትም ደንብና ሥርዓት ይበጃል፣ ሹማምንትም ይሰየማሉ፤
- የበለጠ እድገት የሚገኘው ማኅበሩ ባመጣው ውጤት መጠን ይሆናል፤
ዓላማን ተከትሎ የሚመጣው የአባሎች መሰባሰሰብና ድርጅት መመሥረት ውጤቱ በነጠላው ዓላማውን ማራመድ ብቻ አይደለም፤ አባሎቹን ያቀራርባል፤ ያዛምዳል፤ ዝምድና ከማኅበረተኛነት ይፈልቃል፤ ይህንን እንደተራ ነጥብ ልናየው አይገባንም፤ አሁን በኢትዮጵያ ፖሊቲካ የሚታየው በዘር ላይ የተመሠረተ ዝምድና ተፈልጎ ማኅበሩ በዚያ የዘር ሐረግ ላይ ይተከላል፤ በሌላ አነጋገር ማኅበር ከዘር ይፈልቃል!
ዘረኞቹና ጎሠኞቹ በየትኛው እንደሚመሩ እናውቃለን፤መንግሥት የሚባለው ድርጅት ግን በየትኛው እንደሚመራ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው፤ በብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው አዲሱ የምርጫ መሥሪያ ቤት ምን እንደሚያመጣ አናውቅም፡፡