>

ዓሊ ቢራ- የድሬ ዳዋ አውራ!!! (ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ)

ዓሊ ቢራ- የድሬ ዳዋ አውራ!!!
ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
አዎን! ከማንም በላይ በትዝታ ባህር ውስጥ የመወርወር ሀይል ያለው የድሬ ቡቃያ ክቡር ዶ/ር ዓሊ ቢራ ነው፡፡ በሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ተወደደ አምሳ ዓመታትን ያስቆጠረ የኪነ-ጥበብ ሊቅ! በጣፋጭ አንደበቱና በምትሀታዊ ድምጹ “ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ” የሚለውን ብሂል በተግባር ያስመሰከረ የዜማ ንጉሥ፡፡
ዓሊ ቢራን ከድሬ ነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ ድሬ ዳዋም ከዓሊ ቢራ ጋር ዘወትር ትነሳለች፡፡ እርሱም ይህችን ውብ ከተማ በጣም ይወዳታል፡፡ ያሞካሻታል፡፡ ይዘክራታል፡፡ ይህ አጃዒበኛ ሰው በቦክስ ጊታር ደህና አድርጎ መጫወት እንደለመደ ለድሬ ዳዋ እንዲህ ብሎላት ነበር፡፡
Alattiin Dirree Dhawaa foon malee lafee hinnyaatina jetti
Magaalleen Dirree Dhawa namalee hindubbisina jetti
በዚህ ግጥም ነው እንግዲህ ዓሊ ቢራ ድሬ ዳዋን በጥበብ ስራዎቹ መዘከር የጀመረው፡፡ ዓሊ በዚህ ባህላዊ ግጥም ሁለት ተቃራኒ ባህሪያትን ነው እንደ አንድ አምሳያ አድርጎ ለመግለጽ የፈለገው፡፡ የድሬ ዳዋ ጭልፊት እና የድሬ ዳዋ ጉብል፡፡ የያንዳንዳቸው ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማወቅ የግጥሙን መልዕክት ወደ አማርኛ መልሰን እንየው፡፡
የድሬ ዳዋ ጭልፊት “ስጋ እንጂ አጥንት አትብሉ” እንዳለች
የድሬዋ ጉብልም “ከኔ በቀር ሌላዋን አታናግሩ” ትላለች፡፡
ጭልፊቷ አጥንት አትብሉ ያለችው ለውንብድና ተግባሯ እንደሚያመቻት በማሰብ ነው፡፡ ሰዎች ስጋውን ትተው ወደ አጥንቱ ጎራ ካሉ እርሷ ጦሟን ማደሯ ነው፡፡ ከሰዎች እጅ እየሞጨለፈች ከርሷን የምትሞላበት ስጋ ብርቅ ሊሆንባት ነው፡፡ ስለዚህ ያ እንዳይሆን ለድሬ ነዋሪዎች “የምን አጥንት ማሳደድ ነው? ስጋውን ጠንከር አድርጋችሁ ያዙ እንጂ” እያለች “የብልጠት” ምክር ትሰጣለች፡፡
ታዲያ ዓሊ ቢራ “አጥንት አትብሉ ትላለች” ያለው ነገር ጨዋታ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ የድሬ ዳዋ ነዋሪዎች ልክ እንደ ሀረሪዎቹ አጥንትን በሁልበት መረኽ (የአብሽ ወጥ) ውስጥ መጨመርን እንደ ባህል ከያዙት በጣም ቆይቷል፡፡ እናቶች ወደ ሱጉያ ቤት (ልኳንዳ) ሄደው በስጋው ፈንታ አጥንት ሸምተው የሚመለሱበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ይህ ነገር ቀጣይ ሆኖ ከዘለቀ የጩልሌዋ ህልውና አደጋ ውስጥ መውደቁ ነው፡፡ ይህንን አደጋ ለመከላከል ነው አጅሪት “ምክር እንካችሁ” በሚል አኳኋን “ስጋውን ተመገቡ” እያለች የምትለፍፈው፡፡
የድሬ ቆንጆ “ከኔ በቀር አታናግሩ” የማለቷ ሚስጢር ግን ከጭልፊቷ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ብሂል ይለያል፡፡ በዓሊ አንደበት ሊነገረን የተፈለገው “የድሬ ዳዋ ጉብል ከሁሉም ትበልጣለች” የሚል መልዕክት ነው እንጂ “የድሬ ጉብል ራስ ወዳድ ናት” ለማለት አይደለም፡፡ የድሬ ልጅ በራስ ወዳድነት በጭራሽ አትታማም፡፡
ዓሊ ቢራ የተወለደባትንና አፈር ፈጭቶ ያደገባትን ድሬ ዳዋን በዘፈኖቹ ጣልቃ ማንሳቱነረ ይደጋግመዋል፡፡ ስለ “ለገሀሬ” ባወሳበት ዘፈን እንደገና ድሬን እንዲህ ብሎአት ነበር፡፡
Dirre Dhawaa jirraa Jabuutiin maal jenna.
Atuu nuuf ibsita tirikaan maal jenna.
ድሬ ዳዋን ከልቡ ለሚወዳት ሰው ድሬ ትበቃዋለች፡፡ ከድሬ ሁሉንም ያገኛል፡፡ ከድሬ ሁሉንም ማየት ይቻለዋል፡፡ የዚህ ግጥም መልዕክትም እንዲያ ነው፡፡ ወደ አማርኛ ስንመልሰው እንደዚህ ይሆናል፡፡
ድሬ ዳዋ ነው ያለነው ጅቡቲን ምን እንላታለን?
ያንቺ ፊት እያበራልን ኩሬንቲን ምን እንለዋለን?
ዓሊ ቢራ በመጀመሪያው መስመር “ድሬ ዳዋ ከጅቡቲ አታንስም” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው የፈለገው፡፡ በሁለተኛው መስመር ደግሞ የድሬ ዳዋ ጉብል አስተውሎ ለሚመለከታት ሰው ከኩሬንቲም በላጭ ሆና እንደምትገኝ ነው የገለጸልን፡፡ በርግጥም በላጭ ናት!
በነገራችን ላይ በሁለተኛው መስመር ያለውን “ኩሬንቲ” የሚል ቃል አስተዋላችሁልኝ አይደል? እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ የኤሌክትሪክ መብራት በአማርኛ በዚህ ስም ነበር የሚጠራው፡፡ ወደ ድሬ ዳዋ ወይንም ወደ ሌሎች የሀረርጌ ከተሞች ከወረዳችሁ ግን መብራቱ “ትሪክ” እየተባለ ሲጠራ ትሰማላችሁ፡፡
ዓሊ በዚህ ዘፈኑ ድሬ ዳዋ ያለፈችበትን ጥንታዊነትና ዘመናዊነት በአንድ ላይ አገናኝቶ ነው ያወሳው፡፡ ለምሳሌ የ“ለገሀሬ” ውሃ የሚጠጣው ጥንት እንጂ በዚህ ዘመን አይደለም፡፡ “ትሪክ” ደግሞ ዘመናዊነት ያስገኘው የስልጣኔ በረከት ነው፡፡ ታዲያ ዓሊ ቢራ በዚሁ ዘፈን ማብቂያ ላይ ወደ ኋላ ርቆ ይሄድና ድሬ ዳዋ ራሷን የቻለች ከተማ ሆና ከመጠንሰሷ በፊት አካባቢዋ የሚታወቅበትን የከብት እርባታ ባህል እንደ ዋዛ ይጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ እያለ!
Kheenya Dirree Dhawaa loontu loon hayyisaa
Wahin sitti dhaamaa waan qalbii fayyisaa
በነዚህ ስንኞች ለማለት የተፈለገው ወደ አማርኛ ቢመለስ እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡
በኛዋ ድሬ ዳዋ ከብት ነው ከብትን የሚያግድ
ቀልብን የሚፈውስ ነገር ወደ አንቺ ልስደድ፡፡
አንድ ከብት ሌላኛውን ከብት ያግዳል እንዴ?… እኛ በምንኖርበት ዓለም እንዲህ አይደረግም፡፡ ነገር ግን በኦሮሞ ባህል ውስጥ የአድማጩን ጆሮ ለመሳብ ሲባል ከእውነታው ወጣ እያሉ እንዲህ ዓይነት ግጥሞችንም መግጠም ይቻላል፡፡
*****
ይህ ነው እንግዲህ ዓሊ ቢራ- እውነተኛው የድሬ ዳዋ አውራ፡፡ ይህ ክቡር ሰው ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባው እንዴት ይመስላችኋል? ደስ የሚል ታሪክ አለው፡፡ ነገር ግን እርሱን እዚህ ከማወጋችሁ እናንተው ራሳችሁ ብትደርሱበት ይሻላል፡፡ ታሪኩን በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ስለምታገኙት ጠንቀቅ ብላችሁ ጠብቁ፡፡
ዓሊ ቢራ በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ “ገንደ ቆሬ” በተሰኘው የድሬ ዳዋ ሰፈር ነው የተወለደው፡፡ ሙዚቃን በዚያች የትውልድ መንደሩ ውስጥ ሲጫወት ከቆየ በኋላ ወደ አዲስ አበባው ማዕከላዊ እዝ ኦርኬስትራ (የድሮው “ክቡር ዘበኛ ኪነት”) ተሻገረ፡፡ በማዕከላዊ እዝ እያለም የመጀመሪያ አልበሙን በሸክላ አስቀረጸ፡፡ ከማዕከላዊ እዝ ከለቀቀ በኋላ በ1970ዎቹ ዝነኛ በነበሩት “አይቤክስ” እና “ኢትዮ-ስታር” ባንዶች ሲሰራ ሰነበተ፡፡ በ1977 ግን ስዊድናዊት ባለቤቱ ባደረገችው ጉትጎታ ሀገር ጥሎ ወጣ፡፡ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ አሜሪካ ተሻገረ፡፡ እንዲህ ከተዟዟረ በኋላ በሀገረ-ካናዳ ተደላድሎ ተቀመጠ። ከዚያም ወደ ትውልድ ሀገሩ ተመለሰ። እነሆ ዛሬም በቋሚነት የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡
ዓሊ በሄደበት ሁሉ ድሬ ዳዋን ረስቶአት አያውቅም፡፡ ከመድረክ ላይ በሚወጣባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የድሬ ትዝታዎቹን እያነሳ መጫወት የዘወትር ልማዱ ነው፡፡ ወደ ሀገር ቤት መመላለስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮም ድሬን ይጎበኛታል፡፡ ይጫወትባታል፡፡ ይደሰትባታል፡፡
ዓሊ ቢራ በሙዚቃው አንቱታን ለመጎናፀፍ የበቃው ገና በታዳጊነቱ ነው፡፡ የሰውን ፋይዳ እና ደረጃ መመዘን የሚችለው የድሬ ህዝብ ነው ክብርና አድናቆቱን የደራረበለት፡፡ ከየትኛውም ሽልማት የሚበልጠው ደግሞ የህዝብ ፍቅር ነው፡፡ በተለይ በሚያውቁትና በተወለዱበት ህዝብ መወደድን የመሰለ ክቡር ነገር የለም፡፡
ድሬ የሰጠችን ይህ ውድ ቅርሳችን ውሎ ይግባ እንላለን፡፡ እርሱን ያበቀለችው ውቢቷ ከተማም ለዘላለም ትለምልም!
(አፈንዲ ሙተቂ፡ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ዳዋ”፣ 2006፣ ገጽ 23-26)
Filed in: Amharic