>
2:12 am - Saturday December 10, 2022

የጎሳ ፖለቲካ ልሂቃን "እኔ አውቅልሃለሁ" ብለው ቢነሱም  መድረሻቸው ግን እኔእኔ... ብቻ ነው!!! (ታምሩ ሁሊሶ)

የጎሳ ፖለቲካ ልሂቃን “እኔ አውቅልሃለሁ” ብለው ቢነሱም  መድረሻቸው ግን እኔ-እኔ… ብቻ ነው!!!
ታምሩ ሁሊሶ
* ውይይት ከምክትል ከንቲባ ታከለ ጋር
ባለፈው ሳምንት መጨራሻ ላይ ከጥቂት ጓደኞቼ ጋር የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባን አቶ ታከ ኡማን አግኝተናቸው ነበር። ቀደም ብሎ የገመትነው ለከተማዋ በታሰበ ፕሮጀክት ላይ ያለንን አስተያየት ለመሰንዘር ቢሆንም ከ6 ሰዓታት በላይ ካደረግነው ውይይት ከ4 ሰዓታት በላይ የፈጀነው እንደከታማው ነዋሪዎች ያሉብንን ስጋቶች፤ በሙሉም ባይሆን በከፊል በማንሳት ነበር። በከተማው ላይ የምናያቸውንና የምንታዘባቸውን የስጋት ምንጮቻችንን የምናነሳ ሰዎች እንደነበርነው ሁሉ፤በሌላ ወገን የኛን ሃሳብና ስጋት የሚቃወም አካልም ነበር። የተሳታፊዎቹን ማንነት እዚህ ላይ መጥቀስ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም።
በኛ በኩል የነበርነው ሰዎች አንድ ነገር ላይ ተስማምተን ነበር። ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ውይይቶችና ክርክሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተካሂደዋል። እነዚህ ውይይቶች ለችግሮቻቸን ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ፤ ችግሮቹን የሚያባብሱ ሆነው የተገኙበት አንዱ ምክንያት ነው ብለን ያመንነው ፤ተከራካሪዎች ወይም ተወያዮቹ ለችግሮቻችን ዘላቂ (Strategic) የሆኑ መፍትሄዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ፤የዕለት ወይም የሰዓታት ነጥብ ማስቆጠሪያዎች(Tactical) ላይ በማተኮር ፤አተካራ መፍጠርና መሸናነፍን ወይም መበሻሸቅን ዋነኛ ጉዳይ በማድረጋቸው ነው። በዚህ አይነቱ ጊዜያዊ መሸናነፍና መበሻሸቅ ውስጥ መንግስት ካለበት ደግሞ ጥፋቱ የባሰ ሆኖ ይገኛል። አልፎ አልፎም ውይይቶችን ላልተፈለገ የሚዲያ (የህዝብ ግንኙነት) ፍጆታ በማዋል፤ሌላ የማይፈለግና የማይጠቅም ትርፍ (Tactical advantage) ለመውሰድ መንግስት ሲጥር እናየዋለን። በመሆኑም ውይይቱ መነሻ ላይ የከንቲባ ጽ/ቤቱ ሰዎች እኛን ተነቀሳቃሽ ስልኮቻችንን መጠቀም እንደማንችል ሲነግሩን፤ እኛም በነሱ ካሜራ ፎቶ መነሳት እንደማንፈልግ ገለጽንላቸው። ከኛ በኩል ይህ እንዲሆን ጠንክረው የተከራከሩትን ልጆች ማድነቅ አለብኝ። በመሆኑም በውይይቱ ወቅትም ይሁን በኋላ፤ ምንም አይነት ፎቶግራፍ አልነበረም።
አዲስ አበባ
በነገራችን ላይ አዲስ አበቤ ብዙ የማይዋጥለት  ህገ መንግስት እንኳን በአንቀጽ 49 ላይ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ነች አይልም። አንቀጽ 49 እንደሚገልጸው አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማ ነች። ከዚህ በተጨማሪ ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ራስዋን ታስተዳድራለች። ይህ ማለትም አዲስ አበባ ከተማን ከፌደራል መንግስት መቀመጫነቷ ይልቅ መሬት ወርዶ የሚገልጻት ራሷን በራሷ ማስተዳደሯ ነው። አዲስ አበባ ራሷን በራሷ እያስተዳደረች የፌደራል መንግስቱን ደግሞ ታስተናግደዋለች። ይህ ማለት የፌደራል መንግስቱን ተቋማት ትይዛለች፤የፌደራል መነግስቱን ግን አየር ላይ በተቋማቱ በኩል አንጠልጥላ ትይዘዋለች። በተመሳሳይ መልኩ የኦሮሚያ ክልልንም አዲስ አበባ በቸርተሯ ሁሉ ሳይቀር መስተንግዶ ትሰጠዋለች-ልክ እንደፈደራሉ ሁሉ። ወደ መሬት ሲመጣ ግን አዲስ አበባ ላይ ራሱን የሚያስተዳድር ህዝብ አለ። ስለዚህ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ላይ ያለው ፖለቲካዊ መናኅሪያነት ላሉት ተቋማት ብቻ ነው እንጂ አስተዳደራዊ አይደለም።
ወደ ውይይቱ ስንመጣ ከላይ እነዳነሳሁት ሁሉንም አይሁን እንጂ በርካታ ጉዳዮች አንስተናል። ከነዚህ መካከልም፦
• ከለውጡ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ክፉኛ የስጋት ጫና ውስጥ መግባቱ
• በተለምዶ በርካታ አክራሪዎች “ፊንፊኔ ኬኛ” በማለት ለኦሮሞ ውጣት ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ምን ማለት እንደሆን ሊገለጽ እንደሚገባው
• ከተማ የማንም ብሄር ሊሆን እንደማይችል፤ ከዚህ ይልቅ ከተማ የነዋሪዎቹ፣የፈጠራ ሰዎች፥የነገዴዎች እንዲሁም የተወዳዳሪዎች እንደሆነና፤ከተማ( በጎሳም ይሁን ሌሎች አጥሮች) ያልተዘጋ ክፍትና ማንም በነጻነት ሊወጣ ሊገባ የሚችልበት ቦታ መሆኑን
• አክራሪዎች ደጋግመው እንደሚያነሱት ሳይሆን፤አዲስ አበቤ ከኦሮሚያ በብላሽ የሚያገኘው ምንም ዓይነት አገልግሎትም ይሁን የተፈጥሮ ሃብት እንደሌለ
• ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና በፌደራል መንግስት ቢሮዎች እየታየ ያለው አንድ ብሄርን በሌላኛ የመተካት፤ላለፉት 27 ዓመታት ሁሉም ሲጠላው የነበረው ሁለተኛ ዙር የዘረኝነት መንገድ አግባብ እንዳልሆነ
• አዲስ አበቤ ከተማዋ እንደሌሎቹ ከተሞች የብሄር መልክ እንዲሰጣት (Ethicized) እንደማይፈልግና በሃይል የቋንቋ ጭነት መጫን ከተማዋን የአንድ ብሄር የማድረግ እድል ስላለው ተቀባይነት እንደሌለው
• የኦሮሞ ገበሬን ያፈናቀለው በአዲስ አበቤ ቅቡልነት የሌለውና ከዚያ ይልቅ አሁን ያለው አስተዳደር አብሮት ሲሰራ የነበረው መንግስት እንደሆነና ከዚህ ሁሉ በደል ጀርባ አዲስ አበቤ እጁ ንጹህ እንደሆነና፤አዲስ አበቤን ከተፈናቀለው ገበሬ ጋር የባላንጣ (Hostile) ስዕል መስጠት አግባብ እንዳልሆነ
• ለአዲስ አበቤ (በተለይ ለተወላጁ) አዲስ አበባ፤ ከተማ ብቻ ሳትሆን፤ ቤቱ እንደሆነች፤ በዚህ የከረረና ሀዝብን ከኖረበት በሚያፈናቅል የጎሳ ፌደራሊዝም ውስጥ ፤ ሌላ መድረሻ ወይም መጠባበቂያ አገርና ቀዬ እንደሌለው
• በርካታ የጎሳ ፖለቲከኞች እያንገራገሩም ቢሆን የሚቀበሉት የጎሳ ህገመንግስት፤ ዜጎቸን በተለይም አዲስ አበቤን ማግለሉን፤አዲስ አበቤም ህገመንግስቱን እስከ አሁን ድረስ አለመቀበሉን
• ወደኋላ እየተቆጠረ ታሪካዊ በደልን የምናነሳ ከሆነ መቶ ዓመት ብቻ (ምኒሊክ) ለምን እንደመነሻ (Cut-off) ተደርጎ እንደሚወሰድ ግልጽ እንዳልሆነ፤ከዚያ ይልቅ ኦሮሞዎችም ጦረኞች ሆነው ያፈናቀሉት፤ባላባቶች ሆነው ያሰቃዩት ህብረተሰብ እንደነበረ መረሳት እንደሌለበት
• አዲስ አበቤ ወይም በብሄር መጠራት የማይፈልጉ ዜጎች እስካሁን ምንም አይነት ውክልና ያልተሰጣቸውና ህገመንግስቱ እውቅና እንዳልሰጣቸው
• አዲስ አበባ 27 ዓመታትን እየተንፏቀቀ የመጣው የጎሳ ፖለቲካ የመጨረሻ ምሽግ (The last frontier) እየሆነች መምጣቷን
• ሌሎችም ጉዳዮችን
አነሳንባቸው።
በተቃራኒው አቅጣጫ ያሉት ግለሰቦችም በተለመደው መልኩ አዲስ አበባም ሆነች አገሪቱ የውልደት ችግር እንዳለባት፤አዲስ አበባም በኦሮሞ ገበሬ ተከባ ስታበቃ፤ በከተማዋ ውስጥ ግን የኦሮሞው ቁጥር አነስተኛ የሆነው ሆን ተብሎ በተደረገ ጫና መሆኑን ገለጹ። በእኛ በኩል አግባብ ሆነው ያላገኘናቸው ሌሎች በርካታ ጉዳዮችንም አነሱ።
የተደረገው ውይይት ላይ ማንም በሚያነሳው ጉዳይም ይሁን ሃሳቡን ለመግለጽ በሚውስደው ጊዜ ምንም ዓይነት ጫና ያልተደረገበትና ምክትል ከንቲባውም ረዘም ያለውን ሰዓት በማዳመጥ ያሳለፉበት ነበር።
ውይይቱ ምን እንደሆነ አስቀድሞ ስላልታወቀና ይህ ዓይነቱ ውይይትም አዲስ እንደመሆኑ ፤ በኛ በኩል ጠንከር ያለ ዝግጅት አልተደረገበትም ነበር። ዝግጅት ቢኖር ኖሮ በአዲስ አበባ ላይ አሉን የሚባሉትን ጉዳዮች ከህግ፤ከምጣኔ ሃብት፤ከማህበራዊ፤ከስነልቡና፤ከአካባቢ እንዲሁም ከታሪክ አንጻር በመደልደል፤ በዚያኛው በኩል አውቀው የተኙትን ሰዎች ባይነቁም ለመቀስቀስ የበለጠ እንሞክር ነበር።  ይሁንና ም/ከንቲባው ይህ ዓይነቱ ውይይት ሰፋ ያለ ተሳታፊ ባለበት መቀጠል እንዳለበት፤ይህ እሳቸው የሚገኙበት ትውልድ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ካልቻለ፤ሌላውም ይሁን መጪው ትውልድ ፈጽሞ ሊግባባ እንደማይችል ሊገልጹ ሞክረዋል።
በግሌ የማምነው ነገር ቢኖር እንደኛ ዓይነቱ የእኔ አውቅልሃለሁ (Elitism) ፖለቲካ ውስጥ ያለ አገር በስፋት ውይይት ይገባዋል። የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ልሂቅ እኔ አውቅልሃለሁ ብሎ ሲነሳ ደግሞ፤ የውይይቱ መድረሻ ሁሉ እኔነት(Self-concern) እንጂ ሌሎች (Other-concern)-እወክለዋለሁ የሚለውን ብሄር አባላት ጨምሮ-ሊሆን አይችልም ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ፖለቲካ ነክ ጉዳይ ስጽፍ የብሄር ፖለቲከኞች ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ሰዎቸን ‘የጎሳ ፖለቲከኞች’ በማለት ሆን ብዬ የምጠራቸው። ለኔ እኒህ ሰዎች የግል፤ቢበዛ ደግሞ፤ የጎሳቸው ጥቅም ላይ የሚሽከረከሩ ናቸው እንጂ ብሄር የሆነውን ገበሬና ድሃ አያውቁትም። ቢያውቁትማ አንድ የኦሮሞ ገበሬ ወይም ድሃ ከአማራው፣ከትግራዩ፣ከወላይታው ገበሬና ድሃ እንዴት ሆኖ ተለይቶ ለአንድ ልሂቅ ሊታየው ይችላል? በበኩሌ ለሁሉም ገበሬና ድሃ ያለኝ ሃዘኔታም ይሁን ስሜት አንድ አይነት ነው። ያም መሰለኝ አዲስ አበቤ የሚያስብለኝ።
ለከንቲባውና ውይይቱን ላስተባበሩ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳቸው። ይህ ውይይት በስፋትና በጥልቀት ቀጥሎ ፍሬ ማፍራት እንዳለበትም አምናለሁ።
Filed in: Amharic