>
7:04 am - Wednesday December 7, 2022

በትግራይ እና አማራ መሀከል ተዳፍኖ የተቀበረውን እሳት  አራጋቢው አቢቹ!!!   (ዘመድኩን በቀለ)

በትግራይ እና አማራ መሀከል ተዳፍኖ የተቀበረውን እሳት  አራጋቢው አቢቹ!!!
  ዘመድኩን በቀለ
 ህወሓት ኦሮሞና ዐማራን እሳትና ጭድ አድርጌ 100 ዓመት እገዛለሁ ስትል በቀመረችው የከፋፍለህ ግዛው ቀመር የተጠቀሙት አዲሶቹ የኦሮሞዎቹ ነገሥታት በዐማራው ትከሻ ላይ ተንጠልጥለው ዙፋኑ ላይ ጉብ ብለው ከወጡ በኋላ ያንኑ ከህወሓት የቀሰሙትን የህወሓትን ከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ በረቀቀ መንገድ ፈገግ እያሉና እያሳሳቁ እያስቀጠሉት ይገኛሉ!!!
**”
• ለትግሬውና ለዐማራው ነገድ አባላት።
• ለኦሮሞው ገዢ ቡድን።
• ለአቢቹና ለኦቦ ለማ
• ለኦርቶዶክሱ
• ለሙስሊሙና
• ለፕሮቴስታንቱ
• ለአንድነት ኃይሉ ጭምር የተሰጠ ምክር ቀመስ አስተያየት ነው።
***
ማስታወሻ |~ ለአንዳንድ እኛን ካልመሰልክ ባዮችም መልእክት አለኝ። 
ልዩነት ውበት ነው። ሁላችሁም አንድ ዓይነት ከላይ ያለው ጃንጥላ መያዝ መብታችሁ ነው። እኔ ግን የግድ የእናንተን ዓይነት ከለር ያለው ዣንጥላ መያዝ አይጠበቅብኝም። ብቻዬንም ቢሆን በያዝኩት ጃንጥላ የመኩራት፣ የመጠቀም መብቱ አለኝ። መብቱ የእኔው የራሴ የዘመዴ ነው ማለት ነው።  
•••
ህወሓት ዐማራና ኦሮሞን በማፋጀትና ዕድሜዋን ለማራዘም ስትል በኤርትራዊው ተስፋዬ ገብረአብ ልብ ወለድ ላይ የተጻፈውን “የአኖሌን ሃውልት” በመሃል አሩሲ አቁማ ስታበቃ  ዐማራና ኦሮሞን በማፋጀት ወደ ሥልጣን አካባቢ ዝር እንዲሉ እንዳደረገች ሁሉ ኦህዴድም በዘመነ መንግሥቱ ሁለቱ ነገዶች ዐማራና ትግሬ በያሉበት እየተቆራቆሱ እየተቀጣቀጡ እዚያው አርፈው ይቀመጡ ዘንድ የቀደመውን የህወሓትን የሴራ ፖለቲካ በሚገባ ቀምሮ በመተግበር በፈገግታ ጀምሮ በእልልታ እያሰቀጠለው ነው። ትግሬና ዐማራ እንዳይስማሙ ለማድረግ ኦሮሞዎቹ ህወሓት ቀድማ የገነባችውን ወልቃይት ጠገዴና ራያን የተባለውን የጠብ ምክንያት የሆነ ሃውልት ልክ እንደ አኖሌ ሃውልት አድሰው ጥቅም ላይ ሊያውሉት ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውን እያየን ነው። [ የድንበርና የእርቅ ኮሚሽኑ የሃውልቱ አዳሽ ነው። ያውም ቤንዚን አርከፍክፎ የሚያድስ አዳሽ ነው የሚሉ አሉ። የአኖሌ ሃውልት ግንባታ ላይ ከፕሮጀክቱ ጥንስስ አንስቶ እስከ ሃውልቱ ግንባታ ድረስ እነ አቢቹ አሉበት የሚሉም አሉ። ]
•••
ለዐማራና ለትግሬ ወልቃይት፣ ጠገዴና ራያ ራሱን የቻለ አንድ የተዳፈነ እሳት ነው። ያውም አንድ ጊዜ መንደድ ከጀመረ እንዳይበርድና እንዳይጠፋ ተደርጎ በትግሬና በዐማራ መካከል ተዳፍኖ የተቀበረ እሳት። መንደድ ከጀመረ የማይጠፋ እቶን እሳት። የሚንቀለቀል፣ የሚንቦገቦግና የሚነድ እሳት። የአንድ ባህል፣ ሃይማኖት፣ አባላት የሆኑ የዐማራና የትግሬን ነገድ የሚያፋጅ የሚፈጅም እሳት ነው። እሳቱን ጭራ በዐመድ አዳፍና  እንዲቀመጥ ያደረገችው ደግሞ ትግሬዋ እሜቴ ህወሓት ናት። ይህቺን በደንብበ ያዙልኝማ። በወፍራሙ አስምራችሁ ያዙልኝማ።
•••
ከዚያ ደግሞ “ ጅብ በቀደደው ” ትገባና የድንበር ኮሚሽን፣ የእርቅ ኮሚሽን የሚባል ሌላ እሳት የሚያቀጣጥል ሌንጮ ባቲ፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ አረጋዊ በርሄ የተባሉ ክብሪቶች ቤንዚን አድርገህ ትሾምና ያ የተዳፈነውንና ለመንደድ በቋፍ ላይ ያለውን እሳት የበለጠ እንዲቀጣጠልና እንዲንቦገቦግ ሁለቱ አንድ የሆኑ ህዝቦች በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ የሚያደርግ ሴራ ለማሴር እየተጋህ መሆንህን በቀላል አማርኛ ታውጃለህ። ዐማራና ትግሬ በመሬቴን ስጠኝ አልሰጥም ሲጠዛጠዙና ሲነታረኩ አንተ ምድሪቱን ኢትዮጵያን ያለተቀናቃኝ ወርሰህ ቁጭ ትላለህ። ይኸው ነው።
•••
እኔ በበኩሌ የጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ አድናቂው ነኝ። አቢቹ ስማርት የሆነ ቀሽት ልጅ ነው። ባዶ ሆዱን የሚያፋሽክ ህዝብ እንዴት በሰበካ እንደሚያስገሳው የተካነ እኔነኝ ያለም ምርጥ ተናጋሪና አደንዛዥ ዕፅ የሆነም ሰው ነው። አዳሜ በባዶ ሆዱ ምን ሲነገረው ሳይንበጫበጭ እያጨበጨበ እንደሚኖር፣ ሰጥ ለጥ ብሎ እንደሚገዛም ወደ ሥልጣን ላይ ከመምጣቱ በፊት በደንብ የሰለጠነና ጠንቅቆም የሚያውቅ፣ ሆን ብሎም የተዛገጀበት ምርጥ አደንዛዥ የሰመመን መርፌም ነው። ወደዳችሁም ጠላችሁም እኔ የአቢቹ አድናቂው ነኝ። አቢቹ ሆይ አዳሜ እስኪባንን ድረስ እያስጨበጨብክ፣ ታከለ ኡማ በተባለችዋ ብልጭልጭ የጉማሬ አለንጋህና ጅራፍህ እዠለጥከው አሳሩን አብላልኝማ።
•••
አቢቹ ማለት እኮ ሁለት ሰው ተጠቅቶ ሲያይ ዲያስፖራ አሰባስቦ ኋይትሃውስ በራፍ ላይ እሪሪሪሪ ያዙኝ ልቀቁኝ ይል የነበረውን አርቲስት ታማኝ በየነን ሰብኮ የቀየረ እኔነኝ ያለ ጀግናና እናቱ የወለደችው ወንድ ምርጥ የአጋሮ በሸሻ አራዳ ነው። የዋሽንግተን ሜዳን ሰልፍ በጥበብ ያስቀረ ወንድ ነው። ሁሉንም እስረኞች ፈትቶ ዐማሮችን እስከአሁን በቂሊንጦ የከረቸመም ወንድ ነው። የህዝቡን ጆሮ በተስፋ ያደለበ፣ ያወረ ወንድ ነው። ወንድ ነው አቢቹ ከምር እኔ ቆሜ ነው የማጨበጭብለት።
•••
አቢቹ ስማርት ነው። በዲያቆን ዳንኤል ክብረት በኩል ኦርቶዶክሳዊውን የማኅበረ ቅዱሳን ሠራዊት ጠርንፎ ይዟል። አባ መርቆሬዎስንና አባ ማትያስን አስታርቆ ሁለቱን ሲኖዶስ አንድ በማድረግ በውጭ ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ በአቶሚክ ቦንብ ድራሽ አባቱን አጥፍቶታል። አቢቹ ከኡስታዝ አቡበከር ጋር ፎቶ ተነስቶ እየለቀቀ “ ድምጻችን ይሰማ” ባዮችን ልሳናቸውን ዘግቶት አርፎታል። እሱ ጴንጤ ያውም ፓስተር ሲሆን ከአባ ማትያስና ከአባ መርቆሬዎስ እጅ መስቀል ይሳለማል። ቅሽሽም አይለው።
•••
አቢቹ በአባቱ ወገን እስላም ነውና ይወደዳል። በእናቱ ወገን ክርስቲያን ነውና በኦርቶዶክሱ ይወደዳል። እሱ ለፕሮቴስታንቶች የመጣል የተባለው መሲህ ነውና በፕሮቴስታንቶቹም ዘንድ እጅጉን ይወደዳል። በሚስቱ በኩል ጎንደሬ ነውና በዐማራው ዘንድ ቦታ አለው። ኦሮሞም ነውና በኦሮሞው ዘንድ ተወዳጅ ነው። ትግሪኛ ተናግሮ ትግሬውን አቅሉን አስቶ ጮቤ ያስረግጠዋል። ወርቅ ህዝብ አለን ብለው ምግብ መብላት እስኪያቅታቸው በደስታ ያሰክራቸዋል። ልጁ መልቲ ሲስተም ነው። ሁሉን በእጁ፣ ሁሉን በደጁ አድርጎ ረግጦ ይዟል።
•••
አቢቹ ማለት እኮ ኢሳትን ኢቲቪ ያደረገ፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን የመሰለ ነፃ ጋዜጠኛ፣ ሚዛናዊ ጋዜጠኛ በአደባባይ እያሞካሸ በይሉኝታ የግሉ ካድሬ ያደረገ ጀግና ነው። አቢቹ ማለት እኮ እንደ ህወሓት ለጃሚንግ ሚልዮን ዶላሮችን ሳያፈስ የህዝብ ዓይንና ጆሮ የሆነውን ኢሳትን ዱዳና ደንቆሮ አድርጎ ለጉሞ ያሰቀመጠ ጥበበኛ ነው። አቢቹ ማለት እነ ግንቦት ሰባትን ከአስመራ በረሃ አምጥቶ አዲስ አበባ በቁማቸው ያሰረ ጀግና ነው። ሆቴል አስቀምጦ እየቀለበ ደጋፊው ያደረጋቸው ጥበበኛ። ከምር አቢቹን አለማድነቅ አይቻልም። ህወሓት ጥጋብ ነፍቷት ኦሮሞን አስተነፍስሃለሁ ብላ በአባይ ፀሐዬ በኩል፣ በጌታቸው ረዳና በአቦይ ስብሃት በኩል በትንቦጣረርና የአዲስአበባና የኦሮሚያ ዙሪያ ማስተር ፕላኑን ባታጦዘው ኖሮ የተጣራ 100 ዓመት መግዛት የእጇ ነበር። ጥጋብ ግን ቁንጣን ፈጠረባትና ልክ ገብታ መቐለ አክሱም ሆቴል እንድትቀመጥ ሆነ።
•••
ጅቧ ህወሓት በቀደደችው ቀዳዳ የገባው ኦህዴድ ታዲያ ባላንጣዎቹ ወደ ሥልጣን እንዳይመለሱ ትግሬንና ዐማራን ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ የተባሉ ጊዜ ጠብቀው የሚፈነዱ ፈንጂዎችን እየነካካ ሁለቱ ነገዶች ተፋጠው እንዲኖሩ እያደረገ ዕድሜው የሚያራዝም ጥበበኛ ነውየኦህዴድ ኦነጉ አቢቹ። ህወሓት ዐማራና ኦሮሞን በፈጠራ ታሪክ የተቆረጠ ጡት ሃውልት አኖሌ ላይ አቁማ ዐማራና ኦሮሞን እሳትና ጭድ አድርጋው እንደከረመችው ሁሉ አቢቹም እነ ወልቃይትንና ራያን ለዐማራና ትግሬ እሳትና ጭድ አድርጎ እዚያው እየተጠዛጠዙ ወደ አራት ኪሎ እንዳይመለከቱ አድርጎ ለጉሞ የያዘ የገተረ ጀግና ነው። አሁን ዐማራና ትግሬ አይደለም ወደ 4 ኪሎ ሊመለከቱ ዞሮ መሽኚያ ጊዜም የላቸው።
•••
አቢቹ ትግሬና ዐማራ ከተስማሙ እንደሚያከትምለት ያውቃል። ይህን በደንብ አሳምሮ ያውቃል። ሁለቱ ነገዶች እንዳይስማሙ ደግሞ ህወሓት የሚሏት የዲያብሎስ ታናሽ ወንድም በመቐለ ተዘርፍጣ የጡረታ ዕድሜዋን እየገፋች መቀመጧን ያውቃል። ህወሓት አስቀድማ  ወልቃይትና ራያ የትግሬ ነው ብላ ለትግሬው ሁሉ ሰብካ ትግሬም ይሄን ሰበካ አምኖ ተቀብሎ ከወንድሙ የዐማራ ህዝብ ጋር በዐይነ ቁራኛ እየተጠባበቀ እንዲኖር በመደረጉ በየት በኩል ሁለቱ ህዝቦች ይስማሙ። ለህወሓት የወልቃይትና የራያ ጉዳይ የህልውናዋ ጉዳይ ነው። ይሄ አጀንዳ እስካለ ደረስ ደግሞ ሁለቱ ነገዶች በጭራሽ እንደማይስማሙ ደግሞ ሰይጣንም፣ እነ አቢቹም ያውቃሉ። እናም አቢቹ ይቺን ነገር ነው በደንብ እየተጠቀመበት ያለው።
•••
አሁን የሰሜኑ የኦርቶዶክስ ክርስትናና ጥንታዊው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት የዐማራና የትግሬ ነገድ አባላት በደቡቡ የፕሮቴስታንትና የአክራሪ እስልምና እምነት ተከታዮች ሥልጣናቸውን ተነጥቀው የበዪ ተመልካች ከሆኑ ሰነባብተዋል። ትግሬው በኦሮሞው ተገፍቶ ከኦሮሞው ጋር በእልህ፣ ከዐማራው ጋር በቁርሾ ተፋጧል። ሁለቱ ነገድ ከማዕከላዊው መንግሥት ለሁለት ተጎምደው ከአባይ ማዶና ከራያ ምላሽ ውልፍት እንዳይሉ ተደርገው ተጥለዋል።
•••
በዐማራ በኩል ወደ ትግራይ እህል እንዳይገባ ሲደረግ የአቢቹ መንግሥት መንገዱን ማስከፈት አቅቶት የሚመስለው ካለ ተሸውዷል። ለትግሬዎቹ መልእክት ናት። ወደ አራት ኪሎ አስባለሁ ብትሉ ተጠንቀቁ የምትል መልእክት ናት። በቅማንት ስም ህወሓት ዐማራውን ስታፈናቅለው የአቢቹ መንግሥት አሳምሮ ያውቃል። ማስቆምም ይችላል። ነገር ግን ለዐማራዎቹ መልእክት ሲያስተላልፍ ነው። አርፈህ ካልተቀመጥ ዐማራው ለኦሮሞውም ሆነ ለትግሬው የጋራ ጠላት ስለሆንክ ድራሽህን ነው የምናጠፋው የሚል መልእክት ነው የሚያስተላልፈው።
•••
አሁን ትግሬ ዐማራ ሲጠቃ ጮቤ ከመርገጥ ውጪ ለምን ብሎ አይጠይቅም። ዐማራም ትግሬ ሲጠቃ ኤትአባቱ ከማለት ውጪ ለምን ብሎ አይጠይቅም። ይሄ ደግሞ ለኦህዴድ ሰርግና ምላሽ ሆኖለታል። እያፋጃቸው በያሉበት አድቅቆ እየገዛቸው ነው። ህወሓት አቢቹ ዐማራውን የሚያጠፋላት ከሆነ አቢቹን ለማገልገል ፈቃደኛም ዝግጁም ናት። ይሄንን ዐማሮቹ ስለሚያውቁ በሁለት ጠላት እንዳይቀጠቀጡ ይፈራሉ። ዐማሮቹም አቢቹ ትግሬን ለመዋጋት ቢነሳ ፈቃዳቸው ነው። አብረውት ከአቢቹ ጋር ወደ መቐለ ለመዝመት ዝግጁም ናቸው። አሁን የኃይል ሚዛኑ ያለው አቢቹ ጋር ስለሆነ በሁለቱም ነፍስና ሥጋ ይጫወትባቸዋል። ጢባጢቤ ነው እየተጫወተባቸው ያለው። ጉድ የሚፈላውና ጨዋታው የሚያበቃው ግን ሁለቱ የሰሜን ኃያላን ሰላም ፈጥረው አንድ ላይ የቆሙ ጊዜ ብቻ ነው።
•••
ምኞት እውን አይሆንም እንጂ ምኞት እውን ሆኖ ደንቃራዋ ህወሓት ዕድሜዋን ለማራዘም ከተጎለተችበት ከሁለቱ ነገዶች መካከል ወጥታ ትግሬና ዐማራ ቢስማሙ እመነኝ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት በአንድ ጀንበር ልክ ይገባ ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል ኦርቶዶክስና ዐማራን አከርካሪውን ሰብረነዋል የሚሉ የህወሓት መሪዎች እያሉ በየት በኩል ሁለቱ ነገዶች ይስማማሉ? በፍጹም በአጭር ጊዜ የሚሆን አይደለም። ህወሓት ማለት ለሴራ ፖለቲካ የሚመች ለም መሬት ማለት ናት። እናም በቅርቡ የሚሆን አይመስለኝም። ሆኖም ግን ችግር ሲበዛ፣ መከራ ሲበዛ የማይሆን ነገር የለም። አባይ ፀሐዬና ስዬ አብርሃን፣ ስብሐት ነጋንና ገብሩ፣ አስራት፣ አረጋሽንና ሞንጆሪኖን ለካቲት 11 ያስተቃቀፋቸው የመከራው ደወል መሆኑን ሳይ ማን ያውቃል ነገ ትግሬና ዐማራም ለህልውናቸው ሲሉ አንድ ይሆኑ ይሆናል።
•••
አሁን ኤርትራ እንኳ በተገኘው ክፍተት ተጠቅማ ዐማራና ትግሬን እያጦዘች ነው። አቢቹ ኢሳይያስን ያመጣው ካላረፋችሁ ያው ጃስ እልባችኋለሁ ለማለት ነው። ከታች ዐማራ፣ ከላይ ኤርትራ የገና ዳቦ ያደርጉሻል፣ አርፈሽ ተቀመጪ ዓይነት መልእክት ነው የአቢቹና የኢሳያስ ዕርቅ። ለዚህ ነው የኤርትራ ልዑካን ትግርኛ ተናጋሪውን ትግሬ ዘልለው አስሬ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ አዋሳ በባዶ አዳራሽ ፎክረው የሚመለሱት። ለህዝብ ለህዝብ ግኑኝነቱ መቀሌና አዲግራት ቢሄዱ እኮ ነው አድማጭም የሚያገኙት። ነገር ግን የብሽሽቅና የሴራ ፖለቲካ ስለሆነ አቢቹና ኢሳያስ ህወሓትን ለማስፈራራት ይጠቀሙበታል።
•••
ለጊዜው ኤርትራና ኢትዮጵያ በሕጋዊ አግባብ የተሰመረ ድንበር እንደሌላቸው እየታወቀ ኤርትራውያኑ በየመግለጫቸው ኤርትራና የዐማራ ህዝብ በድንበር፣ በባህል፣ በሃይማኖት አንድ የሆነ ህዝብ ነው የሚሉት አሁን ወልቃይት በትግሬ ሥር መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። ዐማራን ሞቅ፣ ትግሬን ሸምቀቅ በማድረግ ለማጧጧዝ በአቢቹና በኢሱ የተቀመረ የሴራ ፖለቲካ መሆኗ ነው እንጂ።
•••
የወልቃይትን ጉዳይ የሚያጦዙት እኮ የጀዋሩ OMN, ጣቢያ እኮ ነው። በተከፋፈለ ዐማራ፣ በተዳከመ ዐማራ፣ በደቀቀ ዐማራ መኖር ሻአቢያም፣ ህወሓትም፣ ኦህዴድና ኦነግም፣ የአንድነት ኃይሉና ግንቦት ሰባትም ልዩነት የላቸውም። ለዚህ ነው ዐማራን አንዴ በወልቃይት፣ አንዴ በራያ፣ አንዴ በአገው፣ አንዴ በከሚሴ የሚጠበጥቡት። በጀት በጅተው የሚደክሙት። ትግሬ ያልገባው ነገር ግን ዐማራ አይጠፋም እንጂ የሚጠፋ ቢሆን እንኳ በማግስቱ የሚጠፋው ራሱ ትግሬው መሆኑ ነው ያልገባው። ዐማራና ትግሬ ሲጠፉ ኦርቶዶክስ ትጠፋለች ነው የአውሬው ቀመር።
•••
በዐማራው በኩል የመጠቃት ስሜት፣ የመበደል ስሜት ያነገቡ አክቲቪስቶች ናቸው አየሩን የተቆጣጠሩት። እውነት አላቸው። የተበሳጨ ሰው ደግሞ ተረጋግቶ ለማሰብ ጊዜ አይኖረውም። በትግሬው በኩል ደግሞ ቁሳዊ ነገር ልባቸውን የደፈነ፣ የሚያዩት ህንፃና ፎቅ፣ ቪላና ፋብሪካ ዳቦ መስሎት የሚጎርር፣ ያለ ሰቀቀን፣ ያለ ከለካይ፣ ያለ ተቆጪ እግሩን ዘርግቶ ተዘርፍጦ ብቻውን ይመገብበት ከነበረው ማዕድ ላይ ተገፍቶ መቐለ መወሸቁ የበሰጨው፣ በዚያም የከተመና 27 ዓመት ሙሉ የቋጠራት ጥሪት የማታልቅ የመሰለው፣ ልቡ በእብሪት የተወጠረ አክቲቪስት ነው አየሩን የተቆጣጠረው። እናም አልተገናኝቶም።
•••
የትግራይ ልጆች ይሄ ሁሉ የሚታየው ዝግጅት ዐማራውን ብቻ ለማጥፋት መስሏችሁ ከሆነ በጣም ተሳስታችኋል። ለጊዜው በመታወቂያችሁ ላይ ባለው ምልክት ከሚመጣው ጥፋት ልትድኑ ትችላላችሁ። ለጊዜው በባንክና በሰንዱቅ ያስቀመጣችሁት ፈረንካ የሚያድናችሁ መስሏችሁ ይሆናል። ለጊዜው በእጃችሁ ያለው የጦር መሳሪያ ከሚመጣው ጠላት የሚያድናችሁ መስሏችሁ ይሆናል። ፉከራው፣ ቀረርቶው፣ አያድንም። ነገር ግን አይሳካለትም እንጂ የሚመጣው ኃይል ደብረ ማርቆስና ደሴን፣ ባህርዳርና ጎንደርን ብቻ አጥቅቶ የሚቆም አይምሰላችሁ። ይቀጥላል።
•••
ነገርየው አክሱም ሳይገባ የሚመለስም አይደለም። መጪው የኢትዮጵያችን መቅሰፍት የተሳካለት ነገር ቢኖር በህውሓት በኩል ሁለቱን የዐማራና የትግራይ ነገዶችን እንዳይታረቁ አድርጎ መለያየቱ ነው። በሃይማኖት አንድ የሆኑትን፣ በባህልም አንድ የሆኑትን ትግሬና ዐማራን ማናከሳቸው ለመጪው መቅሰፍት ጠቅሞታል። መቅስፈቱ አሁን ሁለቱንም ለያይቶ ለመምታትም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። አቢቹ 12 ሺ ቤት የሚያፈርሰው ትግሬና ዐማራን አይጥና ድመት አድርጎ በደንብ ማቀሳሰሩን ስላየ ነው። ብርሃኑ ነጋና አንዳርጋቸው ጽጌ እንደሆኑ ቤተመንግሥት ገብተው መውጣቱ አይቅርባቸው እንጂ አዲስ አበባ አይደለም ቤት መፍረስ ለምን በጭንቅላቷ አትተከልም። ኬሬዳሽ።
•••
ለዚህ ነው የትግራዩ አክቲቪስት የሆነው አሉላ ሰሎሞን በቅርቡ በቡራዩ ተፈጽሞ በነበረው ጭፍጨፋ ወቅት እንዲህ ዓይነት መልእክት በፌስቡክ ገፁ ላይ በድፍረት ያስተላለፈው። ” ይድረስ ለተጋሩዎች። ለጃዋር ደውየ በተጋሩ ላይ ጥቃት ይደርስ ይሆን ወይ ብዬ ጠይቄው ነበር። አነጋግሬዋለሁም ። ጃዋርም በፍፁም አትስጉ ብሎኛል ” የሚል መልእክት ነበር ያስተላለፈው። ከዚህ መልእክት የምንረዳው ነገር ቢኖር መጪው መቅሰፍት የራስህን ብሔር አይንካ እንጂ ሌላውን ቢጎዳ ጉዳዬ አይደለም በማለት ደረቱን ነፍቶ የተቀመጠ ኃይል አለ ማለት ነው። ነገር ግን እሳቱ አንድ ጊዜ መንደድ ከጀመረ ወዳጄ መርጦ የሚተወው ቤት እንደሌለ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል። ከጠፋንም አንድላይ ነው የምንጠፋው። ከተበላንም አንድ ላይ ነው የምንበላው። አከተመ ።
•••
መከላከያው በኦሮሞ አገዛዝ ሥር ወድቋል። ቢሮክራሲው በሙሉ በኦሮሞ ስር ወድቋል። መከላከያው በትግራይ ጠባየኛ፣ በዐማራ ነፍሰ ገዳይ የሚደረገውም ሆን ተብሎ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ጅቧ ህወሓት በቀደደችው የሴራ ፖለቲካ መንገድ ገብተው የሚተክሉት የጥላቻ መርዝ ነው። ብዙ፣ ብዙ፣ ብዙ ነገር መናገር ይቻላል። ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል።
•••
የትግሬና ዐማራ መጠዛጠዝ ለኦሮሞዎቹ ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል። የመንግሥት መሥሪያቤቶች በኦሮሞ ተተክተዋል። አባዱላ ተቀምጦ በረከት ስምኦን ይታሠራል። ጌታቸው አሰፋ ተቀምጦ ስለ ፍትህና የሕግ በላይነት ይወራል። ይደሰኮራል። የአዲስ አበባ ዲሞግራፊ አዳሜ ዓይንህ እያየ ተገለባብጦ አርፏል። ባንክ ተዘርፎ የሚታሰር የሚቀጣ የለም። ዘርፈህ ብላ። ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው ብሒል በተግባር እየታየም ነው።
•••
አሁን ስደት ከአዲስ አበባ ይጀምራል። በአዲስ አበባ ጫፍ ካራቆሬ እስላም ክርስቲታኑ ተፈናቅሎ በዚያው በካራ ቆሬ ቅዱስ ፋኑኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልሏል። አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ከአቢቹ ቢሮ በር ስር አዲስ አበባዎች ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ፈስሰዋል። ባለጊዜው አፈናቃይ እነ አቢቹ ሆነዋል። አሁን ደግሞ ከ12 ሺ ህ በላይ አባወራ በመቶ ሺ የሚቆጠር ቤቱ በቁሙ እየፈረሰበት የአዲስ አበባን ጎዳና በጎዳና ተዳዳሪ ያጥለቀልቀዋል።
•••
እንዲያም ሆኖ የትግሬ አክቲቪስቶች በዘመነ ህወሓት መልካም የሰሩ ጻድቃን ይመስል መቐለ ተሾግጠው፣ እሰይ ይበለው። ደህና አድርጎ ይቀጥቅጠው። የትአባቱ ይሄ ህዝብ አፈር ከድሜ ያስግጠው ይላሉ። በሩቅ የሚነደው እሳት በደጅህ ላለመምጣቱ ግን ዋስትና የለህምና አስቡበት። ዛሬ ጨቅላ ህጻናትን ወታደራዊ ሥልጠና መስጠት ከተጀመረ ነገ ከነገ ወዲያ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ መልስ ይሰጣል። ወታደር ሲሰለጥን ደግሞ ጠላቱ ተነግሮት እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ለእነዚህ በኦሮሚያ ወታደራዊ ሥልጠና እየተሰጣቸው ለሚገኙ ህጻናት ” ጠላታቸው ” ማን እንደሆነ ይሆን የተነገራቸው?  ማንን እንዲገሉ ይሆን የተመከሩት?  የሰለጠኑትም። ፈጣሪ ይወቅ። ነገርየው ግን እንደቀልድ የሚታይ ከመሰለን ተሳስተናል።
•••
” አንድ ታሪክ ላጫውታችሁና እንደ ሊማሊሞ፣ እንደ ግራካሱ የተጠመለመለውን ነገሬን ልቋጭ “
•••
እስልምና ከተፈጠረባት መካ መዲና ወደ ሰሜን አፍሪካና ወደ አውሮፓ የዘለቀው በጦርነት መሆኑ ይታወቃል። ለእስልምና በቀላሉ መስፋፋት ደግሞ የክርስትናው ለሁለት መከፈል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ምእራባውያኑ ካቶሊክ ነን ሲሉ ምስራቃውያኑ ደግሞ ኦርቶዶክስ ነን ብለው በአንዱ እየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ባህሪያት ላይ ሙግት ያዙ። አንዱም አንዱን ለማጥፋት ጉድጓድ ይምስ ገባ። እናም ይህን ደካማ ጎን የእስልምናው ጦር በደንብ ተጠቀመበት። ነገሩ እንዲህ ነው።
•••
የእስልምናው ጦር መጀመሪያ ካቶሊኮቹ የሚበዙበትን ሀገራት ወርሮ ሲይዝ ምሥራቃውያኑ ኦርቶዶክሳውያን ” እሰይ ይበላቸው። ድሮም ክርስቶስን ሁለት ባህሪይ ነው ብለው እየሰበኩ ይሄ መዓት ባይመጣባቸው ነው የሚደንቀን እያሉ በካቶሊካውያኑ መወረር፣ መጥፋትና መሞት ይሳለቁ ጀመር። ታዲያ የእስልምናው ሠራዊት የካቶሊካውያኑን ይዞታ በቁጥጥሩ ስር ካደረገ በኋል እዚያው ያሰለማቸውን ካቶሊካውያን ወታደር አድርጎ ዘመቻውን ወደ ምሥራቃውያኑ ኦርቶዶክሶች ያደርጋል። ይሄኔ ምዕራባውያኑ የካቶሊክ ሀገራት በደስታ ጮቤ ይረግጣሉ። ” እሰይ ይበላቸው፤ የእኛ እምነት ይከተሉ የነበሩትን ሀገራት የእስልምናው ጦር በወረረ ጊዜ እነሱ ዝም ብለው ያዩን አልነበር? መች አገዙን?  እሰይ ይበላቸው ብለው ዝም ብለው ይቀመጣሉ። የእስልምናው ወራሪው ጦርም መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነለት። የዓረቢያን፣ የሰሜን አፍሪካን፣ የታናሽ እስያን ሀገራት በሙሉ ያለተቀናቃኝ በካቶሊክና በኦርቶዶክሳውያኑ ያለመተባበር አፈር ከድሜ አስግጠዋቸው በአጭር ጊዜ እስላማዊ ሀገር አደረጋቸው። እንደ ሊቢያ፣ ግብጽና ሦርያ የመሳሰሉ ኦርቶዶክሳውያን ሀገራትም በአንድጊዜ ወረራ እስላሞች ሆኑ። የአሌክሳንደሪያና የሦሪያ የኦርቶዶክሳውያን ዩኒቨርስቲዎችም ወደሙ።
•••
ወራሪው የእስልምና ሠራዊት በዚህ ሳያበቃ የተፈጠረለትን የክርስቲያኖቹን መለያየት እየተጠቀመ ጉዞውን ወደ አውሮጳ ለማድረግ መንገድ ጀመረ። የክርስቲያኖች መዲና የክርስቲያኑ ንጉሥ የቆስጠንጢኖስን ሀገር የነበረችውን የዛሬዋን ቱርክ በአጭር ጊዜ ተቆጣጠረ። የቅድስት ሀጊያ ሶፊያንም ቤተመቅደስ ተቆጣጥሮ መስጊድ አደረገው። እናም አሁን በቀጣይ መላ አውሮፓን ለመውረር ዝግጅቱን አጠናቀቀ። ቱርክ ደግሞ ወደ አውሮጳ ለመግባት የመጨረሻዋ ድልድይ የሆነች ሀገር ናት።
•••
በዚህን ጊዜ ሁለቱ ሃይማኖቶች ባነኑ። እስልምና ቱርክን ከተሻገረና አውሮጳ ከገባ አለቀልን ብለውም ሰጉ። እናም መወሰን ነበረባቸውና ውሳኔ ወሰኑ። እንዲህም ተባባሉ። ” እልህ መጋባቱን እንተወው፣ ልዩነታችንም እንዳለ ይቀመጥ። ነገር ግን አሁን የመከራከሪያ ጊዜ ሳይሆን የህልውና ማረጋገጫ ጊዜ ነው። እናም ወደ አንድነቱ መጥተን ይሄን ኃይል ካላስቆምነው በአጭር ጊዜ አውሮጳችንም የሰሜን አፍሪካና የአረቢያ ምድር ዕጣ ነው የሚደርሳት።” በማለት መከሩና ውሳኔም ወሰኑ።
•••
በኢየሱስ ክርስቶስ ባህሪይ፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ምልጃ ባንስማማም በክርስቶስ መስቀል ግን ልዩነት የለንም። እናም በጋራ የመጣብንን ወራሪ ጦር ለመመከት የሚያስችለን የጋራ ጦር እናቋቁምና ይሄንን መቅሰፍት ከተቻለ እናጥፋው። ካልተቻለም ባለበት ገድበን መክተን እናስቀረው። የጦር ሠራዊታችን መለያ ዓርማም ሁላችንንም የሚያስማማን ” የመስቀል ” ምልክት እናድርገው በማለት ተስማሙ። ተስማምተውም ወሰኑ። ጦርነቱም ” የመስቀል ጦርነት ተባለ “። መስቀል የሁሉም ክርስቲያኖች የድል ምልክት ነውና ተባብረው ልዩነታቸውንም አስወግደው ቢያንስ የዛሬዋን አውሮጳን በወቅቱ በኃይልና በጉልበት ሰዎችን በጦርነት ያሰልም ከነበረው የእስልምና ጦር ታደጉ። ወራሪም ከቱርክ ሳይሻገር በዚያው እንዲቆይ አድርገው በዘመኑ ከነበረው ከወራሪው እስልምና ጦር ለመታደግ በቁ ይለናል የዓለም ታሪክ። ይሄው ነው በየቦታው ተጽፎ ተቀመጦ የምናነበው ታሪክ።
•••
ቱርክ የአውሮጳ ኅብረት አባል ለመሆን ጥያቄ ባቀረበች ጊዜ ከመስፈርቶቹ አንዱ የክርስቲያኖች ንብረት የነበረውን አስደናቂውን የሀጊያ ሶፍያ ቤተመቅደስ ከመስጊድነት ወደ ቤተመቅደስነት ለክርስቲያኖች እንድታስተላልፍ ነበር የተጠየቀችው ይባላል። ነገር ግን የቱርክ መንግሥት ቤተመቅደሱን ለክርስቲያኖች አልመልስም። መሥጊድ መሆኑንም አስቀርቼ የሚጎበኝ ሙዚየም አደረገዋለሁ ባለው መሠረት አሁን የቅድስት ሀጊያ ሶፊያ ካቴድራል መስጊድ መሆኑ ቀርቶ ሙዚየም ሆኖ ይጎበኛል። በነገራችን ላይ ክቡ አጼ ኃይለሥላሴ ያሠሩት የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ህንጻ ዲዛይን በቀጥታ በቱርክ ኢስጣንቡል ከሚገኘው ከቅድስት ሀጊያ ሶፊያ ቤተክርስቲያን የተቀዳ ነው።
•••
አሁንም እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ኦሮሞው እንደ ብራና ተወጥሯል። በተለይ የሸዋ ኦሮሞና ኦርቶዶክስ የሆነው ኦሮሞ በሁለት ልብ ተከፍሎ መያዣ መጨበጫ አጥቶ ቁጭ ብሏል። ኦነግን እንዳይደግፍ ” የሜንጫው ታሪክ ” ትዝ ይለዋል። እንዳይቃወመው ደግሞ የሚኒሊክ ሰፋሪ የሚል ቅጽል ስም ተዘጋጅቶለት ይወቀጥበታል። ከማኅበረሰቡም ይገለልበታል። እንዲያውም የሸዋውን ኦሮሞ የእነ ጃዋር ቡድን እንደ ትክክለኛ ኦሮሞም አይቆጥረውም። እናም በአሁኑ ወቅት እንደ ኦሮሞ ክርስቲያኖች የጨነቀው ሰው በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ለዚህ ነው አብያተ ክርስቲያናቱ ነውጠኞቹ የኦነግን ባንዲራ ቤተክርስቲያን ላይ ሲቀቡ እያዩ ጮጋ ብለው የተቀመጡት።
•••
ትግሬው ከላይ እንዳልኩት ነው። የሚጠቃው ዐማራው ስለሚመስለው የራሱ ጉዳይ ብሎ ዘና ብሎ ተዘፍዝፎ ተቀመጧል። አሁን ያሉት የትግራይ መሪዎች ከኦነግ ጋር ሽርክ ስለሚመስለውም ችግሩ የማይነካው መስሎት ተዘልሎ ተቀምጧል። ነገር ግን የሚመጣው መቅሰፍት እሱንም አይለቀውም። አይምረውምም። ምን አልባት በሁለት ግንባር ዐማራውን ሳንድዊች የማድረግ ዕቅድ ካለም ውጤቱን በጋራ የምናየው ይሆናል። ተናግሬያለሁ መታወቂያህ ላይ ያለው ብሔር ማንንም አያድንም። አከተመ።
•••
ለማንኛውም የጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ መንግሥት ጉዳዩን ባላየ ባልሰማ ላሽ እያለው ነው እንጂ በደንብ አሳምሮ ያውቀዋል። ኤርትራ ሄደው ኦቦ ለማ ከኦነግ ጋር ምን ተፈራርመው እንደመጡ መድኃኔዓለም ብቻ ነው የሚያውቀው። እንዲያውም የቲም ለማ ቡድን ኦነግን ጃስ በማለቱ በኩል እጁ እንደሌለበት ማረጋገጥም አይቻልም። አሁን በምዕራብ ወለጋ የዐቢይ መንግሥት ሥልጣኑን በኦነግ ከተቀማ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ባንዲራ ከወለጋ ምድር ወርዷል። የአርበኞች ግንባር መሳሪያውን ለሻአቢያ ጥሎ እንዲገባ ሲፈረድበት ለኦነግ ግን ከነ ሙሉ ትጥቁ እንዲገባ የተደረገው በስህተት የሚመስለው ካለ አሁንም ስህተት ነው።
•••
እኔ የሚገርመኝ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ለጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድና ለኦቦ ለማ መንግሥት ተስፋ ያለመቁረጡ ነው። እንዲያው እንዴት እንደ ሚንሰፈሰፍላቸው እኮ አያድርስ ነው።  አሁን የመደመር ስካሩ በረድ እያለ ስለሚመጣ በቅርቡ ይባንናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ህዝቡ ለእነ ኦቦ ለማ ስፍስፍ ይላል እንጂ እነሱ ለህዝቡ እንዲያ የሚሆኑ ግን አይመስለኝም።
•••
አሁን መንግሥት አቅም ይኑረው አይኑረው፤ እያታለለና እያጭበረበረ ቀሪውን የኢትዮጵያ ህዝብ እያደነዘዘ ይሁን አይሁን፣ እየዋሸንና እየፎገረን ይሁን አይሁን በቀጣይ ሳምንታት የምናውቀው ይሆናል። ያልተቀየረ ያው ወርቅ ቅብ የተቀባው አዲሱ የጠሚዶኮ ዐቢይ መንግሥት በወርቃማ ቃላት እየሸነገለ የተስፋ ዳቦ በህልም እያስገመጠ እስከ የት ድረስ እንደሚቀጥል አብረን የምናየው ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን ሁሉም ሰው በየቤቱ፣ በየሰፈሩና በየመሥሪያ ቤቱ በቀጣይ ሊመጣ ካለው ቁጣና አደጋ እንዴት መከላከልና መመከት እንደሚችል በግልጽ ቢወያይ፣ ቢነጋገገርና ቢመካከር ጉዳት የለውም ባይ ነኝ።
•••
በተለይ ክርስቲያኖች አስቡበት። የቀደመው የኢትዮጵያ ሙስሊም ለኢትዮጵያ አደጋ አይደለም። የቀደመው የኢትዮጵያ ሙስሊም ለኢትዮጵያ ባንዲራ የሞተ፣ አጥንቱን የከሰከሰ፣ አፈር የሆነላት ነው። የቀደመው ሙስሊም አሁን ሰሞኑን በመጡት ነውጠኛ ሙስሊሞች ዘንድ እንደመናፍቅ የሚታይም ነው ይባላል። ከካፊር ወይም ከክርስቲያን አንለየውም ብለው መግለጫ ያወጡበት ጭምር ነውም ይላሉ። እናም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ነገርየውን በጥሞና ተመልከቱት፣ ተወያዩበት፣ አስቡበትም። ” የባለ ሜንጫዎቹ ” አካሄድ ለማንም እንዳይመለስ ይታወቃል። ለእናንተም ጭምር እንደማይመለሱም ሰምቻለሁ። እንዲያውም አሁን አሁን የታዋቂ ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ሼሆችን መቃብር እስከማፍረስ የደረሰ ተግባር እየተፈፀመና የሆነ ነውጠኛ ኃይል እየተፈጠረ እንደሆነም ነው እየሰማን ያለነው። ይኸው ነው።
•••
የሚገርመው ኢትዮጵያ ግን ምንም አትሆንም። የሚያፈርሷት እየፈረሱ፣ የሚያዋርዷት እየተዋረዱ፣ የሚወጓት እየተወጉ፣ እየተቀሰፉም ከምድረገጽ ይጠፋሉ። የዮዴት ጉዴት እሳት፣ የግራኝና የደርቡሽ ሰይፍ፣ ሶማሊያ የግብጽና የጣልያንና ጦርም አላጠፋትም። የሻአቢያ፣ የህውሓት የኦነግና አሁን ደግሞ የኦህዴድ ተንኮልም አያጠፋትም። እመነኝ ኢትዮጵያን በክፉ የሚያስቡ ሁሉ #ይቀሰፋሉ። አባቴ ይሙት። ወላዲተ አምላክ ምስክሬናት ኢትዮጵያና ህዝቧ ምንም አይሆንም። ጥቂት መንገራገጭ ይኖራል። ድንኳኑን ነፋስ ያወዛውዘዋል። የቤቷ እቃ ይሰባበር ይሆናል፣ ጥቂት ደምም ይፈስ ይሆናል። እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ምንም አትሆን። ይልቅ ለራስህ እወቅበት።
ይህንንም ራሴው በእጄ ጻፍኩት ። 004915215070996 ደግሞ የቫይበር ፣ የኢሞና የኋትስአፕ እና የቴለግራም መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው። 
ሻሎም !  ሰላም !
የካቲት 13/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic