>
7:46 am - Wednesday December 7, 2022

ሰዎችን በማፈናቀል መናፈሻ ልትሰሩ?? ... (ጋዜጠኛ - መስፍን ነጋሽ)

ሰዎችን በማፈናቀል መናፈሻ ልትሰሩ?? አይመስለኝም!!!
ጋዜጠኛ – መስፍን ነጋሽ
ኦዲፒ ስለ ሕግ የበላይነት ለመስበክ ከሚችልበት የሞራልና የተቋማዊ ታማኝነት ደረጃ ላይ አለመድረሱን የረሳው ይመስላል። በይቅርታና በሙከራ “ቅጥር” ላይ ናችሁ። ገና አልተመረጣችሁም፤ አልተቀጠራችሁም። አትርሱት!
ብዙው ነገር ሕገ ወጥ እና ኢርትዐዊ በሆነበት አገርና ክልል፣ አቅመ ደካሞቹን “ሕገ ወጥ ስለሆናችሁ” ብሎ ማፈናቀል ይቻል ይሆናል። እስቲ የአካባቢውን መሬት ለዛሬዎቹ “ሕገ ወጥ” ተፈናቃዮች የሸጡትን የራሳችሁን ሰዎች ለሕግ አቅርባችሁ አሳዩን? ስማቸውን፣ ምስላቸውን፣ የነበራቸውን ሥልጣንና ሚና፣ የተጠረጠሩበትን ወንጀል በይፋ ለሕዝቡ አቅርቡ? እያንዳንዱ ተፈናቃይ ለፓርቲያችሁ ካድሬዎችና ሹመኞች በጠራራ ፀሐይ በድምሩ በሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተጠይቆ ከሌለው ላይ ተበድሮ የከፈለ ነው። ከመካከላችሁ ሌቦቹን ከመፈለግ ንጹሐኑን መፈለግ እንደሚቀል እናውቃለን። ችግራችሁ ይገባናል። ተዉ እንጂ! እንደማናውቃችሁ አትሁኑ! ንገሩን አትበሉ!
እንዲህ ያሉትን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ እርምጃዎች “ቅጥራችሁ” እስኪጸድቅ (እስከ ምርጫው) በማቆየት ፋንታ ጥድፊያችሁ ከምን የመነጨ ነው? ያስጠረጠራል! ይህንን እርምጃ ጊዜ ወስዶ፣ ለሚፈናቀሉት ሰዎች የሆነ ጊዜያዊ መፍትሔ እንኳን አዘጋጅቶ ቤቶቹን ማፍረስ አይቻልም ነበር? ጥድፊያ ምንድን ነው? (የመናፈሻ ናፍቆት እንደጸናባችሁ ይገባናል። ቢሆንም ያስጠረጠራል። “መናፈሻ ብቻ እንዲህ አያስለቅስም” አለ አብዲ ኢሌ!)
እነዚህን ሰዎችን በማፈናቀል መናፈሻ ልትሰሩ ነው አሉ! አይ መናፈሻ! የመናፈሻ ሻምፒዮኖች! መናፈሻውን እንደማትሰሩት እናውቃለን። ጥያቄው ይኼ ነው፤ ገና ይቀጥላል ባላችሁት ማፈናቀል ከወጪ ቀሪ እናገኛዋለን የምትሉት የፖለቲካ ትርፍ ፓርቲያችሁንም ይሁን አገራችንን፣ ባስ ሲለም እንወክለዋለን የምትሉትን የኦሮሞ ሕዝብ ይጠቅማል ወይ? አልመሰለኝም።
Filed in: Amharic