አሰፋ ሀይሉ
የፅሁፌ ዋነኛ ዓላማ የወቅቱ የህወኀት መሪዎችና ወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ደጋፊዎቻቸው በአሁን ወቅት እየተከተሉት ያሉት ያገነገነ ተቃውሞና የመገለል ፖለቲካ ወደየት ሊያመራ ይችላል? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የታዩኝን አንዳንድ ፖለቲካዊ ሥጋቶች በግልፅ መጠቆም ነው።
በቅድሚያ ግን – እንደ መግቢያ – ስለ አሁኑ ህወኀታዊ ፖለቲካ አራማጆች ወቅታዊ ትኩሳት የታዘብኳቸውን አንድ ሁለት ነጥቦች ጠቅሼ ልለፍ። የመጀመሪያው በአሁን ወቅት በህወኀታውያኑ ላይ የሚስተዋለው የተፈናቃይነት አጠቃላይ ስሜታቸውን ይመለከታል። ሁለተኛው ደግሞ ያደረባቸውን የተሳዳጅነት ስነልቦና።
ካልተሣሣትኩ በመነሻዬ በድፍኑ የጠቀስኳቸው የወቅቱ የህወኀት ፖለቲከኞች – በአሁን ወቅት – በእነ ዶ/ር አብይ ፊት አውራሪነት እየተካሄደ ባለው ሁሉን-ዓቀፍ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ለውጦች ላይ በጉልህ የሚታይ (እና የማይታበልም፣ የማይስተባበልም) ቅሬታ አላቸው። ቅሬታ ብቻ ሳይሆን የለውጡ ባይተዋር የመሆን ሀሳብ የገባቸው – የባይተዋርነት ስሜት ብቻ ሳይሆን – ጥልቅ የሆነ የተፈናቃይነት (disenfranchised የመደረግ) ስሜት ያደረባቸው ይመስለኛል።
በመሆኑም ነው በመነሻቸው በተበሰሩት ሀገራዊ ለውጦች ላይ በግንባር ቀደምነት ተሣታፊ ሊሆኑ የጀመሯትን የመቶ ሜትር ሩጫም እዚያው ከክቡር ትሪቡኑ ሳይነቃነቁ – በቅድሚያ ወደ ከንፈር-ቅብ – ቀጥሎ ደግሞ ጨርሶ በመለገም – ለማራቶን የታሰበውን ጉዞ – ከአጭር ባጠረች ሩጫቸው ባጭሩ ገትተዋታል።
(ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ – በአንድ የስብሰባ ማዕድ ላይ – አጭር ርቀት ሩጫ የለመደ ረዥም ስናደርግበት ደክሞት ከውድድሩ ይሰናበታል – ያሉት – በአንድምታ ይህን በአጭሩ የተገታ ረዥሙን የህወኀቶች ሩጫ ለመግለፅ ይሆን? … በዚህ እንኳ እርግጠኛ አይደለሁም! ግድየለም ይሄ ይደርሳል። ይቆየን። ላሁኑ ወደ ቁምነገሬ ልመለስ)።
በህወኀታውያኑ አረዳድ – ለውጥ አለ ከተባለ – የዚያ ለውጥ ዓይነተኛ “ታርጌት” እና ውጤቱ – እነርሱኑ ራሳቸውን እና እነርሱ ሲያራምዱት የቆዩትን (ወይም ሲጋደሉለት የኖሩትን፥ ማለትም ሲሞቱለት እና ሲገድሉበት የኖሩትን) ፖለቲካቸውን ከሥሩ ገዝግዞ ለማስወገድ አልሞ የተነሳ ለውጥ ነው ለውጡ።
ስለዚህ በለውጦቹ ጅማሮ ማግስት – የህወኀታውያኑ የፖለቲካ ነባር ሹማምንት – ልክ በጥምር ጦር ሲዘመትባቸው ወደ ትውልድ መንደራቸው ወደ ቲክሪት እንዳፈገፈጉት የኢራቃውያኑ መሪ ሰዳም ሁሴንና ጭፍሮቻቸው ሁሉ – የለውጡ አካሄድ በእነርሱ ላይ ማንዣበቡን የተመለከቱ ሲመስላቸው በባዶ ሜዳ እየተጠራሩ በበላይነት ወደሚያስተዳድሩት ወሰነ ክልል ማፈግፈጋቸውን ሥራዬ ብለው ተያያዙት።
ስለዚህ ባሁኑ ወቅት – ህወኀታውያኑ የፀረ-ለውጥ ኮንሰርቫቲቭ አመራሮች – ተከታዮቻቸውን አሳምነው – በእነርሱ አመለካከት – በእነርሱ ላይ ዳምኗል ብለው በፅኑ የሚያምኑት ወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሠማይ በደንብ እስኪጠራ ድረስ – በለውጦቹ መከፋት ብቻ ሳይሆን – ራሳቸውን ማግለል፣ በእኛ አብዮታዊ ዲሞ ላይ የተቃጣ የጥፋት ሴራ ነው ያሉትን የለውጥ እንቅስቃሴ ሁሉ በቻሉት ድምፅ አጠንክረው መቃወም፣ እና በቻሉት ሁሉ ምድራዊ (እና ሰማያዊ) ነገር ተጠቅመው – ቢቻላቸው የለውጡን አቅጣጫ ለመቀልበስ – ካልተቻላቸውም የለውጡን ወናፍ ከምንጩ ለማስተንፈስ – ጥንቃቄና ሥጋትን በተላበሰ የሞትና የሽረት መንገድ – በግልፅም፣ በህቡዕም መንቀሳቀሱን – እንደ መጨረሻ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ አድርገው የተያያዙት ይመስለኛል።
ይህ ነገር እንዲህ በቀላሉ ትንታኔ ቀርቦበት ባጭሩ የሚጠናቀቅ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ነገሩ በቀላሉ ይቋጭም አይቋጭም ግን ይህ ነገር በቀላሉ የሚታይ ነገር እንዳይደለ ይታወቅ። ለለውጡ ባይተዋርነትና በለውጡ ተፈናቃይነት ዋነኛዎቹ የወቅቱ የህወኀታውያን ፖለቲካ አራማጆችን ውስጠ ሃሳብ (ወይም ልብና ቀልብ) ሰንገው የያዙ ዋነኛ የዕይታ ቱምቢዎች፣ ዋነኛ የአስተሳሰብ ውሃ ልኮች ናቸው።
ከዚህ ከላይ ከገለፅነው የወቅቱ የህወኀታውያን ፖለቲከኞች የተፈናቃይነት አጠቃላይ እሳቤ (አሊያም መደምደሚያ ሀሳብ) ጋር ተከታትሎ – ወይም አብሮ ተያይዞ የተፈጠረው አጠቃላይ ሁሉም “ተጋሩ”ዎች በጋራ እንዲጋሩት የተደረገ ሁለተኛው ወቅታዊ ስነልቦና ደግሞ አለ ፦ አጠቃላይ ይዘት ያለው የተሳዳጅነት ስነልቦና!!
ይህ የተሳዳጅነት ስነልቦና በግለሰብ ደረጃ “ከበቂ ምክንያት በላይ እጅግ ተጋንኖ” ሲያይል – በስነልቦና እና በስነአዕምሮ ሳይንሶች “ፓራኖያ” የሚል ስያሜ ይሰጠዋል። ይሄ ዓይነቱ ሊያጠፉኝ ነው፣ ሊጨርሱኝ ነው፣ ተነስተውብኛል፣ ስለእኔና ስለእኔ ነው የሚያሴሩት፣ እየተዶለተብኝ ነው፣ አድብተውብኛል፣ ከበውኛል፣ ወዘተ ወዘተ ወዘተ የሚሉ በሌሎች የመሳደድን አስፈሪ ቅዠቶች እያመጣ ሲያስደነግጥ ውሎ ሲያስደነብር የሚያሳድረው ይሄ ስነልቦና የጤንነት ጥንቃቄ አይደለም። መረዳት የሚያስፈልገው ቀውስ ነው።
ይህ “ፓራኖያ” ብለን የጠራነው አጠቃላይ የመጠራጠርና ያለማመን እና የተሳዳጅነት ስነልቦና – በግለሰብ ላይ ሲከሰት – ፅኑ ግለሰባዊ ቀውስን ይፈጥራል። የጭንቅላት ሠላምን ያሳጣል። የሰውነት ዕረፍትን ይነሳል።
ፓራኖያው ወይም የተሳዳጅነት መንፈሱ ከግለሰብ አልፎ በማኅበረሰብ ላይ እንዲሰርፅ ሲደረግ ደግሞ – በቶሎ ካልተገታ – ወደ ማኅበረሰባዊ የጋራ ፍርሃት ይሸጋገራል። ይህን የሳይንስ አዋቂዎቹ “ሶሻል ሂስቴሪያ” ይሉታል። ማህበረሰባዊ ውዥንብር። ይህም የባሰ ጉዳትን የሚያስከትል የሠላም ፀር ነውና – መረዳት፣ መግባባትና ውዥንብሩ እንዲመክን መደረግን ይሻል።
/በዚች አጋጣሚ… “ሀገር በወሬ ሳይፈታ – ችግሩን የመፍታት ጥበብ” – የምትል የፍቺ እና የችፌ መፅሐፍ ይዤ ብቅ ልበል ይሆን?!! ቁምነገሬ ኦቨርዶዝ ሆኗል – ግን ቆይ – ቀልዱ ይቆየን ላሁን። አሁን – ወደ ቁም ነገርና – ቁጭ ነገር !!!/
እንግዲህ ይህ አፅንዖት ሰጥቼ በዚህ ፅሁፌ በተቻለኝ አሳጥሬ ለማሳየት የሞከርኩት የወቅቱ ህወኀታውያን ወግ-አጥባቂ የፖለቲካ አራማጆች የወቅታዊ ስነልቦና መሠረታውያን ነገር… እንዲህ በቀላሉ በእኔ የትዝብት ብዕር ብቻ ተነስቶ የሚተው ነገር አይደለም። ብዙ መረዳትና ጥልቅ ትንተና ያስፈልገዋል። ከመፍትሄ ጋር።
በበኩሌ በቀጣይ ፅሁፌ ከህወኀት ወቅታዊ የመገለል ፖለቲካ ጋር አያይዤ ለማቀርባቸው 6ቱ ወቅታዊ (ሀገራዊ) የፖለቲካ ሥጋቶች እንደ ዋና መሠረቶች (“ፕረሚስ”) አድርጌ የምጠቀምባቸው – እነዚህኑ – እስካሁን ለመግለፅ የሞከርኳቸውን አንኳር የወቅቱ ነባራዊ እውነታዎች ነው ፦
Disenfranchisement and persecution dilemmas are the central themes behind the current psychological states of mind of most TPLF’s conservative leaders at this critical moment in Ethiopian political history.
በቀጣይ ፅሁፌ እስክንገናኝ ተሰናበትኩ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
ጤና ይስጥልኝ።
ፎቶግራፉ፦ የጂም ሆላንዴየር ነው። ከኢዩኒታ የአፍሪካን አርካይቭስ በልግስና የተገኘ።
በፎቶው የሚታዩት በግንቦት 20/1983 በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በሚገኘው የጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ቢሮ ገብተው ከሌሊን፣ ከካስትሮ እና ከመንጌ ምስሎች ሥር ለፎቶ የቆሙ ( – የ”ደርግ” መገኛው የጠፋባቸው ? – ) የህወኀት ተጋዳላዮች።