>

"ይቅር በሉኝ ይቅር አልላችሁም!"  (ውብሸት ታዬ)

“ይቅር በሉኝ ይቅር አልላችሁም!”
ውብሸት ታዬ
እነዚህ ዜጎች ናቸው ግብር ከፍለው ልማቷን እውን የሚያደርጉት። እነዚህ ዜጎች ናቸው አገር ተወረረች ሲባል ለሉዓላዊነቷ ልጆቻቸውን መርቀው በክብር እንዲሞቱላት የሚልኩት። እነዚህ ዜጎችም ናቸው ሲኖሩ ኢትዮጵያዊ ሲሞቱ ኢትዮጵያ የሚሆኑት!!
ሰሞኑን መነጋገርያ ከሆኑ አሳዛኝ ጉዳዮች አንዱ ለገጣፎ ላይ ሰነድ የላቸውም በተባሉ ቤቶች ላይ የተወሰደው የማፍረስ እርምጃ ነው። በዚህም በነዋሪዎቹ ላይ የደረሰው ማሕበራዊ ምስቅልቅል ይታወቃል።
ክስተቱን ተከትሎ የተለያየ ጽንፍ ያላቸው አስተያየቶች ሲቀርቡ ቆይተዋል። ጉዳዩን ከዘር ጋር ከማያያዝ አንስቶ ይህንኑ ለማጠናከር ቀደም ሲል ከሶማሊ ክልል ዘግናኝ ግፍ ተፈጽሞባቸው ለወጡ ዜጎች ከተሰጠው ቦታ ጋር እስከማነጻጸር ደርሶ አይተናል። ይህና ሌላው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚል የሚቀርቡ የሁነት አባባሽ ምልልሶች ለተጎጂ ወገኖቻችን በተጨባጭ የሚጨምርላቸው ነገር የለም።
የሆነው፤ ዜጎቹ ሁልጊዜ በዘልማድ እንደሚደረገው ሌት ተቀን ደክመው የያዟትን ጥሪት ይዘው ሄደው ከአከባቢው አርሶ አደሮች ላይ ቦታ ገዙ። ጉዳዩ የሕግ መሠረት ባይኖረውም በዚህ መልኩ በተገዛ ቦታ ሕጋዊ ሰነድ ወጥቶ የሚኖርበት በጣም ብዙ ቤት መኖሩን እናውቃለን። አንዱ በሌላው ቦታ በሚያየው የዚህ ዓይነት ተሞክሮ ተደፋፍሮ ቦታ ሊገዛ፤ ለዓመታት ለፍቶ ያጠራቀመውን ሃብትም አሟጦ በቤት መስርያው ላይ ሊያውለው ይችላል።
ከመሰረቱ ዜጎች ሁሉ በአገራቸው ላይ እንደአቅማቸው ቤት ሠርተው የመኖር ዜግነታዊ መብታቸው ይቅርና ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ የተቀበረ አካላቸው እንኳ በክብር እንዳያርፍ የዕምነት ተቋማት በግሬደር እያስነሱ የንግድ ሱቅና የመሳሰለውን በሚሠሩባት አገራችን፤ የቦታ ግዥው የተፈጸመበትን መንገድ አግንነን (ለቅንጦት ወይም መነሻው ሕግ የመጣስ ፍላጎት ያለመሆኑ እየታወቀ) ሳይሆን ዞሮ ለሚገባባት ጎጆ  በምስኪኑ ደሃ ወገናችን ላይ በጭካኔ “ሕገ ወጥ ስለሆነ ፈርሷል። ሕግ ማስከበርኮ የመንግሥት ሥራ ነው” ብለን ከመፍረዳችን በፊት ሰው ነንና ራሳችንን በተጎጂዎቹ ጫማ ውስጥ ከተን በዚያኛው ወገን(ቦታውን የሸጡላቸው ወገኖች የሰጧቸውን የሕጋዊ እናስደርግላችኋለን ተስፋና ይህንኑ የሚያረጋግጥ የሚመስለው የአከባቢው ሹማምንት ከጅምሩ እስከቅርብ ጊዜ ያሳዩት ዝምታ) መመርመር አለብን።
በግሌ ስለሁኔታው እንደሰማሁ ወዲያው ለመሄድ ባይሳካልኝም ቆይቼ በቦታው ተገኝቼ ሁኔታውን በአቅሜ ገምግሜ ፣ ተጎጂዎቹንና ላገኛቸው የቻልኩትን የአስተዳደሩን የተወሰኑ ሰዎች ለማነጋገር  ሞክሬያለሁ። ከላይ ከጠቃቀስኩላችሁ ፍሬ ነገሮች የተለየ ጭብጥ አላገኘሁም።
በእኔ ግምገማ የማፍረስ እርምጃው እስከዛሬ በተለያዩ ቦታዎች ስናይ ከነበረው ዜጎችን ከቤት ወደጎዳና ያወጣ የአርምሞ ሰንብቶ ድንገት የማመሰቃቀል መንግስታዊ ማናለብኝነት የተለየ አይደለም። ከአስር ዓመት በፊት አንድ ጎልማሳ የሚታወቀውን የሕግ አግባብ ሳይከተል ቦታ ይገዛል። በእነዚህ አስር ዓመታት ሦስት ልጆች ይወለዳሉ። ትምህርት ቤት ይገባሉ፤ ሕይወት ተረጋግታ ትቀጥላለች።
የአስተዳደሩ ሰዎች ይህን ማሕበራዊ መስተጋብር ፈጽሞ ታሳቢ ያላደረገ እርምጃ ውስጥ ገቡ። እንዴት? ሲባሉ ከሰብዓዊ ሚዛን ሳይሆን አስፈላጊ በነበረ ጊዜ ሆን ብለው ወደጎን ያደረጉትን የሕግ መከበር አጣቀሱ። በዚህም በአባት እዳ ልጆችን አስለቀሱ።
*ሁለት ነገሮች
1ኛ፦ በይቅርታው ዘመን ክቡር ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዓብይ መንግሥት ሆን ብሎ ለሠራቸው ‘ጥፋቶች’ ሁሉ ይቅርታ ጠይቀው ጉዞ ጀምረናል። ይቅርታ የተጠየቀባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ምን ያህል መስመር ያለፉ እንደነበሩ የምናውቀው ነው። ይሁን፤ ለኢትዮጵያዊ ከይቅርታ የሚበልጥ የለም ቅቡል ሃሳብ ብለን ተቀብለነዋል። እነዚህ ዜጎች ቦታውን ለማግኘትና ውለው ሲገቡ አካላቸውን ለማሳረፍ የሄዱበት መንገድ ‘ስህተት’ ከመንግስት ጥፋት የሚበልጥ ነውን? “ይቅር በሉኝ፤ ይቅር አልላችሁም” ማለት አይሆንም?
2ኛ፦ ዜጎች ከመንግሥት ጥበቃ የማግኘት የማይገሰስ መብት አላቸው። እነዚህ ዜጎች ናቸው ግብር ከፍለው ልማቷን እውን የሚያደርጉት። እነዚህ ዜጎች ናቸው አገር ተወረረች ሲባል ለሉዓላዊነቷ ልጆቻቸውን መርቀው በክብር እንዲሞቱላት የሚልኩት። እነዚህ ዜጎችም ናቸው ሲኖሩ ኢትዮጵያዊ ሲሞቱ ኢትዮጵያ የሚሆኑት።
በመጨረሻ፦ ለበጎ ነገር መቼም አይመሽም። ከሌሎች አገራት ተሰደው ለሚመጡ ቀን የጎደለባቸው ወገኖች በተደጋጋሚ “መስመር አልፏል” እየተባለ ጭምር አጋርነቱን ያሳየው መንግስት በግራም በቀኝም ያሉ ጉዳዮችን ፈትሾ ከዜጎቹ ቆን ይቁም። መሬት ያልያዙ የሰማኋቸው ተስፋዎች ቢኖሩም፤ የሚፈለገው ፍሬ ነው። ተግባር ነው። ሲነጋ በጎ ነገር ያሰማን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic