>
5:13 pm - Tuesday April 18, 4958

ባዶ ማስተባበያ!!! (አብርሀም አለሙ ዶ/ር)

ባዶ ማስተባበያ!!!
አብርሀም አለሙ ዶ/ር
አቶ ለማ መገርሳ ከሶማሌ ክልልጋ በተደረገ ግጭት የተፈናቀሉ 500፣ 000 ኦሮሞዎችን ወደ አዲስ አበባና ዙሪያዋ አመጥተው በማስፈር “ለኦሮሞ አንድነት የሚበጅ” እና የአዲስ  አበባንን ህዝብ ስብጥር ለመቀየር የሚረዳ ስራ መሰራቱን አስመልክቶ የሰጡትን መግለጫ ተርጉመን ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ አቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ ስለ መግለጫው
“ከአውድ ውጭ” መሆንና “የትርጉም መጣመም” ጠቁመው፣ ለማስተባበል ሙከራ ቢጤ አድርገዋል፡፡
“ሠሞኑን አንዳንድ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች የክቡር ፕረዝዳንት ለማ መገርሳን ንግግሮች ከተነገረበት አዉድ ዉጪ እና ትርጉም ጭምር አጣምመዉ በማቅረብ ፕረዝዳንት ለማን የአሻጥር ፖለቲካ አራማጅ አስመስለዉ በማቅረብ የማጥላላት ዘመቻቸዉን ተያይዘዉታል፡፡”
እኔ ግን እውነት እውነት እላችኋለሁ ምንም ከአውድ ውጭ የወጣና የተጣመመ ትርጉም የለበትም፡፡ የአቶ ለማን መግለጫ ከቪዲዮው የኦሮሚኛ ንግግር ወደ አማርኛ የተረጎምኩና ወደ ጥሁፍ የመለስኩት እኔ ነኝ፡፡ አቶ አዲሱ “ማስተባበያ” ያሉትን ያወጡት ትርጉሙን ስለ ሰራው ሰው የሁለቱም ቋንቋዎች ችሎታ፣ የትርጉም ሙያና ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊ ሀቀኝነት ስለማያውቁ ይሆናል፡፡ ለማንኛዉም አድማጭ/አንባቢ የራሱን ፍርድ መስጠት ይችል ዘንድ እድል ለመስጠት ሙሉውን ቪዲዮ (አቶ ለማና ዶ/ር ዓቢይ ከኦሮሞ “ሊሂቃን” ለተነሱላቸው የሰጧቸው ምላሾች) እና የአቶ ለማን ምላሽ የአማርኛ ትርጉም ከታች ለጥፌያለሁ፡፡ ትርጉሙን በተመለከተ ስህተት አለው የሚል ሙግት ቢመጣ በደስታ መልስ እሰጣለሁ፡፡ ሀዝብ እውነቱን የማወቅ መብት አለው፤ እኔም የማውቀውን እውነት የመግለጥ የዜግነትና ሞራል ግዴታ አለብኝ፡፡
ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር!   
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተደረገ የጨፌ ኦሮሚያ የእርቅ ህዝባዊ ሸንጎ
(አቶ ለማ መገርሳ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጧቸው መልሶች)
ትርጉም በአብርሃም ዓለሙ
አዛውንቶች፣ አዋቂዎቻችንና ወጣቶቻችን ሁሉ ያነሳችኋቸው ሰፋፊና ትላልቅ ሃሳቦች በአንድ በኩል ለኛም አቅም የሚሆኑን ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለምንሰራቸው ስራዎችም ግብአት በመሆን የሚረዱን በመሆናቸው፣ የተነሱትን ሃሳቦች በጠቅላላ ተመልክተን ለወደፊት በምንሰራቸው ስራዎች በሙሉ ውስጥ የምናተኩርባቸው ስለሆኑ ያነሳችኋቸውን ሃሳቦች በዚህ ዓይን ነው የምመለከተው፡፡ እናንተ ያሳሳችኋቸውን ጉዳዮች ለናንተ መረጃ ለመስጠት ያህል አንዳንዱን አስተያየት ልሰጥባቸው እፈልጋለሁ፡፡ የኦሮሞ ጥያቄ አልተመለሰም የሚለውን ሃሳብ በተመለከተ፣ እውነት ነው እኛም የኦሮሞ ጥያቄ ተመልሷል፣ እኛም መልሰነዋል የሚል እምነት የለንም፡፡ እንዲያውም ኦሮሞ ገና ከጅምሩ አንስቶ ሲጮህላቸው፣ መስዋእትነት ሲከፍልባቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ገና አልነካንም ብንል ነው ትክክለኛ መልስ ሊሆን የሚችለው፡፡ ሆኖም እኛ እየሄድንበት ያለነው ወይም ልንሄድበት እየጠረግነው ያለነው መንገድ፣ እነዚያን ጥያቄዎች ለመመለስ መልካም መንገድ ጀምረናል፣ የሚያዋጣ ስልትም ይዘናል ብለን እንድናምን ያስችለናል፡፡ የኦሮሞ ጥያቄ ስንል መመለስና መታየት የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህም መመለስና መታየት አለባቸው፡፡ ሆኖም ባንድ ጊዜ ተመልሰው የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ህብረተሰቡ እስካለ ድረስ፣ በህብረተሰቡም ውስጥ ለውጥ እስካለ ድረስ፣ የህብረተሰቡ ፍላጎትም እየጨመረ እስከመጣ ድረስ፣ ጥያቄ በየትኛውም ጊዜ አያቆምም፤ ሁሌም ይኖራል፡፡ ይሁን እንጂ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ፍቱን የሆኑ ጉዳዮችን በቅደም፟ተከትል እያዩ እየፈቱና እየመለሱ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ሁሉ ግን መመለስ ከባድ ነው፤ ጊዜ ሊሰጠቸው የሚያስፈልጉ፣ ጊዜ ሊገዛበቸው የሚያስፈልጉ ጥያቄዎች ስላሉ፡፡ ለምሳሌ፦ የኦሮሞ ጥያቄ ዋነኛውና ቀዳሚው ነው ልንለው ባንችልም፣ ባለፉት አራት ወይም አምስት ዓመታት ውስጥ ኦሮሞ በአንድ ድምጽ ሲያለቅስለት፣ ሲጮህለት የነበረው የኦሮሞ ቋንቋ የእስር ቤት ቋንቋ ሆኗል፡፡ የኦሮሞ ቋንቋ የእስር ቤት ቋንቋ ሆኗል ማለት የኦሮሞ ልጆች እስር ቤቶችን ሞልተውታል ማለት ነው፤ እስር ቤቶች ውስጥ ተኮርኩደው አሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ ከስፍራ ስፍራ፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ኦሮሞ ሲጠይቀው የነበረ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡
ሌላው የፖለቲካ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው መጀመሪያ ህዝቡ እንደ ሰው ተፈጥሯዊና ሰብአዊ መብቱ ተጠብቆ መኖር ሲችል ነው፡፡ በሰንሰለትና ገመድ ታስሮ እያለ ሌሎች ጥያቄዎች ሊመለሱለት አይችልም፤ ሊመለሱለት አይችሉም ብቻ ሳይሆን ሊጠይቅም አይችልም፡፡ ከእስር እራስን መፍታት፣ ከእስር ሰዎችን መፍታት ተቀዳሚው ተግባር ነው፡፡ ይህም የህዝባችንና የሁላችን ጥያቄ ነው የነበረው፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ ከኦሮሚያ ጀምሮ እስከ ፌደራል ባሉ እስር ቤቶች ኦሮሞ በቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሞት እንኳን የተፈረደባቸውን ሳይቀር ከሞት አተረፍናቸው፡፡ ሰዎችን ከሞት ለማትረፍ፣ ነፍስ የእግዝአብሄር ናት፤ እግዝአብሄር እኛን ተጠቅሞ ሰዎችን ከሞት አትርፎ ይሆናል ለማለት ነው እንጂ፣ እኛ ሰዎችን አተረፍን ማለት አንችልም፡፡ ይሁን እንጂ ከሞት እንኳን ብዙ ሰዎችን ማትረፍ ተችሏል፡፡ ዛሬ የትም ያሉ እስር ቤቶች የኦሮሞን ቋንቋ የሚናገሩ አይደሉም፡፡ ይሄ ታሪክ ነው፤ ይሄ ለውጥ ነው፡፡ ይሄ የሆነው ዝም ተብሎ የእስር ቤቶችን በር ከፍቶ መልቀቅ ስለሚቻል ነው ወይስ ይሄን ማድረግ እንደምን ተቻለ? ይህን ማድረግ ድካም የለበትም? ሰዎችን ዋጋ አላስከፈለምን? ይሄ ውሳኔ ምንድን ነው ብሎ በጥልቀት መመርመር ኝ ተገቢ ነው፡፡ የተፈታ ሰው ሁሉ በሺህ የሚቆጠረው በግፍ የታሰረ ነው፡፡ ደግሞም አልተሳሳቱም ማለት አይቻልም፤ ስህተት አልሰሩምም ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ ውሳኔ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ ኦሮሞን ነጻ ለማውጣት በቅድሚያ ከእስር መፍታት ያስፈልጋል፡፡
ከእስር ቤት የተፈታው ሰው ብዛት ሶስት ሺህም ይሁን አስር ሺህ፣ ዋናው ቁምነገር እሱ አይደለም፡፡ እስር ቤት ያለን ኦሮሞ ከእስር ቤት ማውጣት ማለት፣ ውጭ ያለን ኦሮሞ ከእስር መፍታት ማለት ነው፤ ወኔ እንዲያገኝ፣ ሞራል እንዲያገኝ ማስቻል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የህዝባችን ጥያቄዎች በብዛት ያልተመለሱ እንዳሉ ቢሆንም፣ የተጀመሩ ነገሮች ግን አሉ፤ መንገድ መጥረግ ማለትም አንዱ ይሄ ነው፡፡ ኦሮሞን ብቻ ከእስር ቤት ለመፍታት አልነበረም፡፡ ሀቁ ጠፍቶ፣ እውነት (ፍትህ) ተነስቶ በግፍ እስር ቤት ይማቅቅ የነበረን ሰው ሁሉ፣ በብሄር፣ በጎሳ ሳንከፋፍል ሁሉም ፍትህ እንዲያገኝ ታግለን እንዲሳካ ያደረግነው የመጀመሪያው እርምጃ ይሄ መሆን ስለነበረበት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለሰዎች ፍትህን መስጠት ብቻ ነው ወይስ የፖለቲካ መፍትሄ መስጠት በኦሮሞም ሆነ በሌሎች ብሄረሰቦች ዘንድ ምን ዓይነት ትርጓሜ እንዳለው ነገሮችን አዟዙሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሀገር እራሷ ታስራ ነበር፤ ህዝቡም በሙሉ እስር ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ትናንትና ይሄን ህዝብ፣ ይሄን ሀገር፣ እስር ቤት የገባውን ሰው ብቻ ሳይሆን፣ እጅና እግሩን አስሮ፣ እጅና እግር ማሰር ማለት ሰንሰለት ሲገባልን ማለት ብቻ አይደለም፣ ሰው በነጻነት ወደ ውጭ ወጥቶ መነገድ ካልቻለ እስር ቤት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ምሁር በአእምሮው ውስጥ የሚመላለሰውን ሃሳብ ይፋ አውጠቶ ለመናገርና ለመጻፍ መብት ከሌለው፣ ነጻነት ከሌለው፣ እስር ቤት ውስጥ ነው ያለው ማለት ነው፡፡ የግድ ቂሊንጦ መውረድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ማን ነው ይህን ሁሉ ሰው ያሰረው? ባለቤት አለው፡፡ ይህን ሁሉ ሰው፣ ይህን ሀገር ወደ እስር ቤት ያስገቡት ሰዎች ለምንድን ነው ወደ እስር ቤት ያስገቧቸው? ሊዘርፏቸው ነው፤ ሀብታቸውን ሊወስዱባቸው ነው፡፡ እንዚህን ሰዎች፣ እኛንም ጨምሮ፣ እናንተንም ጨምሮ፣ እዚህ ሀገር ውስጥ ከእግዚአብሄር ቀጥሎ የሚፈሩትን ሰዎች፣ እንኳንስ ሊናገሯቸው ቀና ብሎ እንኳን ለማየት የሚያስፈሩትን ሰዎች፣ እዚህ ሀገር ውስጥ ህግ ከማንም በላይ እንደሆነ፣ ማንንም ይዞ ማሰር እንደሚቻል አሳይተናቸዋል፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ ቀደም ሲል የነበሩትን ነገሮች ተመለከቱ፡፡ ሰዎች በአስራ ሰባቱ ቀናት እንደዚህ ሆኖ ይላሉ፤ ከአስራ ሰባቱ ቀናት አስቀድሞ ሰባት መቶ ቀናት ነበሩ፤ ሰዎች ያንን አላዩም፤ አላዩም ያንን፡፡ በአስራሰባቱ ቀናት አይደለም ነገር የተጀመረው፤ ቆይቷል፡፡ ትግል ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ ዛሬ እዚህ አንናገረውም፤ አንድ ቀን ታሪክ ይናገረው ይሆናል እንጂ፡፡ እኛ ለሰባት፣ ስምንት ዓመታት ስንታደን የኖርን ነን፡፡ ደህንነቶች (ሰምቶ-አደሮች) ከኋላችን እየተከተሉን ሲያስፈራሩን ነበሩ፡፡ ከነበርንበት የተባረርን ሰዎች ነን እኛ፡፡ ዛሬ አይደለም ትግል የተጀመረው፡፡ ለወንበራችንም አልይደለም የታገልነው፤ የወንበር ምኞት የለንም፡፡ የስልጣን ምኞት የለንም፡፡ ለስልጣን ቢሆንማ ስልጣን ላይ ነበረኮ ኦሮሞ፤ በምኒሊክ ዘመን፣ በሀይለስላሴ ዘመን፤ በደርግ ዘመን፡፡ ግን ስልጣን ላይ አልነበረም፤ ቢሮ ውስጥ ነበረ እንጂ ስልጣን አልነበረውም፤ ስልጣን ላይ አልነበረም፡፡ ችግሩ እሱ ነው፡፡ ቢሮ ውስጥ ይቀመጣል፤ ስሙ ጄኔራል ነው፤ ስሙ ሚኒስቴር ነው፡፡ ወንበር ተሰጥቶት ቆንጆ ቢሮ ውስጥ ይቀመጣል እንጂ፣ ስለጣን ላይ ተቀምጦ አያውቅም፡፡ ያቺን ስልጣን ይዘን ለራሳችን ሃጃቺንን ልንወጣ ሳይሆን፣ ለህዝባችን፣ የኦሮሞ ልጆች ከስራችን እየሞቱብን ነበር፣ ደማቸው እየፈሰሰብን ነበር፤ ዓይናችን እያየ፣ ጆሯችን እየሰማ፡፡ የኦሮሞ እናት ናት ስታለቅስ የነበረው፤ ጓዳ ውስጥ ዓይናችን እያየ፡፡ እዚህ ውስጥ ቆመን ስልጣን የምንፈልግበት ቦታ አልነበረም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስነምግባር (ሞራል) የነበረን አልነበርንም፤ ለስልጣን፣ ጥሩ ኑሮ ለመኖር፡፡ የኦሮሞ እናቶች እንባ ነው በየጓዳው ይፈስ የነበረው፡፡ ይህን እንባ እያየን፣ ያን የሚፈስ ደም እያየን፣ የውሻ ደም አልነበረም የሚፈሰው፡፡ የኦሮሞ ልጆች ደም እየፈሰሰ፣ እኛ ስልጣን የምንፈልግበት ጊዜ አልነበረም፡፡ የተመቻቸ ሁኔታ ቢኖር፣ ሀገር የተረጋጋ ቢሆን፣ ሰላም ያለበት ሀገር ውስጥ ቢሆን ስልጣንን ቢመኙት ምንም አልነበረም፤ ጥፋት የለውም፡፡ ትግሉ ውሎ አድሯል፤ ቆይቷል፡፡ መጀመሪያ የኦሮሞ ደም መፍሰስ የጀመረ እለት ነው ትግላችን የጀመረው እንጂ፣ በቀደም እለት እዚህ አዳራሽ ውስጥ በአስራሰባቱ ቀናት አንዳችን የሌላችንን ራስ ያሳመምን ጊዜ የተጀመረ አይደለም፡፡ ማን ነው ወንበር አመቻችቶ ኑና ውሰዱ ያለን? አሳምረውልን ነው የጠበቁን ወይስ እሳት ለኩሰውበት ነው የሰጡን?
ለውጥ ማለት፣ ስለ ለውጥ ውስጡን ጠለቅ ብሎ የሚያውቅ ሰው፣ ልምዱ ያለው ሰው ይህንን ማየት፣ ይህን ማስተዋል፣ ይህን መገመት ይቸገራል ብዬ አላስብም እኔ፡፡ እነዚያን በዚያ ደረጃ የሚፈሩ፣ እራሳቸውን ከሰው በላይ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎችን፣ እንደሰው ዝቅ ብለው ሰው ሆነው እዚያ ቦታ ላይ እንዲቆሙ፣ ወደዚያ ቦታ ወደ ታች ሰዎችን ማምጣት፣ እንደዚያ በጥጋብ የሰከሩ ሰዎችን፣ እንደዚያ እኔ ከሰው በላይ የሆንኩ ሰው ነኝ፣ የፈለኩትን አስሬ፣ የፈለኩትን ገድዬ መኖር የምችል ሰው ነኝ የሚልን ሰው፣ እራሱን እንደዚያ የካበን ሰው፣ የደም ስሩን በእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ያሳበጠን ሰው፣ እስቲ ዝቅ ብለህ እዚያ ታች ቁጭ በል ማለት በጣም ከባድ ነው፤ በጣም ከባድ ነው፡፡ ታዲያ ለውጡ (ሪፎርም) የታለ? ይለናል ሰው፡፡ አንደኛው ለውጥ (ሪፎርም) ሊጀመርበት የሚገባው ይሄ ነው፡፡ ምን ሰራችሁ? እኛ ያታግለናችሁ ለማን ፕሬዚዳንት ለማድረግ ነው? ዐቢይን ጠቅላይ ሚኒስቴር ለማድረግ ነው? ምን አደረጋችሁ፣ እንዲሁ ቦታ ይዛችሁ ቁጭ አላችሁ እንጂ? ዝም ብለን ይዘን አልተቀመጥንም፣ ጎበዝ፡፡
ኦሮሞ ሊያስተውለው የሚገባው ነገር፣ እየተካሄደ ያለው ነገር ቀላል አይደለም፤ እየተሰራ ያለው ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ሊጋጩት የማይደፈርን ነገር ጋር መጋጨት ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ ሌላውን የለውጥ ተግባር ለማከናወን እኮ አስቀድሞ የማይደፈረውን ምሽግ ማፍረስ ያስፈልጋል፡፡ ያን አፍርሶ መሬቱን ካደላደሉ በኋላ ብቻ ነው ማረስ የሚቻለው፤ አርሶ ላዩ ላይ መዝራትም የምቻለው፡፡ ያን ማፈራረስ እስካልተቻለ ድረስ ማረስ የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡ እሱን ማፍረስ ነው አሁን በየቀኑ እየተከናወነ ያለው፡፡ ተመልከቱ፤ ሪፎርም ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ ሪፎርም ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ ሀገር ውስጥ፣ በሸርና በደባ የተተበተበ ፖለቲካ ሲካሄድበት በመጣና አሁንም በሚካሄድበት ሀገር ውስጥ፣ ለውጥ እንዲሁ ሰተት ብሎ ይመጣልናል ብለን ካስብን ከባድ ነው፡፡ የዚህ ሀገር ችግር የግለሰብ ችግር አይደለም፡፡ አንዱን ከወንበር አውርዶ አንዱን ማስቀመጥ ሳይሆን፣ ሲስተሚክ (ስርዓታዊ) ነው፤ ችግሩ የስርዓት ነው፡፡ ይህ የስርዓት ችግር የፈለገ ሰው፣ እከሌ የሚባልን ሰው እንደራሱ ፒኤልሲ፣ ለራሱ እንዲመቻችለት ለማድረግ በሚችለው መንገድ የገነባውና እራሱንም እንዲያገለግለው ሲያደርገው የነበረ ነበር፡፡ ስለዚህ ያን ማፍረስን ይጠይቃል፡፡ የዚህን ሀገር ህዝብ፣ የዚህን ሀገር ብሄር ብሄረሰቦች ማገልገል እንዲችል አድርጎ እንደ አዲስ አፍርሶ መገንባት ይፈልጋል፡፡ ተመልከቱ፤ በሀገር መከላከያ ውስጥ የዛሬ ዓመት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት እያልኳችሁ አይደለም፣ የዛሬ ዓመት የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የሀገር መከላከያ ሲካሰሱ ነበር፤ አይደል? እኔም ፕሬዚዳንት ነበርኩ፤ ወደ መድረክ ወጥቼ ምንም ሳልፈራ፣ እኔው “ርጅሙ” ሰውዬ፣ “እነዚህ ናቸው ህዝባችንን እየጨረሱ ያሉት፤” ብዬ ተናገርኩ፡፡ ህዝባችንን እያስቸገረ ያለው፣ ህዝባችንን እጃችን ላይ እየጨረሰብን ያለው ከሩቅ የመጣ ጠላት ሳይሆን፣ ይኸው መከላከያ ሰራዊት ነው፤ እያልን አልነበር ስንከስ የነበርነው? ሌላ ማንንም አልከሰስንም እኛ፡፡ ያኔ እንዴት ነበር የምንፈላለገው? ጠመንጃዎቻችንን አቀባብለን እየተፈላለግን ነበር፡፡ እኛ እንኳን አልነበረንም፤ የነበራቸው ግን አቀባብለው እየፈለጉን ነበር፡፡
ዛሬስ ትልቁ ጉልበታችን ማን ነው? ይሄ መከላከያ ሀይል ነው፡፡ ዛሬንና የዛሬን ዓመት ጎን ለጎን አስቀምጣችሁ ተመልከቱ፡፡ አሁን ማዶ ለማዶ የነበረን ነገር፣ እሳትና ጭድ የነበረን ነገር፣ አንድ ላይ አምጥቶ፣ በቶሎ አስማምቶ፣ አጣጥሞ፣ ለሰው እንዲስማማ አድርጎ፣ ሌት ተቀን ሰርቶ፣ መንገድ አሲይዞ፣ እንዲህ አድሩጉ፣ እንዲህ ሁኑ ብሎ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሰዎችን እንዲሰማ አድርጎ ማደራጀት ትልቅ ስራ ይፈልጋል፡፡ አንድ ቀን አዳር ሳይሰሩት የሚያድሩት ጉዳይ አይደለም ይሄ፡፡ በዚህ ላይ እየተሰራ ያለው ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ ኦሮሞ ማወቅ ያለበት፣ እዚህ በተመንግስት ውስጥ እናንተንም ጨምሮ አንድ ላይ ነው የገባንበት ዛሬ፡፡ የኦሮሞ ቤተመንግስት ልናደርገው አይደለም፤ የሀቅ ቤተመንግስት፣ የእውነት ቤተመንግስት ሊያደርገው ነው ኦሮሞ የገባበት እንጂ፣ ኦሮሞ ብቻ የሚዘፍንበት ቤተመንግስት ለማድረግ ከሆነ እኛም የትናንትናዎቹን ነው የምንሆነው፡፡ እሱን አንፈልግም እኛ፡፡ እሱን አይደለም የምንፈልገው፡፡ በህግ ከሆነ፣ በምርጫ ከሆነ፣ በስርዓት፣ በህግ ከሆነ ዶክተር ዐቢይ ከዚህ ቤት ውስጥ መውጣት በሚያስፈልገው ጊዜ መውጣት አለበት፡፡ በጉልበት ሊቀመጥ አለበት ብለን አናምንም፡፡ ዛሬ ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ [ዐቢይ] እዚህ የገባበት፣ ማንም ሰው መጥቶ በጉልበት፣ እሳት አንድጄበት ነው የማስወጣው ቢል፣ እንሞታለን እንጂ አንለቅም፤ እንሞታታለን እንጂ፡፡ ይሄ የስልጣን ጉዳይ አይደለም፤ ይሄ ለስልጣን ስለ መስከርም አይደለም፤ ዲጊኒቲ፣ የኦሮሞ ክብር ጉዳይ ነው፤ የኦሮሞ ልጆች ክብር ጉዳይ ነው፡፡ የሚሰራው ነገር እርባና የሌለው፣ ጥፋትና ስህተት ከሆነ የራሱ ስህተት ብቻ አይደለም፣ ወደ ኦሮሞ ነው የሚመጣው፡፡ እሱ እዚህ ፍርሃት ካሳየ፣ ፍርሃቱ የሱ ብቻ አይደለም፤ ኦሮሞን ፈሪ፣ ውዳቂ ያደርገዋል፡፡ ይሄ ብቻ ነው እንጂ የተለየ ኪኒን ተሰጥቶት አይደለም ለሁሉም፡፡ አሁንም እዚህ ወንበር ላይ ሁለት ወይም ሶስት ዓመት መቀመጥ ሳይሆን፣ ስርዓቱ መለወጥ አለበት፤ መለወጥ መቻል አለበት፡፡ ይህም ከፍተኛ ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ የምሁራኖቻችንን ድጋፍ ይፈልጋል፤ የህዝባችንን ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ እንደሌላውም ሁሉ በእውቀት፣ እውቀት በሚያሰፍልግበት ቦታ በከፍተኛ እውቀት ተጋግዘን፣ ብልሃት (መላ) በሚያስፈልግበትም በከፍተኛ ብልሃት ተጋግዘን በውስጡ ማለፍ መቻል ነው የሚፈይደን፤ ለኦሮሞ ሁሉ ነው የሚፈይደው፡፡ ይህን ነገር በአንክሮ መመልከት፣ ማስተዋል ያስፈልጋል፤ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ማስተዋል ካልቻልን የለውጥ ጉዳይ ሊሰወርብን የሚችል ስለሆነ፣ ይሄን ነገር በደንብ ብናጤነው ብዬ ሃሳብ ልሰጥ ነው፡፡
“የከተማ ፖለቲካን (አርበን ፖለቲክስ) ማጤን አለባችሁ፤ ችላ ልትሉት አይገባም፤” ያላችሁት፣ ትክክል ነው፡፡ የከተማ ፖለቲካ (አርበን ፖለቲክስ) ሊጤን ይገባዋል፣ ምክንያቱም የዚህ ሀገር ፖለቲካ ማእከል (ሴንተር ኦፍ ፖለቲክስ) ከተሞች ስለሆኑ ነው፡፡ የዚህን ሀገር ፖለቲካ የሚወስነውም ከተማ ነው፤ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተማ ውስጥ ፖለቲካ ማለት አንድ ቁጥር ዲሞግራፊ (የህዝብ ስርጭት) ነው፡፡ እዚያ ላይ አንዱን ወደዚያ መግፋት፣ አንዱን ወደዚህ መጎተት፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለሙጉዳት ሳይሆን፣ እንደ ኦሮሚያ ብዙ ነገሮች እየሰራን እንዳለን መገንዘብም ያስፈልጋል፤ በቂ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የጀመርነው በጣም አበረታች ነው፡፡ ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ከ 500፣ 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሆኑ ሰዎች፣ እንደምንሆነው ሆነን፣ ገፍተንም፣ ምንም ብለን፣ ከዚህም ከዚያም ብለን፣ የገዳ አባቶችንም፣ ሽማግሌዎቻችንንም ይዘን፣ እንደለመድነው እርቅ ፈጥረን፣ አቅፈን፣ ስመን ወደ ነበሩበት ቦታ ልንመልሳቸው እንችል ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ መመለስ ይቻል ነበር፤ እኛ ግን ልንመልሳቸው አልፈለግንም፡፡ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ለኦሮሞ አንድነት፣ ያንን ችግር ወደ መልካም እድል ለውጠን፣ ዛሬም ችግር ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ገጠር አላሰፈርናቸውም፤ ከተማ ነው ያሰፈርናቸው፣ እነዚህን ሰዎች፣ እወቁ፡፡ በአንድ ጊዜ ከ 500፣ 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ ሰዎችን፣ እንዲያውም አዲስ አበባ ዙሪያና አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6000 (ስድስት ሺህ) አስገብተናል፤ አዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ አይደለም፡፡ እኒህን ከዚያ የተፈናቀሉትን ሰዎች፣ የዚህን አካባቢ ባህል የማያውቁ ሰዎች፣ በብዙ ነገሮች ከአካባቢው ጋር የማይመሳሰሉ፣ ይቸገራል መችም፣ ይቸገር፤ ዛሬ ችግር የማያጣው ቢሆንም፣ ከተቸገረም እዚሁ ከተማ ውስጥ ይቸገር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በእግሩ የሚቆምበት መሬት ይኑረው፤ እሱ ቢቸገርም ለልጆቹ የሚሆን ስለሆነ፣ ብለን ህዝባችንንም አስቸግረን ካለን ነገር ላይ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው ያሰፈርናቸው፡፡ አብዛኛው የሀረርጌ ሰዎች ናቸው፣ እወቁ፡፡ ቦርደዴ ማስፈር ይቻል ነበር፤ ምስራቅ ሀረርጌ ልናሰፍራቸው እንችል ነበር፡፡ ማስፈር ትክክል ከሆነ እንዲያውም እዚያው አካባቢ ነበር ማስፈር የሚገባው፤ ያን ባህል ነው የሚያውቀው፣ ያን አየር ነው የሚያወቀው፡፡ ወደማያውቀው ባህል እዚህ አምጥተን አዲስ አበባ ውስጥ አሰፈርነው፡፡ ቢቸገር ቢቸገር ሁለት ዓመት ነው ሊቸገር የሚችለው፤ ከዚያ በኋላ ሰው ሆኖ ይወጣዋል፡፡ ይሄ በፖለቲካ ላይ ያለው ፋይዳ፣ ሄዶ ሂደም በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ በመሆኑ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ ስለሚፈይድ፡፡
ወጣቱንም ስራ እናስይዛለን ብለን በንግድ ስም፣ በሌላም ነገር ስም ብዙ ነገር ስናደርግ ነበር፤ እናም አብዛኛውን ከተማ ውስጥ አስገባነው፡፡ ወደ ከተማ ስናስገባው የሚኖርበት ቦታ ኖሮት ነው፡፡ ከ 500፣ 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያን ክልል ሰራተኞች ዘንድሮ መሬት የሰጠናቸው ገጠር ውስጥ አይደለም፤ ይብዛም ይነስም ከተማ ውስጥ ነው የሰጠናቸው፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ ነው የሰጠናቸው፡፡ ብዙ ልንቆጥር እንችላለን፡፡ ይሄ በቂ ነው ብዬ አይደለም፤ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ሆኖም ችላ ያልነው ነገር አይደለም፤ እየተሰራበት ያለ ነገር ነው፡፡ ስንሰራም በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ይህም በዚሁ ረገድ ቢታይ መልካም ይሆና ብዬ ነው የማየው፡፡
Filed in: Amharic