>

"ሸገር" የሚለው የአዲስ አበባ  መጠሪያ ልክ እንደ ፊንፊኔ ሁሉ አማርኛ እንጂ ኦሮምኛ አይደለም!  (ሐብታሙ ተገኜ (ዶ/ር )

Map of Addis Ababa.


“ሸገር” የሚለው የአዲስ አበባ  መጠሪያ ልክ እንደ ፊንፊኔ ሁሉ አማርኛ እንጂ ኦሮምኛ አይደለም! 

ሐብታሙ ተገኜ (ዶ/ር )
አዲስ አበባን ሸገር ማለት የተለመደ ነው። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሸገር የሚለው ቃል በጣም እየተዘውተረ መጥቷል። የንግድ እና የመገናኛ ተቋማትም በመጠሪያነት ይጠቀሙበታል። አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት በፊት የተቋቋመው የሸገር ራዲዮ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ስለ ሸገር ያገኘነው የመጀመሪያው የጽሁፍ መረጃ የዡል ቦሬሊ መጽሐፍ ነው። ዡል ቦሬሊ አዲሱ እንጦጦ ለሶስት ዓመታት ተቀምጦ ነበር። ወደ እንጦጦ የመጣው ከተማው ከተቀረቆረ ከሶስት ዓመት በኃላ ማለትም በ1885 ዓመተ ምህረት ነው። ዡል ቦሬሊ እንደጻፈው አጼ ምኒልክ ከተማው እንዲጸና ሰዎችን ከሌላ ቦታ እያመጡ እንጦጦ ያሰፍሩ ነበር። ሰው የማሰባሰብ ስራ “በኦሮሞዎች ዲልዲላ በአማራዎች ሸገር ጨነቅ ተብሎ ይጠራ ነበር” ብሎ ጨምሮ ጽፏል። ቦሬሊ ሸገር ጨነቅ ለሚለው ቃል ፍች ወይም ማብራሪያ አልሰጠም። ቃሉ ሸገር እና ጨነቅ የሚሉትን ቃልቶች በማጣመር የተፈጠረ ነው።
በስርወ ቃላት ትንታኔ “ሸገር” ስር መሰረቱ “ሠገረ” ነው። የሚወክለው ረቂቅ ጽንሰ ሃሳብም “በመነሻ እና በመድረሻ መካከል ያለን ቦታ ማለፍን፣ መዝለቅን” ነው። ከዚህ ረቂቅ ጽንሰ ሃሳብ የውልድ ቃላቱ ፍቺዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ የሚከተለው የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት የ“ሸጐረ” እና የ“ሻገረ” አፈታት ይህን ጽንሰ ሃሳብ ያጎላል። “ሸጐረ፤(ሠጊር፡ ሠገረ)፤ወረወረ ቀረቀረ፤ዘጋ ደነቀረ። ሻገረ፤ተሻገረ፤በወንዝ በዥረት በዠማ በባህር በጎድጓ ስፍራ ላይ ዐለፈ፤ወዲያ ማዶ ኼደ። ስሩ ሰገረ ነው። (ተረት)፤ይህን ውሃ ማ ይሻገረዋል ቢሉ፤ተዝካር ያየ ተማሪ።” ሃሳቡ ከመያዣው ጋር ከተሳሰሩበት ከአማርኛ ወጣ ብለን ፍችውን በእንግሊዝኛ እና በኦሮምኛ ብንመለከት ነገሩ ለአዕምሮ ብሩህ ይሆናል። የደስታ ተክለወልድ ፍችዎች ከእንግሊዝኛዎቹ “cross” እና “bar” ጋር አንድ ናቸው። ሁለቱም የ”መሻገር፣ መዝጋት፣ ማጐሮ፣ መሸጐር” ሃሳብ አለባቸው።
ጨነቅ የሚለው ቃል ‘አጨናነቀ’ ወይም ‘መጨናነቅ’ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ደስታ ተክለወለድ ‘አጨናነቀ’ ለሚለው ቃለ አጠጋጋ፣አቀራረበ ፣አደራረበ” ይሚል ፍች ሲሰጡት ‘መጨናነቅ’ የሚለውን ቃል ደግሞ ‘መጠጋጋት፥መቀራረብ’ ብለውታል። [612-613] “ሸገር ጨነቅ” የሚለው ስያሜ የከተማዋን መመስረት ተከትሎ ከተካሄደው የሕዝብ ሰፈራ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ፣ ይህ “የመዝጋት”፣ “የማጎር”፣ የ”መሸጐር” አስተሳሰብ ከሃረጉ ቃላት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፤ “ከፍ ያለ የሰው ቁጥር በአንድ ቦታ በመስፈሩ የተነሳ የተፈጠረው “የመሸጐር” እና “የመጨነቅ” ስሜት የወለደው ስያሜ ይመስላል። ሌላ ታሪካዊ ማገናዘቢያ በሌለበት በቃላት ፍች ትንተና ላይ ለሚመሰረት ፍለጋ ስለከተማዋ ስያሜ ይህ ትንታኔ ወደእውነቱ የሚቀርብ መላ ሊሆን ይችላል። የኦሮምኛው “ዲልዲላ” ለሸገር ጨነቅ ተጨማሪ ፍንጭ ይሰጣል። ዲልዲላ የኦሮሞኛው መዘገበ ቃላት ድልድይ የሚል ፍች ይሰጠዋል። ስለዚህ ዲልዲላ “መሻገሪያ”፣ “ድልድል”፣ “ድልድይ” ስለሆነ “ሸገር ጨነቅ” “ጠባብ ድልድይ” እንደማለት ይሆናል።
ከላይ የሰጠነው ትንተና ሸገር ጨነቅ ስለሚለው ቃል እና ስለ እንጦጦ ዳግማዊ ለደት ጥሩ ማብራሪያ ቢሆንም ሸገር ለምን እና ከመቸ ጀምሮ የአዲስ አበባ መጠርያ እንደሆነች መልስ አይሆንም። እኛ ለማግኘት የቻልናቸው የታሪክ መረጃቸው ሸገር የሚለው ቃል ለአዲስ አበባ መጠሪያ እንደሆነ ፍንጭ አይሰጡም። ይህ እንደሌሎቹ አርስተ ጉዳዮች ሁሉ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልገዋል። የማህረሰብ የቦታ ስያሜ ትንታኔ (folk etymology) ስለ ሸገር ክፍተቱን በተወሰነ መልኩ ሊሞላ ይችላል ብለን አናስባለን። እንደሚታወቀው የማህረሰብ የቦታ ስያሜ ትንታኔ ብዙ ጊዜ ታማኘንት የለውም። አንዳንዱ በጣም አስቂኝ ነው። ነገር ግን በዚህ መንገድ የሚሰጡ የቦታ ስያሜ ትርክቶች ብዙዎቹ ታማኘነት ባይኖራቸው አንዳዶች በታሪክ ላይ የተመሰረቱ ነቸው። ስለ ሸገር ቀጥሎ የሰጠነው አስተያየት የማህበረሰብ የስያሜ መነሻ አተናተንን ድክመት ያገናዘበ እንደሆነ አንባቢ እንዲረዳልን እናሳስባለን።
ሸገር “የሸጋ አገር” ከፊለ ስም ወይም ቃል ነው የሚሉ ሰዎች አሉ። ይህ እውነት ከሆነ በስርወ ቃላት ትንታኔ የሸጋ መሰረቱ ሸገነ ነው። የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሸገነን ‘አማረ፡ ተዋበ፡ አበበ’ ብሎ ተርጉሞታል። ሸገን የሰው የስም መጠሪያም ነው፤ትርጉሙም መልከ ቀና ወይም መልከ መልካም ማለት ነው። ሸገና ላገር መጠሪያነትም ያገለግላል። ደስታ ተክለ ወልድ ሸጋ የሚለውን ቃል “የሸገነ፡ ያማረ፡የተዋበ፡ ውብ፡ ቁንዦ” ብለው ተርጉመውታል። [1215] ከሳቴ ብርሀን ተሰማ ወልደ ሚካኤል በበኩላቸው የሸገነ የሚለውንቃል “የአማረ፥ የተዋበን ኾነ፥ተሽቀረቀረ፥ተሽቀነደረ” ብለው ሲተረጉሙት ሸገገን “በመልክ፥በልብስ፥ሸጋን፥ውብን ኾነ፥ተዋበ፥አማረ፥መልከ መልካምን ኾነ” ብለውታል። [331] የጉይዲ አምራኛ ጣሊያንኛ መዘገበ ቃላትም ተመሳሳይ ፍች አለው። [227-230] የበይትማንም እንዲሁ [285] ስለዚህ ሸገር ማለት የተዋበ ያማረ የአበበ አገር ማለት ነው።
ከላይ እንዳየነው ሸገነ ‘አበበ’ የሚል ትርጉም አለው። በዚህም ምክንያት ሸጋ አገር እና አዲስ አበባ ተመሰሳይ የትርጉም ይዘት አላቸው። ጸሀፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ንግስት ጣይቱ ፍል ውሃ ሳሉ አካባቢውን በአይናቸው ሲቃኙ ባዩት ነገር ሰለተማረኩ የአገሩን ማማር ስላወቁ ከተማ ለመቆርቆር እንደወሰኑ ጽፈዋል። ጸሀፌ ትእዛዝ እንዲህ ይላሉ፣ “በዚያ ጊዜ ወይዘሮ ጣይቱ ከድንኳኑ ደጃፍ ሁነው ሙቀቱን ማማሩን ሀገሪቱን ተመለከቱ።” ከተማውን አዲስ አበባ ያሉበት ምክንያት ፍል ውሃና አካባቢው ለኑሮ ተስማሚ ሸጋ አገር ሆኖ ስላገኙት ነው።
ከላይ የሰጠነው ትንታኔ ትክክል ከሆነ ሸጋ አገር ቀስ በቀስ ወደ ሸገር ተለውጧል። ይህ ደግሞ የሚያስገርም አይደለም። በአገራችን ባህል ሰወችን ውይም የቦታ ስያሜወችን በሙ ስማቸው ከመጥራት ይልቅ በከፊለ ስማቸው መጥራት በጣም የተለመደ ነው። ሸጎሌ የሚለው የአዲስ አበባ የሰፈር ስም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ሸጎሌ የቦታውን ስያሜ ያገኘው ከሸይክ ኮጀሌ ነው። ሸይክ ኮጀሌ የአሶሳ ባላባት ናቸው። ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመነ ምንግስት መጨራሻ አሶሳን አስተዳድረዋል። ሸይክ ኮጀሌ የተወሰኑ ዓመታትን አዲስ አበባ ግዞት በሚመስል ሁኔታ አሳልፈዋል። ወደ አሶሳ ከተመለሱ በኋላ አዲስ አበባ ሰፍረውበት የነበረው ቦታ በስማቸው ሸጎሌ ተብሎ ተሰየመ። የሰውየው ሙሉ ስም ሸይክ ኮጀሌ ቢሆንም ብዙ ሰው የሰፈሩብትን ቦታ የሚጠራው በከፊለ ሥማቸው ሸጎሌ ብሎ ነው። ሰወችን በከፊለ ስማቸው መጥራት በጣም የተለመደ ነው። ለምሳሌ ኢብራሂምን ይብሬ፣ገላውዴዎስን ገላዴ፣ሙሀመድን ማመዴ ውይም አመዴ፣ ቆስጠንጢኖስን ቆስጤ እና ዲሚጥሮስን ዲሞ ማለት በጣም የተለመ ደ ነበር። ሸጋ አገር ወደ ሸገር የተቀየረበትም ምክንያት በተመሳሳይ ሁኔታ ሊሆን ይችላል።
Filed in: Amharic