>
7:53 am - Wednesday December 7, 2022

ለውጡ እንዳይደናቀፍ…      (አሳዬ ደርቤ)

ለውጡ እንዳይደናቀፍ…
አሳዬ ደርቤ
•••
እድገታችን እንደ ዙፋኑ- በተራ እንዲሆን እንፍቀድ የሚገፉንን እንቀፍ፣ የማይወዱንን እንውደድ ኦነግ ባንካችንን ይዝረፍ- ሚስቶቻችንን ይጥለፍ ኢትዮጵያዊነት ይቀንጭር- ብሔርተኝነት ይግዘፍ ለውጡ እንዳይደናቀፍ…
•••
ፀሐዪ መንግሥታችን- የጨረቃ ቤቶችን ያፍርስ እንደ ዘወትር ጸሎት- የለውጡን ባለቤት እናስታውስ በጃዋር እየተመራን- ወደ ቀብራችን እንገስግስ በአሃዳዊነት እሳቤ – የሰው ወግ፣ባህል ከመጣስ በፌደራል ሥርዓታቸው- እኛን ይጫኑን ይልቅስ
ለውጡ እንዳይቀለበስ…
•••
የምናየውን እንካድ- የምንሰማውን እንመን አጋር ድርጅቶች ይክሰሙ- ገዥው ፓርቲ ይበታተን ኦዴፓ ክራንቻ አብቅሎ- ብቻውን ኢህአዴግ ይሁን፤ ፌደራሊዝሙ እንደ እኛ ቤት- አይሻሻል፣ አይለወጥ ሰላምችን እንደ ሻሜታ- በመንጋ ፍትህ ይበጥበጥ ጡት እንዳልጣለ ሙጫ ልጅ- ለከንቲባችን እንታለል በኦሮ-ማራ እንደለል- በቲም-ለማ እንሸንገል ያልሆነ ነገር ተንፍሰን- ለውጡን ስጋት ውስጥ ከመጣል እንደ ጌታቸው ጥፍት -እንደ ደመቀ ዝም እንበል፣ ለውጡ እንዳይደናቀፍ…
•••
በደሞዛችን ፈንታ ደም-ግፊታችን ይጨምር የአዲስ አበባ ሥያሜ- ‹‹ፊንፊኔ›› ተብሎ ይቀየር በህውሓቶች ወጥመድ ውስጥ-ባቡሩ ገብቶ ሲጠለፍ በዶክተር ዐቢይ ፈንታ- መለስ ዜናዊን እናኩርፍ ለውጡ እንዳይደናቀፍ..
•••
ሳያውቁ የሚያወሩትን- ከዓደዋ ድል ጋር እናውሳ አውቀው የሚሠሩትን- ግንቦት ሃያ ጋር እንርሳ ለዲሞግራፊ ሲተጉ- ለመንቀል፣ለመትከል ሴራ ስለ ዲሞክራሲ እንዘምር- ስለነጻነት እናውራ፡፡ ወታደር ጥይት ተኩሶ- ንጹህ ዜጎችን ሲቀጥፍ
‹‹ኢትዮጵያ ሆነዋል›› እንጂ ‹‹ሞተዋል›› ብለን አንለፍፍ፤ ለውጡ እንዳይደናቀፍ…
•••
ባተሌ መሪዎቻችን- ለቀጠናው ትስስር ሲተጉ ሲዳማና ኦሮሞ ይጋቡ- ትግራይና ዐማራ ይዋጉ ኦዶፓ ያስቀየመን ጊዜ- ለማ ያስከፋን ለታ ‹‹ያሳተው ደጺ ነው›› ብለን -ህውሓቶች ላይ እንበርታ፤ ጌታቸው የሚያዝበት ቀን… እንደ ጌታችን መምጫ ዕለት- በውል ስለማይታወቅ፤ በጸሎታችን በርትተን- ነቅተን እንጠባበቅ ‹‹ለውጡን ጠብቁ›› ስንባል- ‹‹የቱ ለውጥ?›› እያልን አንጠይቅ፤ የዳውድ ኢብሳ መንፈስ- ለማ ላይ አድሮ ሲለፍፍ ‹‹ሱሱ ለቀቀው›› እንጂ- ‹‹ክዶናል›› ብለን አንለጥፍ
ለውጡ እንዳይደናቀፍ…
አሜን!!
Filed in: Amharic